የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂው ከርምጃ ወደ ሩጫ

22

ባለፈው አንድ ዓመት በአገሪቷ የመጣው ለውጥ ያስከተላቸውን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በርካታ ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል። በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉት ሥራዎች የአገሪቱን ግብርና፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂና የመንግሥት አሰራርን ዘመናዊና ተደራሽ በማድረግ ረገድ ትልቅ አቅም እንደሚሆኑ ይታመናል። በዘርፉ ወሳኝ ድርሻ ለመጫወት በአሁኑ ወቅት እየተሰሩ ካሉት ተግባራት መካከል ዋና ዋናዎቹን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እንደሚከተለው ያብራራሉ፡፡

ትኩረት

በ2017 ዓ.ም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት መካካል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን እርግጠኛ ለመሆን ካስፈለገ የቴክኖሎጂ ክምችት (Technological Accumulation) እና የመጠቀም አቅም (Absorption Capacity) ማሳደግ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ከሌሎችም አገራት የምናየው ልምድ ነው፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ‹‹በቴክኖሎጂና በኢኖቬሽን ሥራንና ሀብትን ለመፍጠር የምትመች ሀገር ተገንብታ ማየት›› በሚል አዲስ ራዕይ እና ‹‹የኢኖቬሽን ሥርዓት የሚተገበርበትን ከባቢያዊ ሁኔታን በመፍጠር የሀገሪቱን የዕድገት ቀጣይነት ማረጋገጥ›› በሚል አዲስ ተልዕኮ በመቅረፅ ከርምጃ ወደ ሩጫ የተሸጋገረውን ጉዞውን ከፍተኛ ፍጥነት ባለው ሩጫ ውስጥ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

የዚህም ራዕይና ተልዕኮ ትግበራ ማሳያዎቹ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የስራ ዕድል ፈጠራና የሀብት ፈጠራ በመሆናቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስትራቴጂ ነድፎ በበጀት ዓመቱ ባቀዳቸው ተግባራቱ ውስጥ አካቶ በማከናውን ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ስትራቴጂ ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ በ2011 እና በ 2012 ባሉት 2 ዓመታት እስከ 2ሺህ የቴክኖሎጂ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን፣ ከ20 ሺህ በላይ የቴክኖሎጂ የስራ ዕድል ፈጠራና ከ2 ቢሊዬን የአሜሪካ ዶላር በላይ የቴክኖሎጂ ሀብት መፍጠር የሚያስችል ከባቢያዊ ሁኔታን እውን የማድረግ ዕቅድ ወጥቶ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡

 የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በስሩ ያሉት ተጠሪ ተቋማት፣ ማለትም የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከያ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት፣ ባለፉት ወራት በርካታ ስራዎችን እያከናውኑ ቆይተዋል፡፡

በተጨማሪም በፖሊሲ ማዕቀፍ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚመራውን የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፉን ሊበራላይዝ ለማድረግ፣ መንግሥት ባስቀመጠው የኢኮኖሚክ ሪፎርም እና ‹‹ፕራይቬታይዜሽን›› አቅጣጫ መሰረት ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ሬጉላቶሪ ባለስልጣን ማቋቋሚያ

 አዋጅ በማዘጋጀት ለመንግሥት ውሳኔ አቅርቧል። በተለይም ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ለሀገራችን የልማት ዘርፎች ወሳኝ ሚና እንዲጫወት ለማድረግ ተለይተው ትኩረት ለተሰጣቸውን ዘርፎች ማለትም ለግብርና፣ ለጤና፣ ለማዕድን ልማት፣ ለሀገር ውስጥ ማኑፋክቸሪንግን ዘርፍ፣ ለኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ በተለይም ኢኮኖሚው የሚመራበትን ምህዳር (Ecosystem) ለመፍጠርና ዲጂታል ኢኮኖሚ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መሪ እንዲሆን ለማስቻል እየተሰራ ነው፡፡

የግብርናው ዘርፍ

በበሬ በሚታረስ እርሻ ላይ የተመሰረተ ግብርናን በመከተል የአገሪቷን የግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንደማይቻል ይታመናል፡፡ ይሄንንም ትኩረት በመስጠት ከግል ዘርፉ ቴክኖሎጂ ባለቤቶች ጋር በመተባበር በእጅ የሚገፋ ማረሻ ዲዛይን እንዲደረግና እንዲመረት ድጋፍ በማድረግ አሁን ከብዙ ሙከራዎች በኋላ ምርቱ ተመርቶ ወጥቷል፡፡ በሚቀጥለው አንድ ሳምንት ውስጥም በሀገራችን የተሰራው ይህ ባለሞተር ማረሻ ይመረቃል፡፡ የምርት ማባዛት (Mass Production) ለማከናወንና ለአርሶ አደሩ ማከፋፈል የሚጀምርበት ሁኔታ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ይመቻቻል፡፡

በኢትዮጵያ ግማሽ የሚሆነው የግብርና መሬት በአሲዳማነት የተመታ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ የሚፈለገውን ምርት መስጠት አይችልም፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት የአፈርን አሲዳማነት ሊፈውሱ የሚችሉ አንድ የሀገር ውስጥ እና አንድ የውጪ ሀገር ቴክኖሎጂዎች በመስክ ሙከራ ሂደት ላይ ናቸው፡፡ ወጤታማነቱ ከተረጋገጠ ለአገሪቷ ግብርና ከፍተኛ ተግዳሮት የሆነውን ችግር መፍታት እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

አንድ ጊዜ ተዘርቶ እስከ 20 ትውልዶች ምርት ሊሰጥ የሚችል የማሽላ ዝርያም በምርምር የተገኘ ሲሆን፤ የኢኖቬሽን ዘርፉ ግብርናን ትኩረት አድርጎ ከሚሰራቸው ምርምሮች አንዱ የሆነውን ይህንን ምርት ወደ ገበሬው ለማሰራጨት የሚበቃ የምርት ክምችት እየተዘጋጀ ይገኛል።

በጤናው ዘርፍ

እስከ አምስት ኪሎ ግራም መድሃኒት ወይንም ክትባት ይዞ እስከ 150 ኪሎ ሜትር መብረር የሚችል ሰው አልባ አውሮፕላን ዲዛይን ተደርጎና የመጀመሪያው ምርት ተመርቶ መስራቱ ተረጋግጧል፡፡ ረጅም ጊዜ ከወሰደ የግዥ ሂደት በኋላ ባለፈው ሳምንት ወደ ምርት (Mass Production) ገብቷል፡፡ በዚህም መሰረት በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡

የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን የህክምና አሰጣጥ ስርነቀል ለውጥ ያመጣ ዲጂታል ሲስተም በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ለምቶ ስራ ላይ ውሏል፡፡ ይህ ‹‹ሶፍትዌር›› በሌሎች ሀገራት ከተሰሩት የትላልቅ ሆስፒታሎች ዲጂታል ሲስተም የተሻለ በመሆኑ፣ ላለፉት ስምንት ወራት በጥቁር አንበሳ ስራ ላይ ውሎ አስደሳች ውጤት አሳይቷል፡፡ ከጤና ሚኒስቴርም ጋር በመሆን ለሌሎች የአገሪቱ ሆስፒታሎች እንዲያገለግል ይደረጋል፡፡

በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የህክምና መሳሪያዎችን ለማስፋፋትና በዘርፉ ያለውን መጠነ ሰፊ ችግሮችን ለመፍታት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ኢንቬስትመንት ኮሚሽን ጋር በመሆን ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ በቅርቡም በኢትዮጵያ የተሠራ ‹‹Made in Ethiopia›› የህክምና መሳሪያዎች በኢትዮጵያ ይታያሉ፡፡

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ

አዲስ የ‹‹Designed in Ethiopia›› ፊሎሶፊ በማስጀመር፣ ሀገራችንን የኢንዱስትሪ አካላት፣ የተለ ያዩ የመኪናዎችና የማሽነሪዎች Spare Parts ዲዛይን የሚደረጉበትና የሚፈበረኩበትን ምህዳር (Echo System) ለማከናወን ታስቦ የተጀመረ ሲሆን፤ ይሄንንም ለማሳካት ከውጭ ሀገር ባለሙያዎችን በማስመጣት ከ200 በላይ የሚሆኑ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ወጣቶችን ስልጠና በመስጠት አዳዲስ የቴክኖሎጂ ምርቶችን ዲዛይን አድርገው ማውጣት እንዲችሉ ተደርጓል፡፡

በዚህ ሂደት ትልቁ ተግዳሮት የማምረት አቅም በመሆኑ ይሄንን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው፡፡ ዘላቂ መፍትሔም ይሆናል ተብሎ የሚታመነው በአገሪቷ ውስጥ የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከል መመስረትና አሁን እየታየ ያለውን የወጣቶቻችንን ተሰጥኦ መጠቀም መልካም አጋጣሚዎችን እንደሚፈጥር መገንዘብ ነው፡፡ ለዚህም የቴክኖሎጂ ማበልፅጊያ ማዕከል የሚቋቋምበትን የበጀት ጥያቄ በ2012 በጀት ዓመት ውስጥ ጥያቄ ቀርቧል፡፡

ሌላው የአገሪቷን የማኑፋክቸሪንግ አቅም ያሳድጋል ተብሎ የሚታመነው፤ በየጋራዥ ቤቶቹ ያለው እምቅ የመፍብረክ አቅም ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ዘርፍ እስካሁን ሲመራና ሳይደገፍ ስለቆየ የአቅም ግንባታ ያስፈልገዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ የተወሰኑ ግለሰቦችን በመደገፍ አንዳንድ ወሳኝ ምርቶችን እንዲያመርቱ ተደርጓል።በእጅ የሚገፋ ማረሻውም የተሰራው በዚሁ በየቦታው ተበታትነው ያሉትን በየጋራዥ ቤቱ ያለውን ዕምቅ አቅም በመጠቀም ነው፡፡

የኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ መሰረቶች መጣል

የዓለማችን ቴክኖሎጂ በፍጥነት እየተለዋወጠ እንደሚሄድ ይታወቃል፡፡ በተለይ አሁን ባለንበት ዘመን ዓለማችን የ81 ትሪሊዬን ዓመታዊ ሀብት የሚመነጭባት አንዷ ሀገር ኢትዮጵያ አድርገን ልናስባት እንችላለን፡፡ ከዚህ ውስጥ ከግብርና ዘርፉ የሚመነጨው ሀብት ከሰባት በመቶ ያነሰ፣ ከኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚመነጨው ሀብት ከ30 በመቶ ያነሰ ሲሆን፤ ከ63 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለማችን ሀብት እየመነጨ ያለው ከአገልግሎት ዘርፍ በተለይም ዕውቀትንና ቴክኖሎጂን ከሚጠቀም (Knowledge and Technology Intensive) ከሆኑ ዘርፎች ነው፡፡

በተለይም አሁን ዲጂታል ኢኮኖሚው የአለምን የኢኮኖሚ ዘርፎችን እየመራ ይገኛል፣ በዓለማችን ላይ ካሉ 10 ትላልቅ ኩባንያዎች፣ ሰባት ወይም ስምንቱ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ‹‹Amazon, Google, Microsoft, Apple, Facebook›› ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያም ይህን መረዳት ያስፈልጋል፡ ፡ ወጣቶች ዲጂታል ቴክኖሎጂን ተጠቅመው የስራ ዕድል እንዴት ማግኘት እንደሚችሉና ሀብት እንዴት መፍጠር እንደሚችሉ እንደመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራት ላይ ነው፡፡

ከዚህ በኋላ በጤና፣ በግብርና፣ በትራንስፖርት፣ በኮንስትራክሽን ዘርፎች፣ ሀገር ውስጥ በወጣቶች የተሰራውን ቴክኖሎጂ መቀበል የሚያስችል አሰራሮች መኖር ይኖርባቸዋል ተብሎ ስለሚታመን እየተሰራ ነው፡፡

ነገር ግን አሁንም ትልቅ ተግዳሮት የሆነው በሀገር ውስጥ ያለውን የዲጂታል ሲስተሞችን አለመጠቀም፣ በአንድ በኩል የወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር ይባላል፣ በሌላ በኩል ወጣቶች የሚሰሩትን ሶፍትዌርና ሲስተሞችን ላለመቀበል የወሰነ የሚመስል ሁኔታ ይታያል፡፡

አገሪቷ ድሃ ሆና ባደጉ ሀገራት ላሉት ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠርና የእኛን ሀገር ወጣቶች የስራ ዕድል ማሳጣት ተገቢነት የለውም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ የኢኮሜርስን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስጀመር፣ ረጅም ሂደት ተሂዷል፡፡ በተለይም የአገሪቷን የቡና ምርት በኢኮሜርስ በዓለም ገበያ ላይ እንዲሸጥ በማድረግ የገበሬውን ኑሮ ለማሻሻልና አገሪቷ አሁን ከቡና እያገኘች ያለችውን የውጪ ምንዛሪ ቢያንስ አራት እጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው፡፡

ICT መሰረተ ልማቱን ከመደገፍ አኳያ

የመንግስትን አሰራር ለማዘመን የICT ዘርፉ ቀድሞ መጓዝ ስላለበት፣ እስካሁን የተሰሩትን ተግባራት ታሳቢ በማድረግ፣ ሊጨመሩ የሚችሉትን ጉዳዮችም በመለየት ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ውስጥ የነበረ የብሔራዊ ዳታ ማዕከል የተሻለ አቅም ወዳለው ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዲዛወር ተደርጓል፡፡ ይህም ዳታ ማዕከል ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ‹‹የሆስቲንግ››፣ ‹‹የቪድዮ ኮንፈረንስ›› እና የሙያ ድጋፍ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡ ፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ በማዕከሉ 86 ተቋማት አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ለምሳሌ ባለፈው አንድ አመት 25 ሺህ 186 የሚሆኑ ተሳታፊዎች የቪዲዮ ኮንፍረንስ አገልግሎት አግኝተውበታል፡፡ በ8181 የአጭር መልዕክት አገልግሎት እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው የመንግሥት ተቋማት የማማከር አገልግሎት፣ Online Services፣ የመንግሥት ተቋማት አስራር ዘመናዊ ለማድረግ የቢሮ አሰራር ወረቀት አልባ /paperless office/ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት ወራት ከተሰሩት የICT ስራዎች ዋና ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው መንግሥት ለዜጋው የሚሰጠውን አገልግሎት (e-Governance) ለማሻሻል የሚያስችል፤ ስር ነቀል ለውጥ ሊያመጣ የሚያስችል ቴክኒካዊ ፕሮፖዛል ተሰርቶ በሚቀጥለው በጀት ዓመት ሁሉም ወረዳዎች ላይ የe-Government አገልግሎት ለማስጀመርና የመንግስትን ዘመናዊ አሰራር ወደ ዜጋው ለማውረድ የተደረገው ዝግጅት ነው፡፡

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2011

አዲሱ ገረመው