ወንድማማቾቹ

21

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ አጠገብ መነን አካባቢ ነው ተወልደው ያደጉት። አንድ ማህጸን ያፈራቸው ታላቁ ሙሉዓለም ግርማ ይባላል። ታናሽየው ደግሞ ፍቃደ ግርማ ነው። ታላቅ 31 ዓመቱ ሲሆን ፣ታናሽየው ደግሞ የ25 ዓመት ወጣት ነው።

ወጣቶቹ በልጅነታቸው ቤተሰቦቻቸውን በተለያዩ ሥራዎች ያግዙ ነበር። የቤተሰባቸው የኑሮ ደረጃ ዝቅተኛ የሚባል ስለነበር ከትምህርት ቤት መልስ ጫማ በማሳመር (ሊስትሮነት) በሚያገኙት ገንዘብ ያህል ቤተሰባቸውን ስለሚደጉሙ የእናታቸው ወይዘሮ ፋናዬ ገብረጻዲቅ እና የአባታቸው አቶ ግርማ ከበደ ምርቃትን ተቀብለዋል።

ታላቅ በሰፈራቸው ከሚገኘው የእንጨት ሥራ ቤት ገብቶ ለመስራት ይወስናል። ከትምህርት ቤት መልስም በትርፍ ጊዜው በእንጨት ቤቱ ያለውን የሥራ ሒደት በሙሉ እያጠና መስራቱን ይቀጥላል። በወቅቱ ግን የሚከፈለው ለሳሙና ተብሎ በሳምንት ከአሥር ብር የማይበልጥ ነበር።

ይህም ገንዘብ ቢሆን አንድ ቀን ከቀረ ሊያመልጠው ይችላል። ይሁንና ገንዘቡን ሳይሆን የሙያ ልምዱን ለማግኘት በመሆኑ ፤ ከሙያተኞቹ ስር ስር እየተከተለ ቀስ በቀስ ዕውቀት መቅሰሙን ቀጥሏል። በጎን ደግሞ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ የማምረት ሙያውን በእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ትምህርት ኮሌጅ ገብቶ አጠናክሯል።

ትንሿ የሰፈራቸው እንጨት ቤት ውስጥ ታናሽ ወንድሙም ለመቀላቀል አስቧል። እርሱም ለሳሙና እየተባለ የሚከፈለውን ገንዘብ በሳምንት እየተቀበለ ሙያውን ቢለምድ ፍላጎቱ መሆኑን ለታላቅ ወንድሙ አማከረው። ታላቅም ፈቃደኝነቱን ገለፀለት። በዚህ ጊዜ ወጣት ፍቃደ አላመነታም ከታላቅ ወንድሙ ጋር አብሮ መስራቱን ተያያዘው።

ታላቁ ሙሉዓለም ለአራት ዓመታት ያህል የእንጨት ሥራውን ተቀጥሮ በመስራት ሙያውን በሚገባ መቻሉን አረጋግጧል። ፍቃደም እንደወንድሙ ባይሆንም የተወሰኑ ዓመታትን በመስራት ለምዱን አዳብሯል። ሁለቱ ወንድማማቾች አሁን በቂ የእንጨት ሥራ ልምድ ይዘዋል። እናም የእራሳቸውን እንጨት ቤት መክፈት እንዳለባቸው ተማክረዋል።

ከመነን ሰፈር መኖሪያ ቤታቸው ፊት ለፊት የሚገኝ ያለሥራ የተቀመጠ መሬት ደግሞ ሥራ ለመጀመሪያ እንደሚሆናቸው አጥንተዋል። ከአራት ዓመታት በኋላ የአንድ ማህጸን ልጆች የጋራ ሥራቸውን በመተጋገዝ ሊያከናውኑ ጫፍ ላይ ደርሰዋል። በጥቂት ቀናት ውስጥ ሸራ ላስቲክ ወጥረው መስሪያ ቦታቸውን ከአመቻቹ በኋላ የግል ሥራቸውን አሀዱ ብለው ጀመሩ።

በወቅቱ የነበራቸው መሳሪያዎች በአብዛኛው በእጅ የሚንቀሳቀሱ እንደ መዶሻ እና መጋዝ የመሳሰሉ ቀላል መሳሪያዎች ብቻ ነበሩ። ለሁለት ቆጥበው አራት ሺ ብር የገዟት የመስፊያ ማሽን ደግሞ ዋነኛ የሥራ መሳሪያቸው ነበረች።

ቀን ቀን በላስቲክ በተሸፈነችው መስሪያ ቦታ ሲጠቀሙባቸው የዋሉ መሳሪያዎችን ማታ ላይ ደግሞ በመኖሪያ ግቢያቸው አስገብተው በማሳደር ከሌባ መጠበቅ ግዴታቸው ነበር። ሲነጋም እንደዛው በጠዋት መሳሪያዎቻቸውን አወጣጥተው ሥራቸውን ይጀምራሉ።

ከዚያም ለሁለት በወጉ ያበጃጁትን አዲስ የሶፋ ምርት የሚገዛቸው የመንደር ነዋሪ ባይኖርም ወደኡራኤል አካባቢ ለሚገኙ ነጋዴዎች ጋር ያስረክባሉ። አንዱን ሶፋ በስድስት ሺ አምስት መቶ ብር ያቀርባሉ። ነጋዴው ደግሞ ጨምሮ ለተጠቃሚ ይሸጠዋል።

የሶፋ ሥራቸው ጥራት በእጅጉ በመጨነቃቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰው በሰው እየተነጋገረ ገበያው ደርቶላቸዋል። የእጆቻቸውን ውጤት ያዩ ነጋዴዎች በየጊዜው ለእኔም አቅርቡልኝ የሚለው ጥያቄያቸው በመጨመሩ ቀንና ማታ እየሰሩ ገቢያቸውንም ማሳደግ ችለዋል።

በዚህ ወቅት ግን ትልቅ ፈተና ከፊታቸው ተጋረጠ። የአካባቢያቸው ቀበሌ አስተዳደር ሰዎች ሸራ ወጥረው የሚሰሩበትን ቦታ ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላለፉባቸው። በየጊዜው እየሄዱ ቦታው ላይ ለመስራት ፍቃድ ስለሌላቸው እንዲለቁ ወተወቷቸው። የወንድማማቾቹ ሁልጊዜ የጸና መልስ ደግሞ «ተለዋጭ ቦታ ይሰጠን እና እንለቃለን፤ አለበለዚያ ግን የመስሪያ ቦታችንን ትተን አንሄድም» የሚል ነበር።

የቀበሌ የሥራ ኃላፊዎቹ ወንድማማቾቹ ሥራቸውን በአግባቡ እየሰሩ መሆኑን በተለያየ መንገድ ካጣሩ በኋላ ተለዋጭ የሥራ ቦታ እንደሚሰጣቸው ወሰኑ። የሥራ ትጋታቸውን ያዩት የቀበሌው የሥራ ኃላፊዎች መነን አካባቢ «ለሥራ ፈጣሪ ወጣቶች» ተብለው ከተገነቡት ሼዶች መካከል ለረጅም ጊዜ የተዘጋች ቤት ነበረችና እሷን ለወንድማማቾቹ

 ሊሰጡ ተስማሙ።

ወንድማማቾቹ ቦታውን ካዩ በኋላ ለሥራቸው እንደሚመቻቸው ስላወቁ የሥራ ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደተዘጋጀላቸው መስሪያ ቦታ ገቡ። በዚያም ለተለያዩ ደንበኞቻቸው የሚሆኑ የቤት እና የቢሮ የእንጨት መገልገያዎችን ማዘጋጀታቸውን ተያያዙት።

ቀድሞ የሳሙና ተብሎ በሚከፈላቸው ቤት አብረዋቸው ሲሰሩ ከነበሩ ወጣቶች መካከል የተወሰኑትን ቀጥረው ማሰራት ጀመሩ። በመቶዎች የሚቆጠሩ አልጋ፣ ብፌ፣ የህጻናት እና የአዋቂዎች የልብስ መደርደሪያዎች እና ሌሎችንም የእንጨት ውጤቶችን በጥራትና በብዛት በማምረት ለገበያ አቀረቡ።

ይህን ጥረታቸውን የተመለከቱ እና አዲስ አበባ ሽሮሜዳ አካባቢ የሚገኙ የግብረሰናይ ድርጅት ኃላፊዎች ሥራቸውን የሚያቀላጥፉበት አንድ ማሽን በስጦታ አበረከቱላቸው። ማሽኑ በደቂቃዎች ልዩነት ያላለቁ የእንጨት ምርቶችን ቀለም ሊቀባ የሚችል ኮምፕሬሰር የተባለ መሳሪያ ነበር።

መሳሪያው 200 ሊትር ቀለም ወይንም ፈሳሽ መያዝ የሚችል እና በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ሰዓታት የሚወስደውን ሥራ በማቃለል ረገድ ከፍተኛ ጥቅም ነበረው። ይህን ያገኙት ወንድማማቾች የበለጠ የመስራት ፍላጎታቸው ተነሳሳ።

የመስራት ፍላጎታቸውን የሚፈታተን ጉዳይ ግን ሁሌም ያጋጥማቸው ነበር። በተለይ ያዘዙት ምርት አልቆ ከተረከቡ በኋላ ገንዘብ ቶሎ የማይከፍሉ ሰዎች ያጋጥሟቸዋል። አልፎ ተርፎም ሙሉ ክፍያውን የሚያስቀሩ ሰዎች ከፈተናዎቻቸው መካከል ዋናዋናዎቹ ናቸው። በገንዘብ እጥረት ምክንያት ለአንድ ዓመት የሥራ ቦታ ኪራይ ያልከፈሉበትም ወቅት ነበር። ሼዶቹን ያሰራው ወረዳ ግን እስኪቋቋሙ ድረስ የኪራይ ሒሳቡን ባይከፈሉም ታግሷቸዋል።የተሰሩ ምርቶችን የሚገዛ ሰው ጠፍቶ ገበያው ሲርቅ ወንድማማቾቹ በየፊናቸው ተሰማርተው ገበያ የማፈላለጉን ሥራም የሰሩበት ጊዜ አለ።

ተስፋ መቁረጥን የማያውቁት ወንድማማቾቹ ባለፈው ነገር ከመቆጨት ይልቅ ሥራቸውን እያጎለበቱ መሄዱን ነው የሚመረጡት። በምስል እና በኢንተርኔት የተመለከቷቸውን የውጭ አገራት ምርቶች በተካነ እጃቸው አስመስለው በማምረት ማቅረብ ሁሌም የጥረታቸው አንድ አካል ነው።

ወንድማማቾቹ ቻይና የሚመረቱትን የእንጨት ውጤቶች በአገር ውስጥ ጥሬ እቃ በመተካት በጥራት እያመረቱ ወደገበያ ማስገባታቸውን ቀጥለዋል። የጣውላ የወለል ምንጣፍ (ፐርኬ) እና ዘመናዊ የቆዳ ሶፋዎችን እንዲሁም የእቃቤት ማስቀመጫ ምርቶችን (ኪችን ካቢኔት) በስፋት ያመርታሉ። በሂደት የሥራ ሁኔታቸው እያደገ ስለመጣ በአንድ የሥራ ቦታ ብቻ መወሰን እንደሌለባቸው ወንድማማቾቹ ተስማምተዋል።

ስለዚህ መገናኛ አካባቢ የምርት መሸጫ ቦታ ተከራይተው እየሰሩ ነው። ታላቅ ወንድም የተመረቱ ሶፋዎችን እና ኪችን ካቢኔቶችን እንዲሁም ሌሎቹንም ምርቶች የሚያስተዋውቁበት እና የሚሸጡበት ቦታ ውስጥ ይገኛል። ትልቁ ከቆዳ የተሰራ ሶፋ በ35ሺ ብር መካከለኛውን ደግሞ በ16 ሺ ብር ያቀርባሉ።

ተመሳሳዩ ከውጭ አገራት የሚገባው የቆዳ ሶፋ ምርት ከ70 እስከ80 ሺ ብር እንደሚያወጣ የሚገልጹት ወንድማማቾቹ እነርሱ በአነስተኛ ወጪ እና በጥራት እንደሚያቀርቡ ይናገራሉ። የጥራት ተወዳዳሪነታቸውን ከደንበኞቻቸው እማኝነት በተጨማሪ አቢሲኒያ የተሰኘው የሽልማት ድርጅት በርቱ ብሎ እንደሸለማቸው በመግለጽ ለጥራታቸው ምስክር አድርገው ያቀርቡታል።

በተመሳሳይ ከውጭ የሚገቡ የፈርኒቸር ውጤቶች በአገር ውስጥ አምራቾች መስራት ቢችሉም በርካታ ተቋማት ግን ለቢሮ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች በውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ነው ትኩረታቸው። ይሁንና እንደእነርሱ ላሉ አምራቾች ዕድሉን ቢሰጡ በጥራትም ሆነ በዋጋ አዋጭ የሆኑ ምርቶችን ማግኘት እንደሚችሉ ይናገራሉ። በተጨማሪም በርካታ የውጭ ምንዛሪ የሚወጣበትን ምርት አስቀርቶ በአገር ሃብት እና ዕውቀት በርካታ ገንዘብ መቆጠብ ይቻላል።

ሁለቱ ወንድማማቾች አሁን ላይ ሥራቸውን ለማሳለጥ የሚያስችላቸውን አንድ የቤት መኪና ገዝተዋል። ቤተሰባቸውንም በአግባቡ እየረዱ እና እያስተዳደሩ ታላቅየው ቤተሰብ መስርቶ አንድ ልጅ ወልዷል። ታናሽ አሁንም ከቤተሰብ ጋር ቢሆንም በቅርቡ የእራሱን ህይወት እንደሚጀምር አቅዷል። የወንድማማቾቹ ጥረት ከቀን ወደቀን ገቢያቸውን እያሳደገው በመሆኑ አጠቃላይ ሃብታቸው አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚገመት ይናገራሉ። በሥራቸው ሦስት ሠራተኞችን ያስተዳድራሉ።

ወጣቶቹ ውጥናቸው ሰፊ በመሆኑ ነገ ላይ የፋብሪካ ባለቤት እንደሚሆኑ አስበው እየሰሩ ይገኛሉ። ቀጣይ እቅዳቸው በውጭ አገር ተመርተው የሚገቡ ማናቸውንም የእንጨት ምርቶችን በአገር ውስጥ አምርተው የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት ነው። ለዚህም ሰፊ ሥራ የሚሆኑ ማሽኖችን የማስገባት ፍላጎት አላቸው። ከእነርሱ ጥረት በዘለለ ግን የህብረተሰቡ ብሎም የተቋማት በአገር ውስጥ ምርት የማመን ልምዱ መዳበር እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

በተለይ በተለይ ወጣቶችን አደራጅተው የሚሰሩ ተቋማት እራሳቸው ደግሞ ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ የውጭ አገራት ምርቶችን ሲገዙ ማየት ለአምራቹ ተስፋ የሚሰጥ ተግባር አለመሆኑን ይናገራሉ። በመሆኑም በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የሚሰሩ ምርቶችን በመግዛት ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት በእጅጉ ለታሰበበት ይገባል የሚለው መልእክታቸው ነው።

ከዚህ በዘለለ ግን ማንኛውም ለሥራ የተነሳሱ እጆች ጥራት እና ውበትን ካጣጣሙ በአምራች ዘርፍ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆነው ገቢያቸውን የማያሳድጉበት ምክንያት እንደማይኖር ይናገራሉ። ለወጣቶችም የሞራል ብርታት የሚሆን የሥራ ህይወት እንዳላቸው በመግለጽ ማንኛውም ሰርቶ መለወጥ የሚፈልግ ሰው ቢያማክራቸው መልሳቸው «ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሥራ አቅም በሙሉ ተጠቅመን ስላልጨረስን በአገራችን እየሰራን እራሳችንን እንለውጥ» መሆኑን ይገልጻሉ። መልካም ቅዳሜ!!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 12/2011

በጌትነት ተስፋማርያም