ስትሮክ

125

 ስትሮክ (መግቢያ)

እንደሚታወቀው አንጎላችን በዋናነት የሰውነ ታችንን ሥርዓት የሚቆጣጠር አንዱ እና ዋነ ኛው ክፍል ነው። አንጎላችን እንደ ማንኛውም የሰውነታችን ክፍል በአግባቡ ለመስራት የተ መጣጠነ እና ያልተቋረጠ ምግብ፣ ኦክስጅን እንዲሁም ለስራው አስፈላጊ ነገሮችን ማግኘት ይኖርበታል። እነዚህ አስፈላጊ ግብአቶችን አንጎ ላችን ካሉት የደም ቧንቧዎች በመጠቀም ወደ ተለያዩ የአንጎላችን ክፍሎች እንዲደርሱ ያደርጋል። በአንድ አንድ ክስተቶች አንጎላችን እነዚህን ለስራው አስፈላጊ ግብአቶች ለአጭርም ሆነ ረዘም ላለ ጊዜ የተቋረጠበት እንደሆነ ችግሮችን ይዞ ይመጣል። የሚከሰተውም የችግር መጠን በተለያዩ ሁኔታዎች የሚወሰን ነው።

ለምሳሌ፡- እንደተዘጋው የደም ቧንቧ እና እሱን የሚመግበው የአንጎል ክፍል ይወሰናል። በተጨማሪ የተዘጋው የደም ቧንቧ ለአጭር ወይንም ለረዥም ጊዜ ተዘግቶ የሚቆይበት መጠንም የችግሩን መጠን እና ክብደት ይወስነዋል።

ስትሮክ

ስትሮክ ማለት አንጎላችን በበቂ ሁኔታ ደም ሳያገኝ ሲቀር የሚከሰት የህመም አይነት ነው። ይህም ሲሆን በደም ውስጥ ለአንጎል ስራ የሚሆኑ የተለያዩ ግብአቶች ለምሳሌ እንደ ምግብ፣ ኦክስጅን፣ በበቂ ሁኔታ ስለማያገኙ አንጎላችን ስራውን በአግባቡ ለመስራት ያዳግተዋል። ይህ ክስተት ሲከፋም ለሞት እንዲሁም ለቋሚ ተያያዥ መዘዞች ያጋልጣል። የስትሮክ ህመም ድንገተኛ እና አጣዳፊ (Medical Emergency) ተብለው ከሚጠሩ የህመም አይነቶች አንዱ ነው። ስለሆነም አስቸኳይ የህክምና እርዳታ የሚያስፈልገው ነው። ይህ በሚሆንበት ጊዜ አንጎልን ለበለጠ አደጋ እና ተያይዘው ከሚመጡ መዘዞች /Compvications/ መከላከል ይገባል።

በአሁኑ ወቅት ከቀደምት ጊዜያት ሲነፃፀር በዓለማችን በተለይም በሰለጠነው ዓለም በስትሮክ እና በተያያዥ ህመሞች ወይንም መዘዞች የሚሞቱ እና የሚጠቁ ሰዎች ቁጥራቸው በከፍተኛ መጠን ቀንስዋል። ለዚህም ለህመሙ የሚሰጠው ትኩረት እና ህክምና በዋናነት ይጠቀሳል።

የስትሮክ አይነቶች እና መምጫቸው

የስትሮክ ህመም ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የሚከፈል ነው።የመጀመሪያው የስትሮክ አይነት ኢስኬሚክ ስትሮክ (Ischemic Strok) የሚባለው ሲሆን ከሁሉም የስትሮክ አይነቶች በብዛት የሚከሰት ነው። የስርጭቱ መጠንም 80በመቶ ነው። የዚህ የስትሮክ አይነት አመጣጥ የደም ቧንቧ መዘጋት ወይንም በመጥበብ የሚመጣ ነው።

ለዚህም ሁለት ምክንያቶች በአበይነት ይጠቀሳሉ። አንደኛው ከፍተኛ የሆነ የኮሌስትሮል መጠን በደም ቧንቧዎች ላይ በመለጠፍ የደም ቧንቧዎች እንዲጠቡ እና ደም በአግባቡ እንዳይተላለፍ ያደርጋል። ሌላም እንደ ምክንያትነት የሚጠቀሰው የረጋ ደም ከሌላ የሰውነታችን ክፍል በመነሳት አንጎላችን ውስጥ የሚገኙትን የደም ቧንቧዎች ውስጥ በመወተፍ የደም ዝውውሩን ይዘጋሉ።

ሁለተኛው የስትሮክ አይነት ሔሞራጂክ ስተሮክ /Hemorrhagic/ የሚባለው ነው። ይህ በአንጎላችን ውስጥ የሚገኙ የደም ቧንቧዎች በሚሸነቆርበት ወይም በሚበጠሱበት ጊዜ የሚከሰት የስትሮክ አይነት ነው። የዚህ አይነቱ የስትሮክ መፈጠር የተለያዩ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን በግንባር ቀደምት የሚጠቀሰው የደም ግፊት በሽታ ነው። ሌሎች እንደ የአንጎል እጢ፣ የደም ቧንቧ የአፈጣጠር ችግር፣ የጭንቅላት አደጋ ወ.ዘ.ተ እንደ አንድ አምጪ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ።

የህመሙ ምልክቶች እና አጋላጭ ሁኔታዎች

አንድ ሰው በስትሮክ ህመም የመጠቃት እድሉን ከፍተኛ ከሚደርጉ ዋና ዋና ሁኔታዎች ውስጥ የአኗኗር ዘይቤ እና ተጨማሪ የጤና እክሎች ይጠቀሳሉ። እነዚህ አጋላጭ ሁኔታዎች እንደሚከተሉት ናቸው።

 • ከልክ በላይ ውፍረት (ክብደት)
 • የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ
 • የሲጋራ፣የአልኮል፣ የአደንዛዥ ዕፅን መጠቀም ሲሆኑ ተጨማሪ ህመሞች እንደ፡-
 • የደም ግፊት
 • የስኳር ህመም
 • ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን
 • የልብ ህመም እና የልብ ምት ህመም

ከላይ ከተጠቀሱት አጋላጭ ሁኔታዎች ውጪ እንደ እድሜ መግፋት (ከ 55 ዓመት በላይ መሆን) የህመሙን የመከሰት እድሉን ይጨምራሉ። እንዲሁም የስትሮክ ህመም በወንዶች ላይ እና በዘራቸው የስትሮክ ህመም ያላቸው ሰዎች ላይ የመከሰት እድሉ ከፍ ያለ ነው።

የስትሮክ ህመም ምልክቶች የተለያዩ እና እንደተጠቃው የአዕምሮ ክፍል የሚወሰኑ ናቸው። ነገር ግን በአብዛኛው የስትሮክ ህመም የሚከተሉትን ምልክቶች የሚያሳይ ነው።

 • የፊት ወደ አንደኛው ወገን መጣመም ወይም መዞር፤
 • የእጅ እና የእግር መስነፍ /እንደፍላጎት አለመታዘዝ/፤
 • ለመናገር አለመቻል ወይም የማይገቡ ቃላትን ማውራት፤
 • አንዳንድ ጊዜ እራስን መሳት፤ የመዘባረቅ ሁኔታ፤ ያልተለመደ የሰውነት እንቅስቃሴ (መንቀጥቀጥ) ሊኖር ይችላል።

እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን የህመም ምልክቶች በሚያዩበት ጊዜ በአፋጣኝ ወደ ህክምና መውሰድ አስፈላጊ ይሆናል። ሀኪምዎ የተለያዩ ምርመራዎችን የሚያዙ ሲሆን፤ የስትሮኩን አይነት እና መጠን ለማወቅ እንደ ሲቲ እስካን፣ ኤም አር አይ (MRI) የሚታዘዙ ምርመራዎች ናቸው። ሌሎች እንደ ልብ ምርመራ፣ የስኳር ምርመራ፣ የኮሌስትሮል ምርመራ ከሚደረጉ ምርመራዎች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።

የስትሮክ ህክምና

የስትሮክ ህክምና እንደተፈጠረው የስትሮክ አይነት ማለትም (የደም ቧንቧ መዘጋት ወይም የደም መፍሰስ) የሚወሰን ነው። ለሁለቱ የሚደረገው ህክምና የተለያየ ቢሆንም፤ ለሁለቱ የስትሮክ አይነቶች የሚደረግ የጋራ (ተመሳሳይ) ህክምና አለ። ለምሳሌ ፊዚዮ ቴራፒ (physiotherapy) የደም ግፊትን መቆጣጠር፣ የስኳር መጠን መቆጣጠር፣ የስኳር መጠን መቆጣጠር፣ እንደ አስፈላጊነቱ ከመዘዞቹ ጋር ተያዘው የሚሰጡ ህክምናዎች አሉ።

የስትሮክ ህመም መዘዞች

የስትሮክ ህመም በጊዜያዊነትም ሆነ በቋሚነት የተለያዩ መዘዞችን ይዞ ሊመጣ ይችላል። ከእነዚህም መዘዞች መካከል፡-

 • የተጎዳው የሰውነት ክፍል ማለትም (የእጅ፣ የእግር በቋሚነት ወይንም በግዜያዊነት መስነፍ ወይንም ሙሉ በሙሉ አለመታዘዝ
 • ለመናገር ወይም ለመዋጥ መቸገር ከዚሁ ጋር ተያይዞ ምግብ ወይም ፈሳሽ ወደ ሳንባ በመግባት የሳንባ ምች እንዲፈጠር ያደርጋል።
 • የማስታወስ ችግር እና የማገናዘብ ችግር
 • የስነ አዕምሮ ችግር እንደ ድባቴ እና የመዘባረቅ ባህሪ
 • በስትሮክ የታመሙ ሰዎች ብዙውን ጊዜ እራሳቸውን ችለው እንቅስቃሴ ስለማያደርጉ አብዛኛውን ግዜአቸውን በአልጋ ላይ ያሳልፋሉ። ይህ በሚሆንበት ግዜ እንደ ደም መርጋት፤ የሰውነት በመቀመጫ በትከሻ፣ በተረከዝ ላይ የሚፈጠር ቁስለት እንዲፈጠር ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ የጡንቻ መሟሸሽና የመገጣጠሚያ መድረቅ ይፈጠራል።

ከላይ ስለ ስትሮክ ህመምና ስናወራ ህክምናው እነዚህን መዘዞች መካከል እና ከተፈጠሩ ደግሞ አስፈላጊውን ህክምና ያደርጋል። ከሚደረጉ መከላከሎች መካከል፡-

 • የደም ማቅጠኛ መስጠት /በሐኪም የሚታዘዝ/
 • የፊዚዮ ቴራፒ ህክምና /በባለሙያ የሚሰጥ/
 • በየጊዜው የስኳር ምርመራ እና ህክምና። የደም ግፊት ምርመራ እና ህክምና፤
 • በሰውነታቸው በመተኛት እና ባለመንቀሳቀስ የሚወጣውን ቁስል ለመከላከል በየጊዜው ማገላበጥ እና በተለያዩ የሰውነታቸው ክፍላቸው እንዲተኙ ማድረግ።

ህመሙ ከመከሰቱ በፊት መደረግ ያለበት ጥንቃቄ

1. የደም ግፊት እና የስኳር መጠን ምርመራ ማድረግ፤

2. የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፤

3. የሰውነት ክብደት መቀነስ፤

4. የአጠቃላይ ምርመራ እንደአስፈላጊነቱ በማድረግ እና ሀኪም የሚያዘውን መድሃኒትንም ሆነ ምክርን በአግባቡ መተግበር

5. የአልኮል መጠጥ፣ ሲጋራ፣ እንዲሁም አደንዛዥ ዕፅን የሚጠቀሙ እንደሆነ ማቆም ናቸው።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2011