ማኅበሩ የመንገድ ላይ ልመናን ለማስቀረት ከባንኮች ጋር መሥራት ጀምሯል

17

የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ማኅበር ለኩላሊት እጥበት ገንዘብ እየተቸገሩ ያሉ ወገኖችን ለማገዝና የመንገድ ላይ ልመናን ለማስቀረት ከባንኮች ጋር መሥራት መጀመሩን አስታወቀ።

የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ እንደገለጹት፤ የመንገድ ላይ ልመናን ለማስቆምና ህሙማኑን በቋሚነት ለመርዳት ከባንኮች ጋር አብሮ ለመሥራት አዲስ ፕሮጀክት ተጀምሯል። ለዚህም በአገራችን ባሉ አሥራ ሰባት ባንኮች በየአንዳንዳቸው የድጋፍ ገቢ ማስቀመጫ የሂሳብ ሳጥን ተከፍቷል። ይህንንም ባንኮቹ ለየቅርንጫፎቻቸው አስታውቀዋል።

ከዚህም በተጓዳኝ ሠራተኞቻቸው በየወሩ ሃያ ብር ከደመወዛቸው እየቀነሱ እንዲያዋጡ ማኅበሩ የጠየቀ ሲሆን፤ ይህም ከተሳካ በድምሩ በባንኮች ካሉ አንድ መቶ ሺህ ሠራተኞች በወሩ መጨረሻ ሁለት ሚሊዮን ብር ይሰበሰባል። የሚሰበሰበውም ገንዘብ ከሌሎች ተቋማት ከሚገኙ ድጋፎች ውጪ ብቻውን የተቸገሩና በጎዳና ላይ የሚለምኑ መቶ ሰዎችን ወርሃዊ የኩላሊት እጥበት ወጪ ሙሉ ለሙሉ ይሸፍናል።

አቶ ሰለሞን እንደተናገሩት፤ በመኪና ላይ በየጎዳናው የሚደረገው ልመና በአንድ ጎን በአካባቢው ያለውንና የሚንቀሳቀሰው ሰው ላይ የስነልቦና ጫና የሚያሳድር ነው። አልፎም ህሙማኑ በዚያን ዓይነት ልመና አንድ ሰው ከሚሰጣቸው አንድ ብር ላይ ከወጪ ተርፎ የሚደርሳቸው ሰላሳ ሳንቲም ብቻ ነው። ይህም ደግሞ በቋሚነት ሊደግፋቸው የሚችል አልሆነም።

ማኅበሩ «ከራስ ቀንሶ ለራስ ማዋጣት» በሚልም እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰለሞን፤ በዚህም ሰዎች በየባንኮቹ በተከፈቱ የሂሳብ ቁጥሮች ከአስር ብር ጀምሮ ያላቸውን እያዋጡ ነው። እነዚህን ገቢዎች በማሰባሰብም በማኅበሩ ተመዝግበው ካሉ 676 ህሙማን መካከል 413 የሚሆኑትን ማገዝ እንደተቻለ ነው የገለጹት።

«እቅዳችንን ካሳካን ሁሉንም ማገዝ እንች ላለን።» ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ከባንኮች በተጨማሪ አርባ ለሚደርሱ ተቋማት ተመሳሳይ የድጋፍ ጥሪ ለማድረግና ገቢዎችን በቋሚነት ለማሰባሰብ ደብዳቤዎች እየተላኩ መሆኑንም አስታውሰዋል።

የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አያይዘውም፤ ህሙ ማን ለኩላሊት እጥበት ወደ ህክምና ማዕከላት የሚመላለሱበት የትራንስፖርት አገልግሎት በቅናሽ እንዲሆንላቸውም ከታክሲ ባለቤቶች ጋር እየተነጋገሩ ነው። ይህም ከመደበኛው ሂሳብ ውጪ በኪሎ ሜትር ዝቅ ያለ ዋጋ እንዲከፍሉ ለማድረግና ወጪያቸውን በተወሰነ መንገድ ለመቀነስ የሚያስችል እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ማኅበር ከባንኮች ጋር ያለውን የጋራ ሥራ ለማንቀሳቀስ ያስችለው ዘንድ፤ ባሳለፍነው ሐሙስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ከአስራ ሦስት ባንኮች ለተውጣጡ የባንክ ኃላፊዎች በቶም የኩላሊት እጥበት ማዕከል ጉብኝትና ገለጻ አድርጓል።

አዲስ ዘመን ሚያዝ 13/2011

 ሊድያ ተስፋዬ