የፓርቲዎች ውህደት ለተሳካ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ!

13

አገራችን ኢትዮጵያ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጎሪጥ ከሚታዩበት፣ አልፎም ተርፎ እንደ አውሬ ከሚታደኑበት ዘመን ወጥታ ለዴሞክራሲ ሥርዓቱ ወሳኝ አካል መሆናቸው በታመነበት የለውጥ ዘመን ውስጥ ትገኛለች፡፡

ከሰባት ወር በፊት በዜጎች ርብርብ በሀገሪቱ እውን የሆነውን ለውጥ ተከትሎም መንግሥት በስደት የሚገኙትም ሆነ መሣሪያ አንግበው ጫካ የገቡት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቀሴ ውስጥ በነፃነትና በንቃት እንዲሳተፉ ለማድረግ ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው አመለካከታቸውን በነፃነት እያራመዱ ይገኛሉ፡፡

ምንም እንኳ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት የአመለካከት ብዝሃነት የሚንፀባረቅባት ለመሆን ብትበቃም የመጨረሻ ግብ ግን ይህ አይደለም፡፡ የፓርቲዎቹ በነፃነት መንቀሳቀስ መቻል ግቡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሀገርም ህዝብም የተጠሙት ይህንኑ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ፓርቲዎቹ ህዝብና መንግሥት እንዲሁም አባሎቻቸው የሚጠብቁባቸው ይህን ሥርዓት እውን እንዲያደርጉ መሆኑን አውቀው ጠንከረው መሥራት ይኖርባቸዋል፡:

ይህን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የለወጡን አቅጣጫ መከተል፣ መደገፍና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦና ተወያይቶ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአመለካከት ተመሳሳይ ከሆኑ ፓርቲዎች ጋር በመዋሀድም ጠንክረው መገኘት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ወሳኝ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ አሁን ባለው የሀገራችን ሁኔታ ግን ከ70 በላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሀገሪቱ እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ በእዚህ ሁኔታ ለየብቻቸው ተንቀሳቅሰው አይደለም ህዝብን አሳምነው መንግሥት ሊሆኑ ህልውናቸውም አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡

ከዚህ በኋላ መንግሥት እንዳለፉት የምርጫ ዘመናት የይስሙላ ምርጫ አያካሂድም፤ ለእዚህ ሰባል ይፈስ የነበረውን ግዙፍ ሀብትም ውጤቱ አስቀድሞ ለሚታወቅ ምርጫ አያውልም፡፡ ዜጎችም ሆኑ ገዥው ፓርቲ ይህ ለውጥ እንዲመጣ መስዋዕትነት የከፈሉት ለእዚህ አይደለም፡፡ አውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንጂ፡፡

መንግሥት መጪውን ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ወስኗል፡፡ ለዚህም እንዲረዳ በሁሉም ወገን ተቀባይነት ያገኙ አዲስ የምርጫ ቦርድ ሰብሰቢ ሰይሟል፤ የቦርዱን አሠራር ለማዘመንና በአጠቃላይ ሪፎርም ለማድረግም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ይሁንና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እውን ሊሆን የሚችለው ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሲኖሩ ነው፡፡ መንግሥት በሀገሪቱ በርካታ ፓርቲዎች መኖራቸውን ቢፈልግም ፓርቲዎቹ ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ መሆን የሚችሉት ተመሳሳይ ፕሮግራም ያላቸው እየተወሃዱ ሦስት እና አራት ሲሆኑ ብቻ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ይህንንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተደጋጋሚ አስገንዝበዋል፡፡

ይህ ሲሆን ፓርቲዎቹ በምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል መንግሥትም ፓርቲዎቹ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለመስጠት ይረዳዋል፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህን የመንግሥት እርምጃ በሚገባ በማጤን ለዴሞክራሲ ሥርዓቱ እውን መሆን ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ዘመኑ የመባላት ሳይሆን ተቀራርቦ የመሥራት ነው፡፡ ስለሆነም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይፈለጋል፡፡ ይህ ደግሞ አብሮ በመሥራት መዋሀድ ካለባቸውም በመዋሃድ ሊሆን ይገባል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታም የተፎካካሪ ፓርቲዎች መዋሀድ ወሳኝ ነው፡፡ በቅርቡም ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተዋህደዋል፡፡ አሳዳጁ የቀድሞው ኦህዴድ የአሁኑ ኦዴፓ እና ተሳዳጁ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በቅርቡ ተዋህደዋል፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቁ ቀደም ሲል ተዋህደዋል፡፡ ይህ አርአያነት ያለው ጅምር ሊበረታታ ይገባዋል፡፡ አሳዳጅና ተሳዳጅ መዋሃድ ከቻሉ ሌሎች የማይዋሀዱበት ምንም ምክንያት አይኖርም ብሎ መውሰድም ይቻላል፡፡

ሌሎች ፓርቲዎችም ይህ በመንግሥት፣ በህዝብና በፓርቲዎች ጭምር የታመነበትንና የሚያዋጣቸውን የመዋሀድ ሀሳብ ፈጥነው ተግባራዊ ሊያደርጉት ይገባል፡፡ የምርጫው ወቅት እየተቃረበ እንደመሆኑ መንግሥት የፈጠረውን የውይይት መድረክ በመጠቀም ለውህደት ፈጥነው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡

የፖለቲካ ምሁራን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሊዋሀዱ የሚችሉባቸውን አግባቦች በማመላከት ውህደቱን ስኬታማ ለማድረግ ድጋፍ ማድረግ የሚኖረባቸው ሲሆን፣ መገናኛ ብዙኃንም ውህደትን የተመለከቱ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስና ጠቀሜታውን በማጉላት ለውህደቱ መሳካት ጠንክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ውህደቱ ጠንካራ እንዲሆን መሥራትም ለነገ ይደር ሚባል ተግባር አይደለም፡፡ ዛሬ ተዋህደው እንደ ጨዋታው ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ አይነት የልጆች ጨዋታ ነገ የሚለያዩ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ሥርዓቱ ቀርቶ ለራሳቸውም አይጠቅሙም፡፡ ስለሆነም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጊዜ ወስደው፣ አባሎቻውን አወያይተው፣ ውህደቱን በሚገባ አምነውበትና ከአባሎቻቸውም ጋር መክረው ሊፈጽሙት ይገባል፡፡

ገዥው ፓርቲ አህአዴግ ፓርቲዎች እየተዋሐዱ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆኑ እያከናወነ ያለው ተግባር የሀገሪቱ ህዝብ ሲናፍቀው ለኖረው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እና ሥርዓት እውን መሆን ያለውን ቁርጠኝነት ያመልክታል፡፡ የፓርቲዎች እየተዋሐዱም ሆነ ግንባር እየፈጠሩ መንቀሳቀስ እንደ ጦር እየተፈራ እንዲበተኑ ሴራ ሲጠነሰስበትና የጥፋት ክተት ሲጠራበት የኖረው አካሄድ እያከተመ መሆኑንም ያስገነዝባልና ለመንግሥት ቁርጠኛ ተግባር ፓርቲዎቹ በመዋሐድ አዎንታዊ ድጋፋቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወቅቱ በጊዜ የለንም ስሜት ውህደት የሚፈጽምበት ሊሆንም ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ህዳር 25/2011