ጠንካራው የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት ማሳያ

20

ኢትዮ-ቻይና የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸው የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1970 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።ግንኙነቱ በጋራ የስልጣኔ እሴቶች ላይ የተመሰረተ እና ታሪካዊም ነው። ሁለቱም ሀገራት ግንኙነታቸውን ሲያስቡ ጥንታዊ ስልጣኔያቸውንና ረጅም የታሪክ ባለቤትነታቸውን ከግምት ውስጥ ይገባል። በመሆኑም ባለፉት አመታት በርካታ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚና ማህበራዊ ግንኙነቶችን መመስረት ችለዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ‹‹ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭ›› ላይ ኢትዮጵያና ቻይና ያላቸው አጋርነት ተጠቃሽ ነው።

‹‹ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭ›› የቻይና መንግስት አዲሱ አለም አቀፍ የልማት ፕሮጀክት ሲሆን በፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ተቀርፆ በፈረንጆቹ 2013 መስከረም ላይ ይፋ የሆነ ከ4 እስከ 8 ትሪሊዮን ዶላር ወጪ ይደረግበታል ተብሎ የሚገመት ነው።

ይህ ፕሮጀክት አውሮፓንና እስያን ማዕከል አድርጎ በአፍሪካና ሌሎች ክፍለ አህጉሮች የሚገኙ ሀገራትን የየብስና የውሃ ትራንስፖርትን ጨምሮ በዘርፈ ብዙ መሰረተ ልማቶች ለማስተሳሰር የተነደፈ እቅድ ነው። ዋነኛ አላማው ደግሞ በሀገራቱ መካከል የኢኮኖሚ ትብብርን ማሳደግ ነው። ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን የሚያካትት በመሆኑ በተግባራዊነቱ ትሰራለች።

የ‹‹ቤልት ኤንድ ሮድ›› የመጀመሪያ ፍኖተ ካርታ 65 ሀገራት ላይ የሚያርፍ ቢሆንም ማንኛውም ለመሳተፍ ፈቃደኛ የሆነ ሀገር የሚቀላቀልበት ይበልጥ እየሰፋ ለመሄድ ክፍት የሆነ ሁሉን አቀፍ የልማት ስትራቴጂ በመሆኑ ኢትዮጵያም ለተግባራዊነቱ የድርሻዋን ትሰራለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ትናንት በቤጂንግ ተገናኝተው በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው ግንኙነትና በ‹‹ቤልት ኤንድ ሮድ›› ፕሮጀክት ዙርያ መክረዋል። ሀገራችን ኢትዮጵያም በዚህ ፕሮጀክት ማዕቀፍ ከቻይና ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ፈቃደኝነቷን ከመግለፅ ባለፈ በጉባኤው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራ የልኡካን ቡድን ይሣተፋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ሁለቱ ሀገራት ያላቸው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግንኙነት ከፍተኛ የመተማመን ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳየ ውይይትና ስምምነቶችን አከናውነዋል። ይህም የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት አሁንም በመተማመንና በመደጋገፍ ወደ ላቀ ደረጃ መድረሱን ማሳያ መሆኑ መታወቅ አለበት።

በውይይቱ ወቅትም ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የኢትዮጵያን እስከ ፈረንጆች 2018 መጨረሻ ድረስ የተጠራቀመ የብድር ወለድ ሙሉ በሙሉ መሰረዛቸውን ይፋ አድርገዋል። ይህ ለለውጡ አመራርም ለሃገርም ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ነው።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለኃይል ማሠራጫና ማከፋፈያ መሥመር ዝርጋታ ከተለያዩ ኩባንያዎች የስራ ሃላፊዎች ጋር በአደረጉት ውይይት የ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ ለሁለቱ አገራት በተለይ ደግሞ ለአገራችን ኢትዮጵያ ትልቅ ፋይዳ አለው። በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባው የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ማሳያም ነው። የኢፌዴሪ መንግስት የውጭ ግንኙነት ስራ ውጤታማነትም አመላካች ነው።

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት ለማሳደግ የምታከናውናቸው ተግባራትና እየተገኙ ያሉ ውጤቶች የሃገራችን የውጭ ግንኙነት ስራ ፍሬያማነት ያረጋገጠ ሆኗል።

ቻይና ለኢትዮጵያ የሰረዘችው የብድር ወለድ ሆነ ለኃይል ማሠራጫና ማከፋፈያ መሥመር ዝርጋታ የተደረገው ስምምነት አገሪቱ አሁን ያለባትን የውጭ ምንዛሬ ከመደጎሙ ባለፈ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት የተጀመረው ሃገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴውን በቀጥታ የሚደግፍ ነው።

በዚህም ሁኔታ ቻይና አሁኑ ያለውን ለውጥ ሂደት መደገፏን በፕሬዚዳንቷ አማካኝነት አረጋግጣለች። ኢትዮጵያም ይሕን እድል በሚገባ እየተጠቀመችበት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አመልክተዋል።

ሁለቱ አገራት ታሪካዊ የሚባል የፖለቲካል ኢኮኖሚ ድጋፍ ውስጥ ሲገቡ አንዱ በአንዱ ላይ ጫና ሳይሆን አቅም በመፍጠር ላይ ያተኮረ ነው። ቻይና ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ኢትዮጵያ ላስመዘገበችው የኢኮኖሚ እድገት አቅም ሆና ዛሬ ላይ ደርሳለች። ዛሬም ድጋፍ እያደረገች ነው። ይህ የሚያሳየው የሁለቱን አገራት ግንኙነት ጠንካራና በመተማመን ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው።

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2011