የፕሬስ ነጻነት ሌጣ ፈረስ አይደለም፤ የራሱን ልጓም ይፈልጋል!

15

 የፖለቲከኞች ዋነኛ አጀንዳ ነው። ብዙሃን ለእነዚህ መብቶች መከበር የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ከፍለዋል። የሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎቶችም ናቸውና ሊያፍኗቸው የተንቀሳቀሱ መንግሥታት መጨረሻም አላማረም። ለብዙዎች ከስልጣን መውረድም ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው። የሰብዓዊና ዴሞክራሲ መብቶች!

በአገራችንም ለንጉሳዊውም ሥርዓትም ሆነ ለደርግ አገዛዝ መውደቅ ዋነኛዎቹ ምክንያቶች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ረገጣ መሆናቸው ግልጽ ነው። በኢህአዴግ አገዛዝ ዘመንም ምንም እንኳን አገሪቱ እስካሁን ከመጣችበት ታሪክ ጋር ሲነጻጸር በሰብዓዊ መብት አያያዝም ሆነ በዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የተሻለ ነገር ቢኖርም ከህጸጾች የጸዳ አልነበረምና ለህዝቦች አመጽ ዋነኛ መንስዔ መሆኑ አልቀረም። ሥርዓቱ ባመጣው የልማት ድልና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የተነሳ የሚያሞግሱት እንዳሉ ሁሉ በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መጣስ ግን ያለመታከት ሲከሱት ኖረዋል።

ዴሞክራሲያዊ መብትን ስናነሳ በግንባር ቀደምትነት የሚነሳው ደግሞ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ወይም የፕሬስ ነጻነት ነው። ሰው በተፈጥሮው ነጻነቱን የሚሻ ፍጡር ነውና ሀሳቡን በተለያዩ መንገዶች መግለጽን ይፈልጋል። ይህ ሀሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብቱ በማንም አካል እንዲታፈንም አይፈቅድም። ይህን መብቱን የሚጋፋው አካል ሲኖርም ምላሹ ተቃውሞና አመጽ ይሆናል። ለዚህም ነው በተለያዩ ቦታዎች ከሚነሱ አመጾችና ህዝባዊ እምቢተኝነቶች ጀርባ የዴሞክራሲ መብት ይከበር የሚለው ጥያቄ ሁሌም የሚኖረው።

በአገራችን በተለይም በዘመነ ኢህአዴግ ገና ከጅምሩ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እጅግ በሚያጓጉ አንቀጾች የተገለጸ ቢሆንም በተግባር ሳይተገበር ግን ቆይቷል። ከዚህም ባለፈ በርካታ ጋዜጠኞችና ብሎገሮች በተናገሩት ንግግርና በጻፉት ጽሁፍ የተነሳ ለወህኒ በቅተዋል። ይህም ሁኔታ ከለውጡ ቀደም ብሎ ባሉ ዓመታት በአገሪቱ ለተቀሰቀሱ አመጾች ዋነኛ ምክንያት እንደነበርም አይረሳም።

በህዝቦች የመረረ ትግል በኢህአዴግ ውስጥ ለውጥ ተከስቶ አገሪቱ በለውጥ አመራር የመመራት ዕድል ስታገኝም መሻሻል ከተደረገባቸው ጉዳዮች ቀዳሚው ነገር የፕሬስ ነጻነትን የማረጋገጡ ጉዳይ ነው። በዚህም ከሃሳብ ነጻነት ጋር በተያያዘ በወህኒ የነበሩ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችና ጸሐፊዎች ሙሉ በሙሉ ከወህኒ እንዲለቀቁ ተደርጓል።

ነጻነት በማጣታቸው ምክንያት በውጭ አገር መቀመጫቸውን ያደረጉ እንደ ኢሳትና ኦ ኤም ኤንን የመሳሰሉ መገናኛ ብዙሃን ወደ አገራቸው ገብተው በነጻነት የሚሰሩበት ዕድል ተፈጥሯል። አሸባሪ የሚል ታርጋ ተለጥፎላቸው የነበሩት እነዚህ መገናኛ ብዙኃን ዛሬ ዛሬ እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው ያለምንም መሳቀቅና ይሄ ይደርስብኛል የሚል ፍራቻ ነጻ ሆነው ሥራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

እንዳይሰሩ ታግደው የነበሩ በርካታ ብሎገሮችና ዌብሳይቶችም አፈናው ተነስቶላቸው ሀሳባቸውን በነጻነት እያንሸራሸሩ ይገኛሉ። ከሚያቀርቡት ለመንግሥት እጅግ የወገነ ዘገባ የተነሳ አዝማሪ የተባለ ስያሜ ተሰጥቷቸው የነበሩ የህዝብ መገናኛ ብዙሃንም ከለውጡ ማግስት አንስቶ ደፈር ብለው መንግሥትን እየተቹና ስህተቶችን እያጋለጡ የሚሰሩበት ጅምር እንቅስቃሴ ታይቷል። በአጠቃላይ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሙሉ በሙሉ በአገራችን ተረጋግጧል የሚባልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ማለት ይቻላል።

ይሁንና መንግሥት ይህን ያህል ተነሳሽነት ወስዶ የፕሬስ ነጻነት የእውነት እንዲከበር ቢያደርግም በስመ ነጻነት ኃላፊነት በማይሰማው መልኩ የሚዘግቡ መገናኛ ብዙሃን እንዳሉም በገሃድ እየታየ ነው። ገለልተኝነት የሚለውን የመገናኛ ብዙሃን መርህ ወደጎን በመጣስ የፖለቲካ ፓርቲ እስኪመስሉ ድረስ ለአንድ ወገን ያደላ ዘገባ ማቅረብ፤ ያልተጣሩና የተፈበረኩ መረጃዎችን ማሰራጨት፤ ሥም ማጥፋት፤ መረጃዎች የሚያስከትሉትን አደጋ ሳያገናዝቡ መልቀቅን የመሳሰሉ ግድፈቶች በመገናኛ ብዙሃኑ ላይ አሁን በተጨባጭ የሚታዩ ግድፈቶች ናቸው።

እነዚህ ግድፈቶች በአገርና በህዝብ ላይ የከፋ አደጋን የሚጋብዙ ከመሆናቸውም በላይ በህዝቦች መስዋዕትነት ቦግ ብሎ የበራውን የፕሬስ ነጻነትን ችግር ላይ የሚጥሉም ናቸው። በርዋንዳ የተከሰተው የዘር አልቂት መነሻም የመገናኛ ብዙሃኑ መረን የለቀቀ ተግባር እንደነበር አይረሳም።

ለማንም ግልጽ እንደሆነው ነጻ ፕሬስ ሌጣ ፈረስ አይደለም። ለህዝብና ለአገር ደህንነት ሲባል የሚቀመጥለት የራሱ ልጓም አለው። በአጠቃላይ የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም እንደሚባለው መረን የለቀቀ ፕሬስ በሌላው አገር ላይ ያደረሰው ችግርና አደጋ በእኛም አገር ሳይደገም የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለዚህ አካሄዱ ልጓም ሊያበጁለት ይገባል!

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2011