የአዲስ አበባ ቀማኛ ‹‹ጭልፊቶች››

1802

በከተማዋ አንዱ ክፍል በሆነው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለቡ በሚባለው አካባቢ ወደ ላፍቶ ለመሄድ ባጃጅ ውስጥ ገብቻለሁ።ያዘው! ያዘው ! …የሚል ድምጽ ሰማሁ፤ወደ አንድ አቅጣጫ ሰዎች ሲሮጡም ተመለከትኩ።\

እኔም ሌሎች ባጃጇ ውስጥ የሚገኙት ተሳፋሪዎችም ወርደን ጉዳዩን መከታተል ጀመርን።ወዲያው ያዘው ያዘው የሚለው ጥሪም ቆመ፤ከግርግር በቀር ሌላ የለም።

ሁኔታውን በቅርበት የተመለከቱ ሰዎች አንድ ሌባ ከአንዲት ወጣት እጅ ሞባይል ቀምቶ ሞተር እያሟሟቀ ይጠብቀው ከነበረው ሞተር ሳይክል ላይ ወጥቶ መፈትለኩን ነገሩን።ሞተር ሳይክሉን ሊያቆመው የሞከረ አይደለም ያሰበም እንዳልነበረም ጉዳዩን በቅርበት አይቻለሁ ያሉ ገለጹልን።

ጉዳዩ አጀንዳ ሆኖን ባጃጅ ውስጥ ማውራታችንን ቀጠልን። ሁላችንም በዚያ የተንጣለለ የለቡ አዳባባይ እንኳን ይህን ዓይነት ስርቆት ሃሳቡም ይኖራል ብሎ መገመት እንደሚከብድ በውይይቱ ተነሳ፤ያም ያችም በሞተር ሳይክል እየተፈጸመ ያለው ቅሚያ የእለት ተዕለት ትዕይነት እየሆነ መምጣቱን ጠቀሱ።በአደባባዩ የትራፊክ ፖሊሶች በብዛት ይታያሉ፤ፖሊሶች አይኖሩም ብሎ ለመገመት ይከብዳል፤ግን አልነበሩም።

ይህን ወሬ ለሥራ ባልደረቦቼ ሳነሳላቸው አንድ ባልደረባችን የባሰውን ነገረችን። ሰሚት እየተባለ በሚጠራ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን መጋቢት 27 ቀን 2011ዓ.ም ንግስ ደመቅ ያለ ሥነሥርዓት ነበር።በግቢ ውስጥ ለህንጻ ማሰሪያ እና ለመሳሰሉት በሚል ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ ይሰራል።

በማግስቱ የተሰበሰበው ገንዘብ በኮሚቴ እየተቆጠረ እያለ በእዚህ መካከል በሞተር ሳይክልና በመሳሪያ የታገዙ ዘራፊዎች ገንዘብ ከሚቆጠርበት ስፍራ መጥተው ትልቁን ቦርሳ አፈፍ አርገው እግሬ አውጪኝ ይላሉ።በቆጠራ ላይ ነበሩት ምዕመናን የሚችሉትን ቢያደርጉም ዘረፋው በቪትዝ መኪናም ጭምር የታገዘ ነበርና ብን ብለው ይጠፋሉ።እነዚህኞቹ በመሳሪያም ለማስፈራራት ሞክረዋል።

የድፍረታቸውን ልክ ተመልከቱት።ደግነቱ ያ ቦርሳ ዘራፊዎቹ የቋመጡለት የቤተክርስቲያን ገንዘብ አልነበረበትም፤የአንድ ጸበልተኛ ቦርሳ ነበርና ባሰቡት ልክ አልተሳካላቸውም። ጉዳዩ ግን ዝርፊያው የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ በሚገባ ያመለክታል።የእምነት ቦታዎችን ያልማረና ያላከበረ ፣የተሰበሰበውን ህዝብ ከቁብ ያልቆጠረ በማን አለብኝነት የሚፈጸም ዘረፋ እየበዛ ለመሆኑ ሌላ ማሳያ ነው።በሞተር ሳይክል እየተፈጸመ ስለሚገኝ ዘረፋ ‹‹እህ›› እያለ አድማጭ ካለ በርካታ ነው።

በሀገራችን አንድ አባባል አለ።ስለ እባብ ፣ስለአውሬ ፣ወዘተ በጣም ሲወራ እባቡ፣አውሬው ቀርቧል ማለት ነው የሚል ። እኔም ስለእነዚህ የሞተር ሳይክል ዘራፊዎች ሳነሳ ስጥል አጠገቤ ደርሰው ይሆን ስል ጠረጠርኩ። በሞተር ሳይክል ሌቦች ቦርሳቸውን የተቀሙ ሴቶች፣ሊቀሙ ሲሉ ያስጣሉ፣ ሞባይላቸውን የተነጠቁ ሰዎች ጥቂት አይደሉም።በእዚህ ጉዳይ ላይ የከተማዋ ነዋሪዎች በሙሉ ገጠመኛቸውን እና የሰሙትን ሁሉ ያጋራሉ።

ነገርን ነገር ያነሳዋልና አዲስ አበባ በዚህ ዓይነቱ የሞተር ሳይክል ሌቦች ቅሚያ ክፉኛ ታማለች።በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች በአደባባይም በየመንደሩ ቅሚያው ተጧጡፈዋል። ከየአቅጣጫው የሚሰማውም የቅሚያ ዜና ነው። በእነዚህ ጭልፊቶች በከተማዋ ሁሉም አካባቢዎች ተመሳሳይ ድርጊቶች ይፈጸማሉ።በእርግጥም ጭልፊቶች።ይህን ድርጊት ተነስቶ በተወራበት ሁሉ ያየውን የሰማውን የማያክል የለም ማለት ይቻላል።

ፊት ያሳስብ የነበረው ሞተር ሳይክሎች ከተማዋ ውስጥ ያለ ታርጋ መንቀሳቀሳቸው፣ሲያሽከረክሩም ሥርዓት አለመጠባቃቸው ነበር።በዚህ የተነሳም በብዛት ሰዎችን እየገጩ እንደሚጠፉ ነበር የሚታወቀው። ከኋላ ታርጋ አንስተው ወይም የሀሰት ሰሌዳ ለጥፈው የሚንቀሳቀሱ ወይም ሰሌዳቸውን እንዳይታይ አድርገው የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው አደጋ አድርሰው እንደማይያዙ ነበር የሚነገረው።በእዚህ የተነሳም ግጭት ደርሶባቸው ደመከልብ የሆኑ ጥቂት አይደሉም።እነዚሁ ሰሌዳ አልባ ሞተር ሳይክሎች ሰዎችን እየገጩ እየተሰወሩ በመሆኑም አደጋ የደረሰበት ሰው ደመ ከልብ እየሆነ ነው ሲል ቆይቷል፤ ይህን የህዝቡን ቅሬታ የሰማ ግን የለም።

አሁን ሞተር ሳይክሎች እንደ ቄራ ባሉት አካባቢዎች ተራ ፈጥረው የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ውስጥ ገብተዋል፤በሌሎች አካባቢዎችም ምሽት ከየመሸታ ቤቱ ሰዎች ያመላልሳሉ ይባላል፤ሰካራም አንዱ ተገልጋይ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፤ ሰካራም ከሞተር ወድቆ በዚያ ሌሊት ቢሞት ወይም ቢጎዳ እንዲሁም ወደ አንዱ ሰዋራ ስፍራ ወስደውት በዘርፉትስ ማን ይጠየቃል? ሰካራም ስለሆነ ተብሎም የራሱ ጉዳይ አይባልም።

አሁን ችግሩ እየተባባሰ መጥቷል።ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት ሰዎች በሞተር ሳይክል በጠራራ ጸሐይ ይቀማሉ ፤ይዘረፋሉ።ሆን ተብሎ ይገጫሉ ከዚያም ይዘርፋሉ። ወደ ሞተር ሳይክል ትራንስፖርት ሥራ ውስጥ ለምን ይገባል፤በሞተር ሳይክል የሚደርስ ግጭት እየበዛ ነው፤ክፋቱ ደግሞ ገጭቶ ማምለጥ ብቻ አይደለም፤ወርዶ መፈተሽም ይኖራል ።

ችግሩ ከዚህም እየከፋ ነው። ሌቦቹ ያጋልጡናል ያሏቸውን ሰዎች ማጥቃትም ጀምረዋል። በቅርቡ ጎፋ ካምፕ አካባቢ የሆነውም ይህ ነው።ወንድም ወንድሙን እንዳያስጥል በማስፈራራት ጭምር ወንድሙን መትተው ጥለው በስለት ወግተውት አምልጠዋል። ደግነቱ እነዚህ የድርጊቱ ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል።

በዚህ ዓይነት ሁኔታ አዲስ አበቤዎች በጠራራ ጸሐይ ክፉኛ እየተዘረፉ ናቸው።በሞተር ሳይክል ስርቆት የሚፈጽምን ቀማኛን አባሮ ለመያዝ አይቻልም፤እንኳን እነሱን በእግረኛ የሚፈጸመውን ቅሚያምም ማስጣል ይከብዳል።ቅሚያው የተደራጀ ነው።ሌባ ተከታትለው የያዙ ሰዎች አጋጠመን እያሉ ያሉትም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው።የተዘረፈው ወይም ሲዘርፍ የተመለከተ ሌባ ሲከታተል ከተገኘ ዘረፋው የቡድን ነውና ተጎጂዎች ሌባ ተብለው የተደበደቡበት ሁኔታ እንዳለም ነው የሚነገረው።

በጠቆሙ ለችግር መዳረግ በዝቷልና አባረው መያዙም ለችግር እያደረገ ነውና እነዚህን ቀማኞች ማን ጠቁሞ እንደሚያስይዛቸው እንጃ። ስለዚህ ሰው እያየ ነው ቅሚያው የሚካሄደው ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በሞተር ሳይክል የታገዘ አይደለም በእግርም የሚደረግን ዘረፋ ለመቆጣጠርም ሆነ ለመከላከል የሚያስችል ሁኔታ የለም ።የሞተር ሳይክል ፍጥነት ምንም ጥቃትን ለማስቀረት አያስችልም።አያድርስ ከማለት ውጪ።

ይህ ሁሉ ሲሆን ፖሊስ አለመኖሩ ፣ ፖሊስ የት ሆኖ ነው የሚሰራው ያሰኛል። መንደር ውስጥ ዘረፋ ተፈጽሞ በአቅራቢያው ፖሊስ ሲፈለግ ከሌለ ፣ህዝብና ተሽከርካሪ እንደጎርፍ በሚፈስበት አካባቢ ፖሊስ ከሌለ የት ነው የሚገኘው ታዲያ።

በከተማዋ ከመቼውም ጊዜ በላይ በህዝብ ገንዘብ የማህበረሰብ ፖሊስ ጽህፈት ቤቶች በየመንደሩ ተገንብተው ባለቡት ሁኔታ ቅሚያ እና የተደራጀ ሌብነት እንዲህ መንገሱ በእጅጉ ያሳስባል።

ፖሊስ ቅሚያውን የፈጸሙትን ወዲያውኑ መያዝ ባይችል ተከታትሎ መያዝ ግን ይጠበቅበታል።የወንጀሉ ዓይን ያወጣ መሆን ግን ፖሊስ ምንም እርምጃ እየወሰደ አለመሆኑን ነው የሚጠቁመው።

ፖሊስ የሞባይል ስርቆትንና ሌቦችን ጉዳይ እንደ ተራ ጉዳይ እያየ ይመስለኛል።ከታክሲና አውቶብስ ተራ ሞባይል ሲሰርቁ የተያዙ ሌቦችን ይዞ ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አይወስድም።ባለቤቱ የማይፈልጋቸው ከሆነ እዚያው ምክር ቢጤ ሰጥቶ ይለቃል።

ባለቤቱ ሌቦች ቢጠየቁ ይፈልጋል።ይሁንና መክሰስ የማይፈልገው ፍርድ ቤት መመላለሱን ጠልቶ ነው።በሀገራችን ከመክሰስ ይልቅ መከሰስ ይሻላል እየተባለ ያለውም በዚህ ሳቢያ ነው።24 ሰዓት እንኳ ማረፊያ ቤት ማቆየት ፣መረጃ መሰብሰብ ፎቶውን አሻራውን መያዝ ለምን አልተፈለገም።ይህ በጣም ያሳስባል።

ይህ ችግር እየሰፋ መጥቶ ዘረፋው ወደ ሞተር ሳይል እንዲሸጋገር ሆኗል።ሰሞኑን የወጡ ዘገባዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ጥቆማዎች ደግሞ ዘረፋው ወደ በመኪና እና በመሳሪያ የታገዘ ወደ መሆን ተሸጋግሯል።መኪና ይዘው መሳሪያ ታጥቀው በቡድን ሆነው በሌሊት ዝርፊያ የሚፈጽሙ አካላት እየተበራከቱ ይገኛሉ።እዚህም ላይ አሳሳቢው ችግር ይህን ችግር ለፖሊስ ለማመልከት ጣቢያ የሄዱ ተጎጂዎች ፖሊስ አገር አማን ብሎ ተኝቶ ነው ያገኙት።ፖሊስ መረጃው ሲደርሰው ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ መንቀሳቀስ ሲገባው ተኝቶ የሚገኝ ከሆነ ይህ ዝርፊያ የበለጠ እየተስፋፋ መልኩን እየቀየረ እንደሚሄድ ጥርጥር አይኖረውም።

ወንጀለኞችን ለመያዝ የህብረተሰቡ ትብብር ወሳኝ ነው የሚለው የፖሊስ የዘወትር ጥያቄ በቀጣይ ምላሽ አያገኝም። መረጃ ሰጥቶ መጎዳትና መሞት የሚፈልግ አይኖርም። የሚያስጥለው ይፈልጋል።ድርጊቱ የሚፈጸመው በተደራጀ አግባብ እንደመሆኑ ይህን ለማጋለጥ የሚመክሩ ወገኖች የበለጠ ለአደጋ እንደሚጋለጡ ስለሚያስቡ ዝምታን ይመርጣሉ።

ሌቦቹና ዘራፊዎቹ ህብረተሰቡ ውስጥ ስለመሆናቸው ጥርጥር የለውም።ለዚህም ነው የህብረተሰቡ ትብብር የሚጠየቀው።ሊስትሮዎችና የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ለፖሊስ እንደሚተባበሩ ይታወቃል።ወንጀል መከላከል ሥራ እንደሚተባበሩ የሚገልጽ ጃኬት ለብሰውም ይታያሉ።ይሁንና አንድ ሌባ አሰልፈው ስለመስጠታቸው የሚታወቅ አይመስለኝም።እንዲሰሩ ተደርጎ ቢሆን በየአደባባዩ በሌባ እየተበረበሩ መሄድ የሚባል አይኖርም ነበር፤የሞባይል ስርቆት የቀልድ ያህል አይቀልም ነበር።

ፖሊስ አሁንም ራሱን በመፈተሽ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በራሱ መንገድ ይህን ድርጊት ማቆም ይኖርበታል። የወንጀል መከላከል አለበለዚያ ስርቆቱ ለእነሱም አይመለስም። ፖሊስ አይሰረቅም ያለው ማነው፣ ይሰረቃል፤ህይወቱንም ሊያጣ ይችላል።

በአንድ ከተማ ነዋሪዎች በሰላም ወጥተው በሰላም የማይመለሱ ከሆነ ፣በየጎዳናው የሚዘረፉ ህይወታቸው አደጋ ውስጥ የሚገባ ከሆነ ፣ድርጅታቸው ሥራቸው የሚዘረፍና ህልውናቸው አደጋ ውስጥ የሚገባ ከሆነ ችግሩ ለመንግሥትም ይሆናል።እነዚህ ሌቦች ከህብረተሰቡ የሚሰርቁት ላይበቃቸው ይችላል፤በዚህ የተነሳ ገንዘብ የሚሰጣቸው የትኛውም አካል የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ከመፈጸም አይመለሱም።

ይሄኔ ችግሩ ይበልጥ ቤቱን ስለሚያንኳኳ መንግሥት የሚወሰድው እርምጃ ህብረተሰቡን ሳይሆን ራሱን የሚከላከል ስለሚሆን ይህ ከመሆኑ በፊት አሁን የአዲስ አበባ ጭልፊት የሆኑትን በሞተር ሳይክል የታገዘ ቅሚያ ፈጻሚዎች መቆጣጠር ይገባል።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2011

በዘካርያስ