የወጣቶች በጎ አስተሳሰብ ለበጎፍቃድ አገልግሎት

20

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ዋና ከተማ አሶሳ ከተማ ለአጭር ቀናት በነበረኝ የሥራ ቆይታ ከተማዋን ለመቃኘት እድሉን አግኝቼ ነበር። ከተማዋ በዘመኑ ቋንቋ ፈታ፣ ቀለል ያለች ናት። በጎዳናዋ ላይ መጨናነቅ አይታይባትም። በአንዳንድ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚታየው የልመናና ጎዳና ላይ የሚተኙ ሰዎችን አላስተዋልኩም። ከመንግሥት ሥራ በተጨማሪ ነዋሪው በንግድ ሥራ ነው የሚተዳደር መሆኑ ግን እንቅስቃሴው ያሳብቃል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ወዲህ በከተማዋ መነቃቃትና ለውጥ መኖሩን አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ነግረውኛል። አሶሳ ቀደም ሲል ያልነበሯት ህንጻዎች እና ሆቴል ቤቶች ግንባታዎች እየተከናወኑ ነው። በተለይም በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት ክልሉን በቅርብ ከሚያዋስነው ከሱዳን የሚያስገቧቸውን ሸቀጣሸቀጦች ወደ ከተማዋ ለሚመጡ እንግዶች በመሸጥ ተጠቃሚ እንደሆኑ አጫውተውኛል። ከወራት በፊት በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል ተከስቶ የነበረው ግጭት በገበያቸው ላይ ተጽእኖ ማሳደሩንም አልደበቁም። በቅርቡ በሁለቱ ህዞቦች መካከል ሰላም በመፈጠሩ ገበያቸው ወደ ቀድሞ እየተመለሰላቸው መሆኑንም ጠቆም አድርገዋል፡፡

አሶሳ ከተማ በእድገት እንቅስቃሴ ላይ ብትሆንም የከተማዋ ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት መዝናኛም ሆነ ትምህርታዊ እውቀት የሚያገኙበት ማዕከል እንደሌለ አንዳንድ የከተማዋ ወጣቶች ነግረውኛል።

አሶሳ ከተማ ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታ ግንባር ቀደም ተጋላጭ ከሆኑ የኢትዮጵያ ከተሞች አንዷ መሆኗን የጤና መረጃዎች ያመለክታሉ። ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመስራት ደግሞ የወጣት ማዕከላት መኖር አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ በከተማዋ የሥነ ተዋልዶ ጤና ትምህርትን በመስጠት፣ ወጣቶች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ በተለያየ መርሃግብር እንደዝንባሌያቸው በማሳተፍ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር መሆኑን በማህበሩ ሥር ሆነው የበጎፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ አንዳንድ ወጣት የማህበሩ አባላት አጫውተውኛል።

ወጣት ናታን አብተው እና ወጣት አቶምሳ ኢንሰርሙ በማህበሩ ውስጥ ስላላቸው እንቅስቃሴ ቆይታ አድርጌያለሁ። ወጣት ናታንና አቶምሳን ያገኘሁት በቤንሻንጉል ጉምዝና ኦሮሞ ህዝቦች መካከል ተከስቶ የነበረው ግጭት በርዶ ሰላም መውረዱን አስመልክቶ በተካሄደ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ ነው። በወቅቱም በማህበራቸው አማካኝነት የሙዚቃ ዝግጅት ያቀርቡ ነበር። ወጣት ናታን በሙዚቃ መሳሪያ በማጀብ፣ ወጣት አቶምሳ ደግሞ በድምጽ ነበር ታዳሚውን ያዝናኑት። ወጣት አቶምሳ ባቀረበው ዘፈን በኮንፈረንሱ የታደሙ ወጣቶችን ያስደመመ ነበር።

ወጣት አቶምሳ እንደነገረኝ ዘፈኑ ‹‹ሀገሬ ናፈቀኝ፣…›› የሚል መልዕክት ነበረው። ተወልዶ ያደገባትን ወንበራ የምትባለውን አካባቢ በማውሳት በመረዋ ድምጹ ተጫውቷል። የማህበሩ የሙዚቃ ቡድን የተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሙዚቃ ሥራ በማቅረብ የተዋጣለት እንደነበር ታዳሚው ከሚሰጠው ምላሽ ለመገንዘብ ችያለሁ። ወጣት ናታን በማህበሩ የሙዚቃ ክፍል ኃላፊ ሲሆን አባላቱን በማስተባበርና በሙዚቃ መሳሪያ በማጀብ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በአሶሳ ከተማና በዙሪያዋ ያሉ ወጣቶች አልባሌ ሥፍራ እንዳይውሉ በተለይም እንደጫትና ሀሺሽ ካሉ አደንዛዥ እጾች በማራቅ አእምሮአቸውን ለመልካም ነገር እንዲያውሉ እንዲሁም በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ የአቻ ላቻ ትምህርታዊ ቅስቀሳዎች በሙዚቃ በማጀብ ነው ሥራቸውን የሚያከናውኑት። ወጣቶች ጊዜያቸውን በንባብም ሆነ የተለያዩ የፈጠራ ችሎታቸውን የሚያዳብሩበት በከተማዋ ባለመኖሩ አልባሌ ቦታ ለመዋል ይገደዳሉ። ችግሩ ከአሶሳ ከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች የሚብስ በመሆኑ ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት በማስተማረና በማዝናናት የበጎ ፈቃድ ሥራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

ወጣት ናታን በአሁኑ ጊዜ በማህበሩ የሙዚቃ ክፍል ውስጥ በድማጻዊ፣ የሙዚቃ መሳሪያ በመጫወት፣ በዳንስ፣ በሥነ ጽሁፍ፣ በድራማ በርካቶች በመሳተፍ ላይ ናቸው። አንዳንዶችም የሙያው ባለቤት ሆነው ገቢ ማግኘት ችለዋል። ሥራ ያልነበራቸው የማህበሩ አባላት ሥራ ካገኙም በኋላ ማህበራቸውን በማገልገል ተሳትፎአቸውን ያጠናከሩ አባላትም መኖራቸው አገልግሎቱን እንዲያጠናክር ብርታት ሆኖታል።

ወጣት ናታን ኪቦርድ የሙዚቃ መሳሪያ መጫወት ተምሯል። የተማረውን ሙያ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማዋልና ሙያውን በማካፈል ብቻ ሳይሆን በማህበሩ ውስጥ ተቀጥሮ የሂሳብ ሰራተኛ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። ማህበሩ ባለው ክፍት የሥራ ቦታም ለአባላት ቅድሚያ በመስጠት ወጣቱን በማገዝ ላይ ይገኛል። የአሶሳ ከተማ ወጣት በማህበሩ ተጠቃሚ ካደረጋቸው መካከል አንዱ እርሱ እንደሆነ የሚገልጸው ወጣት ናታን በተወለዱበት አካባቢ መልሶ ማገልገልም ትልቅ የመንፈስ እርካታን እንደሚሰጥ ተናግሯል፡፡

ወጣት ናታን አሶሳ ከተማ ለወጣቶች ምቹ ስለመሆኗ ላቀረብኩለት ጥያቄ ምቹም ናት አይደለችም ብሎ ምላሽ ለመስጠት አልደ ፈረም። እንደ ችግር ወይም ተግዳሮት ያነሳው ወጣቱ ጊዜውን የሚያሳልፍበት እንደ ሲኒማ ቤት ያሉ መዝናኛዎች፣ ክበባት እና እርስ በርሱ ለመማማር የሚሰባሰብበት ቦታ አለመ ኖሩን ተናግሯል። ይህ መሆኑ ደግሞ ወጣቱ ጫት በመቃም ለማሳለፍ እንዲገደድ ማድረጉ ቁጭት ይፈጥራል።

‹‹በከተማዋ የተከ ፈቱት የምሽት ዳንስ ቤቶችም ወጣቱን በቀ ላሉ ለችግር የሚዳር ጉትና በተለይም ለኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ የሚያጋልጡት በመሆኑ የበለጠ መስራት ይጠበቅ ብናል›› ያለው ወጣት ናታን ማህበራቸው ወጣቱን ለመታደግ ጥረት የሚያደርግ ቢሆንም ከከተማ ወጣ ብሎ በሚገኙ እንደ ወንበራ፣ ፓዌ፣ መተከልና ሌሎችም እስከ አራት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙ አካባቢዎች በስፋት በመንቀሳቀስ እያዝናኑ ትምህርት ለመስጠት የገንዘብ እጥረት እንዳለበትና ይሄም የበጎፈቃድ አገልግሎቱ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ያስረዳል፡፡

እርሱ እንዳለው ማህበሩ እቅድ አውጥቶ አባላትን ይዞ ከከተማ ወጥቶ ለመስራት የትራንስፖርት እና የተለያዩ ወጭዎችን ለመሸፈን የገንዘብ አቅም የለውም። ከማህበሩ ጋር በመተባበር የሚሰሩ መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ማህበሩ ድጋፍ ሲያደርጉ ብቻ ነው የሚንቀሳቀሱት። የማህበሩ የሙዚቃ ክፍል አልፎ አልፎም በአንዳንድ ዝግጅቶች ላይ የሙዚቃ ሥራ በመስራት በሚያገኘው ገቢም ጥረት ቢያደርግም ውጤቱ አጥጋቢ አይደለም።

አሶሳ ከተማ ውስጥ ግን የማንንም እገዛ ሳይጠብቁ አባላቱ ይንቀሳቀሳሉ። ይህም ሆኖ ግን ጥቂትም ቢሆን በበጎፈቃድ አገልግሎቱ ስኬቶች መመዝገባቸውን ይገልጻል። ማህበሩ በሚያደርገው እንቅስቃሴ እየተሳቡ አባል ሆነው መልሰው ማህበረሰባቸውን በተለይም ወጣቱን የሚያገለግሉ ወጣቶችን መፍጠር መቻል አንዱ ውጤት መሆኑንና እራሳቸውም ለውጤት ለመብቃት ዝግጁ መሆናቸው ሌላው ውጤት እንደሆነ ተናግሯል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙት በርታ፣ ሽናሻ፣ ማኦ እና ኮሞ ነባር ብሄረሰቦች በተጨማሪ በክልሉ የሚኖሩ የሌሎች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋ ተናጋሪዎችን ማዕከል አድርጎ ነው ማህበሩ የሚንቀሳቀሰው፡፡

ወጣት ናታን በበጎፈቃድ አገልግሎት ሥራውና በሙዚቃ መሳሪያ ተጨዋችነቱ ስመ ጥር መሆን ይመኛል። እርሱ ያለፈበትን መንገድ ለሌሎች ወጣቶች ተሞክሮውን በማካፈል መልካም የሆኑ ወጣቶችን መተካት ከፍተኛ ፍላጎት አለው። ይህን ፍላጎቱን ለማሳካትም ጠንክሮ እንደሚሰራ ነው ያጫወተኝ።

ድምጻዊ ሆኖ በማህበሩ ውስጥ የበጎፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለው ወጣት አቶምሳ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን በምትገኘው ወንበራ ቱሚ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው ውልደቱና እድገቱ። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም የተማረው በዛው በወንበራ ሲሆን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ‹በጂኦግራፊ ኢንቫይሮመንታል ስተዲስ›› በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል፡፡

በሥራ ዓለምም በመምህርነት ለሶስት አመት፣ በርዕሰ መምህርነት ለሶስት አመታት አገልግሏል። አሁን ደግሞ በአሶሳ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ውስጥ የህዝብ ቅሬታና አቤቱታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል። ከሥራ ውጭ ደግሞ በኢትዮጵያ ቀይመስቀል ውስጥ በበጎፈቃድ ያገለግላል። ወጣት አቶምሳ በተማረው ሙያም ሆነ የበጎፈቃድ አገልግሎቱን እየሰጠ ያለው በአካባቢው ነው።

እየሰጠ ስላለው አገልግሎትም እንደተናገረው በቤንሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል ተከስቶ በነበረው ችግር ዜጎች ከቤትና አካባቢያቸው ሲፈናቀሉ ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ቀድሞ የደረሰው ቀይመስቀል ነው። የዚህ ተቋም አባል ሆኖ ለሰብዓዊ ተግባር አስተዋጽኦ ማድረጉ አስደስቶታል።

በተለይም ወጣቱ በጤና እክልና ከወሊድ ጋር በተያያዘ ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ደም በመለገስ እና በሌሎችም ሰብዓዊ ድጋፎች ላይ እንዲሳተፍ እና እርሱም የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ለማበርከት በማህበሩ በሙሉ ፍላጎት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። የበጎፈቃድ አገልግሎት በወጣቱ መለመድ እንዳለበትም ያምናል፡፡

ወጣቶቹ እንዳሉት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በሚገኙት ሶስት ዞኖችና 20 ወረዳዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎታቸውን ተደራሽ ለማድረግ እንዲችሉ የክልሉ መንግሥት እገዛ ያስፈልጋቸዋል። በተለይ በከተማዋ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች የበጎ ፍቃድ ስራው ሊጠናከር ይገባል።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2011

በለምለም መንግሥቱ