የወንጀለኛው ጁንታ የንግድ ድርጅቶች የአገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ መጉዳታቸው ተገለፀ

ተገኝ ብሩ

አዲስ አበባ፡- ወንጀለኛው የህወሓት ጁንታ የንግድ ድርጅቶች በህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ መጉዳታቸውን ምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ አዲሱ እጥፉ አስታወቁ። የሀገሪቱን ሀብት ከመበዝበር ወደ ውጭ ለማሸሽ መሳሪያ እንደነበሩም ጠቆሙ።

አቶ አዲሱ እጥፉ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገ ለጹት፦ የህወሓት ጁንታው የንግድ ድርጅቶች በሀገ ሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያሳደሩት አሉታዊ ተፅዕኖ እጅግ የከበደ ነው።ተቋማቱ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በበላይነት በመቆጣጠርና በህገወጥ መንገድ በመዝረፍ የአገሪቱን ሀብት ወደውጭ ሲያሸሹ ነበር።

የንግድ ተቋማት አሰራራቸው ብቻ ሳይሆን አጀማ መራቸውም ህገ ወጥ እንደነበሩ የገለፁት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ ተቋማቱ ላለፉት በርካታ ዓመታት በማናለብኝነት ሀገሪቱን ሲመዘብሩ መቆየታቸውና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን አስታውቀዋል።

ጁንታው የፖለቲካ የበላይነት ለመያዝ የኢኮኖሚ የበላይነት ማረጋገጥ አለብኝ ብሎ የሚያምን ድርጅት መሆኑን የተናገሩት ባለሙያው፣ በህገወጥ ተቋማቱ አማካኝነት ይህንን እምነቱን ተጨባጭ ለማድረግ የሄደበት መንገድ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አመልክተዋል።

ተቋማቱ በተጠና መልክ የተሳሰሩና በሰንሰለት መልክ የተደራጁ ሁሉም ለአንድ አላማ የተቋቋሙ እንደሆኑ የሚናገሩት ባለሙያው፣ አንዱ ተቋም የአንደኛው ግብዓት አቅራቢ በመሆን ለሌላው በመሸጥና ኢኮኖሚውን በተለያየ መልኩ በመቆጣጠር የበላይነቱን ተቆጣጥረውት ቆይተዋል ብለዋል።

የህወሓት ጁንታ በነበረው የፖለቲካ የበላይነት ተጠቅሞ የአገሪቱ የወጪና የገቢ ንግድ ሆን ተብሎ ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር የተያያዙ እንዲሆኑ ማድረጉን ያመለከቱት ባለሙያው፣ ተቋማቱ ያለገደብ የባንክ ብድ ርና የውጭ ምንዛሪ ያገኙ እንደነበር ገልፀው” ይህ ደግሞ ከሌላ ህጋዊ ድርጅቶች በተለየ መልኩ ኢኮኖሚውን እንዲቆጣጠሩ እድል እንዲሰጣቸው አስታውቀዋል ።

የድርጅቱ ባለስልጣን የሆኑት አቶ ስብሀት ነጋ በ2003 ዓ.ም ለአሜሪካ ድምፅ “የህወሓት ተቋም የሆነው ኤፈርት የአገሪቱ ቁጥር አንድ ሀብታም ድርጅት ነው” ማለታቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ተቋማቱ ከልማት ባንክና ከንግድ ባንኮች በብድር መልክ የወሰዷቸው ገንዘቦች እንደማይመልሱና የተበላሸ ብድር እየተባለ እንደሚመክን ያስረዱት አቶ አዲሱ፣ እነዚህ ተቋማት አትራፊ መሆናቸውና እጅግ ትልልቅ ገንዘቦች ማዘዋወራቸው እየታወቀ ተቋማቱ ኪሳራ ላይ ናቸው በሚል የተበደሩትን ገንዘብ ሳይመልሱ እንዲቀሩና የመንግሥት ገንዘብ እንዲመዘበር ሆን ተብሎ ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀዋል።

በህጉ መሰረት አንድ ተቋም መክሰሩ ታውቆ የተበ ደረው ብድር መመለስ እንደማይችል ሲረጋገጥ ብድሩ ተበላሸ እንደሚሰኝ ገልፀው ፣የህወሓት ጁንታው ተቋማት ግን አትራፊ መሆናቸው እየታወቀ የተበደሩትን ገንዘብ እንዳይመልሱ የተለያዩ ምክንያቶች ያቀርቡ እንደነበር ጠቁመዋል።

ጤነኛ የንግድ ህግ ተከትለው ይሰሩ የነበሩ ተቋማት በቡድኑ ህገወጥ ድርጅቶች በደረሰባቸው ጫና ከገበያ እንደወጡና በአንፃሩ ደግሞ በቡድኑ የሚተዳደሩ ተቋ ማት በአገሪቱ ግዙፍ የገንዘብ ዝውውር የሚያደርጉና በህገወጥ መንገድ የከበሩ እንደነበሩ አስታውቀዋል። ተቋማቱ ከአገሪቱ በተለያየ መንገድ የዘረፉት ገንዘብ ወደውጭ በማሸሽ ሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲገጥማትና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዋ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲፈጠር ምክንያት እንደነበሩ ገልጸዋል።

ከአመሰራረታቸው ጀምሮ ህገወጥ በሆነ መልኩ የተቋቋሙት የህወሓት ጁንታው የንግድ ተቋማት በአገሪቱ ላይ የፈጠሩት ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑንም ገልፀዋል። ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት የንግድ ሥራ ውስጥ መሳተፍ የለበትም ያሉት አቶ አዲሱ ተቋማቱ በ1952 ዓ.ም የወጣውን አገራዊ ህግ በሚፃረር መልኩ የተቋቋሙና በህገወጥ መልኩ ሲሰሩ የቆዩ ናቸው ብለዋል።

በመንግሥት ቁጥራቸው 34 የሚሆኑ የንግድ ቋማት ተለይተው የተገለፁ መሆኑንና ጉዳያቸው በህግ ሂደት ላይ ቢሆንም የድርጅቱ የንግድ ተቋማት ግን ቁጥራቸው ከዚያ እጅግ እንደሚበልጥና በመንግሥት በኩል በትክክል ተለይተው ከህገወጥ ተግባራቸው ሊገቱ እንደሚገባም አመልክተዋል ።ተቋማቱ ለመንግሥት ግብር በስርዓት የማይከፍሉና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መሬቶችን በመውሰድ እና መልሶ በመሸጥ ለህገወጥ ተግባራቸው መጠቀሚያ ያደርጉ እንደነበር ጠቁመዋል።

ዓለምአቀፉ የፋይናንስ ሀቀኝነት ድርጅት በፈረ ንጆች በ2010 ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሰረት የጁን ታው ድርጅቶች ከአገሪቱ ከ17 ቢሊዮብ ብር በላይ በማሸሽ በውጭ ሀገር በሚገኙ የተለያዩ ባንኮች ላይ አስቀምጠዋል። ይህ ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱንና እስካሁን ይፋ የተደረገ ሪፖርት ብቻ መሰረት በማድረግ ከአገሪቱ በተለያየ መንገድ የዘረፉት ከ36 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከ1.4 ትሪሊዮን ብር በላይ በተለያዩ አገራት ባንኮች ላይ ማስቀመጣቸውን አስታውቀዋል።

ተቋማቱ የአገሪቱ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን በመሸጥና ወደውጭ በማሸሽ ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ሲፈጽሙ መቆየታቸውንም የገለጹት አቶ አዲሱ፣ ተቋማቱ ገለልተኛ በሆነ መልኩ ተጣርተው አገሪቱ ላይ ያደረሱትን ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ በመመርመር ተጠያቂ ሊደረጉ እንደሚገባ አመልክተዋል።

አዲስ ዘመን ህዳር 28/2013

Recommended For You