‹‹የአገሪቱ ተስፋ ሥጋት የፈጠረባቸው አካላት ጫና ለመፍጠር እየሠሩ ነው›› – ኡስታዝ አቡበከር አህመድ

ምህረት ሞገስ

አዲስ አበባ፡- በከፍተኛ ድህነት ከሚጠቀሱ አገሮች መካከል የሆነችው ኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ ወደ ዕድገት በሚያመራ መንገድ ላይ መጓዝ መጀመሯና ትልቅ ተስፋን ሰንቃ መራመዷ ያሰጋቸው አካላት ጫና ለመፍጠር እየሠሩ መሆናቸውን ኡስታዝ አቡበከር አህመድ አስታወቁ። ወቅታዊ ሁኔታ በመግለጽ መልካም ገጽታ መገንባት ላይ የተሰራው ሥራ ውስን መሆኑ ዋጋ በማስከፈል ላይ እንደሚገኝ አመለከቱ።

ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በአገሪቱ የለውጥ ሂደት ውስጥ የሚያደናቅፉ ችግሮች መታየታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ኢትዮጵያ ወደ ጥንካሬ የሚወስደውን ጎዳና መከተሏና ከዕርዳታ የምትወጣበት ተስፋ መፍጠሯ ሰላም የማይሰጣቸው አገራት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ውጤት ማምጣቱ ሥጋት ፈጥሮባቸዋል። በመሆኑም ሂደቱን ለማደናቀፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ግንኙነት በመጠቀም የተለያዩ ጫናዎችን በመፍጠር ላይ ናቸው።

ድሀና ፈላጊ ሁልጊዜም ታዛዥ እና የሌሎች ፍላጎቶች ማስፈፀሚያ እንደሆነ ያስታወቁት ኡስታዝ አቡበከር፣ ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው የዕድገት መስመር ደግሞ ከተረጂነት ሊያላቅቃት የሚችል በመሆኑ አንዳንድ አገሮችና ተቋማት ‹እኛ ከምንፈልገው መስመር ልትወጣ ትችላለች› በሚል ሥጋት አሳድሮባቸዋል ብለዋል። የዓባይ ጉዳይ ላይ ጠንካራ አቋም መያዙ በአገሪቱ ላይ ጫና ለመፍጠር ሌላኛው ምክንያት ነው የሚል እምነት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

እንደኡስታዝ አቡበከር ገለፃ፤ ዓባይን ከተጠቀመች እና ከፍ እያለች ከመጣች ከእነርሱ እና ከሌሎች ታዛዥነት ትላቀቃለች በማለት የሰጉ አካሎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ኢትዮጵያ በወንዙ እንዳትጠቀም የሚፈልጉ አገሮችም ግድቡን በሚመለከት ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ አካላትን ተጠቅመው ጫና ለመፍጠር እየሞከሩ ነው።

በኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታና የያዘቻቸውን እውነታዎች በሚመለከት በሚፈለገው መልኩ ለውጭው ዓለም በማሳወቅ ረገድ የተሰራው ሥራ ክፍተት እንዳለበት ያመለከቱት ኡስታዝ አቡበከር፣ ይህም በራሱ ሀገሪቱን ዋጋ እያስከፈለ ነው ብለዋል።

ችግሮችን እራሳችን መፍታት ሲገባን የውስጥ ጉዳያችንን አሳልፈው ለውጭ ጠላቶች ለመስጠት የሚደረገው ጥረት ሌላው ጫና ለመፍጠር አንደኛው መንገድ ሆኖ መገኘቱን ጠቅሰው፤ የአገርን ጥቅም በሚነካ መልኩ የአገር ውስጥን ጉዳይ አሳልፋ ሌሎች እንዲገቡበት ማድረጉ ለዘለቄታው ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ሁሉም በዚህ ላይ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያውያኖች እንደትናንቱ የአገሪቱን ጥቅምና አንድነት በሚነኩ ጉዳዮች ላይ ዛሬም የጋራ ጠንካራ አቋም መያዝ እንዳለባቸው የገለጹት ኡስታዝ አቡበከር፤ በአገር ጉዳይ ላይ የፖለቲካ አስተሳሰብ መለያየት፣ የሃይማኖት ልዩነት አጀንዳ ሊሆኑ እንደማይገባ አመልክተዋል። በምሳሌነት የዓድዋ ድልን በመጥቀስ ንጉሥ ምኒልክ ጦር ይዘው ሲወጡ የእርሳቸውን እምነት እና አመለካከት ደግፈው ከሚራመዱ በተጨማሪ እርሳቸውን የሚቃወሙና ጠብ የነበራቸው ሳይቀሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው ለጋራ የአገር ጉዳይ ከፊት በመሰለፋቸው ድሉ መገኘቱን አስታውሰዋል።

ይህ ድል የተገኘው የአገርን ጥቅም፣ ክብርና የበላይነት በማስቀደም መሆኑን ያስታወቁት ኡስታዝ አቡበከር፤ በአገር ጉዳይ ላይ አንድም ዜጋ መለየት እንደሌለበትና የጋራ አቋም መያዝ እንዳለበት አሳስበዋል።

አገራዊ መግባባትና እርቅ ላይ በማተኮር ጠላት ጣልቃ እንዲገባ በር የሚከፍቱ ቀዳዳዎችን የመዝጋት ሥራ መሠራት እንዳለበት የጠቆሙት ኡስታዝ አቡበከር፤ እጅ ለእጅ በመያያዝ ችግሮቻችንን በራሳችን አቅም ለመፍታት መነሳት ከተቻለ ውጤት ይመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል።

ኢትዮጵያውያን በዓለም አደባባይ አንገታቸውን ዝቅ አድርገው እንዲሄዱ የታሰበውን ሃሳብ ለማክሸፍ በመንግሥት ተሹመው ከፊት ካሉ አምባሳደሮች በተጨማሪ፤ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ዜጎች የአገራቸው አምባሳደር በመሆኑ የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ለውጭው ዓለም ማሳወቅ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም

Recommended For You