‹‹በጣም ብዙ ፍቅር የተሰጠው ሰው ከመውደድ ውጪ አማራጭ የለውም››- ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር

ጽጌረዳ ጫንያለው

በሰሜን ኮርያ በዲፕሎማትነት ለአራት ዓመታት ሰርተዋል።በውጪ ጉዳይም እንዲሁ በኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ ዙሪያ ከዚህ ያላነሰ እድሜ አገልግለዋል።በእነዚህ ጊዜያትም አገርን ሊጠቅሙ የሚችሉ ለውጦችን አምጥተዋል።ከዚህ ሁሉ ግን ገጠራማው ቦታ ላይ ወርደው የሰሩት ሥራ ብዙ ሴቶችንና ወጣቶችን የለወጠ እንደነበረ ይነገርላቸዋል።እርሳቸው በሥራ ቁርጠኛ ናቸው።ያሰቡትን ከግብ ሳያደርሱ የማያቆሙና ውጤቱን ሲያዩ የበለጠ ለመስራት የሚታትሩ አይነት እንደሆኑ በብዙ ሥራቸው የሚታወቁም ናቸው።

ዛሬም ቢሆን በሀላፊነት በሚሰሩበት ተቋም ላይ ብዙዎች ያመሰግኗቸዋል።ምክንያቱም ለሁሉም እኩል ምልከታ ያላቸውና እውነትና ሀቀኝነትን ይዘው የሚሰሩ በመሆናቸው ነው።እናም ከዚህ የህይወት ተሞክሯቸው እንማር ዘንድ ለዛሬ ‹‹የህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊትን፤ መልካም ንባብ።

ልጅነት በነጻነት

ትውልዳቸው በአዲሱ የሲዳማ ክልል ውስጥ ሲሆን፤ ልዩ ቦታዋ ጩኮ ትባላለች።ከተማ መልክ ያላት፣ ቅልጥ ያለ ንግድ የሚካሄድባት፤ ብዙ የገንዘብ ልውውጥ የሚደረግባት ሞቅ ያለች ከተማ ቀመስ ቀበሌ ነች።እንደውም 01 ቀበሌ በመባልም ይጠራ እንደነበር ያስታውሳሉ።ብዙ ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፋ የያዘችም ነች።ይህ ደግሞ ለእንግዳችን ከሁሉም ጋር በሁሉም ባህልና እሴት እንዲያድጉ እድል የሰጣቸው ነው።የሁሉንም ብሔር ፣ ሀይማኖት እንዲወዱና ቀምሰው እንዲኖሩት መንገድ ጠርጎላቸዋል።በተለይ በሀይማኖቱ በኩል ያለውን መተሳሰብ በየበዓላቱ ማየታቸውና ማክበራቸው ለሁሉም እኩል ምልከታ እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል።

በመምህርነትና ቆይተው ደግሞ በአስተዳደሩ ሥራ ምስጉንነታቸውን ያሳዩ አባት ያላቸው በመሆናቸው ደግሞ ልጅ ከአባታቸው ብዙ ልምዶችን እየቀሰሙ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።በተለይ በሚያስተምሩበት ጊዜ እርሳቸውም ተማሪያቸው ሆነው ያውቃሉና በጣም ይወዷቸው ነበር።እናም አባታቸው ለእርሳቸው ትልቅ ቦታ የነበራቸው የልጅነት አዕምሯቸው ገንቢና ቀራጭ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።የመምህር ልጅ መስለው እንዲያድጉም ያደረጓቸው መልካም መምህር በመሆናቸው እንደነበር ይናገራሉ።በእርግጥ ጊዜው መምህር የሚፈራበት፤ የሚከበርበትና ልዩ ቦታ የሚሰጥበት ነው።በተመሳሳይ የመምህር ልጅም ማንም የማይነካው ልጅ ሆኖ ያድጋል።ስለዚህም እርሳቸውም በዚህ ባህሪ ውስጥ ነው ልጅነታቸውን ያሳለፉት።

በትምህርታቸው ጎበዝም ነበሩ።ይህ ደግሞ የሆነው አባታቸው እንዳይሰደቡባቸው ከመጨነቅ አንጻር ነው።በእርግጥ የሚሰጣቸው ነጻነትም የበለጠ ጠንካራና ምስጉን ልጅ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።በራስ መተማመን፤ አልችልም የሚል ስሜት እንዳይኖርባቸውም አግዟቸዋል።ሁሉን የሚሞክሩና ከግብ ሳያደርሱ የማያቋርጡ አይነት ልጅ እንዲሆኑም መሰረት የጣለው ይህ ነጻነታቸው ነው።

በእነ ሰላማዊት ቤት እንግዳ ሲመጣ ወደ ጓዳ የሚባል ነገር የለም።ይልቁንም ‹‹ነይ፤ ና ተዋወቀው ዘመዳችን፣ አጎታችን ነው።አጫውቷቸው›› ተብለው ይበልጥ ከእነርሱ ጋር እንዲጫወቱ እድል ይሰጣል። ይህ መሆኑ ደግሞ ሁሉም ልጆች ከሰው ጋር የመግባባትና የመናገር ባህላቸውን እንዲያዳብሩ አስችሏቸዋል።የእንግዳችን ጨዋታ ወዳድነት፤ የማሳመን ባህል ምንጩም ይህ እንደሆነ ይናገራሉ።እንደውም ጨዋታ የወንድ የሴት ሳይሉ በነጻነት እንዲጫወቱ የሆኑት ለዚህ ነው።በሁሉም የጨዋታ አይነት ማሸነፍን ግባቸው አድርገው የሚጫወቱበት እድል የመጣውም ከዚህ ነጻነት እንደሆነ ያወሳሉ።

እግርኳስ ጨዋታ የእርሳቸው መለያ ነበር።ጥሩ ተጫዋችም እንደነበሩ አይረሱትም።በዚያው ልክ የክርክር መድረኮች ላይም ቢሆን ሁልጊዜ ተሳትፈው አሸናፊ እንጂ ተሸናፊ ሆነው አያውቁም።ይህም የመጣው በነጻነት በቤት ውስጥ መወያየትና መናገር በመቻላቸው ነው።አሳምነው ለነገሮች ምላሽ እንዲሰጡ ተደርገው በማደጋቸውም ነው።ለዚህ መሰረታቸው ይህ ብቻ እንዳልሆነም ያነሳሉ።የጎረቤት አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑንም ያስረዳሉ።

የጎረቤት እንክብካቤና ተግሳጽ ሁሉም ህይወታቸው ውስጥ መኖሩን ይናገራሉ።ስለ ጎረቤቶቻቸው በልጅነት አይን ሲያስረዱም እንዲህ ነበር ያሉን።‹‹ጎረቤት ልክ እንደእናትና አባት ለአካባቢው ልጅ ሙሉ ሀላፊነት እንዳለበት የሚያምን ነው።አንዱ የአንዱን ሸክም ተሸክሞ ፣ ተረዳድቶ ችግሩን ያልፋል።ምን አገባኝ የሚባል ነገር በጎረቤት ዘንድ አይቼ አላውቅም።የፈለጉት ቦታ ላይ ደርሶ ለመመለስ ያዝልኝ የሚባለውና ሀላፊነት የሚሰጠው እርሱ ነው።ጥፋት ሲያጠፋና ከባህሉ ሲያፈነግጥ የእንትና ልጅ ነው ምን አገባኝ በማንም ዘንድ የለም፡፡

ይልቁንም ሁሉም እንደ ልጁ ይቆጣዋል፤ ለመመለስም ይረባረባል።ካስፈለገም የፈለገውን ያክል ይገርፈዋል።በዚህም የሚከፋ አንድም ቤተሰብ የለም።ልጅም ቢሆን እከሌ መታኝ በጭራሽ አይልም።ምክንያቱም ዳግመኛ ቅጣት ሊከተለው ይችላል።ስለዚህም በጥፋቴ ተመታሁ ብሎ ዋጥ ያደርገዋል።ከስህተቱም ለመመለስ ይጥራል።ይህ ደግሞ የጎረቤት ውለታ በእያንዳንዱ ልጅ ውስጥ እስከህይወት ፍጻሜ እንዲቆይ የሚያስችል ነበር›› ይላሉ።የጎረቤት በልጅ ላይ የሚሰራው ሥራ ልጆችን በባህሪ ብቻ ሳይሆን በባህልም በታሪክም የሚሰራ ነው።ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ምስክር ነው የሚሉት ባለታሪካችን፤ አሁን እየቀረ መምጣቱ እንደሚያሳስባቸውና እንደሚያሳዝናቸው አጫውተውናል።ሊታሰብበት እንደሚገባም ያነሳሉ።

በባህሪያቸው እልኸኛ ልጅ ሲሆኑ፤ የፈለጉትን እንዳያደርጉ ሲከለከሉ አይሰሙም።ያንን ደጋግመው አድርገው ውጤቱን ማየት ይፈልጋሉ።ለምን አቃተኝ የሚል ቁጭት መለያቸው ነው።በዚህም በሥራቸው ሁሉ ውጤት እያዩ እንዲሄዱ ሆነዋል።በተለይ ከትምህርት በኋላ በቤት ውስጥ ለሚያደርጉት እገዛ ይህ ባህሪያቸው ለየት እንዲያደርጋቸው እድል ሰጥቷቸዋል።በቤት ውስጥ ቡና ማፍላትና ቤት ማጽዳት እንዲሁም እቃ ማጠብ የሚወዱትና ስሩ ሲባሉ የሚያስደስታቸው ነው።ስለዚህም ሳይታዘዙ ሰርተው ያሳያሉ።ይሁንና ቡና ሲያፈሉ በጣም ጎበዝ ቢሆኑም ስለማይዳረስላቸው ይወቀሱ እንደነበር ያስታውሳሉ።ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ብዛት ሳይሆን ጥራት ላይ ማተኮራቸው ነው።

ወይዘሮ ሰላማዊት ለቤተሰቡ ሦስተኛ ልጅ ሲሆኑ፤ እርሳቸውን ጨምሮ ሁለት ብቻ ሴቶች ናቸው ያሉት።አምስት የሚሆኑት ወንዶች ናቸው።ስለዚህም ከወንዶቹ የተለየ ጫና እንዳይኖርባቸው ይደረግላቸዋል።ይህ ደግሞ ፈልገው ሥራዎችን እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል።በተለይ እንግዳችን ልዩ ቦታ ይሰጣቸው ነበር።ምክንያቱም እርሳቸው ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ይፈለጋል።አባታቸውን መምሰልም ስለሚፈልጉም ይህ መለያቸው ሆኖ እንዲቀጥል ይበረታታሉ።እንደውም ህልማቸው ልክ እንደ አባታቸው ሀላፊነት የሚሰማው ሰው መሆን ነበርና ያንን የመሆን ተግባራቸውን ሲያከናውኑ ቤተሰቡ ይደሰትባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ሌላው እንግዳችንን ልዩ የሚያደርጋቸው ጥሩ ግጥም የሚጽፉ ልጅ መሆናቸው ነው።እርሳቸው ግጥምን የውስጣቸው መተንፈሻና የደስታቸው ምንጭ ያደርጉታል።ከዚያ ላቅ ብለውም እንደመዝሙር ይገለገሉበታል።ጓደኞቻቸው ግን እንደ መማሪያ ነው የሚወስዱት።እርሳቸው ግን ‹‹ለራሴ እንጂ ለሰው ማስተማሪያ ብዬ ጽፌ አላውቅም›› ይላሉ።ሆኖም በሚጽፉት ግጥም የማይደሰት እንዳልነበረ አጫውተውናል።እርሳቸው ግጥምን የሚጽፉት ልክ እንደመጣላቸው ብቻ አይደለም።ቆይተውም ዳግም መልዕክቱም ሆነ ተከታታይነቱ ሳይዛባ መጻፍ ይችላሉ።ይህ ደግሞ ስጦታቸው ልዩ እንደሆነ እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል። ይህ ባህሪያቸውም ዛሬ ድረስ የዘለቀ እንደሆነ ይናገራሉ።

ከጩኮ እስከ አዲስ አበባ በትምህርት

ገና እድሜያቸው ለትምህርት ሳይደርስ ነው ትምህርትን ከታላቅ እህታቸው ጋር ለመማር የገቡት።ከቤታቸው በትንሽ ርቀት ባለ መዋዕለ ህጻናት ነውም ድክ ድክ እያሉ በሁለት መምህራን ትምህርታቸውን የጀመሩት።ከዚያ መደበኛውን ትምህርት ቤቱን ተቀላቀሉ።በእርግጥ እዚህም ሲገቡ ገና እድሜያቸው ለትምህርት አልደረሰም።ይሁንና የመምህር ልጅ በመሆናቸውና ከታላቅ እህታቸው አልለይም በማለታቸው ማንም አትገቢም ሊላቸው አልቻለም።ስለዚህም ጩኮ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል እንዲማሩ ሆነዋል።

እንግዳችን በትምህርታቸው በጣም ጎበዝ ቢሆኑም ከክፍል ክፍል ደብል በመምታት ማለፍ አልቻሉም።ምክንያቱም ከላይ እንዳነሳነው የእድሜያቸው ጉዳይ አሳሳቢ ነው።ስለዚህም አባት ቀስ እያሉ ደረጃ በደረጃ እንዲማሩ አደረጓቸው።ይህ ቢሆንም እርሳቸው አልተከፉም።ምክንያቱም በእነዚህ የትምህርት ጊዜያት ብዙ ትምህርቶችን ደረጃ በደረጃ እንዲማሩ ሆነውበታል።በተለይም በጣም የሚወዱትና ዛሬ ድረስ ቢኖሩ ብለው የሚመኟቸው ትምህርቶች በመኖራቸው ደስተኛ ናቸው።ከእነዚህ መካከል እጅ ሥራ፣ ኑሮ ዘዴና ሙዚቃ ትምህርቶች አይረሷቸውም ነበር።ገና በልጅነት አዕምሮ ሰፊ ዓይን እንዲኖር ያስቻሏቸውም እንደነበሩ ያወሳሉ።የምንመርጠውንና መሆን የምንፈልገውን እንድናውቅ፤ ልዩ ተሰጥኦዋችንን እንድንለይ፤ በየጊዜው አዳዲስ ነገር እንድንፈጥር የሚያበረታታም ነበር።እናም ተማሪው ብዙ አቅምና እውቀት ኖሮት የሚያልፍበት አድርጎታልም ይላሉ።ከሁሉም ትምህርት ህብረተሰብን በጣም የሚወዱት እንደነበርም ያስታውሳሉ።ምክንያታቸው ደግሞ ተፈጥሮን በደንብ ለማወቅ ያላቸው ጉጉት እንደነበርም ይናገራሉ።

እንግዳችን ከዘጠነኛ ክፍል በኋላ ያለውን ትምህርታቸውን አባታቸው በተዘዋወሩበት ትምህርት ቤት እየተዘዋወሩ ነው የተማሩት።

በዚህም ከጩኮ  ወጥተው ዘጠነኛ ክፍልን የጀመሩት በሐዋሳ ከተማ ሆኗል።እናም እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤትን በአዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃና በታቦር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።ከዚያ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት በማምጣታቸው ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀሉ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ትምህርት መስክ እንዲሰሩ ሆነዋል።

ሌላው የትምህርት ጉዟቸው አዲስ አበባ ላይ የሚያደርሰን ሲሆን፤ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል።የመረጡትና ትምህርቱን የተማሩበት የትምህርት መስክ ደግሞ ፒስ ኤንድ ኮንፍሊክት ሪዞሊሽን የተሰኘ ነው።በጥሩ ውጤትም እንደተመረቁበት ያነሳሉ።በመቀጠል የትምህርት አቅማቸውን ያዳበሩት በስልጠና ሲሆን፤ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን የመስራት ፍላጎት እንዳላቸውም አጫውተውናል።

ገጠር ባይኖሩም ገጠሩን በልማት

የመጀመሪያ ሥራቸው የተጀመረው አባታቸው ቀደም ሲል አስተዳድረውት በነበረበት ቦታ ሲሆን፤ ከሀዋሳ ወደ 35 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ጎርጂ የሚባል የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው።በዚህም ወደዚያ ቦታ ሲሄዱ ‹‹አትችለውም፤ ሁኔታው ይከብዳታል፤ ብዙም አትቆይም›› ተብለው እንደነበር አይረሱትም።ይሁንና እርሳቸው አይበገሬነታቸውን አሳይተው ቦታ እየቀያየሩ ሲሰሩ ቆይተዋል።ምክንያቱም አትችለውም መባልን አይፈልጉም።አልችለውም ማለትም መሸነፍ እንደሆነ ውስጣቸው ያምናል።እናም የተሰጣቸውን ሀላፊነት ለመወጣት በብዙ ከባድ ፈተናዎች ውስጥ እያለፉ ሰርተዋል። በእርግጥ መጀመሪያ አካባቢ ብዙ ነገሮች ከብደዋቸው ነበር።በተለይም የመብራት ጉዳይ፤ የመንገድና የሰው የአኗኗር ሁኔታ እጅግ ፈታኝ ነው።እርሳቸው የኖሩት ደግሞ ውሃም ሆነ መብራት በማይታጣበት መንገዱም ቢሆን አስፓልት በሆነበት ነው።ይህ ደግሞ ተቃራኒ ሲሆን ቶሎ ወደ ሁኔታው ለመግባት እጅግ አስቸጋሪ ነው።ግን ሰው ከኖረበት እኔስ መኖር ለምን ያቅተኛል በሚል ነበር ሲሰሩበት የቆዩትም።

መጀመሪያ ወደዚያ ቦታ ሲመደቡ የእናቶችን የገቢ ምንጭ ማሳደግና ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ ማገዝ ላይ እንዲሰሩ ነው።ይህ ማለት በሴቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ሀላፊነት ነበር።እናም እርሳቸውም የተሰማሩለትን አላማ ግብ ለማድረስ ወደ መታተሩ ገቡ።ችግሩን ስፈታ እኔም ችግሬ አብሮ ይፈታል በማለትም ለራሳቸው እንደሚሰሩ ሆነው መስራታቸውን ቀጠሉም።እንደውም የማይረሱት ነገር አባታቸው ጋር ሄደው የጠየቁት ጥያቄ ነው።ይህም ‹‹ ሰራን ያላችሁት ምኑን ነው›› የሚል ሲሆን፤ እርሳቸውም የችግሩንና የህዝቡን ብዛት በሚገባ አስረድተዋቸው ነገሩን ትተውት ወደ ሥራ እንደገቡ ያስታውሳሉ።

አባታቸው ያልሰሯቸው ሥራዎች በእርሳቸው እንዲመለስ ያልቆፈሩት ድንጋይ አልነበረም።መጀመሪያ የሴቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ቢመደቡም በተለይ የእናቶች የሀብት ምንጭ ያድግ ዘንድ ብዙ ለፍተዋል።ለዚህም ማሳያው በደንብ ቋንቋውን እንኳን የማይችሉትን ሲዳምኛን ለምደው ችግሩን ከስር መሰረቱ ለማጥናት ሲሰሩ መቆየታቸው ነው።ከዚያ ሴቶችን በማደራጀት ሥራ የሚሰሩበትን ሁኔታ ወደማመቻቸቱ ገቡ።ፕሮጀክት እየሰሩም ገንዘብ በማፈላለግ ጥሩ ውጤታማ ለውጥም አመጡ።ትወጣለች የተባሉትም በችግሩ ስላዘኑና መፍትሄ መስጠት እንዳለባቸው ስላመኑ ቀልጠው ቀሩ።እንደውም በየጊዜው የሚያሳዩት ውጤት አመራሩን ጭምር ያስገርመው እንደነበር ይናገራሉ።

በስራቸው የተደመሙ ሀላፊዎች ከመደነቅ አልፈው የበለጠ የሚሰሩበትን ቦታ ላይ እንዲቀመጡ አደረጓቸው።ይህ የሆነውም ከስድስት ወር በኋላ በሹመት ነበር።እናም በዚህ ምክንያት የሴቶች ጉዳይ ሀላፊነታቸውን ትተው የወጣቶችን ገቢን እንዲያሳድጉ የወጣቶች ጽህፈት ቤት ላይ በሀላፊነት ተቀመጡ። መጀመሪያ አካባቢ ምን ማለት እንደሆነና ለምን እዚህ ቦታ ላይ እንዳመጧቸው አልገባቸውም ነበር።ሆኖም ሥራው ከዚህ በፊት ሲያከናውኑት የቆየ ስለነበር አልከበዳቸውም።በተለይ ወጣት ሴቶችን ወደ ሥራ ማስገባትና የገቢ ምንጫቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ ላይ በርካታ ሥራ ሰርተዋል።ወንዶቹም ቢሆኑ እንዴት የገቢ ምንጫቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ በማሰልጠንና በፕሮጀክት ደረጃ ገንዘብ በመሰብሰብ ብዙ ተግባራት ላይ በማደራጀት እንዲሳተፉ አድርገዋል።በመንግስት ለወጣቶች ተብሎ የተለቀቀ ገንዘብም በመኖሩ ተግባር ላይ እንዲውል በማድረጉ ዙሪያ ብዙ የለፉ ናቸው።

በዚህ ሥራ ላይ አልረሳውም የሚሉት ጉዳይ በተመደቡበት ቦታ ላይ ያለውን የቢሮ ሁኔታ ነው።ብዙ ጊዜ ቢሮዎች ሲሰጡ የሚታየው መንገድ ዳር መሆናቸው ብቻ ነው።ከዚያ ውጪ ግርግዳ ካላቸው ይበቃል።በርና መስኮት ምናም ግድ አይደለም።እናም ባለታሪካችንም እንዲህ አይነት ቢሮ ነበር የተሰጣቸው።ቢሆንም ብዙ አልተገረሙም።ምክንያቱም ብዙ ከዚያ የባሰ ችግር ማህበረሰቡ ላይ አይተዋል።እናም ያሉበትን ቦታ የማሳመር ግዴታ የእርሳቸው እንደሆነ ያውቃሉ።በዚህም የቻሉትን ያህል ጥገና አስደርገዋል።ነገር ግን እርሳቸው ያላሰቡት ማህበረሰቡና ከሐዋሳ የሚመጡ ሰዎች ያዩት አስገራሚ ነገር በቢሮው ላይ ተፈጥሯል።ይህም ግርግዳ ላይ ለሥራ ብለው የሚሰሩት ግራፍ ለቢሮው ውበት ሰጥቶት የሁሉንም አይን ስቧል።

እንደውም አንዳንዶች ሲያልፉ ቢሮው በጭቃ የተሰራ በመሆኑ የሚሰሩትን ግራፍ በደንብ ጎልቶ እንዲወጣ አድርጎታል።በዚያ ላይ በተለያየ ቀለም እየለያዩ ስለሚጽፉም ቢሮው ከአካባቢው የተለየና ጽዱ ሆኖ ታይቷል።በዚህም አላፊ አግዳሚው ‹‹እንዲህ ያለ ውብ ቤት በዚህ ደረጃ የሰራው ማነው›› ይባላል።ብዙዎችም ያደንቋቸዋል።በእርግጥ ይህ ሥራቸው ሁለት አይነት መልዕክት ያለው ሲሆን፤ በዋናነት ግራፉ የሚይዘው የወረዳው ወጣት ብዛት ምን ያህሉ ወደስራ ገባ፣ ምን ያህል ቀረ ፣ ምን ያህሉ ተለወጠ የሚለውን በመሆኑ ቀሪው ወጣት ለለውጥ እንዲነሳና ወደ ሥራ እንዲገባ የሚያበረታ ነው።ሁለተኛው ደግሞ ውበትን እንዴት ማስተማሪያ ማድረግ እንደሚቻል ማሳያ ነው።በዚህም ባላሰቡት ነገር ማህበረሰቡን በማስደሰታቸው ደስተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ።

ከሰባት ወር ሥራ በኋላ ይህንን ስራቸውን የተመለከተ ወረዳው የፋይናንስ ክፍል ሀላፊ አድርጎ ያስቀመጣቸው ባለታሪካችን፤ በዚህ ቦታ ላይም ቢሆን በርካታ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ እርሱን በመፍታት ዙሪያ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል።ብዙ ለውጦች እንዲመጡም ተግባብተው ሲያገለግሉ ነው የቆዩት።ይህ መሆኑ ደግሞ ለሌላ የሥራ እድል አሳጭቷቸዋል።ይህም በአዲስ አበባ የውጪ ጉዳይ ላይ ከየክልሉና ዞኑ ለውድድሩ ብቁ የሆኑ ሰዎች ምርጫ ሲከናወን ዞኑን ወክለው እንዲወዳደሩ እድሉ ተሰጣቸው።በዚህም የሥራ ጉዟቸውን ውጪጉዳይ አዲስ አበባ ላይ አደረጉ።

መጀመሪያ በውጪ ጉዳይ ለመስራት ምንም እንኳን የተወዳደሩበት የትምህርት መስክ ቢኖርም በቀጥታ መስኩ ላይ እንዲቀመጡ አይደረግም።ሁሉንም ሥራ የመልመድ ግዴታ አለባቸው።ስለዚህም ለስድስት ወር ያህል በየክፍሉ እየተቀያየሩ ሰርተዋል።ይህ የልምድ ሥራ ካለቀ በኋላም ቢዝነስ ዲፕሎማሲ ላይ በቋሚነት እንዲሰሩ ሆኑ።በዚህ መስክ ላይ ሲቀመጡም ቢሆን መስራት የለመደ አያርፍምና ከተለያዩ አገራት ጋር የዲፕሎማሲ ስራቸውን ያጧጡፉት ጀመር።በተለይ ከቻይና ፣ ከቱርክ ፣ በአጠቃላይ ከኢዥያ አካባቢ በስፋት የሚመጡ ኢንቨስተሮች ጋር ተቀራርበው በርካታ ስራዎችን አከናውነዋል።ጥሩ ቡድንም ስለነበር በአጭር ጊዜ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ሆነዋል።በዚህም ለአራት ዓመታት አገልግለዋል።

ከዚያ በዲፕሎማትነት ተመርጠው ወደ ሰሜን ኮርያ ያቀኑ ሲሆን፤ በዚያም አራት ዓመታት የዲፕሎማትነት ሥራቸውን አከናውነዋል።ለተወሰኑ ዓመታት ደግሞ ሥራ አቁመው የተለያዩ አገራትን በራሳቸው ሲዘዋወሩ አሳልፈዋል።ይሁንና አገር እንደማገልገል የሚያረካ ተግባር እንደሌለ ስለሚረዱ ዳግም በአገራቸው ለመስራት መጡ።የዛሬውን ቦታቸውንም አግኝተው ሥራቸውን ጀመሩ።የዛሬው ሥራቸው የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሲሆን፤ ኤጀንሲው ከተቋቋመ ጀምሮ እየሰሩበትና እየመሩት ይገኛሉ።አሁን በሥራው ሁለት ዓመት ሊሞላቸው ነው።

የህይወት ፍልስፍና

ቀናነትና እውነትን መሰረት አድርጎ መኖር ህይወትን ያቃናል ብዬ አምናለሁ።ሁለቱ ነገሮች ለእኔ ተነጣጥለው የሚታዩም አይደሉም።ማንም ሰው እውነት ላይ ተንተርሶ ቀና ሆኖ መኖር ከቻለ የራሱንም ህይወት በሰላም ይመራል።ለሌሎችም ተስፋ ይሆናል ፤ ሰላምም ሰጪ ነው ብዬ አምናለሁ።ስለዚህም ይህ ፍልስፍና የሰዎች ሁሉ ልምድና መለያ ቢሆን እመኛለሁ ይላሉ።

ከእኔ ቢወሰድ

ሰዎች ከእኔ ቢወስዱ የሚሉት ቆራጥ ሰራተኝነትን ሲሆን፤ ስራን የሚያዩበትን አይን ቢወርሱት ይጠቀሙበታል ባይ ናቸው።ማንም ሰው ሥራን ሲሰራ እኔ የተፈጠርኩለት ነው ብሎ ማሰብ አለበት።በህይወቱ የሚሰራውን ሥራ በግልም ይሁን በመንግስት መስሪያቤት ቁምነገሬ ብሎ መያዝ አለበት።ውጤታማ እንዲሆንበትም መቶ በመቶ ገብቶ መስራት ይኖርበታል።የጀመሩትን ነገር ሳያጠናቅቁ አለማቆምንም ልምድ ሊያደርጉት ይገባል።ምክንያቱም ጀምሮ እንደማቆም የሚያከስር ሥራ ስለሌለ እምነታቸው ነው።

ሌላው ከእኔ ቢወሰድ የሚሉት ነገር ቀና መሆንን ነው።አወንታዊ እይታን ሰዎች ልምዳቸው ማድረግ አለባቸው።ምክንያቱም እሺ ከሺ ይበልጣል።ለእኔ አስቦ ነው ማለት የበለጠ ነገርን ያጎናጽፋል።ከሰው ባይገኝም ከአምላክ የሚገኘውን በረከት ያበዛል።መስራትን፤ ውጤታማ መሆንን ያላብሳል።እንቢና አሉታዊ እይታ ግን ለራስም ለሰውም አይሆንም።እናም ቀናነትን ከመልካም መልካሙን ማየት ጋር ሰዎች አቀናጅተው ቢይዙት ይጠቀሙበታል የምለው ነው ይላሉ።

እናትነት

‹‹ሁሉም እናት ተንከባካቢ ናቸው ብዬ አስባለሁ።እኔም ለአንድ ልጄ እንዲህ አይነት እናት ነኝ የሚል እምነት አለኝ።እኔ በአደኩበት ልክ ልጄን አሳድጌዋለሁ።ማለትም እኔ ነጻና በውይይት የማምን ልጅ የሆንኩት በቤተሰቦቼ እገዛ ነው።ልጄም ያንን ሆኖ እንዲያድግ የተቻላትን የምታደርግ እናት ለመሆን እጥራለሁ።በዚያው ልክ እንደ እናት መገደብ ያሉብን ነገሮች ላይም ቆራጥ ነኝ።ለቀጣይ የሚያስፈልገውን ለማሟላት የምታስብ አይነት እናትም ነኝ።ተቆጪ አይደለሁም።ምክንያቱም ልጅን መቆጣት ሳይሆን ማስረዳት የበለጠ ይገነባዋል ብዬ ስለማምን።ስለዚህም ሲያጠፋ የምነግርበትን መንገድ አስቤና ተጨንቄ ነው።

ልጄ በራሱ እየወሰነ የሚሄድ አይነት ሆኖ እንዲያድግ አደርገዋለሁ።ምክንያቱም የሚቆጭብኝ እናት እንዳልሆን ስለምሻ።ነገር ግን ከባህልም ከሥርዓትም እንዲወጣ አላደርገውም።መቆጣት ያለብኝ ላይ እቆጣዋለሁ።የተቆጣሁበትን ነገርም በአግባቡ እያስረዳሁ የምሄድ አይነት እናት ነኝ ብዬ አምናለሁ›› ይላሉ።በተለይ ባለቤታቸው በውጪ አገር የሚኖር ስለሆነ ‹‹ለልጄ ያለሁት እናትም አባትም ሆኜም ነውና እርሱን እንከባከበዋለሁ።ይህም መለያዬ ነው›› ብለውናል።

መልዕክት

ኢትዮጵያ በጣም ብዙ ጸጋ ያላት አገር ነች።ብዙ አይነት ማህበረሰብንም አቅፋ ደግፋ የምትኖር ብቸኛና ልዩ አገር ነች።እናም በእነዚህ ብሔር ብሔረሰቦቿ ለእያንዳንዱ ዜጋ ብዙ ፍቅር ሰጥታ ነው ያሳደገችው።በጣም ብዙ ፍቅር የተሰጠው ሰው ደግሞ ከመውደድ ውጪ አማራጭ የለውም።ስለዚህም እኛም ለልጆቻችን ፣ ለጎረቤቶቻችን ለማንኛውም የሰው ልጅ የመጀመሪያ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባን ፍቅርን መሆን አለበት።ብዙ የተወደደ ሰው ከመውደድ ውጪ አማራጭ የለውም የሚለውንም ማመን አለብን።አሁን ላይ የምናደርገው ማንኛውም ነገር ይበቅላል።ስለሆነም መለያየትን፣ ክፋትን የመሰሉ መጥፎ ባህርያትን መስጠት ማቆም ይጠበቅብናል።ከዚያ ይልቅ ከዚህ ቀደም የነበረውን ፍቅርን አብልጠን እንስጥ።ነገ እናተርፍበታለንና የሚለው የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።

ሌላው ያነሱት ነገር “ቀናና አወንታዊ ምልከታ መኖር መለያችን ይሁኑ፤ አሉታዊ አይኖቻችን ይከደኑ” ይላሉ።ምክንያቱም እነዚህ ምልከታዎች ተጠራጣሪ ያደርጉናል። ራሳችንንም እንዳናዳምጥና ለሌሎች ጭምር እንዳንኖር እንቅፋት ይሆኑናል።ሰላማችንንም ይነሳሉ።እናም አወንታዊውን ማስቀደም እናዳብር ይላሉ።በተለይም በማህበረሰባችን ላይ ይህ አስተሳሰብ እንዲኖር መስራት ያስፈልጋል ባይ ናቸው።ዛሬ ላይ የምናሳድገው ቂም በቀል ነገ መልሶ ለራሳችን ይሆናል።እኛ ጋር ካልደረሰም ለልጆቻችን መሆኑ አይቀርም።ስለሆነም በምንም አጋጣሚ የምናገኛቸውን ልጆች ስናስተምርና ከእኛ ልንሰጣቸው የሚገባው ነገር ሰላማዊ መሆን አለበት።መግባባት፣ ፍቅር መሆን ይገባዋልም መልዕክታቸው ነው።

ቀደም ሲል የነበረው የማህበረሰቡ ማህበራዊ ካፒታል እየተሸረሸረ መጥቷል።ይህ ደግሞ አሁን ላይ የምናፈራቸውን ልጆች መቅኔ አሳጥቷቸዋል።ብዙ የተለየ ባህሪም እንዲያሳዩ አድርጓቸዋል።ከዚህም በላይ ደግሞ የነገዎቹ ምን ይሆናሉ ሲባል ያስፈራልም፣ ያሳስባልም።ስለዚህ ይህ ጉዳይ ከዚህ በበለጠ መልኩ አስፈሪ እንዳይሆን የቀረውን የፍቅር ባህል ማውጣትና እነርሱ እንዲኖሩት ማድረግ ላይ እያንዳንዱ ዜጋ ሊሰራበት ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን ይቋጫሉ።እኛም ምክራቸው ተግባራዊ ይሁን እያልን ተሰናበትን።ሰላም!!

አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም

Ad Widget

Recommended For You