‹‹ህይወታችንን ከፈለግናት ሲሆንብን ሳይሆን ሲሆንባቸው ባየነው ለመማር እንጣር››- ፕሮፌሰር አበበ ጌታሁን

ጽጌረዳ ጫንያለው

የፓን አፍሪካ አሳና አሳ ሀብት ማህበርን በፕሬዳንትነት ለአምስት ዓመታት የመሩ ናቸው:: የኢትዮጵያ ዓሳና የውሃ ሳይንስ ማህበርንም በምክትል ፕሬዚዳንትነት ከዚህ ያላነሰ እድሜ መርተዋል:: የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የቦርድ አባልም በመሆን ለረጅም ዓመት አገልግለዋል:: በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲንም ነበሩ:: በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ሻላ ላይ፤ በቀይ ባህር ላይ፣ በአዋሽ፣ ጣናን የመሰሉ የተለያዩ ሀይቆችና ወንዞች ላይ ትልልቅ ጥናቶችን በማድረግ የዓሳ ምርት በአገር የሚታወቅበትን ሁኔታ ከአመቻቹ መካከልም ይጠቀሳሉ::

ዓሳን በተመለከተ አገር ተጠቃሚ የምትሆንበትን ሥራ ከተለያዩ የውጪ ድርጅቶችና መንግስታዊ ተቋማት ጋር በመሆንም ሰርተው ውጤት ያመጡም ናቸው:: የተማሩት አሜሪካ ቢሆንም ማገልገላቸው ግን አገራቸውን ብቻ እንዲሆን አምነው በሙያቸው አገራቸውን ለመጥቀም እየታተሩ ያሉ አገር ወዳድ ግለሰብም ናቸው ፕሮፌሰር አበበ ጌታሁን:: እናም ከእዚህ ሁሉ የህይወት ተሞክሯቸው ልምዳቸውን ያጋሩን ዘንድ አጠር ያለች ቆይታን አድርገናል:: ልምዳቸውን ለህይወታችሁ መመሪያ መኖሪያ ታደርጉት ዘንድ ተመኘንና ለዛሬ ‹‹የህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳ አደረግናቸው፤ ተጋበዙልን::

ብቸኛው ልጅ

ዛሬ ድረስ ለእናታቸው ብቸኛም የመጀመሪያም ልጅ ናቸው:: አባታቸውም ቢሆኑ ብዙ ከቆዩ በኋላ ነው ሌላ ልጅ የወለዱት:: ስለዚህም እንግዳችን በቤቱ ውስጥ ተሞላቆ ያደገ ልጅ ነበሩ:: የፈለጉትንም እየተደረገላቸው ከወላጅ በተጨማሪ ለአያት ቅድመአያቱ ብርቅ ሆነውም ነው ልጅነታቸውን ያሳለፉት:: በተለይ ለወላጆቻቸው በጣም ሀብታም የሚባሉም ባይሆኑም የተሻለ ሀብት ባለቤት ናቸውና ከፍቅርም ከቁስም ተጠቅመው እድገታቸውን እንዲያጣጥሙ ተደርገዋል:: አባታቸው ገበሬም፣ ነጋዴም ፣ የራሳቸው መኪና ኖሯቸው የሚሾፍሩ፣ ልብስ ሰፊም መሆናቸው ደግሞ ይበልጥ የጎደላቸው ነገር እንዳይኖር አግዟቸዋል:: የፈለጉት ነገር በፈለጉት ጊዜ ይቀርብላቸዋልም::

ከሁሉ ነገር ግን ዛሬ ድረስ ያኖራቸው አንድ ነገር እንደሆነ ያወሳሉ:: ይህም በፍቅር ማደጋቸው ነው:: ‹‹ፍቅር ከቤተሰብ ሲሰጥ ያደገ ልጅ ሁሉ ጊዜ መልካሙን እንጂ መጥፎውን አያይም:: ይህንን ሊያደርግብኝ ይሆናል የሚል ምልከታም አይኖረውም:: እንደውም አወንታዊውን አይቶ ስህተት እንኳን ቢሆን በመልካም አይን ያልፈዋል:: ይህ ደግሞ ከመሰቀቅ፣ ከፍርሀት ይታደገዋል:: መልካም ለማድረግም ያበረታል:: እናም ለእኔ ቤተሰቤና ጎረቤቴ የሰጠኝ ፍቅር መልካም የሚታይበት ዓይን ነው:: ይህ ደግሞ ይደረግብኛልን ሳይሆን ይደረግልኛልን ብቻ እያሰብኩ ወደፊት እንድራመድ አድርጎኛል›› ይላሉ::

‹‹በፍቅር ያደገ ልጅ ዛሬ እንኳን ያለው ነውጥና ግጭት አያናጋውም:: ውጣልኝን ፈጽሞ አያስብም:: ቀድሞ የተደረገለትንና የሆነውን ብቻ እያየ ነው ወደፊት የሚገሰግሰው:: ሁልጊዜ የልቡን ጥሪ እንጂ ዛሬ የሚሆነውን ለአይኑም ለውስጡም አይነግረውም:: ለዚህም ማሳያው አብረን ያደግነው ልጆች በብሔር ሳንከፋፈል ለትውልድ ቀያችን የተለያዩ የልማት ስራ መስራታችን ነው:: በአሰላ ብዙ ብሔር ያለው ልጅ አድጓል:: ጎልምሶ እያረጀም ነው:: ነገር ግን ብሔሬ ብሎ ለተወለደባት፣ ላደገባትና ለጎለመሰባት ማድረጉን አልተወም:: ዛሬ ይህንን ሳይ ነው ልጅነቴን የምደሰትበትም›› ባይ ናቸው::

መምህራን ከተለያየ ቦታ መጥተው በባህልና በስነምግባር ኮትኩተው ማሳደጋቸው ሌላው ልጅነታቸውን በፍቅር የሰራላቸው እንደነበር የሚያወሱት ፕሮፌሰር አበበ፤ ኢትዮጵያዊ ሆነው እንዲኖሩና እንዲያድጉ እንዳደረጋቸውም ይናገራሉ:: በዚያ ላይ በወቅቱ የነበረው ክብራቸው፣ እውቀታቸው፤ ስነምግባራቸው እንዲሁም አኗኗራቸው ከሁሉም ሰራተኛ የተሻለ መሆን እነርሱን ጭምር መሆን እስከመመኘት ያደረሳቸው እንደነበር ያስታውሳሉ::

ትውልዳቸው አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ውስጥ ሲሆን፤ በዚህ ሥፍራ ያልተጫወቱት ጨዋታ አልነበረም:: በተለይ ግን እግር ኳስና የእጅ ኳስን መጫወት አጥብቀው ይወዱ ነበር:: በእንግሊዝኛ የሚያደርጉት ክርክርም በልጅነታቸው ከሚያስታውሱትና ከሚያደርጉት ነገር አንዱ ነበር:: ይህ ደግሞ ጎበዝ ተማሪ እንዲሆኑ እንዳገዛቸው አይረሳቸውም::

ከሽርካ እስከ አሜሪካ

ከበቆጂ 30 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሽርካ ከተማ ጎቤሳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቤት ነው የትምህርት ሀሁን የጀመሩት:: በትምህርት ቤቱ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረውበታል:: ከዚያ ወደ አሰላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወይም በቀድሞ ስሙ ራስዳርጌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገቡ:: 12ኛ ክፍልንም በጥሩ ውጤት አለፉ:: ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት ሲያስቡም ምርጫቸውን ግብርና አደረጉ:: ምክንያታቸው ደግሞ አሰላ በግብርና ዘርፍ በርካታ ስራ የሚሰራባት መሆኗና ሲውድኖች በስፋት የሚሰሩበት ዘርፍ በመሆኑ ብዙ ልዩ ጥቅምም ለውጥም አለው:: እናም ግብርናን መርጠው ጉዞ ወደ ሐረምያ ዩኒቨርስቲ አደረጉ::

ትምህርት ጀመሩ:: ነገር ግን ወቅቱ የ66 አቢዮት የተጀመረበት ነበርና ቀጣዩን የትምህርት ጉዞ ማድረግ አልቻሉም:: በዚህም ትምህርቱ ተቋረጠ:: ሁለት ዓመታትም በተለያየ መልኩ አለፉ:: መማሩ ግድ ሆነናም ወደ ሐረሞያ ተመልሰው ትምህርቱን ጀመሩ:: የመጀመሪያ ዓመት በውጤትም ቢሆን ነገሮች ስላልተረጋጉ እንደምንም ብሎ ተጠናቀቀ:: ሁለተኛ ዓመት ላይ የትምህርት ክፍል ምርጫ ይደረግ ነበርና ከጓደኞቻቸው ጋር መመካከር ጀመሩ:: ከፍተኛ ውጤት ነበራቸውና የፈለጉት ግብርና ቢሆንም ጓደኞቻቸው ‹‹ማን ገበሬ ይሆናል›› ሲሏቸው እርሳቸውም አንገራገሩ:: ሀሳባቸውም ተቀየረና ሜዲስን ለማጥናት ወሰኑ::

ሜዲሲን መርጠው ቅድመ ትምህርቱን ለመማር ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያቀኑ ሲሆን፤ ትምህርቱ ሳይጠናቀቅ የመንግስት ግርግር በመፈጠሩ የተነሳ አሁንም ትምህርቱ እንዲቋረጥ ሆነ:: ዳግም የጀመሩትም ከሁለት ዓመት የሥራና የእስር ቆይታ በኋላ ነበር:: ሲመለሱም ቢሆን ሁሉም ነገር እንደጠበቁት አላገኙትም:: ይልቁንም ያላሰቡትን ትምህርት እንዲማሩ ነው የሆኑት:: ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቅድመ ሜዲስን የሚባል ትምህርት ቆሟል:: አንደኛ ዓመት ተብሎ ነው ትምህርቱ እየተሰጠ ያለው:: ስለዚህ አንዱን ዓመት ትተው ካልገቡ በስተቀር በዚህ መስክ መቀጠል አይችሉም ነበር:: ይህም ቢሆን አልሆነም:: ከዚያ ይልቅ እሳቸውን ማንም ሳይጠይቅ መምህራኑ ግራ ስለገባቸው ዝም ብለው ሁለተኛ ዓመት የባዮሎጂ ተማሪ እንዲሆኑ መዘገቧቸው::

ምርጫቸው መማር ብቻ በመሆኑም የተሰጣቸውን እድል ተጠቀሙበት:: ሳያንገራግሩም ትምህርቱን ቀጠሉ:: በከፍተኛ ውጤትም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አጠናቀቁ:: ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም በዚሁ ዩኒቨርስቲ የተከታተሉ ሲሆን፤ የትምህርት መስኩ ደግሞ ዚኦሎጂ ነው:: ለዚህ ደግሞ ያገዛቸው አስመራ መስራታቸው እንደነበር ያስታውሳሉ:: ምክንያቱም ምርምራቸውን በቀይ ባህር አሳዎች ላይ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል::

ሦስተኛ ዲግሪያቸውን የተማሩት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተቀይረው ከመጡና ከሦስት ዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ ሲሆን፤ በራሳቸው ተጽፈው የትምህርት እድሉን በአሜሪካ አገር አግኝተው ነው:: በዚህም በዩኒቨርስቲ ኦፍ ኒወርክ የውሃ ሥነ-ምህዳር ፣ ዝግመተ ለውጥ እና ባህሪ ትምህርት መስክ ትምህርቱን አጠናቀዋል:: በሙሉ ወጪ የትምህርት እድል የሰጣቸው የአሜሪካ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ሲሆን፤ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ አምስት ዓመት ተኩል ቆይተዋል:: ከዚያ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድና በማስተማር እንዲሁም በማማከርና የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በመስራት፤ መጸሐፍቶችን በመጻፍ ነው እውቀታቸውን ሲያዳብሩ የቆዩት::

ጎጃም፤ መሬ፤ ሐረር፤ አስመራና አዲስ በሥራ ላይ

የሐረማያ ተማሪ ብቻ በመሆናቸው ይሰሩ ዘንድ ኤክስቴንሽን ፕሮጀክት ኢንፕላንቴሽን የተባለ ድርጅት ወስዷቸው በመረሀቤቴ የሠሩት ሥራ የመጀመሪያ የሥራ ቅጥራቸው ነበር:: ለሦስት ወር አማካሪ በመሆን አገልግለውበታል:: ከዚያ ወደ ዘመቻ የገቡ ሲሆን፤ የዘመቱትም ጎጃም ውስጥ ዳንግላ ነው:: በዚህ ቦታ የተማሩ በመሆናቸው ክብርና ሞገስ ይሰጣቸዋል:: አዛዦች፤ መሬት ሰጪና ነጣቂዎችም ሆነዋል:: ግን ብዙም ደስተኛ አልነበሩበትም:: ምክንያቱም ሥራው ምቾት አልሰጣቸውም:: በዚህም ጠፍተው ለመሄድ ሲሞክሩ ከፍተኛ ስቃይን አሳልፈዋል::

ለአብነት ወደ አገራቸው ለመመለስ ከአስመራ የሚመጣውን መኪና ጠብቀው አስገድደው ተሳፈሩ:: ሆኖም ጎጃምን ሳይለቁ ደብረማርቆስ ተደውሎ ተነግሯቸው ነበርና እዚያ የሚኖሩ ወታደሮች ያዟቸው:: በወቅቱ በሰላም ወደ አቢዮቱ እንዲቀላቀሉም አላደረጓቸውም ነበር:: ምክንያቱም ከሀዲ ተብለዋል:: ስለዚህም ገና ከመኪና እንደወረዱ ጀምሮ ነው ሥቃያቸውን ያበረቱባቸው ጀመር:: ወቅቱ ክረምት ስለነበር መጀመሪያ ኦራል መኪና በጎማው ያረሰው መሬት ውስጥ በልባቸው እስከነልብሳቸው እንዲሳቡ አደረጓቸው::

በውሃና በጭቃ መጨማለቃቸው ሳይለቃቸው ደግሞ አመሻሽ ላይ ሊሾው ሲሚንቶ በሆነ ቤት አስገብተው ለቀቋቸው:: ምንም ልብስም ሆነ ምግብ አልሰጧቸውም:: በጣም ሲመሽም አንድ ደረቅ ዳቦ ከውሃ ጋር አመጡላቸው:: ግን አይደለም ለራበው ለጠገበም ከጉሮሮ አይወርድም ነበር:: ምርጫ የለምና የተሰጣቸውን በልተው አደሩ:: በጠዋት አንስተው በኦራሉ ጭነው ብርድ እየጠበጠባቸው መልሰው ወደ ዳንግላ ተወሰዱ:: ያንኑ ሥራቸውን እንዲሰሩም የውዴታ ግዴታ ተጣለባቸው:: ግን ይህም ቢሆን ተስፋ አልቆረጡም:: በግል መውጣት እንዳለባቸው አምነዋል:: ማንም ሊያደርገው ባይችልም:: ከዓመት በኋላ ግን በራሳቸው ፈቃድ ነገሮች ስለተረጋጉ ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ፈቀዱላቸው:: በዚህም ትምህርታቸውን ሀረማያ ገብተው አጠናቀቁ:: ሦስተኛው የሥራ ቦታቸውም የጀመረው ከዚህ በኋላ ነው::

በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት ሐረርጌ መቻራ ተመድበው በመምህርነት መስራት ጀመሩም:: ዓመት ከአስተማሩ በኋላ አሁንም ሌላ ግርግር ተነሳ:: የኢህአፓ ግርግር :: እዚህ ላይ ደግሞ በእነርሱ ጊዜ ትልቅ ትኩረት ይሰጠዋል:: በፖለቲካው የተሞሉ ስለነበሩ ግርግሩን መቀላቀልም ወደውት የሚያደርጉት ነው:: እናም እርሳቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ወጣቶች ሊግ አባል ስለነበሩ ሲሰሩ በመደረሱ ለእስር ተዳረጉ:: ስምንት  ወርም በማረሚያ ቤት ቆዩ:: ከተፈቱ በኋላም በዚያው በመቻሬ በአስተዳደሩ ትዕዛዝ ለአራት ወራት ተጨማሪ አስተማሩ:: ይሁን እንጂ የእርሳቸው ጉዞ ከትምህርት ቤት ቤት ቢሆንም አሁንም የሚኮንናቸው አልጠፋም ነበር:: እናም እንቅስቃሴውን እያስፋፉ ነው ተብለው ዳግም ወደ ወህኒ ወረዱ::

በማረሚያ ቤት ብዙ ፈተና አይተዋል:: በተለይ ግን በጣሪያው ለማምለጥ የሞከሩበት አይረሱትም:: ምክንያቱም ያን ጊዜ የወረደባቸውን የጥይት ናዳ በእግዚአብሔር ቸርነት ካልሆነ በፍጹም እተርፋለሁ አያስብልም:: ጥግ ይዘው ግን አልፈውታል:: ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ አብሯቸው የታሰረው የመንግስት ሰላይ ሲሆን፤ ከፍተኛ ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ እንደሚያመልጡ ተማምነው ዝናቡ ሲጥል ጣሪያውን አውልቀው አራቱ እንደወጡ ዝናቡ አቆመ:: ሰላዩም ጩኸቱን አቀለጠው:: የዚህን ጊዜ ጠባቂዎቹ መጡ:: ሲያዩት ጣሪያው ተነስቶ ታራሚ አምልጧል:: በተረፉት ላይም አንደኛው ከላይ ወጥቶ ጥይቱን ያርከፈክፍ ጀመር:: ግን ማንም አልተነካም ነበር:: ይሁን እንጂ ከጥይቱም ቢተርፉም የነበራቸው እንቅስቃሴ ታይቶ እርሳቸው ተረፉ እንጂ ከመካከላቸው አይን በአይን የተረሸኑ ነበሩ:: እናም ይህንን ጊዜ ሲያስታውሱት ‹‹ ትረፍ ያለው ነብስ ሆኖ ነው›› ይላሉ::

ከማረሚያ ቤቱ ቢወጡም በእግርም በእጅም ካቴና ታስረው ሌላ ማረሚያ ቤት ተወሰዱ:: አራት ወር እንዲቆዩም ተደረጉ:: ከዚያ የኢህአፓ እንቅስቃሴና ቀይሽብርም በመዳከሙ ምንም አያመጡም ተብለው ተፈቱ:: ወዲያው ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ቦታውን ለቀቁ:: በምንም መልኩ ይሁን ትምህርታቸው ገብተው የሚማሩበትን መንገድ እንዲፈጥሩላቸው ጠየቁ:: ተፈቀደላቸውና በቀደመው ሳይሆን በባዩሎጂ ትምህርት መስክ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ይዘው በከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን አማካኝነት አስመራ ዩኒቨርስቲ ለሥራ ተመደቡ::

በአስመራ ለአምስት ዓመታት የቆዩ ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመስራት ከመጡበት ጊዜ ውጪ ብዙ ለውጦችን በአካባቢው ላይ አምጥተዋል:: ከዚያ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲቀየሩም እንዲሁ ትልልቅ አንቱታን ያተረፉላቸው ሥራዎችን መስራት የቻሉ ናቸው:: በቆዩበት 25 ዓመታት ውስጥም በተለይም አዳዲስ ዲፓርትመንቶችን በማቋቋምና በመምራት የተዋጣላቸው ነበሩ:: በመማር ማስተማር ሥራውና በምርምሩም ዘርፍ ቢሆን በተለይ በዓሳ ዙሪያ እውቅ ፣ ተወዳጅ እንደሆኑም ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል::

ሙሉ ፕሮፌሰርነት የተሰጣቸውም ከሰሯቸው ሥራዎች አንጻር ነው:: 15 ተማሪዎችን በሦስተኛ ዲግሪ 40 ተማሪዎች ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ አስመርቀዋል:: ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመስራት ነው:: በዚህም ከተማሪዎቻቸውና ከሌሎች የሥራ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን እንዲሁም በራሳቸው ወደ ስድስት የሚደርሱ መጽሐፍ ጽፈው ለንባብ አብቅተዋል:: ወደ 80 የሚሆኑ አርቲክሎችንም በአለምአቀፍ መጽሔቶች ላይ አሳትመዋል::

በአጠቃላይ በሥራ ህይወታቸው ሰራሁ ከሚሉት ውስጥ በዋናነት የሚያነሱት በአስመራ የማሪን ሁኒት አቋቁመው እርሱን መምራቱ አንዱ ነው:: ምጽዋ ላይ ደግሞ ስቴሽነሪ በመስራት ተማሪዎችም ሆኑ የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን ያደረጉትም ተጠቃሽ ነው:: በአዲስ አበባ የሳይንስ ኮሌጅ ተባባሪ ዲንም ሆነው መስራታቸው ሌላው ሲሆን፤ ከአስር ዓመት ለማይበልጥ ጊዜ ደግሞ የባይሎጂ ትምህርት ክፍልን በሦስት ክፍል ከፍለው ሲመሩ ቆይተዋል:: የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚዬምን በዳሬክተርነት የመሩም ናቸው::

የኢትዮጵያ ዓሳና የውሃ ሳይንስ ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት፤ የፓን አፍሪካ ዓሳና ዓሳ ሃብት ማህበር ፕሬዝዳንት በመሆን ለዓምስት ዓመት ያህል አገልግለዋልም:: የብሔራዊ የአሳማ ልማት አማካሪ ቦርድ አባልም ሆነው ያገለገሉትም ይጠቀሳል:: በኢትዮጵያ ውስጥ አነስተኛ ደረጃ ያላቸው የውሃ ውስጥ የውሃ ማጠራቀሚያዎችን ማስተዋወቅ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖርም ከፋኦ ጋር በመሆን ሰርተዋል:: የተባበሩት መንግስታት ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ውስጥ የውሃ ሀብትን በዘላቂነት ለመጠቀም የውሃ እና የውሃ ውስጥ የውሃ ልማት እንዲኖር ብዙ የለፉ ናቸው::

የባዩሎጂካል ሶሳይቲ ላይም እንዲሁ መስራችና ሀላፊም ነበሩ:: የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የቦርድ አባል፣ ገንዘብ ያዥ ሆነው ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል:: በእነዚህ የሥራ ውጤታማነታቸው በርካታ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን፤ የአፍሪካ የሙያ ሽልማት እስከማግኘት ያደረሳቸው ነው:: ይሁንና ከሁሉም የሚረኩበት በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የሚገኘውን የሰዎች እርካታ ነው:: እናም ሁልጊዜ ይህ ተግባራቸው ስለሚያረካቸው አሁንም በሙያቸው ፣ በጉልበታቸውና በገንዘባቸው አድርግ ሳይባሉ ጭምር በርካታ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ:: ከእነዚህ መካከል ደግሞ በአካባቢያቸው ከአገሬው ሰውና እንደርሳቸው በተለያየ ሥራ ላይ ካሉ ሰዎች ጋር በመሆን ማህበር መስርተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ::

ሽርካ አካባቢ ላይ እነርሱ ሲማሩ መኪና እንኳን አይገባም ነበር:: በዚያ ላይ መብራትና ስልክም ችግር ነው:: እናም እነርሱ የደረሰባቸው ሌሎቹ እንዳደርስባቸው በማህበራቸው አማካኝነት እነዚህን ነገሮች አድርገዋል:: ትምህርት ቤቶችንም እንዲሁ ሰርተዋል:: የቴክኒክና ሙያን ጨምሮ:: አሁንም የጭላሎ ተራራን ለማስዋብ የሚደረጉ ሥራዎችን እያከናወኑ ነው::

ቤተሰብ ራስን ይመስላል

ራስን ሙሉ ለማድረግ በአንድ በኩል ብቻ መጓዝ አያመጣውም:: በየአቅጣጫው መርምሮ መራመድን ይጠይቃል:: አስተማሪው ከሚያስተምረው በተጓዳኝ ሌላ የሚሰራውንም ማለም አለበት:: ለዚህ ደግሞ ይህንን ሀሳቡን ሊሞላለት የሚችል አጋር ግዴታ ነው:: እናም ሰው ብቻውን ሙሉ ሊሆን አይችልምና ጎዶሎዬን የምትሞላልኝ አጋርን ፈለኩ አገኘሁም ይላሉ ስለ ባለቤታቸውና የእርሳቸው ግንኙነት ሲያወሱ:: መጀመሪያ ግንኙነታቸው የጀመረው በጓደኛቸው አማካኝነት ነው::

ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እየተማሩ ሳለ ጓደኛቸው ደግሞ ኮተቤ ያስተምር ነበር:: ድግሪውን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይከታተላል:: እናም አንድ ጊዜ ኮተቤ አንድ ጊዜ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እያሉ ስለሚያጠኑ በዚያ አጋጣሚም ነበር እርሷን ያገኙዋት:: እርሷም እንደ ጓደኛቸው ኮተቤ ነበር የምትማረው:: እናም በተደጋጋሚ ኮተቤ በሚሄዱበት ጊዜ ስለሚያገኟትም ውስጣቸውን ገዛቻቸው:: መልከመልካም ብቻ ሳትሆን የውስጥ ንጽህናዋም ልባቸውን ማርኳቸዋል:: ስለዚህም ጊዜ ሳይፈጁ ውሃ አጣጪያቸው እንድትሆን ጠየቋት:: ፈቃደኛ ሆነችናም ተጋቡ:: ዛሬ የሦስት ልጆቻቸው እናትም ሆነችላቸው::

እንግዳችን እንደሚሏት እርሷ ጠንካራ ሴትም ነች:: ምክንያቱም ብቻዋን ትቼ ለሦስተኛ ድግሪ ትምህርት ስሄድ ሁለቱን ልጆቼን ተንከባክባ ነው ያሳደገቻቸው:: ያው ተፈቅዶልኝ ይዢያቸው እስክሄድ ድረስ:: በእያንዳንዱ ነገርም ከጎኔ እንደሆነች ነው:: በተለይ በምሰራቸው ሥራዎች የእርሷ ድጋፍ መቼም አይለየኝም:: እናም እርሷ ለልጆቼ አናጺ ለእኔ ደግሞ ምርኩዝ ነች ይሏታል::

ፕሮፌሰር ስለ ልጆቻቸውም ያሉት ነገር አለ:: ልጆቻቸው እንደእርሳቸው ሆነው እንዲያድጉ ብዙ ሰርተውባቸዋል:: ለዚህም ማሳያው አሜሪካ እየተማሩ ሳለ በራሳቸው ጥረት ከፈለጉት መጥተው መማር ይችላሉ ብለው ከትምህርት ገበታቸው ነጥለው ይዘዋቸው መምጣታቸው ነው:: በተለይ ሁለተኛዋ ልጃቸው በጣም ጎበዝ ተማሪ ከመሆኗ የተነሳ ራሳቸው አሜሪካዊያን ልዩ ችሎታ ካላቸው ውስጥ አካተዋት ትምህርት ጀምራ እያለ ነው አስወጥተው አገሯ እንድትማር ያደረጓት:: ነገር ግን ከብዙ ዓመታት በኋላ በትምህርት እድል በፊት የነበረችበት አገር ገብታ እርሳቸው የተማሩበት ዩኒቨርስቲ ትምህርቷን መከታተል ችላለች::

ሁለተኛዋ ልጃቸው ሌላም ታሪክ አላት:: በጣም አንባቢ በመሆኗ የተነሳ ሜዲስን የመግባት እድሉ ገጥሟት ነበር:: ገብታም ልክ እንደ አባቷ የመጀመሪያ ዓመትን ተማረች:: ሆኖም ጥሪዋ ያ እንዳልሆነ ተሰምቷት ለቀቀች:: አርኬዎሎጂ አዙራም በማዕረግ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆና ተመረቀች:: ትምህርቱ እንደተጠናቀቀ በወሩ ሦስተኛ ድግሪ የመስራት እድሉ ገጠማትና ወደ አሜሪካ አቀናች::

የመጀመሪያው ልጃቸውም ቢሆን በአገሩ ባህልና ወግ ተምሮ ካጠናቀቀ በኋላ በራሱ ጥረት አሜሪካ በመሄድ አርክቴክቸርን ተምሮ ወደ አገሩ በመመለስ በኢሲኤ ተቀጥሮ እየሰራ ይገኛል:: እናም እርሳቸው በአገር ፍቅር ማደግን በደንብ ስለተረዱት ልጆቻቸውም በአገር ፍቅር ስሜት እንዲያድጉ አድርገዋቸዋል:: ሁሉም ስለአገራቸው የተለየ ስሜት እንዲኖራቸውም ሰርተውባቸዋል:: ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ በወሬ ሳይሆን አሳይተው ነው:: ምክንያቱም በአሜሪካ ተምሮ የተመለሰ ኢትዮጵያዊ ጥቂት ቢሆን ነው:: እርሳቸው ግን ከአገሬ ማንም አይበልጥም የሚል እምነት ስላላቸው ተመልሰዋል:: ብዙዎች በዚህ ተግባራቸው ዛሬ ድረስ እንደሚናደዱባቸው ያወሳሉ:: ግን እርሳቸው አገር በምን ትተካለች መርሀቸው ነው::

መልዕክት

ልጅነት ላይ መስራት አገርን ከችግር መታደግ ነው:: ሲያድጉ ይዘውን የሚጓዙት ፍቅር፤ መታዘዝ፤ መፍጠር፤ አንድነት፤ ትብብር ብዙ ነገራቸውን ለነገ የሚያስቀምጡበት ነው:: ለዚህ ደግሞ ቤተሰብ የመጀመሪያውን ድርሻ ይወስዳል:: አትችልም፤ ከእንትና ጋራ አትሁን፤ ስደበው፣ ምታው እያሉ ማሳደግ ቁልቁል ልጁንም ሆነ አገሩን መክተት ነው:: ምክንያቱም ሲያድግ እርሱም የሚጨምርበት ነገር ይኖራልና:: ከጎረቤትም የሚያዳብረው ነገር ብዙ ነው:: ዛሬ መመለሻ ያጣንለት ጥላቻ የመጣውም ከምንም አይደለም:: ራሳችን ከሰራናቸው ልጆች ነው:: ስለዚህም ዘራችን ፍሬያማና ተቆርጦ ሳይመር የውስጥን ሰላም እንዲሰጠን ከፈለግን ልጆቻችንን በፍቅር መንፈስ ብቻ እናሳድጋቸው የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው::

ዛሬ ጎረቤትን ውጣልኝ የምንልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል:: ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ጎረቤት አይቶ ከጥፋቱ የሚመለስ ትውልድ መጥፋቱ ነው:: ጎረቤትም ቢሆን ምን አገባኝን መርሁ አድርጓል:: ትውልዱን መንከባከብ፤ መምከርና ጥሩ መንገድን የሚያሳይ ጎረቤት ካለ ምንም ስህተት የሚፈጽም ልጅ አይኖርም:: ቢኖርም ቶሎ የሚነቃና የሚታረም ነው የሚሆነው:: ለሰፈሬ፣ ለብሔረ የሚልም አይሆንም:: ይልቁንም ለአገሬ ለሰው ልጅ ማለት ይጀምራል:: ይህ ሲሆን ደግሞ በእያንዳንዳንዱ አካባቢ ላይ የችግር መንስኤ የሚሆነው ብሔር፣ ሀይማኖት ቦታ አይኖረውም:: ስለሆነም እናም ያ የቀደመ ባህሉን ወደ ተተኪው ላይ ማምጣት አለበት:: የአገር ደህንነት በእነርሱም ዘንድ ነውና::

በውጪ መኖር ብቻ በራሱ ሀብታምነት አይደለም:: አገርን ለመጥላትም ምንም አይነት መሰረት አይኖረውም:: ምክንያቱም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለስሙ አሜሪካ ኖረ እንጂ በብዙ ችግር ውስጥ እንደሚኖር እሙን ነው:: በዚያ ላይ ችግሩን እንኳን የሚጋራው ዘመድ አዝማድ የለውም፤ እንደኢትዮጵያም አይዞህ የሚለው ከስንት አንድ ነው:: ለያውም ኢትዮጵያዊ ከሆነ:: በዚያ ላይ በሰው አገር ሲኮን ያለው የባዕድነት ስሜት መቼም ነጻ አያደርግም:: ልፋት እንጂ ሀብት የሌለበት አገር ነው:: ስለዚህም ሁሉ ነገር በአገር እንደሚያምር እውጪ ያሉትም ሆኑ በአገር ውስጥ የሚኖሩ መረዳት አለባቸው::

ማማራቸውና መበልጸጋቸው በአገራቸው ብቻ መሆኑንም መረዳት አለባቸው:: ስለዚህም ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ በቻሉት ሁሉ አገራቸውን መደገፍ ይገባቸዋል:: እውቀት፣ ጉልበት፣ ገንዘብ እናጋራው ብንል ብዙ አለንና ለዛሬው ፈውሳችን እንጠቀምበት ይላሉ::

በሁሉም አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተጋመደ ቤተሰባዊነት የመሰረቱ ናቸው:: ውጣልኝ ቢባሉ ቤተሰብ እንጂ ግለሰብም አይወጣባቸውም:: እናም ዛሬ ላይ ያለነው ሰዎች አንድ ነገር ቆም ብለን ማየት አለብን:: ሁኔታው ዘለቄታዊ ነውይ የሚለውን:: ምክንያቱም ድርጊቱ ነግ በኔ ያለበት ነው:: ማንም ንጹህ ብሔር ተሰጥቶት የተወለደ የበለጠ አይደለምም:: ስለዚህም ሂደት ያመጣውና ሂደቱ የሚሽረው መሆኑን አምነን ድርጊቱን መቃወም ፈጣኖች ሆነን መማር አለብን::

ህይወታችንን ከፈለግናት ሲሆንብን ሳይሆን ሲሆንባቸው ባየነው ለመማር መጣሪያ ጊዜው አሁን እንደሆነ እናስብ:: እንደውም ለሚያደንቅ ሰው ሰፊዋ ኢትዮጵያ የተሰራችበትን ታሪክና ብሔረሰብ ማድነቅ ነው ያለበት:: ምክንያቱም እስከዛሬ ኖሯል:: ወደፊትም ቤተሰብ ስለሆነ ይኖራል:: ማንም ማንንም ሊያጠፋው አይችልም:: እናም ይህንን ማሰብና ጠልቆ ማየት ይገባል የመጨረሻ መልዕክታቸው ነው

አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2013

Ad Widget

Recommended For You