ተግባራዊ አብሮነት

 ምንጊዜም ቢሆን እያንዳንዱ ዘመንና ወቅት የሚፈልገው፣ የሚጠይቀው የራሱ የሆነ ፍላጎት (አንዳንዴም “ልዩ ፍላጎት”) አለው። በተለይም አንዳንድ ያልተለመዱ፤ ያልተጠበቁ ሁኔታዎችም ሆኑ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ያ እነዚ(ያ)ህ ሁኔታዎችና አደጋዎች ያጋጠሙት ዘመን አስቸኳይ በሆነ መልኩ ተግባርን ይፈልጋል፤ በመሆኑም ያ ተግባር ይፈፀም ዘንድ እራሱ ዘመኑ ያስገድዳል ማለት ነው። የአሁኑ ዘመናችን፣ ሁኔታችንም ሆነ ይዞታችን የሚፈልገው ተግባር አለና ስለ እሱ መነጋገር ይገባናል፤ ስለ ተግባራዊ አብሮነታችን።

“ተግባራዊ”ነት አንድ በፍጥነት የሚያሳስበው፣ ወይም ወደ አእምሯችን ጓዳ እንዲመጣ የሚጋብዘው መልእክት ቢኖር ወዲያውንነትን፣ አሁንነትን፣ ፍጥነትን ነው፤ ጊዜ የሚሰጥ ጉዳይ አለመኖሩን፣ አንድ በተቻለ ፍጥነት ሊወገድ የሚገባው አደጋ መኖሩን ነው ሹክ የሚለን። በመሆኑም ተግባራዊ አብሮነታችን ከምንግዜውም በላይ የሚያስፈልግበት ግዜ ቢኖር አሁን፤ ዛሬ ነውና እጅ ለእጅ ተያይዞ ለተግባራዊ አብሮነት መነሳት ይገባል።

ተግባር ከቃለ-ነቢብ ይለያል፤ ተግባር በድርጊት ይገለፃል። ማድረግ መከወንን ያመለክታል። በመሆኑም አሁን ያለንበት ወቅት ይህን ይፈልጋልና ነባሩ አብሮነታችንን መሰረት ያደረገ “ተግባራዊ አብሮነት”ን ስራ ላይ ልናውለው፤ (ማለትም አብረን ተባብረን በጋራ ልንጋፈጠው፣ ልናስወግደው የሚገባን ትልቅ ጉድፍ አለ ማለት ነውና) በተግባር የተደገፈ አብሮነታችን እጅጉን ይፈለጋል።

ድሮም፣ ዛሬም ሆነ ወደፊት የአብሮነታችን ጉዳይ የታወቀ እሴታችን ነው። በእርግጥ ስለ ታወቀ ጉዳይ መልሰን ማውራት አያስፈልግም ይሆን ይሆናል። ነገር ግን ከላይ እንዳልነው ዘመኑ፣ ያለንበት ወቅት ከሚፈልገው ተግባራዊ ርምጃ አኳያ መወሰድ ያለበትን ተገቢና ጠቃሚ ርምጃ ለመውሰድ ይቻል ዘንድ ወቅታዊ አብሮነታችንን በተመለከተ አንዳንድ ሀሳብ ልንለዋወጥ፤ በተለዋወጥንበትም ላይ አጥብቀን ልናስብበት፣ አስበንም ተግባራዊ ልናደርገው የሚገባ ተግባራዊ አብሮነት ያስፈልገናል የሚል መሰረታዊ ሀሳብ ማንሳት ግን የግድ ያስፈልጋል፤ የሚያስፈልገው ደግሞ ከሁሉም በላይ ጉዳዩ የጋራ ደህንነት ጉዳይ፤ ጉዳዩ የጋራ ህልውና ጉዳይ፤ ጉዳዩ የህዝብ ጉዳይ፤ ባጠቃላይ ጉዳዩ የአገር ጉዳይ በመሆኑ ነው።

ለመሆኑ ይህ ጉዳይ የምንለው ጉዳይ እራሱ ምንድን ነው? አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ነውና

 አፍረጥርጠን እናውራው።

ያለንበት ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅግ የከፋ ነው። ክፋቱም ያነጣጠረው ውድ የሰው ልጅ ህይወት፤ ለዛውም የንፁሀን ህይወት ላይ ነው። ዛሬ በዚህች ቅድስት አገር እሳት እዚህም እዛም ይነዳል። በነበልባሉ እየነደዱ ያሉት ደግሞ እሳቱን የለኮሱት የሚያቀጣጥሉት ሳይሆኑ ባብዛኛው ህፃናትና እናቶች ናቸው። ነገ አገሪቱ የሱ ነች የሚባልለት ወጣትም በማያውቀው፤ በማያገባው እየገባ፣ በፌስቡክ አሉባልታ እየተገፋፋ እሳቱ ውስጥ በመግባት እራሱንም፣ ቤተሰቡንም አገሩንም እየጎዳ ነው።

የእነ ግብፅ ረጃጅም እጆች ከባንዳው እጆች ጋር በመያያዝ ጓዳችን ድረስ ዘልቀው እያጋደሉን፤ እያገዳደሉን ይገኛሉ። እነ ሆድ አምላኩ ለወገን እልቂት ምን ተግዴ በመሆናቸው ብቻ አገር ቁና እየሆነች መመልከት ከጀመርን ከራረምን። በመሆኑም ነው ዛሬ በዚህች ብጣቂ ገፅ ከምን ግዜውም የበለጠ ዛሬ ተግባራዊ (በተግባር የሚገለፅ) አብሮነት ያስፈልገናል ማለትን የመረጥነው።

ይህንን እሳት ለማጥፋት ግለሰብ አቅም የለውም፤ ይህንን መተላለቅ ለማስቆም ቡድኖች ክንዳቸው አይችልም። ይህን አደጋ ለመቀልበስ (ሰሞኑን ከሀይማኖት ጋር በተያያዘ ተደግሶልን የነበረውን አሰቃቂ ውድመት እንዳከሸፍነው) የሁሉም ሰው ክንድ፤ የጋራ አብሮነትና ትግልን የግድ ይላልና “ሁሉም ለእናት አገሩ ዘብ ይቁም!!!” የሚለው ዛሬም ይሰራል ማለት ነው።

ወቅቱ፤ ያለንበት ብቻ አይደለም ቀደም ካሉት አመታት ጀምሮ እኛና አጠቃላይ አገራችን (የተፈጥሮ ሀብቶች ሳይቀሩ) በተሳሳተ የፖለቲካ ቀመር (አንዳንዴም በተራ ብሽሽቅ) ምክንያት በየጊዜው እየከፋ በሚሄድና ከዚህ መለስ በማይባል ችግር ተተብትበን የምንገኝበት ክፉ ወቅት ነው።

እንደሚታወቀው ማንኛውም ሰው ወይም አገር ችግር ያጋጥመዋል። ልዩነቱ እያንዳንዱ ችግር የገጠመው አካል ከዛ ችግር ለመውጣት የተጠቀመበት ብልሀት ሲሆን፤ ከተሳካለት አመለጠ ካልተሳካለት ግን ቀለጠ ማለት ነው።

በአሁኑ ሰአት እስከ አንገታችን ካጠመቁን ፖለቲካ አመጣሽ ችግሮች ለመውጣት፤ ብሎም ለመገላገል በብዙዎች እየተመከረ፣ በመንግስት እየተነገረ፣ በጥናቶች እየተመለከተ ያለው አዋጭ መፍትሄ “አብሮነት”፤ በተለይም “ተግባራዊ አብሮነት” – አሁኑኑ በተግባር የሚገለፅ አብሮነት ነው። ይህ ነው ከአሁኑ ክፉ ዘመን (ደዌ) ችግራችን መሸጋገሪያችን።

በማንኛውም መንገድ አብሮነት ጥንካሬ ነው፤ አብሮነት ውበት ብቻ ሳይሆን ጉልበትም ጭምር ነው። አብሮነት ከነጠላነት በባህርዩም በግብሩም ይለያል። መለየት ብቻ አይደለም፤ አብሮነት የነጠላነት ተቃራኒ ነው። በመሆኑም ችግሮች፤ በተለይም የአሁኑ አይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ ከነጠላነት ይልቅ በርእሳችን “ተግባራዊ አብሮነት” ባልነው አብሮነት ብቻ ነው መቋቋም የሚቻለው።

አገርና ህዝቦቿ ችግር ውስጥ ናቸው ከተባለ ያለምንም ግራ መጋባትና የትርጉም መዛባት ዜጎች አንድ ግዙፍ የሆነ የጋራ ጠላት አጋጥሟቸዋል ማለት ነው (ከላይ ያልነውም ይህንኑ ነው)። እውነቱ ይሄው ነው። ቀዳሚው እውነት ይህ ከሆነ ቀጥሎ ያለው እውነት የጋራን ጠላት መከላከል ወይም ማሸነፍ፣ ወይም ጥሎ ማለፍ የሚቻለው ደግሞ በጋራ ነው ማለት ነው። ይህ እውነት ከሆነ “ተግባራዊ አብሮነት”ን ተግባራዊ ማድረግ የህልውና፤ ለዛውም የአገርና ህዝብ ህልውና ጉዳይ ነውና ጊዜ የሚሰጥ፣ “ቆይ” የሚያሰኝ ባለመሆኑ ፈጣን ፍጥነትን ይጠይቃል።

ጥቂት ከማይባሉ አመታት ወዲህ በእነ ቦኩሃራም እየተንገላታች ያለችው ናይጄሪያና ህዝቦቿ ከአገሪቱ ታዋቂ ሰዎች፣ የአንድነት ኃይሎችና ማህበራዊ ተቋማት የተላለፈላት ወሳኝ መልእክት ቢኖር ናይጄሪያ አሁን የገጠማትን መጠነ ሰፊ ችግር ለመቋቋምና አሸንፋም ለመውጣት የሚያስፈልጋት አንድ ወሳኝ ነገር ቢኖር ህዝቡ ተባብሮ፣ አንድ ሆኖ፣ በአንድነት ተሰልፎ፤ በመደራጀት እራሱንና አገሩን ከጥቃት እንዲከላከል፤ ይህንንም የናይጄሪያ መንግስት እንዲቀበለው፤ አውቆም በመንግስታዊ መግለጫ እውቅና እንዲሰጠው፤ እንዲፈቅድና በአስቸኳይም በህዝቡ አማካኝነት ተግባራዊ እንዲደረግ የሚል ነው።

እኛም (የናይጄሪያ ታዋቂ ሰዎች፣ የአንድነት ኃይሎችና ማህበራዊ ተቋማት እንዳሉት) የጋራ ጠላትን በጋራ፤ በተባበረ ክንድ እንጂ በተናጠል እወጣዋለሁ ብሎ መፍጨርመር ለራስም፣ ለአገርም፣ ለህዝብም አይጠቅምምና አንድ ሆነን በጋራ ልንረባረብና ሰላም የሰፈነባት አገር እንድትሆን፤ የንፁሀን ዜጎች ህይወት እንዳይቀጠፍ፣ ሀብትና ንብረት እንዳይወድም እናድርግ እንላለን።

አሁን የገጠመን ችግር ግልፅ ነው። ግልፅነቱም ችግሩ ወደ መጠፋፋትና መጥፋት እየወሰደን መሆኑ ነው። በመሆኑም ይህ አስከፊ አደጋ (በተለይም ምርጫን አስታኮ) ሙሉ ለሙሉ ከጭንቅላት ወደ መሬት ሳይወርድና ሰይጣናዊ ተልእኮውን ሳይወጣ ሁላችንም በጋራ ሆነን፤ እንደ ቀድሞው የአድዋው ድል (እንደ አሁኑ የህዳሴ ግድባችን) ሁሉ በጠነከረ አብሮነት ልንታገለውና ሁለንተናዊ ህልውናችንን ልናስከብር ይገባል።

Recommended For You