‹‹የህዳሴ ግድቡ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካንም የወደፊት የልማት አቅጣጫ የሚወስን ነው››- ዶክተር አየለ በከሬ

አሜሪካ ወደ 35 ዓመት ያህል ኖረዋል። በቆይታቸውም በመጀመርያ ተማሪ፤ ቀጥሎ አስተማሪ ሆነው አገልግለዋል። ዋና ጥናት ያደረጉት በኢትዮጵያ ፊደል ላይ ሲሆን፣ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩት የአርሜኒያ ፊደል ከኢትዮጵያ ተወሰደ ወይስ አልተወሰደም በሚል ርዕስ ላይ ነው። በዚህም የአርሜኒያ ፊደል ከኢትዮጵያ መወረሱን ለማሳየት ሞክረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ፊደል ዙሪያም መጽሐፍ ጽፈዋል። በተጨማሪም በዓድዋ ላይ ብዙ ጥናት አካሂደዋል። በዓድዋ ላይ የሚቋቋመው የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባልም ናቸው። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በቅርስ ጥናት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆነው ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን፣ በኮቪድ 19 ምክንያት ወደአዲስ አበባ ለመምጣት ተገደዋል። ቀጥሎም በአካባቢው፤ መንግሥት ሕግ ለማስከበር ባደረገው ዘመቻ ወደስፍራው ለመመለስ ባለመቻላቸው በአዲስ አበባ የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህም ሥራዎች መካከል የመከላከያ ሙዚየም ሥራ ተጠቃሽ ሲሆን፣ እሱን በማማከር እንዲሁም የጥንቱን ታሪክ በማቀናበር ትርክቱን በማዘጋጀት ላይ ናቸው። የዛሬው እንግዳችን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አየለ በከሬ። አዲስ ዘመን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእኚህ ምሁር ጋር ቃለ ምልልስ አካሂዶ እንደሚከተለው አቅርቦታል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።

 አዲስ አበባ፡በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ከፊት ለፊቷ ሁለት ትላልቅ ጉዳዮች ይጠብቋታል፤ ምርጫና የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት፤ ለመሆኑ እነዚህ ጉዳዮች ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት የሚኖራቸው ፋይዳ ምንድን ነው ይላሉ?

ዶክተር አየለ፡ እነዚህ ሁለቱ ለአገሪቱ በጣም ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው። ለምሳሌ የህዳሴን ግድብ በምንወስድበት ጊዜ ሁለተኛው ሙሌት ከተሳካ እሱ የሚያሳየን ወደመጨረሻው እየሄድን መሆናችንን ነው። ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት 13 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ስለሚይዝ ከዚህ ቀደም በአንደኛው ዙር ከተሞላው 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ጋር ሲደመር ሱዳንና ግብጽ ተንኮል ቢያስቡ እንኳ መጀመሪያ የሚያጠፋቸው እነርሱኑ መሆኑ ነው።

ዋናው ቁምነገር ግን አሁን ላለብን ጫና ምስጢሩ የዓባይ ውሃ መገደቡ ነው። ምክንያቱም ይህን ስታደርግ እንግሊዞች የቁጥጥር ሥርዓቱን በፈጠሩት መሰረት እስካሁን ድረስ ውሃውን በባለቤትነት ትቆጣጠር የነበረችው ግብጽ ነበረች። በመሆኑም ግብጽ ዋና ማስተር ፕላን ይዛ ትቆጣጠረው ነበር። በዚህም በጣም ተጠቃሚ ነበረች። የሁለተኛውን ዙር ውሃ መሙላታችን ግብጾችን ቢረብሻቸውም ዋናው ነገር ዕቅዳችንን በአግባቡ እየተገብርን ስለመሆናችን አመላካች ነው። ይህ በመሆኑ የግብጾች ሴራና ተንኮል እየቀነሰ ይመጣል። ይህ ደግሞ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ህልውና እንዲሁም ለታሪካችንም ሆነ ለነፃነታችን ወሳኝ ነው።

አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ሱዳን እስከ አምስት ስድስት ግድብ እንዲሁም ግብጽ ደግሞ ትልቁን የአስዋን ግድብ ጨምሮ ሌላም ግድብ አላት፤ እኛ ግን በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ የለንም። እነሱ አሁን ላይ እየናቁን ያሉት በዓባይ ላይ ምንም አይነት ግድብ ስለሌለን ጭምር ነው። ስለዚህ ግድብ መገደባችን ረሃባችንን ለማስታገስም ጭምር ነው። በመሆኑም ግድቡ ሁለንተናዊ ፋይዳ አለው ማለት ነው።

ሌላው ነገር ደግሞ በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜም ሆነ በደርግ ዘመን ቢባል እንዲያውም ከአፄ ምኒልክ ጀምሮ ግድብ ለመገደብ ብዙ ጥረት ነበር፤ ነገር ግን ግብጾች በሚያደርጉት በተለያየ ተጽዕኖ ምክንያት ግድቡን መጀመር አቅቶን ቆይቷል። እናም አሁን ይህ የወጠነው ዓላማ መሳካቱ በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል። ስለዚህ ያን ያህል ክብደት ያለው ነገር ስለሆነ መጠናቀቅ አለበት ማለት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ምርጫን በሚመለከት ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ድረስ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ ተካሂዶ አያውቅም። በቀጣይ ግን ሙሉ ለሙሉ እንከን የለውም ባይባልም በተሻለ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ ነው የምረዳው። ምርጫ በውጭ ተቃውሞ ሊስተጓጎል አይችልም፤ ምርጫ ስናካሄድ ለኢትዮጵያውያን ነው፤ ያ ምርጫ ደግሞ አስፈላጊነቱም ለኢትዮጵያን ነው እንጂ ለአሜሪካውያን አሊያም ለፈረንሳውያን ወይም ደግሞ ለአውሮፓውያን አይደለም። ስለሆነም እኛው በምናወጣው ዕቅድና አካሄድ ራሳችን ወስነን ካካሄድነው ለኢትዮጵያ ብዙ ነገር ቀላል ይሆናል።

ስለሆነም ምርጫም ሆነ የህዳሴ ግድብ ሙሌት ለእኛ ወሳኝ ናቸው። እነዚህን ሁለት አንኳር ጉዳዮች ማሳካት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ይቀይረዋል። አሁን ያለውም ጫናም ቢሆን ፀጥ ይላል።

አዲስ ዘመን፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከውስጥም ሆነ ከውጭ በኢትዮጵያ ላይ እየደረሱ ያሉ ጫናዎች አሉ፤ እነዚህ ከምን የመነጩ ናቸው ይላሉ?

ዶክተር አየለ፡ የጫናው መብዛት ብቻ ሳይሆን ጫናውን የሚያሳድሩ አካላት ሌላ ሥራቸውን ትተው ሙሉ በሙሉ ትኩረታቸውን የሰጡት ለእኛ እስከሚመስል ድረስ ነው ጫናው የበረታው። ጫናውን ስመለከት የማስተውለው ነገር ቢኖር የውጭውና የውስጥ ኃይሉ ተናቦ የመሥራት ነገር ነው። ነገር ግን በአገር ላይ መደራደር አስፈላጊ አልነበረም። ከመንግሥት ጋር እንኳን ጥል ቢኖር የአገር ጉዳይ ከተነሳ ያለውን ልዩነት ወደጎን በመተው አብሮ መቆም ነው የሚኖርብን።

ነገር ግን አሁን ላይ የምናየው ነገር ያ የውጭ ኃይል ከውስጥ ኃይል ጋር በመሥራት አገራችንን ለመበታተን ነው እንቅስቃሴ እያካሄደ ያለው። ይህ ሁኔታ ደግሞ የሚያሳየን እ.ኤ.አ በ1884 እና 1885 አካባቢ አውሮፓውያን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ይህ የፈረንሳይ፣ ይህ ደግሞ የእንግሊዝ፣ ያኛው የፖርቹጋል እያሉ የተከፋሉበት (Scramble for Africa) በሚል በርሊን ላይ ኮንፈራንስ ነበር።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ሁኔታ ሳይ ያንን ያስታውሰኛል። ኢትዮጵያን የመቀራመት (Scramble for Ethiopia) ሁኔታ ነው ያለው። ይህን በደንብ ለመረዳት ከተፈለገ በተለይ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ለማሳደር መናበባቸው ምስጢሩ ምንድን ነው ካልን ወደ 27 እና 30 ዓመት ወደኋላ መሄድ ይኖርብናል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የተደረጉና በይፋ ያልወጡ ምስጢራዊ ስምምነቶች አሜሪካንን ዙፋኑ ላይ አስቀምጧት ነበር። በዙፋኑ ላይ መቀመጥ ደግሞ ከኢትዮጵያ የሚያስገኝላት ብዙ ጥቅማጥቅም አለ ማለት ነው።

አሁን እነዚያ ጥቅማጥቅሞች ምንጫቸው በድንገት ነጠፈ። በመሆኑም እንደእኔ ግምት ከሆነ ዴሞካራቶቹ ገና የነጩ ቤተ መንግሥትን ደጃፍ ከመርገጣቸው በኢትዮጵያ ላይ ሌትም ቀንም እያደረጉ ያለው ነገር የሚያሳየን ባለፉት 27 እና 30 ዓመታት በእነሱ ቁጥጥር ሥር መሆናችንን ነው። እነሱ ወሳኝ እንዲሁም ፈላጭ ቆራጭ መሆናቸውን ነበር።

አሁን ደግሞ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በእኛ ዘንድ የብሔራዊነትና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ መምጣት ጀመረ። ይህ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በአንድ በኩል ኢትዮጵያን ለማልማትና ለማሳደግ ነው፤ ነገር ግን ለእነርሱ ይህ ነገር ልክ እንደ የዓደዋ ድል የቅኝ አገዛዝን ለማጥፋት እንደረዳን ሁሉ አሁን ደግሞ ያለው የልማትና የተለያዩ መልካም እንቅስቃሴዎች በሙሉ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም የአፍሪካ አገር ተምሳሌት ሆኖ የእኛን ጥቅም ያሳጣናል በሚል ነው የመቀራመቱ ጉዳይ እያሳሰባቸው ያለው።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ችግሮች አሉባት። በዘር፣ በኃይማኖት ሰው እርስ በእርስ እንዲጋጭ እየተደረገ ነው፤ መንግሥትም ይህን ማስተዳደር አልቻለም በሚል ሰበብ ተቀራምተው ሊከፋፍሏት ነው የሚያስቡት። ለዚህም ነው ህወሓትን ከመንግሥት ጋር እኩል አድርገው ለማሳየት የሚጥሩት። ምክንያቱም ህወሓት የብጥበጣው ዋና ተጫዋች በመሆኑ ነው። ለዚህም ነው እሱ አሁንም ተሰይሞ ወንበሩን እንዲይዝ የሚፈልጉት።

አሜሪካ ከእኛ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከጀመረች ከአንድ ምዓተ ዓመት የዘለለ ነው፤ በብዙ ነገር አጋር ነን፤ በተለያየ መስኩ የምንተባበር ሆነን ሳለ ያንን ሁሉ ታሪክ ዘንግተውና ችላ ብለው በድንገት ፀረ መንግሥት ሆነው ቁጭ አሉ። ይህ ሁሉ የሆነው ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ጥቅም በማጣታቸው ነው። አሁን ለየት የሚያደርገው ነገር እነሱን ይወክል የነበረው ኃይል ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውንና ሌሎችንም ይቆጣጠር ነበርና ይህን በእሱ አማካይነት ይቆጣጠር የነበረውን ነገር አሜሪካውያኑ ስላጡ ይህንኑ ኃይል ወደ አራት ኪሎ ለመመለስ በማሰባቸው ሁለት ዓመት ሙሉ ዝግጅት አድርጎ ሞከረ። መንግሥት ደግሞ ይህ ሕገ ወጥ ነው በሚል ሕግን የማስከበር ተግባሩን ተወጣ። አሜሪካውያኑ ይህን ኃይል በመመልመል ነው አገራችንን ለማዳከም ጥረት እየተደረገ ያለው። ነገር ግን ምርጫ እስከተደረገ ድረስ ምንም የሚመጣ ተግዳሮት አይኖርም ብዬ ነው የማምነው።

አዲስ ዘመን፡ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከአሜሪካ እየደረሰባት ያለው ጫና እንዴት ያዩታል? ጫናውን ለመቋቋም ምን ማድረግ አለባት ይላሉ?

ዶክተር አየለ፡ ጫና እንዲደረግ ጎትጓቿ ግብጽ ናት፤ ቀደም ሲል የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከነበሩት ትራምፕ ጀምሮ አዲሱ አስተዳደራቸውም ለግብጽ ሲሉ ኢትዮጵያውያንን ለመጫን ነው ጥረት የሚያደርጉት። ይህን የሚያርጉት ለስትራቴጂክ ፍላጎታቸው ሲሆን፣ ግብጽንም ለማስደሰት ሲሉ ነው። በተለይም ደግሞ በ27 ዓመታት ውስጥ ይቆጣጠሩት አካላት እንደገና ተመልሰው የአሜሪካንን የአስተዳደር ስልት ተጠቅመው ኢትዮጵያውያንን እናምበረክካለን በሚል ነው የተነሳሱት። ይህን የሚያደርጉት እንደእነ ሱዛን ራይስ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት የእነሱ ተጠሪ የሆነች ሰው እና ሌሎች ውስን ሰዎች ናቸው። እነዚህ አካላት ከቀደመው መንግሥት ጋር በጣም የቅርብ ትስስር ያላቸው ናቸው። እነዚህም ኢትዮጵያን እንደሶሪያ፣ የመንና ኢራቅ በመበታተን ለመጠቀም አስበው የሚንቀሳቀሱት እንጂ የአሜሪካ ሕዝብ በኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ያለውን ጫና የዚያን ያህል የሚያውቅ አይደለም። ምክንያቱም እኔ በ1977 ዓ.ም አሜሪካ ነበርኩና በዚያ በተራብን ጊዜ ሕዝቡ ያሳየውን ደግነት አልረሳውም።

ኢትዮጵያን እንደሌላው አፍሪካ አገር ማሰብ የማይቻል ነው። በቅኝ ያልተገዛ ህዝብ በቀላሉ እጅ የሚሰጥ አይደለም። ስለዚህ አሁንም በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና እውነታውን ለሚመለከተው በማሳወቅ ማክሽፍ ነው የሚጠበቅብን።

አሜሪካ ግብጽ ውጥረት ውስጥ እንድትገባ የማትፈልገው የአሜሪካ ቁልፍ አገልጋይ በመሆኗ ነው። የግብጹ ፕሬዚዳንት የአገር ውስጥ ተቃውሞ አለባቸው። በዛ ተቃውሞ እንዳይወድቅ እና በዛ ተቃውሞ ረብሻ እንዳይነሳ ነው የሚጥሩት፤ ይህ ከሆነ በመካከለኛው ምሥራቅ ከባድ ፈተና ይሆናል። በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የአሜሪካ ዋና ዓላማ ደግሞ የእሥራኤል ደህንነትን ማስጠበቅ ነው። ግብጽንም የሚፈልጓት በዓረቡ ዓለም መቶ ሚሊዮን ህዝብ ያላትና ትልቅ ተጽዕኖ የምታደርግ አገር ስለሆነች እነሱም ከሶቬዬት ሕብረት እጅ ፈልቅቀው ነው የወሰዷት። እዚህ ላይ አንድ መታወቅ የሚገባው ነገር ለግብጽ የአስዋንን ግድብ የሠራችው ራሽያ ናት።

የግብጽ ስሌት ሁሌም ቢሆን የናይል ወንዝ ነው። መነካት የለበትም ብለው ነው የሚያምኑት። ስለዚህ ወንዙ የእኛ ነው ብለው ስለሚያምኑ በአገራቸው ሕገ መንግሥት ውስጥ ሁሉ አስገብተውታል። ስለዚህ ግብጽ የምትለው ነገር፤ የእሥራኤል ደህንነት እስከተጠበቀ ድረስ ለእኔ ደህንነት ኃይልን መቆጣጠር ስላለብኝ ከዚህ የተነሳ አሜሪካ እኔን መደገፍ አለባት ነው፤ በዚህም በዓመት አስከ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ይሰጣቸዋል። መሣሪያም በገፍ ይቀርብላቸዋል። ስለዚህም ነው ሁለቱ አንድ ላይ ቅንጅትን እየፈጠሩ ያሉት ማለት ነው።

ግብጽ፣ አሁን አሜሪካንን እየተጫነች ያለችው ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ እየሠራች ያለው ሥራ የእኛን በናይል ላይ ቁጥጥር የማድረጋችንን ኃይል እየቀነሰ ይመጣል። ስለዚህ እሱ ደግሞ ጥሩ አይደለምና እናንተ አሜሪካውያንም ከጎናችን ሆናችሁ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደር አለባችሁ በሚል ነው። ጫናው በአንድ በኩል የመጣው ኢትዮጵያን እያስፈራሩ የሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ሐሳብ ለማስቀየር በማሰብም ጭምር ነው። ከዚህ አለፍ ሲልም ደግሞ መንግሥት መገልበጥ ድረስ ለመሄድ የሚያስችል ሥራ እየሠሩ ነው ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡ጫና ከሚያሳድሩት መካከል ሱዳን አንዷ ስትሆን ከዚህም ጫና አንዱ በቅርቡ የኢትዮጵያን መሬት ወራለች፤ ይህ ወረራ ምንን ያሳያል?

ዶክተር አየለ፡ ወረራው ተቀባይነት የሌለው ሲሆን፣ ይዋል ይደር እንጂ መቀልበሱ አይቀርም። ኢትዮጵያ ሳትቻኮል ሕግ የማስከበር ዘመቻዋን ትታ ወደእሱ አለመሄዷ አግባብነት ያለው ነው። እኔ የሱዳንን ማንነት አሳምሬ አውቀዋለሁ። ይህን ወረራ ያካሄደችው በራሷ አይደለም። ሱዳኖች ሁልጊዜ ቅጥረኞች ናቸው። በተለይ የሱዳን ወታደር ቅጥረኛ ነው። ገንዘብ ያፈሰሰለትን መከተል ነው። ለምሳሌ በሊቢያ ቅጥረኛ የሱዳን ጦር አለ፤ የመን ላይ ሳዑዲ ዓረቢያ ቀጥራ የሚዋጋ አለ። በሙሉ ዓረብ አገር ቅጥረኛ ወታደር ሲፈልጉ የሚወስዱት ከሱዳን ነው። ታሪካቸው የሚያሳየን የውጭ ኃይሎች ሁልጊዜ የሚቆጣጠሯቸው ናቸው።

በነገራችን ላይ ግብጽንም ቢሆን ያልገዛ የውጭ ኃይል የለም ማለት ይቻላል። ግሪክ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ የቱርኩም ቢሆን ገዝቷቸዋል። ለዚህም ነው ግብጾች አፍሪካውያን ነን ለማለት የሚቸገሩት። የግብጽ መሪዎች የመጣነው ከሳዑዲ ዓረቢያ ነው የሚሉት። አሁንም ቢሆን የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሄ ሲባል ያንገራገሩት። ሥነ ልቦናቸው ትንሽም ቢሆን ወደ አፍሪካ ያዘነበለው ዓባይ ላይ ግድብ ሊገደብ ነው ሲባል ነው።

ስለዚህ አሁን ሱዳን ያደረገችው በግብጽ ተገፍታ ነው። ሱዳን በራሷ ችግር ነበረባት። የእኛ መንግሥት ነው ብዙ ሲያደርግላት የነበረው። ከተረጋጉ በኋላ እንኳ ሲታይ ሥልጣን የያዙት ጀነራሎቹ ናቸው። አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያን የካዱት እነዚሁ ጀነራሎች ናቸው። ሕዝቡ በዳቦ እጦት ችግር ፈጥሮ ነበር። ሌላው ቀርቶ ቀደም ሲል ነፃነቷን እንድታገኝ የረዷትም አፄ ኃይለሥላሴ ናቸው፤ አሁንም ቢሆን መሬቱን የወረረችው በግብጽ ተገፍታ ነው።

የሚያሳዝነው ነገር ግብጽ ቀደም ሲል በጣም ሰፊ መሬት ከሱዳን አሊሃብ የሚባል ቦታ ነጥቃ ወስዳለች። ይህ ቦታ ደግሞ በርካታ የተለያየ ማዕድን የተገኘበት ነው። ይህንንም ቦታ ግብጽ እስካሁን ድረስ አልመልስም ስትል ይዛ ቆይታለች። ይህን ቦታቸውን ሱዳኖቹ ግብጽ እንደወሰደችባቸው ሳያነሱት ኢትዮጵያ ይህንና ያንን አድርጋለች፤ መሬታችንን ወስዳለች ማለታቸው የሚገርም ነው። ይህን ያሉት ደግሞ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል መንግሥት ሕግ ለማስከበር እንቅስቃሴ ባደረገ በሳንምቱ አካባቢ ነው። በዚያን ጊዜ ያለውን ክፍተት ለመጠቀም አስበው ነው። ወረራውን ያካሄዱትም ከውጭ ኃይሎች ከፍተኛ ገንዘብ ተስጧቸው ወይም ደግሞ ቃል ተገብቶላቸው ነው።

እንደሚታወቀው ደግሞ ሱዳን እስከ 60 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ አለባት። ከዚህ በተጨማሪም የአሸባሪዎቹ አለቃ የነበረው ቢላደን ሱዳን የነበረ ከመሆኑም በላይ በተለያዩ ቦታዎች ቦምብም በመፈንዳቱ ከዚህ ጋር ተያይዞ ለተጎጂዎች በሚል ካሳም እንድትሰጥ መደረጓና ለእሥራኤል ምቾት ሲባል ከእሥራኤል ጋርም ስምምነት እንድትፈጥር መደረጓም ይታወቃል። ከዚህ የተነሳ ሌሎች በሚያደርሱባት ጫና ኢትዮጵያን ብወጋ ምናልባት ነገሮች ሊቀየሩልኝ ይችላሉ በሚል ተነሳስታ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያን ስትወጋ ተቀጥራ ስለሆነ ገንዘብ ታገኝበታለች። ጀነራሎቹ ገንዘብ ያገኙበታል። ስለዚህ የእኛ መንግሥት ያደረገው ትክክል ነው ባይ ነኝ።

አዲስ ዘመን፡የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 80 ከመቶ በላይ ደርሷል፤ በመጪው ክረምትም የውሃ ሙሌቱ እንደሚካሄድ ይታወቃልና ይህ የውሃ ሙሌት ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የሚኖረው አስተዋጽኦ ምንድን ነው?

ዶክተር አየለ፡ የህዳሴ ግድብ ተጀምሮ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ የእኛን ወይም የአፍሪካን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ነው። እስካሁን ወሰን ተሻጋሪ ግድቦች ላይ የተገደቡ ግድቦች ላይ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የታየበት አይነት ክርክርና ትኩረት መሳብ አልታየባቸውም። ሌላው ደግሞ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ የመገደቡ ጥንስስ የተጀመረው የዛሬ አስር ዓመት ሳይሆን በ50ዎቹ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን አሜሪካውያኑን ጠይቀው ኢንጂነሮችን አማክረው 20 ሚሊዮን ዶላር ከፍለው ጥናት አስደርገዋል። በወቅቱም የጥናቱ ውጤት አራት ዋና ዋና ግድቦች ሊሠሩ እንደሚችሉም አመላክተዋል። ከአራቱ ግድቦች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንደኛው ነው።

ይህም ማለት አሜሪካውያኑ ባጠኑት ጥናት መሰረት ነው ጉባ የተባለው ቦታ የተመረጠው። በወቅቱ ንጉሡ ይህን ግድብ ለመጀመር ሲያስቡ ጣሊያን መጣና አገራችንን ወረረ። በ1960ዎቹም አካባቢ ግርግር ነበር። ንጉሡ ሥልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ የደርግ አገዛዝ አገሪቱን ማስተዳደር ጀመረ። ደርግ ደግሞ እንኪያ ሰላንቲያ ውስጥ ገባ። በዚህ ሁሉ ግብጽ ጉዳዩን በተመለከተ ብድር እንዳናገኝ አደረጉና በወቅቱ ግድቡ እውን እንዳይጀመር ተደረገ።

የህዳሴ ግድብ መገደብ አሁን የሚፈጥረው ነገር አንዲት ድሃ የተባለች አገር በአፍሪካ ትልቁን ግድብ አቅዳ መሥራት በመቻሏ የሚደረግባትን ተጽዕኖ ይቀይረዋል። ከዚህም ባሻገር በአህጉሪቱ አርዓያነቷ ከፍ ያለ መሆኑን አመላካች ነው። ለምሳሌ የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ እንዲቋረጥ ያደረጉት ግብጾች ናቸው። ውሃውን በቅኝ ግዛት ስልት መጠቀም አቁመን በተለይም ግብጽን ብቻ መጥቀሙ ይቅርና ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች የሚጠቀሙበት ፍትሃዊ እና የጋራ በሆነ መርህ እንዲሄድ ነው የኢትዮጵያ ፍላጎት። ይህ ግድብ ከተጠናቀቀ የቅኝ ግዛት አይነት መርህ ያበቃለታል ማለት ነው። ኢትዮጵያም በራስ መቆም እንዴት እንደሆነ ተሞክሮ የምታሳይበት ነው። ስለዚህ የህዳሴ ግድብ የእኛን ብቻ ሳይሆን ለወደፊት የአፍሪካንንም የልማት አቅጣጫ የሚወስን ነው።

አዲስ ዘመን፡አንዳንድ ሰዎች ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እያሳደረች ያለችው በኢትዮጵያ በኩል ያለው የዲፕሎማሲ ሥራ ስለተዳከመ ነው ይላሉ፤ እርስዎ በዚህ ጉዳይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?

ዶክተር አየለ፡ በከፊል እውነት ነው፤ በከፊል ደግሞ እውነት አይደለም። እኛ የነቃነው ከአስር ዓመት ወዲህ ነው። ግብጾች የናይል ወንዝን ለራሳቸው ብቻ ለማድረግ ኢንስቲትዩት ከፍተዋል። የውሃ ኢንስቲትዩታቸው በዓለም የታወቀ ነው። በጣም ብዙ በውሃው ዘርፍ ያጠኑ ምሁራን አሏቸው። ይህ ሁሉ ድካም ለምንድን ነው ቢባል በዓባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን ፍላጎት እና ጥቅም ለማስጠበቅ ነው። ስለዚህ የእኛ ሁኔታ የማይቀየርበት ምክንያት የለም። ግድቡ አልቆ ጥቅም ላይ በሚውልበት ጊዜ ኤክስፐርቶች ያስፈልጉናል። ኢንስቲትዩት እንከፍታለን። ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በዛ ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት ይጀምራሉ። ልክ እንደእነሱ በኢትዮጵያ በዘርፉ ዓለም አቀፍ እውቀት ያላቸው ምሁራን ይፈጠራሉ። ምሁራኑ በሚፈጥሩበት ጊዜ ዘርፈ ብዙ ሥራ ወዳላቸው ድርጅቶች ውስጥ ይገባሉ። በዚህም የኢትዮጵያ ተሟጋች ይሆናሉ።

ቀደም ሲል ስጠቅስ እንደተናገርኩት አሜሪካውያኑ በዓባይ ላይ ግድብ ለመገደብ የሚያስችለውን ጥናት ባካሄዱበት ወቅት ይፋ ያደረጉት 30 የውሃ ፕሮጀክት ነው። መረሳት የሌለበት ነገር ደግሞ የዓባይ ወንዝ ዋናው ይሁን እንጂ 90 መጋቢ ወንዞች እንዳሉት ነው። ከጣና ሐይቅ የሚወጣው ሰባት በመቶ ያህል ብቻ ነው። ስለዚህ እኛን እንድንተኛ ያደረገን ሁኔታው ነው። የዲፕሎማሲው አካሄዱ ፈጣን ያልሆነው ሁኔታ ነው፤ አሁን ግን በግድቡ ዙሪያ የተለያዩ ጥሩ የሆኑ ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶችን እያስተዋልን ነው። ለምሳሌ የውሃ፣ መስኖና ኢንርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ በስፋት እየሠሩ ያሉ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖንና መሰል ባለሙያዎችን ስንመለከት ሁኔታዎች እየተቀየሩ ስለሚሄዱ ሌሎቻችንም እየተነሳሳን እንመጣለን ማለት ይቻላል። ሱዳንም ሆነች ግብጽ በጉዳዩ ብዙ ልምድ ያላቸው ቢሆኑም ኢትዮጵያ ከእነሱ እኩል ተቋቁማ እኩል እየተጓዘች መሆኗን መርሳት የለብንም። ስለዚህ ደካማ የሚለው አስተያየት አጠቃላይ የሆነ እይታ ነውና አንዳንድ ጥሩ የተሠሩ ሥራዎችን የሚያቋሽሽ በመሆኑ እኔ አልቀበለውም።

አዲስ ዘመን፡ሰሞኑን የአሜሪካ መንግሥት ያደረገው የቪዛ ክልከላ መነሻው ምንድነው ብለው ያስባሉ?

ዶክተር አየለ፡ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መንገድ የያዘችው አቋም ማጋጋል ሳይሆን ማርገብ ነው። ይህ ደግሞ በእኔ አተያይ ጥሩ አካሄድ ነው። ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት የአሜሪካ ህዝብ ጉዳዩን ጠንቅቆ የሚያውቅ አይመስለኝም። የአሜሪካው ሎሳንጀለስ ያለው የሆቨር ግድብ ትልቁን የሎሳንጀለስ ከተማን መብራት የሚያበራ ነው። ግድቡን ሲገነቡም ፍፁም የሆነ ሉዓላዊ መብታቸውን ተጠቅመው ነው።

ወደእኛ ሲመጣ ደግሞ ግብጽ ሁሌ የምታነሳው ጉዳይ ኢትዮጵያውያኑ እኛን ሳያማክሩ የሚል ነገር ነው። የግብጽ አስዋን ግድብ ሲሰራ ግን ዋናዋን ኢትዮጵያ አላማከሩም። ሌሎቹንም የተፋሰሱ አገሮችን ሳያማክሩ ነው የገደቡት። እኛ ግን አሁንም ከእነርሱ ጋር የሦስትዮሽ ድርድር እያደረግን ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረስነው። ኢትዮጵያ ደግሞ የእነርሱንም ጥቅም እስካልነካች ድረስ ግድቡን የመገንባት ሙሉ ጥቅም አላት። አሁን አሜሪካ በባለስልጣናቱ የቪዛ ማዕቀብ የመጣሏ ምስጢር ሁለተኛው የውሃ ሙሌት ላይ ጫና ለመፍጠር በማሰብ ነው።

ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ስትስማማ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ አይደለም። ግልጽ የሆነ ስትራቴጂክ ነው የፈጠሩት። ይህ መደረጉ ደግሞ ለኢትዮጵያ የራሱ የሆነ ጥቅም አለው። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያደረገችው ስምምነት እነርሱ በኤርትራ ላይም ሆነ በኢትዮጵያ ላይ ሊያስቀምጡ የሚፈልጉትን ዕቅድ አፍርሶታል። ከዚህም የተነሳ ነው በጉዳዩ ተናድው ማዕቀቡን ሊጥሉ የቻሉት። ነገር ግን በረጅም ጊዜ ዕቅድ ከእኛ የሚያገኙት በጣም ብዙ ጥቅም ስላለ በጉዳዩ የሚቀጥሉበት አይመስለኝም።

አዲስ ዘመን፡በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መንግሥት ምን አይነት ሥራዎችን ማከናወን አለበት ይላሉ?

ዶክተር አየለ፡ እኔ የአዲስ አበባ የሰላም ምክር ቤት አባል ነኝ። እውነቱን ለመናገር አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነቱን የሚያውቅ፣ በሰላም መኖር የሚፈልግ፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር በሰላም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ለመቀራረብ የሚፈልግ ሕዝብ ነው። እርግጥ ባለፉት 27 እና 30 ዓመታት ብሔር ተኮር የሆኑ አቀራረቦች በሕዝቡ መካከል በተወሰነ መልኩም ቢሆን አለመቀራረብ ሁኔታ አሳይቷል።

ትንሽ ያልኩት ምክንያት ስላለኝ ነው፤ ይኸውም አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርሶ አደርና አርብቶ አደር ነው። በመሆኑም ከጠዋት እስከማታ ሥራ ላይ ናቸው። ጠዋት ይወጣሉ ይሠራሉ፤ ሥራው በቀጣዩም ቀን አያልቅም፤ ስለዚህ በየትኛው ጊዜያቸው ነው እነዚህ ሰዎች አማራን፣ ኦሮሞን ወይም ሌላውን ሊጠሉ የሚችሉት። ይህ አይነቱ ጥላቻ ከውጭ የሚመጣባቸው ነው።

ለምሳሌ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች ላይ ሲደርስ የነበረው አሰቃቂ ድርጊት ሁሉ ቢፈተሸ ምንጫቸው ከውጭ ነው። ዓላማቸውም ብሔራዊ መንግሥቱን አዳክመው አገሪቱን ለመበታተን ነው። ብዙ ጊዜ ሲባል የሚሰማው አሐዳዊ መንግሥት ነው፤ ይህ ከሆነ ታድያ እንዴት ነው ከ80 በላይ ቋንቋዎች ሊኖሩ የቻሉት ብሎ ለመጠየቅ ያስገድዳል። አንደኛው ብቻ በዚህ ቋንቋ ብቻ ተናገር ብሎ ቢያስገድድ ዛሬ ላይ የሚታየው ቋንቋ ከየት ሊመጣ ይችላል። እኛ ብዙ ታሪክ ያለንና በጣም የተቆላለፍን ሕዝብ ነን። ማንም እንደሚለን በትንሽ ነገር የምንበታተን አይደለንም። በእርግጥ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩልሽ ኢትዮጵያን የመቀራመት ፍላጎት አለ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ብዙ ከባድ አይሆንብንም። ነገር ግን እነዚህን ኃይሎች ደግሞ ልንንቃቸው አይገባንም። ልክ አሁን እንደተጀመረው አይነት የኢትዮጵያዊነትን የጋራ መንፈስ ማሳደግ ይጠበቅብናል። ሁሉም በየሥራው ውስጥ ይህን የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ከፍ ማድረግ ይኖርበታል። ይህን የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ እስከጠበቅነው ድረስ በአገራችን ውስጥ ዘላቂ ሰላም በቅርቡ ይስፍናል የሚል እምነት ነው ያለኝ።

አዲስ ዘመን፡ለሰጡኝ ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።

ዶክተር አየለ፡ እኔም አመሰግናለሁ።

 አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሰኔ  1/2013

Recommended For You