ለአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩ ስኬታማነት የሁሉም አካላት ርብርብ ወሳኝ ነው!

 የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ዓላማ የአየር ሁኔታ ለውጥን መመከትና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው። አረንጓዴ አሻራ የውሃ ጉዳይ ነው፤ የጤና ጉዳይ ነው። በምግብ ራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት ዋነኛ መሳሪያም ነው። በአጠቃላይ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን ተግባራዊ ማድረግ ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ መንግስት ጠንካራ አቋም ይዞ ወደ ስራ ገብቷል።

አሁን እንደሀገር በተያዘው ፕሮግራም መሰረትም በ2013 ዓ.ም ሊተከል የተዘጋጀው ችግኝ ሰባት ቢሊየን ሲሆን ስድስት ቢሊየን በሀገር ውስጥ አንድ ቢሊየኑ ደግሞ ለጎረቤት ሀገራት የሚከፋፈል ነው። ይሄ የተፈጥሮ ጸጋዎችን በጋራ አልምቶና ጠብቆ በጋራ ተጠቃሚ መሆንን ያለመ ነው። በዘንድሮ ዓመት የተዘጋጀው ችግኝም የአካባቢን ስነምህዳር ከመጠበቅ ባለፈም ሀገር በቀል እጽዋትን የመመለስ እንዲሁም ፍራፍሬዎችን በማልማት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን አብሮ የቃኘ ነው። ዛፍ በአንድ በኩል መልክአ ምድሩን ይጠብቃል፤ ለሰዎችና ጥላን ለሚሹ እጸዋቶች ጥላ ሆኖ ያገለግላል፤ መልሶም ምግብ ይሆናል፤ ተሸጦ የገንዘብ ምንጭ ሆኖ ወደ ኪስ ይገባል። በአጠቃላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው።

በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በ2011 ዓ.ም አራት ቢሊየን ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ ሲጀምር ብዙዎች ቀጣይነት ይኖረዋል ብለው አልገመቱም፤ ቀጣይነቱ ላይ ብቻም ሳይሆን የተያዘው አራት ቢሊዮን ችግኝ የመትከል እቅድ ይሳካል ? እንክብካቤ ተደርጎለት ሊጸድቅ ይችላል ወይ? የሚል አከራካሪ ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጎ ነበር። ሆኖም ግን ህዝብ የመሪውን ሃሳብና ዕቅድ ተቀብሎ በቀናነት እና በእኔነት ስሜት ወደ ስራ ገብቷል። በታሰበው ደረጃም ወደፊት ተራምዶ ወንድ ሴት ፣የተማረ ያልተማረ ፣ ህጻን አዛውንት … ሳይል ሁሉም አሻራውን ለማኖር በቆራጥነት ተሳትፏል። በአንድ ቀን 200 ሚሊየን የመትከል አገር አቀፍ ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ሲገባ ከ350 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል የአለምን ክብረወሰን እስከ መጨበጥ የተቻለበት ክስተት ነበር። ከተተከሉት ችግኞች መካከልም 84 በመቶው ጸድቋል። ይሄ አመርቂ በሚባል ደረጃ የተገኘ ውጤት ነው። ይሄ የሚያሳየው ምንም አይነት ነገር ለሀገር ልማት የሚጠቅም እስከሆነና በጥሩ አመራር ተመርቶ ወደ ተግባር እስከተገባ ድረስ ህዝቡ ተባባሪና ሰራተኛ መሆኑ የተረጋገጠ ነው። ይሄ የሚያስመሰግንም የሚያኮራም ነው።

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ግብ መሰረታዊ ግብ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ 20 ቢሊዮን ዛፎችን መትከል ነው። በዚሁ ዕቅድ መሰረት ሁለት ዙሮችን አገባደን ሶስተኛው ዙር መርሀግብር ዋዜማ ላይ እንገኛለን። የ2013 የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ሰባት ቢሊየን ችግኝ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ስድስት ቢሊዮን በሀገር ውስጥ አንድ ቢሊዮኑን ደግሞ ለጎረቤት አገራት ለማከፋፈል አብሮ መልማትን ያለመ ሲሆን ለዚህም ዝግጅት ተደርጓል።

በበጋው ወቅት በመላው ሀገሪቱ የሚፈለጉትን ችግኞች በብዛት ለማዘጋጀት የተለያዩ የችግኝ ጣቢያዎች በሥራ ተጠምደው ቆይተዋል። እነሆ ጊዜው ደርሶ የ2013 የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በክልሎች መተግበር ጀምሯል። ለችግኝ ተከላው አስፈላጊው የቦታ መረጣ ካርታና ችግኝ ዝግጅት ተደርጎ ለጎረቤት አገራት የሚሰጡ ችግኞችም ዝግጅት ተጠናቋል።

ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሶስተኛው የአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአማራ ክልል አስጀምረዋል። በክልሉ ከአንድ ነጥብ 83 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ይተከላሉ፡፡ በክልሉ በሀምሌ ወር መጀመሪያ በአንድ ቀን የአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የክልሉን ህዝብ በንቃት በማሳተፍ 247 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል እቅድ ተይዟል። በሶስተኛ ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከሚተከሉት ችግኞች መካከልም ወይራ፣ዋንዛ ፣ዝግባ ፣አቮካዶ፣ ቡናና ማንጎ ይገኙበታል።

በአረንጓዴ ልማት መርሀ ግብር መላው ህዝብ በስፋት በመሳተፉ ዛሬ የደረስንበትን አመርቂ ውጤት ለማየት ችለናል። የደን ሽፋኑ ከነበረበት በጣት ከሚቆጠር ዝቅተኛ ደረጃ አሁን ወደ 17 ከመቶ ደርሷል። አሁንም ይበልጥ በመሳተፍ ሀገራዊ እቅዱ ግቡን እንዲመታ መተባበር ይገባል። በአጠቃላይ ለአረንጓዴ ልማቱ ግብ ስኬት በመጪው ክረምት ወራት ችግኝ በመትከልና የተተከሉትን በመንከባከብ ሀገራዊ ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል!

አዲስ ዘመን ሰኔ 2 ቀን 2013 ዓ.ም

Recommended For You