ችግር ያላንበረከከው ሕይወት

ጤነኛ ልጅ ወልዶ ማሳደግ የሁሉም ሰው ምኞት ቢሆንም በአንዳንድ አጋጣሚዎች ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ልጆች ሲያጋጥሙ አብዛኛውን መከራ ቀድመው የሚቀበሉት እናቶች ናቸው። በተፈጥሮ ህግም በህጻንነት ዘመን ልጆችን ተንከባክቦ የማሳደግ ሀላፊነት በእናቶች ላይ የተጣለ ነው። ይህም ሆኖ አንዳንድ እናቶች ምንም እንኳን ለልጆቻቸው የሚኖራቸው ፍቅር ከጥርጣሬ የማይገባ ቢሆንም ጠንከር ያለና ከአቅማቸው በላይ የሆነ ችግር ሲገጥማቸው ልጆቻቸውን ይዘው ለጎዳና ህይወትና ለተመጽዋችነት ሲዳረጉ ይስተዋላል። የዛሬ እግዳችን ደግሞ ለአመታት የተፈራረቁባት ችግሮች ቢኖሩም በጠንካራ መንፈስ ክፉውን ቀን ለማለፍ እየተውተረተረች የምትገኝ አንዲት ወጣት እናት ነች።

ወይዘሮ ርብቃ አራጌ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው አርባ ምንጭ ከተማ፣ ጋሞ ዞን አካባቢ በምትገኝ ቦንኬ ላቃ ወረዳ፣ ሻራ ቆላ የምትባል አካባቢ ነው። ርብቃ እድሜዋን በትክክል ባታውቀውም በልጅነቷ ነበር ከወላጆቿና ከወንድምና እህቶቿ የተለያየችው። በወቅቱ ቤተሰቦቿ ችግርተኞች በመሆናቸው ነበር እራሷን ለማስተዳደር በማሰብ ገና በልጅነቷ እድሜዋ ወደ አርባ ምንጭ ከተማ ያቀናችው። አርባ ምንጭ ከተማ ደርሳ የተወሰነ ጊዜ በሰው ቤት በመቀጠር ካሳለፈች በኋላ የፈለገችውን ለውጥ ባለማግኘቷ ከጎዳና ላይ ንግድ ጀምሮ ራሷን ለማስተዳደር ጉልበቷ የፈቀደውን፣ አእምሮዋ የደረሰበትን ሁሉ ስራ ስትሰራ ቆይታለች።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆና ስምንት አመታትን ያህል ካሳለፈች በኋላ አንድ እንደሷው በጉልበት ስራ ከተሰማራ የአርባ ምንጭ ከተማ ወጣት ጋር የፍቅር ግንኙነት ትጀምርና በስምምነት ወደ ትዳር ያቀናሉ። በግንኙነታቸው መጀመሪያ ሰሞን ሁለቱም አፍላ ፍቅር ውስጥ ስለነበሩ ለርብቃ ነገሮች ያን ያህል አስቸጋሪ አልነበሩም። ውሎ እያደር ግን ርብቃን ድርብ ድርብርብ ችግሮችና ፈተናዎች ከፊቷ እየተጋረጡ እንኳን ያሰበችውን የደስታ ህይወት ልትመራ ይቅርና ለእለት ጉርሷም አብዝታ የምትጨነቅባቸው ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መምጣት ይጀምራሉ።

ርብቃ ከባለቤቷ ጋር የሶስት ጉልቻን ጉዞ “ሀ” ብለው በጀመሩ በወራቶች እድሜ ውስጥ የበኩር ልጇን ለመውለድ ትበቃለች። ያን ጊዜ ጉልበቷም ስላልተነካና ሰርቶ የመለወጥ ፍላጎቷ ጠንካራ በመሆኑ ለአራት ወር ያህል ልጇን በራሷ እቅፍ ካሳደገች በኋላ የባለቤቷ ገቢ ብቻውን በቂ ስላልሆነና የባሏም ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ የአቅሟን እየሰራች ቤቷን ለማሞቅ፤ ልጇንም በደስታ ለማሳደግ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሳትጨነቅ ቤት ኪራይ ለመክፈል ታቅድና ስራ ለመጀመር ትወስናለች። እናም የአራት ወር ህጻን ልጅ ይዛ እንደ ልቧ እየተንቀሳቀሰች ስራ መስራት ስለማትችል አንዲት ትንሽ ልጅ ለልጇ ጠባቂ አስቀምጣ የቀደመ የንግድ ስራዋን መስራት ትጀምራለች።

ባሰበችው መልኩ ለአንድ ሳምንት ያህል ከቆየች በኋላ ግን እንደሷ ገለጻ “በአንዲት ያልተባረከች ቀን” ወፍጮ ቤት እያለች የሰፈር ሰዎች ፈልገው በመሄድ ልጇን እንዳመመው ሲነግሯት እየተጣደፈች ወደ ቤቷ ትመለሳለች። እቤት ስትደርስም ልጇ ህይወቱ ያለፈች በሚመስል ሁኔታ ራሱን ስቶ ታገኘዋለች። ወዲያውኑም በጎረቤት እርዳታ ልጇን ይዛ ወደ ሆስፒታል ታቀናለች። የሆስፒታሉ ቆይታ ግን እሷ እንዳሰበችው በሰአታት፣ በቀናት አልያም በወራት የሚጠናቀቅ ሳይሆን ይቀርና ልጇን የማሳከሙ ጉዳይ ለአመታት ይዘልቃል። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም ቢሆን የልጇን ህመም ትክክለኛ መነሻም ሆነ የሚድንበትን መንገድ የሚያመላክታት አላገኘችም ነበር።

አንዳንዶቹ ሀኪሞች ህመሙ እሷ በምጥ ወቅት የመውለድ ችግር አጋጥሟት ጽንሱ በህክምና ማሽን ተስቦ ስለወጣ በዚያ ሂደት የተፈጠረ ክስተት ነው ሲሏት፤ ጎረቤቶቿና የሰፈሩ ሰው ደግሞ ሆስፒታል በወሰደችው ጊዜ የተወጋው የማጅራት ገትር በሽታ መድሀኒት ነው እንዲህ ያደረገው ይሏታል። አንዳንዶቹ ደግሞ እንድትይዘው የሰጠቻት ህጻን ልጅ ሲወድቅባት የተፈጠረ መሆኑን ይነግሯታል። አንዳንድ ግዜ ደግሞ ልጁ አሁን ላለበት ሁኔታ ሊዳረግ የቻለው እነዚህ ችግሮች በሙሉ በመደራረባቸው ሊሆን እንደሚችል ግምት እንዳላቸው ያስረዷታል። አምና የሄደችባቸው ሀኪሞች ግን አሁን ከማስታገሻ ውጪ ከአንገት በላይ ህክምና ሊደረግለት ስለማይችል የተሰጠሽን መድሀኒት እየተጠቀምሽ ጠብቂ ብለዋት ነበር። ርብቃ የሁሉንም አስተያየት አምኖ ለመቀበልም ሆነ ላለመቀበል አልወሰነችም።

ይህም ቢሆን ግን በልጅነት እድሜዋ ከከተማ ከተማ እየተዟዟረች በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ እንዲሁም የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን በመቸርቸር ስትሰራ የገዛቻቸውን የወርቅ ጌጣጌጦችና የቤት እቃዎቿን ሁሉ በመሸጥ አቅሟ እስከፈቀደ በከተማዋ ባለው ህክምና ጥግ ድረስ በመሄድ ልጇን ማሳከሙን ትያያዘዋለች። እጇ ላይ ያለው ገንዘብ ሲያልቅ ደግሞ የነጻ ህክምና ታስፈቅድና በየሆስፒታሉ ለልጇ የጀመረችውን ደህንነት ፍለጋ ትቀጥላለች። ነገር ግን የትኛውም መላ ምት ሆነ የርብቃ ውጣ ውረድ ልጇ አፉን ከፍቶ እንዲያወራ፤ እግሩን አንስቶ እንዲራመድ ያሻውን እንዲጎርስ ሳያስችለው ይቀራል።

በዚህ ሂደትም አንዳንድ እጃቸው የረጠበ የሚያውቋት ሰዎች የሚያደርጉላት ድጋፍም እየተመናመነ ይመጣና ቤት ኪራይ መክፈል ልጇንም ማብላት የማትችልበት ደረጃ ላይ ትደርሳለች። በዚህ ጊዜ በቅርብ ስትደግፋትና ስትከታተላት የነበርች አንዲት አስራት ንጉሴ የምትባል የአካባቢዋ ነዋሪ ያላት እድል ቀበሌ ሄዳ ማረፊያ መጠየቅ እንደሆነ ታስረዳትና ከተሳካላት ለቀለቧ ሌላ መላ እንደሚፈለግላት ሹክ ትላታለች። ርብቃ ቀን የጨለመባት ጊዜ ባጠገቧ የምታዋየው የቅርብ ወዳጅ ባይኖራትም ለራሷ “ይህን ህመምተኛ ልጅ ይዤ የጎዳና ተዳዳሪ ሆኜ እጄ ላይ ከሚያልፍብኝ ኮረንቲ ይዤ ራሴን አጠፋለሁ” እያለች ታስብ ነበር።

የአካባቢዋ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አስራት ንጉሴ የጠቆሟትን መንገድ ተከትላ ቀበሌ በመሄድ ያለችበትን ሁኔታ ትገልጽና ቢያንስ ያንገት ማስገቢያ ቤት እንዲሰጧት ትማጸናለች። አያይዛም የጠየቀችውን ሊያደርጉላት ካልቻሉ ግን ህይወቷ አደጋ ላይ መሆኑን ትነግራቸዋለች። የቀበሌው አመራሮችም ያለችበትን ሁኔታ በቦታው በመገኘት ካረጋገጡ በኋላ ቤት እንድታገኝ ያደርጓታል። የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ በህክምናው ይሄ ነው የሚባል ለውጥ ባለማግኘቷና እሷም ለምትቀርባቸው ሀሳቧን ትናገር ስለነበር ገንዘብ አዋተው ልጇን ይዛ ለአንድ ወር ጸበል እንድትሰነብት ያደርጓታል። ርብቃ በጸበል ቆይታዋ ልጇ በመሬት ላይ እየተንፏቀቀ ከመሄድ፣ በድጋፍ መንቀሳቀስ፤ ቀና ማድረግ የማይችለውን አንገቱንም ማወዛወዝ ስለጀመረላት ትንሽ ተስፋ ትሰንቃለች። ነገር ግን የተረከበችውን ቤት ማቃናት ስላለባት ወደ ከተማ በመመለስ አዲሱ ቤቷ መኖር ትጀምራለች።

ይህ ሁላ ሲሆን ባለቤቷ ይኖር የነበረው የራሱን ህይወት ብቻ ነበር። የተጋቡ ሰሞን ፍጹም ጭምት የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ጸባዩ እየተቀየረ ይመጣልና ሲያሻው ለወራት ጠፍቶ ይሰነብትና ድንገት ይከሰታል። አለሁ ብሎ እቤት ከሰነበተም በእንጨት ለቀማ የሚያገኛትን ብር ለሱሱ አውሏት ባዶ እጁን እቤት የሚገባበት ቀን ይበዛ ነበር። ይሄ ሲሆን ደግሞ ርብቃ ሶስተኛ ተቀላቢ ጨመረች እንደማለት ነው። ርብቃ እስከተወሰነ ጊዜ ለልጁም ለሷም አንዳንድ ነገር ማድረግ እንዳለበት ስታሳስበው ብትቆይም ይባስ ብሎ ለምን ተናገርሽኝ እያለ ዱላ ማንሳት ይጀምራል። “እኔ ከሞትኩ ለልጆቼ ማን አላቸው?” ያለችው ርብቃም ዛሬ ሲመጣ እጇን ዘርግታ ትቀበለዋለች፤ ሲሄድም በሯን ከፍታ ከማሰናበት ውጭ ምንም ማድረግ ሳትችል አብራው ለመቀመጥ ተገድዳለች። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች ነበር እሷ በቂ ዝግጅት ባይኖራትም ሁለተኛ ልጇን ጸንሳ ለመውለድ የበቃችው።

ርብቃ የመኖሪያ ቤት ችግሯ ከተቀረፈላት በኋላም በአቅምም በዝግጅትም የትም ተንቀሳቅሳ የመስራት ፍላጎት ነበራት። አሁን ስድስት አመት የሞላው ልጇ ከጸበል መልስ በፍጥነት እየተንገዳገደ ስለሚንቀሳቀስና የሚረግጠውንና የሚጨብጠውን መለየት ስለማይችል ከቤት ትታው መሄድ አልፈቀደችም። ይልቁንም የጥሪት ነገር እግር ከወርች ያሰራት ቢሆንም ከዛሬ ነገ አንድ ነገር ተፈጥሮ በግቢዬ ሰርቼ ልጆቼን አስተዳድራለሁ ብላ ያገኘችውን እየሰራች በተስፋ መኖሯን ትቀጥላለች። እስከ ቅርብ ጊዜ ለአካባቢው ሰው ሚጥሚጣ፣ በርበሬና ዳጣ በማዘጋጀት ስትሰራ ብትቆይም ስራው ትንሽ ትርፍ የሚኖረው ለአመት በአል ሰሞን ብቻ ነበር።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች ከወራት በፊት የከተማው ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ጥቂት መነሻ ካፒታል ሰጥቷት እዚያው ግቢ ውስጥ የባልትና ምርቶችን በማዘጋጀት ለመቸርቸር እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። የከተማዋ ሴቶች ጉዳይ ሀላፊዎችም ከሚያደርጉላት ድጋፍ ባለፈ ለመጪው አመት ልጇን ትምህርት ቤት ለማስጀመር ቃል ገብተውላታል። እሷም በበኩሏ ጥቂት ጊዜያት ልጇ መዋያ አግኝቶ ትንሿን ልጅ ይዛ በነጻነት መንቀሳቀስ ከቻለች ከቀበሌ የትብብር ደብዳቤ አጽፋ ከአንገት በላይ ህክምናው አለበት ወደተባለው ወላይታ ወይንም ሀዋሳ በመውሰድ ለልጇ ደህንነት ለማስገኘት ህልም እንዳላት ትናገራለች።

ወይዘሮ ገነት አይኑሼ የርብቃ ጎረቤት ሲሆኑ ያለፉትን ስድስት አመታትም አብረው አሳልፈዋል። ወይዘሮ ገነት ርብቃ ጠንካራ ሴት መሆኗን እንደሚከተለው ይገልጻሉ። ርብቃ የማይቻለውን የቻለች እናት ናት። የሷ አይነት ችግር የገጠማቸው እናቶች ቶሎ የጎዳና ህይወትን ይቀላቀላሉ። እሷ ግን በኮሮና ወቅት እንኳን ተስፋ አልቆረጠችም ነበር። በየቤቱ እየሄደች ስትሰራ የነበረውንም ስራ ያቆመችው እሷ ልጇን ተሸክሞ መስራት ደክሟት አልነበረም። ይልቁንም የሚያሰሯት ሰዎች አንዳንዱ ለራሱ እየሰጋ፤ አንዳንዱም እንዲህ አይነት ልጅ ይዛ እንዴት አሰራታለሁ እያለ በመሳቀቅ ስለማይቀጥሯት ነው። በባህሪዋ ሰው መለመን፣ ሰው መጠየቅ አትወድም።

አንድ የምታስቸግራት ሰው ብትኖር ጎረቤቷ የሆነችውን ወይዘሮ አስራት ንጉሴን ብቻ ነው። እሷም የተማረችና አስተዋይ በመሆኗ ለልጇም ሆነ ለእሷ ሳትጸየፍ የአቅሟን ታደርግላቸዋለች። በቀበሌ በኩል ድጋፍ እንዲደረግላት እንኳን የጠየቅናትም ሁኔታዎችንም ያመቻቸንላት እኛው ነን። ለእኛም ችግሯን ማካፈል የጀመረችው ከተቀራረብን በኋላ ነው። ሁሌም ሀሳቧ ራሷን ለመቻል በመሆኑ ያገኘቻትን ትንሽ ድጋፍ ትልቅ አድርጋ ተቀብላ ብዙ ነገር ትሰራበታለች ሲሉ ይገልጿታል።

“ርብቃ ለመረዳትም ራሷን ለመለወጥም ዝግጁ ናት” የሚሉት ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ የህጻናት ደህንነት ማስጠበቅ ቡድን መሪ ወይዘሮ ባንቺወሰን ወንድሜነህ ናቸው። ቡድን መሪዋ እንደተናገሩት ርብቃ እየተደረገላት ያለው ድጋፍ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚኖሩ ህጻናት ከወላጆቻቸው ሳይለዩ በሚሰጥ አንድ ፕሮግራም ነው። ፕሮግራሙ ለወላጆች ስራ የሚፈጠርበት ሲሆን የሚፈጠረው ስራ ግን ከልጆቻቸው ሳይለዩ የሚሰሩት ብቻ ነው። በዚህ ሁኔታ የተመረጡት ብዙዎች ቢሆኑም አንዳንዶቹ የሰው እጅ ስለለመዱ የተፈጠረላቸውን ስራ በአግባቡ ከመስራት ይልቅ ወደ ልመና መሄድ ይፈልጋሉ።

ርብቃ ግን በጣም በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆና እንኳን ገንዘብ ማግኘት የምትፈልገው በጉልበቷ ሰርታ ነው። አንዳንድ ቤተሰቦች ከፍተኛ ገቢ እያላቸውም ቢሆን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለን ልጅ ለማሳደግ በሚቸገሩበት አካባቢ እሷ ካለትዳር አጋሯ ብቻዋን ይዛ መቀመጥ ችላለች። ይህም ከተደጋፊዎቹ መካከል ቀዳሚ አድርጓት ከሶስት ወር በፊት በቂ ባይሆንም የራሷን ስራ እንድትፈጥር ድጋፍ እየተደረገላት ይገኛል። ዛሬም ቢሆን ርብቃ ልጇን የሚጠብቅላት ካገኘች አልያም የልጇ ጤና ከተመለሰላት ለሌሎችም የምትተርፍ ጠንካራ ሴት ናት። አሁንም ቢሆን ቢሮው አቅሙ በፈቀደ የሚያደርግላትን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2013

Recommended For You