«እየሰራን ሥራዎቻችን ደግሞ ለትውልድ የሚተላለፉበትን መንገድ እየፈጠርን ከሄድን በእርግጠኝነት ኢትዮጵያ የምናስበውን ብልጽግና ማረጋገጥ ትችላለች» ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

እንደምን ሰነበታችሁ ውድ የአዲስ ዘመን ቤተሰቦች፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት «ዐሻራ» በሚል ርዕስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያደረጉትን ንግግር በመጽሐፍ መልክ በማጠናቀር ለህትመት አብቅቷል።የመጽሐፉ የምረቃ ሥነሥርዓት ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደው በዚህ የምረቃ መርሃግብር ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ንግግር አድርገው ነበር።እኛም በዛሬው ዝግጅታችን እሳቸው ያደረጉትን ንግግር ሙሉ ቃል ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ቆይታ።

ፕሮግራሙ በዚህ መልክ ከፍ ያለ መሆኑን አላወኩም ነበር።ጠዋት ጎንደር ከሰዓት በኋላ ደግሞ ጎጃም ደብረማርቆስ ነው የዋልነው። የመጣሁበት ዋና ምክንያት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዐሻራ ስለሆነና እንደዚህ ዓይነት አንጋፋ ተቋማት ጥሪ አድርገው ሥራዎቻቸውን ሲያስመርቁ በመገኘት እነሱን ማክበር ጠቃሚ ስለሆነ ነው።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የብዙ ዜናዎች ምንጭ፣ የብዙ መረጃዎች ምንጭ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ የታሪክ ምንጭም በመሆን እያገለገለ ያለ ተቋም ነው።በዚህ ሁኔታ 80ኛ ዓመት በዓሉን ስናከብርና መጽሐፍ ስናስመርቅ በበኩሌ በጣም ደስተኛ ነኝ።

ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ፣ ዶክተር ፍጹም አሰፋ፣ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው መጽሐፉን በሚመለከት ጊዜ ወስደው ስላብራሩ፣ እኔም መጽሐፉን አየት አየት አድርጌዋለሁ በዚህም ደስ ብሎኛል።እንደ ተናጋሪና አንባቢ ሆኖ ማየት ስለሚለያይ ማለት ነው።ከዚህ መጽሐፍ ውስጥ የምንታዘበውና የምንማረው ነገር ሰው ሁሉ ሃሳብ አለው፣ ሃሳቦቻቸውን በቃል ለሌሎች ያጋራሉ፤ ቃሎች ተከሽነውና ታቅደው ተግባር ይሆናሉ፤ ተግባር ዐሻራ ይሆናል።ይህ መጽሐፍ በዐሻራና በቃል መካከል ድልድይ የሚሆን መጽሐፍ ነው።ሃሳብን ብቻ አይደለም የማየው፤ ሃሳብን በአንድ ጎን ተግባርን መካከል ላይ በማድረግ ዐሻራውን ያሳየው መጽሐፍ ለትውልድ እጅግ ጠቃሚ ስለሆነ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጊዜ ወስዳችሁ ይህንን መጽሐፍ ስላዘጋጃችሁ እጅግ አድርጌ ላመሰግናችሁ እፈልጋለሁ።

እየሰራን ሥራዎቻችንን እየተከልን ለትውልድ ደግሞ የሚተርፍ ዐሻራ እየተውን መሄድ ያስፈልጋል።እየሰራን ካልሆነ ዐሻራውን አናየውም፣ ዐሻራ ሥራ ስለሚፈልግ በየጊዜው እየሰራን ሥራዎቻችን ደግሞ ለትውልድ የሚተላለፉበትን መንገድ እየፈጠርን ከሄድን በእርግጠኝነት ኢትዮጵያ የምናስበውን ብልጽግና ማረጋገጥ ትችላለች።

ቀደም ሲል ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ስለ አንዳንድ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሲያነሱ ትውስታ ስለፈጠሩብኝ አንዳንድ ማስታወሻዎች እየያዝኩ ነበር፤ ብዙ ሰዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ መፈናቀል፣ ግጭት፣ ጦርነት፣ ኮሮና፣ አምበጣ እና ጎርፍ እንዲሁም አለመረጋጋቶች ይበዛሉ፤ ብለው ይናገራሉ። መናገር ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ ችግሮችና ፈተናዎች እንዳሉ እናውቃለን።

ነገር ግን በእነዚህ ብዙ ችግር ባሳለፍንባቸው ዓመታት ውስጥ ባለፉት አስር ዓመታት በንጽጽር የነበረውን ጊዜ ብናወዳድር ከጂኦ ፖለቲክስ አንጻር አሁን ያለብን ዓይነት ጫና አልነበረም።አሁን በሰሜን የገጠመንን ችግር አንዳንዶች ከኢትዮ ኤርትራ ግጭት ጋር አንዳንዶች ከካራማራ ጋር ያወዳድራሉ። ወታደር ስለሆንኩ ሁሉም ልዩነት አላቸው። ምክንያቱም ከጣሊያን ጋር ስንዋጋ በጎራዴም ቢሆን እኛም ያለንን ይዘን እነሱም መሣሪያቸውን ይዘው ነው።ከኤርትራ ጋርም ስንዋጋ እኛም ባለን እነሱም ባላቸው ነበር።ካራማራም ተመሳሳይ ነው።አሁን ግን የነበረው ውጊያ የእኛን ክላሽ፣ የእኛን ጥይት፣ የእኛን ትጥቅ፣ እኛንም የእኛን መከላከያለማፍረስ የተካሄደ ነው።

እኛም ጠላትም ኃይል ይዞ ሳይሆን የእኛ ኃይል ዋና (ኮር) ክፍሉ በጠላት ቁጥጥር ስር ሆኖ «70 እና 80 በመቶ ትጥቅ እኛ ጋር ነው እርሱን ተማምነው ነው ውጊያ የገጠምነው፣ እንደዚህ ዓይነት ነገር ይገጥመናል ብለን አላሰብንም ነበር» እያሉ እንዳለው የዚህ ዓይነት ውጊያ ነው።ይሁንና እስከአሁን ድረስ በእነዚህና መሰል ችግሮች ውስጥ እያለፍን መሆናችን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በእነዛ በንጽጽር የተሻለ ጊዜ በምንላቸው ጊዜያት ላይ ብቻ ያለውን ማሳያ ማስቀመጥ በቂ ነው።

የዛሬ 7/8/9 እና 10 ዓመት በፊት ተጀምረው ሊጠናቀቁ ያልቻሉ 10 ትላልቅ የስኳር ፋብሪካዎች ነበሩ፤ በዚያን ጊዜ ማዕቀብ የሚባል ነገር በማይወራበት፣ የውስጥም የውጭም ጫና በሌለበት፤ በምሥራቅ፣በሰሜን ግጭት ባልነበረበት ጊዜ 10 ስኳር ፋብሪካዎች ጀምረን መጨረስ ተቸግረን ነበር።ባለፉት የመከራ ጊዜያት 7ቱን አጠናቀናል።በንጽጽር ሰላም በነበረበት ሰዓት ፕሮጀክት ጀምረን መጨረስ አቅቶን ችግር በነበረበት ሰዓት ፕሮጀክት ጀምረን መጨረስ ብቻ ሳይሆን ከ92 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ አውጥተንባቸዋል።በነገራችን ላይ ስምንተኛው የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ሥራው ተጠናቋል።ትልቁ ችግር አገዳ ነው፤ አገዳ ለማምረት ደግሞ ሌላ ግድብ መስራትና ውሃ መያዝ ይጠበቅብናል።

አግሮ ኢንደስትሪ ፓርክ እንደ አገር አራት ጀምረን ሦስቱ ተጠናቀው ሥራ ጀምረዋል።የተጀመሩት በንጽጽር የተሻለ ጊዜ በምንለው ሲሆን የተጠናቀቁት ግን በንጽጽር የከፋ ጊዜ በምንለው ወቅት ነው።የኢንደስትሪ ፓርኮችንም ብንወስድ ኮምቦልቻ፣ መቀሌ እና ሀዋሳ ላይ ስምንት ኢንደስትሪያል ፓርክ ተጀምረው ያጠናቀቅናቸውና ሌሎች የያዝነው በዚህ ሦስት ዓመት ውስጥ ነው ።

ጅማ፣ አዳማ፣ ሰመራ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ ደብረብርሃን፣ ቦሌ፣ ለሚ አንድና ሁለት የተጠናቀቁት በዚህ ሦስት ዓመት ውስጥ ነው።ተጀምረው የነበሩ እንደ ኢንሳና የመከላከያ ሕንፃዎች እንዲሁም ሌሎች ተጀምረው ሳይጠናቀቁ አስር ዓመት የወሰዱትም እንዲጠናቀቁ የሆነው በዚህ ሦስት ዓመት ውስጥ ነው።

ከግድቦች አንጻር ብንመለከት ህዳሴ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገሌ ዳዋ ከለውጡ ሦስት ዓመት በፊት ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ግን ደግሞ ውሃ መያዝ ስላልቻለ ኢነርጂ አያመርትም ነበር፤ ከለውጡ በኋላ ውሃ ይዘን ኢነርጂ አምርተናል፤ ኮይሻም እንደዚሁ ሥራው ቆሞ ነበር ህዳሴ እንደምታውቁት ነው።

ህዳሴና ጣና በለስን ለየት የሚያደርገው ነገር ጣና በለስ ችግሩን ከለየን በኋላ በአዲስ መልክ ገንዘብም ሰውም መድበን ሥራ ስንጀምር አምስት ወር የፈጀብን ቀድሞ ፋብሪካ ሳይገቡ ፋብሪካ የገቡ የሚመስሉ አላስፈላጊ ዕቃዎችን ማንሳት ነው። ህዳሴ ግድብም እንደዚሁ በአላስፈላጊ ሁኔታ ተሞልቶ የነበረውን የሜካኒካል ክፍሉን ማንሳት ነበር ጊዜ የወሰደው።ይህ ከለውጡ በኋላ የመጡ ነገሮችን ሳላነሳ በንጽጽር ሰላምና የተሻለ ጊዜ ላይ ተጀምረው መጠናቀቅ ያልቻሉና በከፋ ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቁ ሥራዎችን ያመላክተናል።ይህ የእሳቤ እና የህልም ውጤት ነው፤ ሃሳቦቻችንና እቅዶቻችንን የምናከብራቸው ከሆነና ለተፈጻሚነታቸውም የምንተጋ ከሆነ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ያለምነውን ማሳካት እንደሚቻል ያሳያል።

ይህንን ዓይነት ነገር እንዳልነበር ማየት መሞከር አግባብ አይደለም፤ ከሦስት ሰዓት በፊት ወደዚህ ቦታ ስትመጡ ፀሐይ ነበረች፣ፀሐይን መካድ አይቻልም፤ ነገር ግን የሚቻለው ዓይንን መጨፈን ነው፤ ዓይንን ጨፍኖ ራስን ማጨለም ይቻል ይሆናል እንጂ ለዓለም የምትተርፍን ብርሃን የለችም ብሎ መሞገት አይቻልም።

አሁን ብዙ ሰዎች እየመጣ ያለውን ተጨባጭ ለውጥ ማመንና መቀበል የሚቸገሩት ዓይናቸውን ጨፍነው ውስጣቸውን ስላሳወሩ ነው።ይህ ነገር ለኢትዮጵያ ብልጽግና አይጠቅምም።በሌላ መንገድ ደግሞ በመንግሥት ሥራ ላይ ያላችሁ የሥራ ኃላፊዎች በጣም ዕድለኛ መሆናችሁን ተገንዝባቸው በሰራችሁት ሥራ የምትኩራሩና ድላችሁን ብቻ የምትዘክሩ ሳትሆኑ ይበልጥ ለመስራት መትጋት ከሁላችን የሚጠበቅ ነገር መሆኑንማሰብ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ አሁን ባለው ፍጥነት 10 ስኳር ፋብሪካ ጀምረን 7 እያጠናቀቅን፤ 4 አግሮ ኢንደስትሪ ጀምረን ሦስት እያጠናቀቅን ከሄድን ብልጽግናን ማረጋገጥ አንችልም።10 ስኳር ፋብሪካ ጀምረን 15 እና 20 አድርገን መስራት ስንችል ብቻ ነው የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚረጋገጠው።ገና ብዙ ልንሰራ የሚገባን ሥራ እንዳለ አሁንም ሰዓት እንደምንቆጥር ብዙ ሩጫ እንዳለበን ማሰብ ያስፈልጋል።

ናይጄሪያውያን አንድ አባባል አላቸው «50 አዳኝ ሆነው ወጥተው አስር አዳኞች አንበሳ ገድለው ቢመለሱ ከሆነ ጊዜ በኋላ ይገጠምላቸዋል፣ ይወደሳሉ፤ ይዘፈንላቸዋል፤ ይጻፍላቸዋል።ነገር ግን ከ50ው 40ው በአንበሳ ተበልተው ቢሆን አንበሶች ታሪካቸውን መጻፍ ስለማይችሉ የሚነግርላቸው አያገኙም» ።ታሪክ የአሸናፊዎች ብቻ ሳይሆን የእውነት ጠበቃ ነው መሆን ያለበት።

ታሪክን ያሸነፉ ሰዎች የሚጽፉት የተሸነፉ ሰዎች ሳይጽፉ ሲቀር የሚዘነጋና የሚዘለል ከሆነ አስተማሪ አይሆንም።ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ የሚጽፉ ጀግኖች የሚጻፍላቸው ጀግኖች ኖረው ያልተጻፈላቸው ያልተዘመረላቸው፤ በርካታ ጀግኖች ከእነሱ ልንማር የሚገባንን ነገር ሳንቀስም የምንቀረው። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በእኔ እምነት እራሱም ዐሻራ ስለሆነ የእኔን ንግግሮች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከእኔ የተሻለ እውቀትና አቅም ያላቸው ኢትዮጵያውያን በተለያየ መንገድ የሚያደርጓቸውን ንግግሮች በዚህ መንገድ ጽፎ ለትውልድ እንዲሸጋገሩ ማድረግ ከተቻለ አሁን ከታሪክ ጋር የምንጣላው፤ የምንሰዳደበው ይቀንሳል።

የዛሬና የነገ ዜና ተሰናስሎ ተደምሮ ነው ታሪክ የሚሆነው፤ ዛሬ የምትሰሙት ዜና እንደተፈለገ ተዛብቶ የሚጻፍ ከሆነ ነገ አደገኛ ነው።የውሸት ዜና እንዳይበዛ እውነተኛ ዜና እንዲበዛ ከሰራን የዛሬ ዜና ድምር ውጤት ደግሞ እውነተኛ ታሪክ ለትውልድ እንዲሸጋገር ያደርጋል። በዚህ መንፈስ የምንጽፍ ሰዎች በተቻለ መጠን ለዛሬ ስሜታችን ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችን እያሰበን እንድንሰራ አደራ እያልኩ መጽሐፍ ማንበብ ጥሩ ከመሆኑም በላይ የጻፉ ሰዎችን ማክበር እና ጽሑፍም ለትውልድ እንዲሸጋገር ማድረግ በሁላችንም ዘንድ እንዲሰፋና እንዲበረታታ አደራ እላችኋለሁ።

አንድ እርማት ለመስጠት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው የተረዱበት አውድ ይገባኛል፤ በእርሶ አገላለጽም ትክክል ነው።ነገር ግን ለእኔ የኢትዮጵያውያን ሥነ ጽሑፍ ስናነሳ በጋዜጣ በሰዎች የተሰራጨ ጽሑፍ በመቶ ዓመት መገደብ የለብንም።ከሺህ ዓመታት በፊት ጀምሮ በስዕል በኋላም በቅርጽ ቀጥሎም በጽሑፍ ኢትዮጵያውያን ታሪክን፣ እምነትን አሸጋግረዋል።

ነገር ግን በአግባቡ ስላልገለጽነው ዛሬ ላይ የአፍሪካ ህብረት የሥራ ቋንቋ አረብኛ߹ እንግሊዝኛ߹ ፖርቹጋል߹ ፍሬንች የሆነውና አንድም አፍሪካዊ ቋንቋ ያልተካተተው ለዚህ ነው።ነገር ግን የራሳችን አልፋቤት ኖሮን፤ መጻፍ ቅዱስና ቅዱስ ቁርዓን በእጃችን በወረቀት ሳይሆን በቆዳ ጽፈን ያሸጋገርን ሕዝቦች ታሪካችንን በመቶ ዓመት መሰብሰብ የለብንም። በሺህ ዓመት የሚቆጠር በጽሑፍ ግዕዝም ይሁን በአማርኛ የታጻፉ ታሪኮች ያሉን ሕዝቦች ስለሆንን ይህንን ነገር እኛ ካልነው ትክክለኛ ታሪክ ስለሚሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

አፍሪካውያን የራሳቸው ቋንቋ ያላቸው አይደሉም ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ህብረት ውስጥ አንድ የአፍሪካ ቋንቋ የሥራ ቋንቋ አልሆነም።አሁን እንኳን እንዲሆን ለመፍቀድ ትንሽ ጊዜ ፈልገዋል። ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት ደግሞ የገደሉን ይጽፋሉ፤ አንበሶቹ አይጽፉም።ስለዚህ እባካችሁ አንበሶች ብትነቁ ይሻላል።

የኢትዮጵያ ሰላም፣ ብልጽግናና የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ብንፈልግም ባንፈልግም ይረጋገጣል፤ ዋናው የዚህ ታሪክ አካል መሆን ነው።እንደምናስበው እንደምንናገረው ሁሉ በተለይም ችግኝ በመትከል ለትውልድ መልካም ነገር እንድናቆም አደራ እላለሁ።

እፀገነት አክሊሉ

 አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2013

Recommended For You