‹‹የጉራጌ ሕዝብ የአንድነትና የመሰባሰብ ባህል የኢትዮጵያ ጣዕም ሆኖ እንዲቀጥል ጥሪ አቀርባለሁ» – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ:- የጉራጌ ሕዝብ የአንድነትና የመሰባሰብ ባህል የኢትዮጵያ ጣዕም ሆኖ እንዲቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ አቀረቡ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ለጉራጌ ባህል ማዕከል መገንቢያ ቦታ አስረከበ።

በወዳጅነት ፓርክ የጉራጌ ልማት ማህበር ዓመታዊ ኮንፍረንስ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ትናንት በተካሄደበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፤ የጉራጌ ሕዝብ የአንድነትና የመሰባሰብ ባህል የኢትዮጵያ ጣዕም ሆኖ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የጉራጌ አባቶች የአንድነትን ጠቀሜታ ጠንቅቀው የሚያውቁ ነበሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብዙ የጉራጌ አባቶችና እናቶች ለእኩልነት በተለይም ለፆታ እኩልነት የታገሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለአገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት መነሳት አለብን፣ በልዩነት ውስጥ አንድነታችንን ማጎልበት ይገባናል፣ ጉራጌዎችም አንድነትን በተግባር እንዳሳዩን ጠቁመዋል።

ብዙ ሰዎች ጉራጌን ሲያታውሱ ክትፎን ያነሳሉ እኛ በቅርበት ስናውቀው ግን ጉራጌ ብዙ ምግቦችንም ለኢትዮጵያ ያስተዋወቀ ነው፤ ‹‹ጉራጌዎች ለአዲስ አበባ፣ ለኢትዮጵያ ጣዕም ናቸው…ጉራጌዎች የመደመር ምሰሶዎች ናችሁ›› ብለዋል ።

በአንድነት፣ በፍቅር ኢትዮጵያን በማስቀጠልና ጣዕም መሆን፣ ለአፍሪካ ደግሞ ጨው መሆን አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ዛሬም እንደ ትናንቱ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ፈርጥ አድርገን እናስቀጥላለን ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በኮንፈረንስ ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ለጉራጌ ባህል ማዕከል ግንባታ የሚውል ቦታ አስረክበዋል።

ከርክክቡም በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ የባህል ማዕከል መኖር በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዕድገትና የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር በማድረግ ፋይዳ እንደሚኖረው የከተማ አስተዳደሩ ያምናል ብለዋል፡፡ ከዚህ የተነሳም የጉራጌ ሕዝብ በከተማችን የባህል ማዕከል ለመገንባት የጠየቀውን ጥያቄ አስተዳደሩ በበጎነት እንደተቀበለው አስታውቀዋል።

ማዕከሉ ጎብኚዎች ተጨማሪ አማራጭ እንዲኖራቸውም ያግዛል ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ «የጉራጌ ሕዝብ በሄደበት ሁሉ በሥራና በማልማት የሚታወቅ ነው። ይህን ባህል ልናስተምርበትና ከፍ አድርገን ልናወሳው ይገባል» ብለዋል።

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው፤ ጉራጌ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በጋራ በመስራት የሚመሰከርለት ሕዝብ ነው፡፡ ዛሬም ለአገራችን የጉራጌ ሕዝብ እሴት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የጉራጌ ሕዝብ እድርና እቁብን ለኢትዮጵያ ያበረከተ ነው ብለዋል፣ በማህበር ተደራጅቶ አካባቢን የማልማት ባህል ያለው ሕዝብ ነው። የጉራጌ ልማትና የባህል ማህበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል አስተዳደር የሚችለውን ትብብር እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሐመድ ጀማል በበኩላቸው፤ የጉራጌ ልማትና የባህል ማህበር ባለፉት ጊዜያት ብዙ የልማት ሥራዎችን እንደሰራ አስታውሰው፣ የዞኑ ተወላጆችና የማህበሩ አባላት የዞኑንም ሆነ የአገሪቱን ልማት በተጠናከረ መንገድ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

 የሱፍ እንድሪስ

አዲስ ዘመን ሰኔ  3/2013

Recommended For You