‹‹ስምምነቱ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር እና ታሪካዊ ነው›› – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ፡- ‹‹ግሎባል አሊያንስ ፎር ኢትዮጵያ›› ኩባንያ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ሥራ ለመጀመር የሚያስችለውን ስምምነት መፈራረሙ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር እና ታሪካዊ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።

በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት ጨረታ ያሸነፈው ‹‹ግሎባል አሊያንስ ፎር ኢትዮጵያ›› ኩባንያ በኢትዮጵያ ሥራ ለመጀመር የሚያስችለውን ስምምነት ከትናንት በስቲያ በአንድነት ፓርክ ተፈራርሟል።

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንዳስታወቁት፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት መንግሥት የተለያዩ የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት ሴክተሮች ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዘዋዋር በርካታ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

ጥረቶቹ ተደምረው ስኬታማ ውጤቶችን ማስገኘታቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቴሌኮሚኒኬሽን ዘርፉ የግል ኢንቨስትመንትን በማሳተፍ ረገድ በተከናወኑ ተግባራት ደህንነቱ የተጠበቀ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት መቻሉንም አመላክተዋል። ዕለቱም የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚሸጋገርበት ታሪካዊ ክስተት እንደሆነም አስታውቀዋል።

የኩባንያዎቹ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትም አገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከዘመኑ ጋር በማዘመን ረገድ ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቴሌኮም ዘርፍ የሚፈጠረው ውድድር ሁሉንም ሴክተሮች የሚያነቃቃ እና የሚያዘምን ነው›› ብለዋል።

የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት በሆነው በግብርና፣ በፋይናንስ እንዲሁም በትምህርት አገልግሎቶችን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ እንዲሁም ተደራሽነትን ለመጨመር እንደሚያግዝም አብራርተዋል።

በቀጣይም የአገሪቱን ሪፎርም አጀንዳዎች በማስቀጠል ሂደት በሁሉም ኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ የለውጥ ሥራዎች እንደሚሰሩ እና የግሉን ዘርፍ በስፋት የማሳተፍ ሥራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ለማዘዋወር የሚከናወኑ ተግባራትም በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ በበኩላቸው፣ አገራቸው የዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞን ቀድማ መጀመሯን አስታውሰው፣ የኢትዮጵያ ውሳኔንም የሚደነቅ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያና ኬንያ የቆየ የባህልና ታሪክ ትስስር እንዳላቸውና በቴሌኮም ዘርፉ የተጀመረው አጋርነትም ለሁለቱ አገሮች የልማት ትስስርም ለበለጠ የትብብር ግንኙነት አጋዥ መሆኑን አስገንዝበዋል። መሰል ትብብሮችም ከተናጠል ባሻገር ለቀጠናዊ መስተጋብር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩም አመልክተዋል።

ስምምነቱም ለኢትዮጵያ ብዙ ዕድሎችን ይዞ እንደሚመጣ አፅንኦት የሰጡት ፕሬዚዳናንቱ፣ ‹‹በውጤት የሚጠበቀው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና ኢንቨስትመንትም ከመንግሥት አገልግሎት እስከ ከገበያ እና መረጃ ተደራሽነት በሁሉም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አውድ ላይ ታሪክ የሚቀይር ነው›› ብለዋል።

በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ሥራ የሚጀምረው ግሎባል አሊያንስ ፎር ኢትዮጵያ የተባለው ኩባንያ የስድስት ኩባንያዎች ጥምረት ሲሆን የኬንያው ሳፋሪ ኮም 56 በመቶ ድርሻ እንዳለው መረጃዎች ያመላክታሉ። የኩባንያው ተሳትፎም 127 ዓመታትን ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ የቴሌኮም ኢንዱስትሪ መልክ ይቀይረዋል ተብሎም ይጠበቃል።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ፣ ከቮዳኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሻሚል ጆሱ፣ ከሳፋሪ ኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፒተር ኢድግዋ እንዲሁም ከሲሚቶሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማይሽ ማሂሽታ ጋር ተፈራርመዋል።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሰኔ  3/2013

Recommended For You