በትግራይ ክልል 55 በመቶ ሆስፒታሎችና 52 በመቶ ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተገለጸ

– በክልሉ ለምግብ አቅርቦት ከ5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፦ በትግራይ ክልል 55 በመቶ ሆስፒታሎችና 52 በመቶ ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በክልሉ 170 ሺ 798 ሜትሪክ ቶን ምግብ መቅረቡ፤ ለዚህም ከ5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉ ተጠቆመ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ከጤና ሚኒስቴር እና ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመሆን በትግራይ ክልል የጤና አገልግሎት አሰጣጥ እና ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ ያተኮረ ጋዜጣዊ መግለጫ ትናንት በሰጡበት ወቅት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳስታወቁት፣ በክልሉ የጤና አገልግሎትን መልሶ ለማጠናከር እና ምላሽ ለመስጠት የፌዴራል መንግሥት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ግብረ ኃይል አቋቁሞ በቅንጅት እየሰራ ነው፡፡

በክልሉ የጤና ተቋማትን ወደ ሥራ ለማስገባት በተሰራው ሥራ 55 በመቶ ሆስፒታሎችና 52 በመቶ ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ያሉት ዶክተር ሊያ፣ 89 በመቶ የሚሆኑት የጤና ተቋማቱ ባለሙያዎችም መደበኛ ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በክልሉ 14 ሆስፒታሎችና 58 ጤና ጣቢያዎች ተጠግነው መደበኛ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ከፌዴራል መንግሥት በጀት ተመድቦ እየተሰራ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

በክልሉ በሚገኙ የጤና ተቋማት የኮቪድ-19 መመርመሪያ ኪቶች፣ የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያዎች፣ የኮቪድ-19 ክትባቶች፣ ማይክሮስኮፕ፣ መድኃኒቶች እና ሌሎች የሕክምና መርጃ ግብዓቶች እየቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የክልሉን የጤና አገልግሎት ለማስጀመር በሚደረገው ጥረት እስካሁን ከ310 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚያወጣ መድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያ ወደ ክልሉ መላኩን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ጤና መልሶ መቋቋም እንቅስቃሴ ምላሽ በማገዝ ሂደት የጤና ሚኒስቴርም ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ከ215 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ ለክልሉ መተላለፉንም ጠቁመዋል።

የጤና አገልግሎት ባልተጀመረባቸው አካባቢዎችም ተንቀሳቃሽ ቡድኖችን በመጠቀም ኅብረተሰቡን ተደራሽ የማድረግ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሆነም አስታውቀዋል።

በክልሉ የጤና አገልግሎትን ዳግም ለማስጀመርና ተደራሽነቱን ለማስፋት መንግሥት ከሚያደርገው አበረታች ጥረት ጎን ለጎን ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሰ በበኩላቸው፣ በክልሉ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከተጀመረ ወዲህ በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ለ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ በሁለተኛና በሦስተኛ ዙር 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በክልሉ 170 ሺህ 798 ሜትሪክ ቶን ምግብ መቅረቡን ገልጸው፤ ለዚህም ከ5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አስታውቀዋል።

በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዙር በክልሉ ለተሰራጨው ምግብ ከወጣው ወጪ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው በመንግሥት የተሸፈነ መሆኑን አመልክተው ፣ ቀሪው 30 በመቶ ደግሞ በዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች የተሸፈነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ ወርልድ ቪዥን፣ ኬር ኢንተርናሽናል፣ የትግራይ መልሶ ማቋቋም ድርጅት እና ፉድ ፎር ሀንግሪ በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎች ላይ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

«ይህም መንግሥት ከአጋሮች ጋር ተቀራርቦ እየሰራ እንደሚገኝ ያሳያል» ያሉት አቶ ምትኩ፤ በአሁኑ ወቅት 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቀዋል።

በጋዜጣ ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ  3/2013

Recommended For You