በሐዋሳ ከተማ በአንድ ቢሊዮን ብር ሲከናወኑ የቆዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተገለጸ

ሐዋሳ፡- በሐዋሳ ከተማ በአንድ ቢሊዮን ብር ሲከናወኑ የቆዩ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የከተማ አስተዳደሩ ዓመቱን ሙሉ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ፤ የማደግና የመልማት ጥያቄዎች እልባት ለመስጠት አበክሮ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

በክራሞቱም ጎልተው የሚታዩ ተግባራትን መከወኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰር ጸጋዬ፣ በዚህም አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ሲሠራ መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ የጤና ጣቢያዎች፣ የአስፋልት መንገዶች፣ የውስጥ ለውስጥ ጥርጊያ መንገዶች፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የትምህርት ቤቶች፣ የንጹህ ውሃ ፕሮጀክቶች እና ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብርን የሚያፋጥኑ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ከተሞች በዘመናዊ አመራርና በትክክለኛው መንገድ ተመርተው ሲያድጉ ትልቅ የምጣኔ ሀብት እና የሥልጣኔ ምንጭ የመሆን ዕድል እንዳላቸው በሳይንስ የሚታመንና እውነታ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ ሐዋሳ ከተማ አስተዳደርም ይህን ታሳቢ በማድረግ እየሠራ ነው ብለዋል።

ከዚህም በዘለለ በዙሪያው ያሉ የወረዳ ከተሞች እና አጎራባች ቀበሌዎች ወደ ከተማ ለማደግ በሚያደርጉት መውተርተር ውስጥ የሚገጥማቸውን የዘመናዊ ከተሜነትና አስተዳደር ችግሮች ለማቃለል የሐዋሳ ከተማ ከአገር እና ከውጭ አገር የቀሰማቸውን ልምዶች በማካፈል ብሎም ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማፋጠንና የከተሞችን በሁሉም ዘርፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ መሠረት ልማቶች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው በመታመኑ ሰፊ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውንና በቀጣይም ይህ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

እንደ ምክትል ከንቲባ ጸጋዬ ገለፃ፤ ሐዋሳ ከተማ በንፅፅር ሲታይ በርካታ መሠረተ ልማቶች የተሟሉላት ሲሆን በብዙ መንገድ ለሌሎች ከተሞች መመስረትም እንደ መነሻ እያለገለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም ሐዋሳ ከተማን መሰረት አድርገውና በቅርበት ለሚመሰረቱ ሌሎች አዳዲስ ከተሞች ሐዋሳ ከተማ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የወንዶ ገነት ከተማ ከንቲባ አቶ እርዳቸው ኤሊያስ በበኩላቸው፤ ሐዋሳ ከተማ ከራሱ አልፎ በዙሪያው ለሚገኙ ከተሞች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ ለወንዶ ገነት ከተማም ከአምስት ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡

ከተማዋ የቱሪስቶችንና ባለሀብቶችን ትኩረት የምትስብ ለማድረግ በነበረው ጥረት ላቅ ያለ እገዛ መደረጉንም ጠቁመው፣ በዚህም ሐዋሳ ከተማ ለሌሎች ከተሞች መመንደግ እና መሰረተ ልማቶች መፋጠን እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚያስመሰግነው እንደሆነ አስታውቀዋል። እንደ አገርም በአርዓያነት የሚወሰድ ዓይነተኛ ማሳያ ስለመሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ሰኔ  3/2013

Recommended For You