ትብብሩን ለኢትዮጵያና ኬንያ የላቀ ግንኙነት!

ኢትዮጵያ ለ127 ዓመታት ያለ ተወዳዳሪ የዘለቀውን የቴሌኮም ዘርፏን ተወዳዳሪ ማድረግ ያስቻለ ስምምነት ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ ከተሰኘ የቴሌኮም ኩባንያ ጋር ከትናንት በስቲያ ፈርማለች። አዲሱ ኩባንያም ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፉን ለውድድር ክፍት ለማድረግ አውጥታው በነበረው ዓለም አቀፍ ጨረታ አሸንፎ ከኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ያገኘ ነው።

በስምምነቱ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተገኝተዋል። ኡሁሩ ኬንያታ የተገኙትም በትብብሩ ትልቁን ድርሻ የያዘው ሳፋሪ ኮም የተሰኘው የቴሌኮም ኩባንያ የኬንያ ኩባንያ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ነው።

ትብብሩ ካካተታቸው የቴሌኮም ኩባንያዎች መካከል ሳፋሪ ኮም፣ ቮዳ ኮምና ቮዳ ፎን የተሰኙ የቴሌኮም ኩባንያዎች ይገኙበታል። የግሎባል <ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ> በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ላይ ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑ እንዲሁም የአገሪቱን ኢኮኖሚም በወሳኝ መልኩ እንደሚያነቃቃው ታምኖበታል።

የትብብሩ ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ፋይዳ ከኢትዮጵያም የተሻገረ ሆኗል። የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታም ይህንኑ አረጋግጠዋል። እሳቸው እንዳሉት ደግሞ፤ በትብብሩ በኩል የሳፋሪ ኮም ወደ ኢትዮጵያ መግባት የኢትዮጵያና ኬንያ ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት ይበልጥ ያስተሳስረዋል። ሳፋሪ ኩባንያ ትልቅ ድርሻ ለያዘበት ትብብር ፈቃድ ለመስጠት ኢትዮጵያ የደረሰችበት ውሳኔ ለሁለቱ አገሮች ዘመናትን የዘለቀ ግንኙነት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው።

ኢትዮጵያና ኬንያ ከቴሌኮም በተጨማሪ በቅርቡ በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችም ትስስራቸውን እያጠናከሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ለዜጎቻቸው የተሻለ ነገን ይዞ ይመጣል ብለዋል። በዚህ ረገድ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ኩባንያ ከትርፍ የዘለለ ዓላማን ይዞ ሊገባ እንደሚገባው አስገንዝበው፣ ዘላቂው የቢዝነስ ግብ መሆን ያለበት ለማህበረሰቡ ትርፍ መፍጠር ሊሆን እንደሚገባው አስታውቀዋል። ትብብሩም በአገልግሎቱ በኩል ትስስር በፈጠረው ላይ ሁሉ ለውጥ በማምጣት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያና ኬንያ በተለያዩ ዘርፎች ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው እንደመሆናቸው ይህን ትስስር ይበልጥ በማሳደግ በኩ

 የትብብሩ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። ትብብሩ ኢትዮጵያ በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ ያላትን ድርሻ ማሳደግ እንደሚጠበቅበት ሁሉ ሁለቱ አገሮች በሁሉም ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት ማሳለጥ ላይ በትኩረት መሰራት ይኖርበታል። በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የኢኮኖሚ ግንኙነት ባደረገ ቁጥር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱም እያደገ ይመጣል።

የትብብሩ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ከኢትዮጵያም አልፎ የኢትዮጵያና ኬንያን ዘመናትን የዘለቀ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያደርሰው ታምኖበታል። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያና ኬንያ በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው። አገራቱ በአየር እና በየብስም ይገናኛሉ።

ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት እየሰጠ የቆየው የአዲስ አበባ ሞያሌ ኬንያ መንገድ ደረጃ እንዲያድግ ተደርጓል። ኢትዮጵያ ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ እየሰራች ትገኛለች። በሞያሌ አካባቢ ትልቅ የኢኮኖሚ ኮሪደር በመፍጠር የኢኮኖሚ ግንኙነቱን ይበልጥ ያሳድገዋል የተባለው የላሙ ወደብም ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ይጠበቃል።

ሁሉም የአገሮቹን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የተከናወኑ እና እየተከናወኑ የሚገኙ እንደመሆናቸው በትብብሩ በኩል በሚፈጠረው ዲጂታል ትስስር ደግሞ ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ይቻላል።

ዘመኑ የዲጂታል ነው። የቴሌኮም ዘርፍ የሁሉም ዘርፍ ማሳለጫ ነው። ከዚህ አንጻር የቴሌኮም ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ መግባት ወቅታዊም ተገቢም ነው። የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ማድረስ የሚፈለግበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። በነባሮቹ ግንኙነቶች ላይ ይበልጥ መነቃቃት በመፍጠር፣ ወደ ሥራ ይገባሉ ተብለው በሚጠበቁት ላይም ሚናውን ለመወጣት በመስራት የአገሮቹን ግንኙነት በሚጠበቅበት ልክ ማሳለጥ ይኖርበታል።

ግሎባል አልያንስ ፎር ኢትዮጵያ የተሰኘው ይህ ኩባንያ እጅግ ግዙፍ ኩባንያ ነው። የተለያዩ ልምዱ ያላቸውን ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችንም ያካተተ ነው። በኢትዮጵያ የሥራ ፈቃድ ለማግኘት 850 ሚሊዮን ዶላር ከፍሏል። ሳፋሪ ኮም፣ቮዳ ኮምና ቮዳ ፎን የተባሉት ኩባንያዎች ብቻ በዓለም ከ334 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያላቸው ሲሆኑ፣ በአፍሪካ ብቻ ከ180 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ያስተሳሰሩ ናቸው። ትብብሩ በቀጣይ አስር ዓመታት ለኢትዮጵያ 8 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ መዋዕለ ነዋይ እንደሚያስገኝ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በእጅጉ አንደሚያነቃቃ ታምኖበታል።

በእርግጥም ይህን ያህል አቅም ያለው ኩባንያ ወደኢትዮጵያ መምጣቱ ለኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ለኢትዮጵያና ኬንያ ግንኙነት የላቀ ደረጃ መድረስ ትልቅ አቅም በመሆን ያገለግላል። የኡሁሩ ኬንያታ በዚህ ታሪካዊ ስምምነት ላይ መገኘትም የሁለቱን አገሮች የዘመናት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እየተጓዘ ስለመሆኑ አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። የሁለቱ አገሮች ባለሀብቶች አንዱ በሌላው አገር ኢንቨስት የሚያደርጉበትን ሁኔታም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይታመናል። ኢትዮጵያ ለኢንቨስተሮች ምቹ አገር ሆና መቀጠሏንም ያመለክታል!

አዲስ ዘመን ሰኔ  3/2013

Recommended For You