አረንጓዴ የአመራረት ሂደትና አምራች ኢንደስትሪዎች

በአንድ በኩል ኢንደስትሪ እንዲስፋፋ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት እንዲሰጠው ይፈለጋል:: ሁለቱን እንዴት አጣጥሞ ማስኬድ ይቻላል? በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስቲትዩት የአካባቢ ጥበቃ ሙያ ደህንነትና ኢነርጂ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ዓለሙ አምራች ኢንደስትሪዎች ዘላቂ የልማት ግቦችን፣ በተለይም አረንጓዴ የአመራረት ሂደትን በደንብ መረዳት እንዳለባቸው ይገልጻሉ:: እርሳቸው እንዳሉት ኢኮኖሚ፣ ማህበረሰብና አካባቢ የዕድገት መሠረት ናቸው:: እነዚን ሶስት አስፈላጊ ነገሮች ማዕከል ያላደረገ ንግድ ወይንም ትርፍ ዘላቂነት አይኖረውም:: ሂደቱ አንድ ቦታ ላይ ይገታል::

‹‹አካባቢን ንጹህ አድርጎ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ካለብን ባለሀብቱ ወይንም አምራቹ የሚያገኘውን ገቢ ከማህበረሰቡ፣ ከአካባቢ ጥቅም ጋር ማጣጣም ይኖርበታል:: ባለሀብቱ ኃላፊነቱን እንዲወጣ መንግሥት ተከታትሎና ተቆጣጥሮ መፈፀሙን ማረጋገጥ፣ ተግባራዊ ያላደረገውን በህግ መጠየቅና ወደ ትክክለኛው መሥመር እንዲገባ ማድረግ ይጠበቅበታል:: እየበከልን እናመርታለን የሚለው አካሄድ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም:: የኢትዮጵያ አረንጓዴ ስትራቴጂም በግልጽ ስላስቀመጠው የሚያሻማ ነገር መኖር የለበትም:: እስካሁን ባለው ተሞክሮ አምራች ኢንደስትሪዎች የአረንጓዴ ጉዳይ እንዲነሳባቸው አይፈልጉም:: በአካባቢ ጉዳይ ላይ በጀት መድቦ መሥራትን እንደኪሳራ የማየት ጉዳይ በብዙዎቹ ላይ ይስተዋላል:: ይሄ አካሄድ ግን ቀጣይነት አይኖረውም:: አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ነፃ የገበያ ሥርዓት ነው:: ይህ ሲባል አምራች ኢንደስትሪዎች ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ሲያቀርቡ ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ ምርት ማምረታቸውን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ማቅረብ ወይንም ማሳየት ይጠበቅባቸዋል:: ጥሬ ዕቃ የተፈጥሮ ሀብት በመሆኑም በአግባቡ መጠቀም ይኖርባቸዋል:: ይሄን መረዳት አለባቸው፡ ፡››ሲሉም አስረድተዋል::

እንደ አቶ ዳዊት ገለጻ የአምራች ኢንደስትሪዎች መሥፋፋት ይፈለጋል:: ነገር ግን ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ተደርገው ቢወሰዱም አገልግሎታቸው ከሚሰጡት ጥቅም በላይ ጉዳት የሚያስከትል መሆን የለበትም:: አምራች ኢንደስትሪዎች ለምርት አገልግሎቶች በፈሳሽና በዱቄት መልክ የኬሚካል ግብአቶችን በስፋት ይጠቀማሉ::መጠቀማቸው ግድ ነው:: ኬሚካል ሁሉ ጎጂ ተደርጎ መወሰድም የለበትም::ትኩረት መደረግ ያለበት የሚጠቀሙት ኬሚካል ተቀባይነት ያለውና ለአካባቢ ተስማሚ መሆኑ ነው:: በዚህ ረገድ ክፍተት ከሌለና በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ አስፈላጊነቱ የጎላ ነው::

የኬሚካል ግብዓት ችግር የሚሆነው ለዋጋ ቅናሽ ተብሎና አላስፈላጊ ተጠቃሚ ለመሆን ጊዜ ያለፈበትን ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት ሲደረግና ያለጥቅም ተከማችቶ በአካባቢ ላይ ብክለት፣ በሀብት ላይም ብክነት ሲያስከትል ነው:: ሌላው አምራች ኢንደስትሪው የሚወገደውን ቆሻሻ በአግባቡ አክሞ መልሶ በመጠቀምና በአግባቡ በማስወገድ ችግሩን መቀነስ አለመቻሉ ሲሆን፣ እነዚህ ተደራራቢ የሆኑ ችግሮች በሰው፣ በእንስሳት፣ በዕጽዋት በአጠቃላይ የተፈጥሮ ሥነምህዳርን በማዛባት ተጽዕኖ የሚያሳድር ሆኖ ሲገኝ ነው::

ኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስቲትዩት ባካሄደው ጥናት ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊየን ኪሎግራም በላይ የተከማቸ ኬሚካል በተለያየ አካባቢ መገኘቱን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል:: የጥናት ግኝቱ ኢኒስቲትዩቱ ከሚመራው ከአንድ የኬሚካል ኢንደስትሪ ዘርፍ ብቻ የተገኘ በመሆኑ የችግሩን ስፋት የሚያሳይ አይደለም::ጥናቱ ሰፋ ቢል ከዚህም በላይ ክምችት ሊኖር እንደሚችል መገመት ይቻላል:: ምንም እንኳን ኢንስቲትዩቱ ክምችቱ ወደ ሌላ ነገር ተለውጦ በፍንዳታ መልክ የሚያስጋ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ ባይጠቅስም የኬሚካል ክምችት ያሰጋል:: በቅርቡም በቤሩት ሊባኖስ የኬሚካል ክምችት ፈንድቶ ባስከተለው የዕሳት አደጋ በሰው ህይወት፣ በንብረትና አካባቢን በመበከል ያደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት ማስታወስ ይቻላል::

በኬሚካል ክምችትና ከአምራች ኢንደስትሪዎች በሚወገደው ቆሻሻ በአካባቢ ሥነምህዳር ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖ፣አቶ ዳዊት እንዳብራሩት በጥናት የተገኘው የኬሚካል ግኝት ከሀብት አንጻር ያስከተለው ብክነት እጅግ ከፍተኛ ነው:: ቀላል በሆነ ምሳሌ እንኳን በአንድ ብር ዋጋ ቢታሰብ አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊየን ብር ኪሳራ አስከትሏል:: በውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የገባበት በትክክለኛው ዋጋ ቢሰላ ኪሳራው እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ለማመላከት ነው በአነስተኛ ምሳሌ ለማስረዳት ጥረት ያደረጉት:: ሀብቱ የህዝብ በመሆኑ ኪሳራውም የህዝብ ነው:: ይህ ገንዘብ ሌላ ጥቅም ላይ ቢውል ሊኖረው የሚችለውን ትርፍ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ያስረዱት::

አምራች ኢንደስትሪዎች የሚጠቀሙት ኬሚካል ምን ያህል ደረጃውን የጠበቀና ተቀባይነት አለው? ከአካባቢ ጋር ስላለው ተስማሚነት የሚለው ትልቅ ሀሳብና መሠረታዊ ነገር እንደሆነ በመጥቀስ አቶ ዳዊት ተጽዕኖው ኢትዮጵያ ያደጉ ሀገሮች ቆሻሻ መጣያ ነው የሆነችው እስከማለት ነው በማለት በቁጭት ይገልጻሉ:: እርሳቸው እንዳሉት የአገልግሎት ዘመኑ ሊያልቅ ወራት የቀረውና ቀኑ ያለፈበት ኬሚካል ወደ ሀገር ወስጥ ይገባል::እንዲህ ያለው ክፍተት እንዳይፈጠር ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ ሀገሪቱ ህግ አውጥታለች:: ነገር ግን ህጉን አክብሮ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ መተግበር ላይ ክፍተት መኖሩን ኢንስቲትዩቱ ባደረገው የቆጠራ ሥራ አንዱ ክፍተት እንደሆነ ለይቷል:: የመጠቀሚያ ጊዜው ከ18 ወር በታች የሆነ ኬሚካል ሀገር ውስጥ መግባት እንደሌለበት የሀገሪቱ ህግ ይከለክላል::ባለሀበቱ ጋርም ሰፊ ክፍተት ይስተዋላል::የዋጋውን መቀነስ በማየት ብቻ ያስመጣል::ሌላው በዕውቀት አለመመራቱ ነው::ስለሚያስመጣው የኬሚካል አይነት ዕውቀት የሌለው ባለሀብት መኖሩንም ኢኒስቲትዩቱ ማረጋገጥ ችሏል::

አትዮጵያ ያወጣችው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጅ እንዲተገበር አምራች ኢንደስትሪዎቹ ለአካባቢ ተስማሚ የሆነ የአመራረት ሂደት እንዲከተሉ ማድረግ ይጠበቃል::ይሄን መተግበር የሚቻለው የሚጠቀሙት ጥሬ ዕቃ አካባቢን የማይበክል፣ከመጠን በላይ ያልሆነ የውሃ አጠቃቀምን በማስወገድ፣ የሚጠቀሙት የተፈጥሮ ሀብትም ለብክነት የማያጋልጥ፣ የኃይል አጠቃቀማቸውም በተፈጥሮ በሚገኘው በፀሐይ፣በንፋስና በሌሎችም የታዳሽ አማራጭ ኃይል በመተካት ቀደም ሲል ይጠቀሙ የነበሩትን ለአካባቢ ብክለት ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉትን ናፍጣ ነዳጅ በማስቀረት የአካባቢ ተጽዕኖን ማስቀረት ይቻላል::በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ሰፊ ሀብት ስላላት ለመጠቀም የሚያስችል ዕድል አለ:: ኢንስቲትዩቱ የሀገርን ችግር ይፈታል ብሎ ከያዘው አቅጣጫ፣የገንዘብ ድጋፍና ፕሮጀክት ያገኘበት አንዱ በተለይ የሲሚንቶ ኢንደስትሪዎች የድንጋይ ከሰል በአማራጭነት የሚጠቀሙ ቢሆንም ከውጭ በውድ ዋጋ በማስገባት በመሆኑ የእንጨት ውጤቶች ከሚያመርቱ ድርጅቶች የሚወገደውን ተረፈምርት(ሰጋቱራ)፣በአፋር አካባቢ የሚበቅለው መጤ አረም ለማገዶ በማዘጋጀት የኃይል አቅርቦቱ በነዚህ ግብአቶች እንዲተካ ማድረግ ተመራጭ እንደሆነ ታምኖበታል::ይህን መጠቀም ከተቻለ ኢንደስትሪዎቹ ለኃይል የሚያወጡት ወጭ ይቀንሳል::ተወዳዳሪነታቸው ይጨምራል::የአካባቢ ብክለትም ይቀንሳል::

በዚህ በኩል አበረታች ውጤቶች ታይተዋል:: ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የምርት መጠኑ ከፍተኛ በመሆኑ የኃይል ፍጆታውም ከፍተኛ ነው::በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ የቡና ገለባ፣ የእንጨት ውጤት ተረፈምርት(ሰጋቱራ)፣የሸንኮራአገዳ ተረፈምርት፣ለኃይል አገልግሎት በማዋል እየተጠቀመ ሲሆን፣ ዳንጎቴ እራሱ ያመነጨውን ቆሻሻ እራሱ ያስቀረዋል:: ጎማ፣ ፕላስቲክና ማንኛውንም የሚወገድ ቆሻሻ መልሶ ግብአት በማድረግ አበረታች የሆነ ሥራ እየሰራ ይገኛል:: ድሬዳዋ ላይ የሚገኝ ሸሙ የተባለ የሳሙና ፋብሪካም በተማሳሳይ በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩትን በማስቀረት በአርአያነት ይጠቀሳል::የአካባቢ ንጽህና እንዲጠበቅና ለዜጎችም የሥራ ዕድል እንዲፈጠር በማድረግ ዘርፈብዙ ጥቅም የሚያስገኝ ሆኖ ተገኝቷል:: ሌሎች አምራች ኢንደስትሪዎችም ወደዚህ አሰራር ውስጥ እንዲገቡና ተሞክሮው እንዲሰፋ በኢኒስቲትዩቱ በኩል በኃላፊነት እየተሰራ ነው::

ከአወጋገድ ጋር ተያይዞ ስላለው አሰራርም አቶ ዳዊት እንዳስረዱት በካይ ወይንም አመንጭውን አካል ተጠያቂ የሚያደረግ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲና ህግ ወጥቷል:: የመንግሥት ድርሻ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ህጉን ማስከበር ነው:: ጥቅም ላይ የሚውሉትን ጥቅም ላይ ማዋል:: የማይውሉትን ደግሞ በመቅበር ወይንም በሌላ ዘዴ ማስወገድ ከአመንጪው አካል ይጠበቃል:: ጉዳዩን አነጋጋሪ የሚያደርገው ግን ችግሩን በመፍጠር የህግ አውጭውና አስፈጻሚው አካል የመንግሥት ተቋማት መኖራቸው ነው:: በብዙ የመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ ጊዜ አልፎባቸው ጥቅም ላይ ያልዋሉ የኬሚካል ክምችት ተገኝቷል:: ኢኒስቲትዩቱ ሀገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ግዥና ንብረት አስተዳደር፣ ከተውጣጡ አባላት ኮሚቴ ተዋቅሮ በቅንጅት መሥራ ከጀመረ ሶስተኛ ወሩን ይዟል:: ክምችቱ እንዴት ይወገድ፣ግዥ ሲፈጸምም በምን መልኩ መከናወን እዳለበት ኮሚቴው እየተነጋገረበት ይገኛል::አሰራሩ ወደፊት ወደ አንድ አቅጣጫ ይመጣል የሚል እምነት ተወስዷል::

ኢኒስቲትዩቱ ሳያውቅና የብቃት ማረጋገጫ ሳይሰጥ የኬሚካል ግዥ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባም አሰራር ተቀምጧል::ጉሙሩክ ኮሚሽንም ሆነ ንግድና ኢንዱስትሪ በዚህ ጉዳይ ላይ እንደማይገቡ ስምምነት ተደርጓል:: ህግም ወጥቷል:: በዚህ መልኩ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ ወደ ሥራ ቢገባም፤በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል የለም::ኢኒስቲትዩቱ ከሌሎች ተቋማት ጋር የሚገናኝበት በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሰራር ሥርአት አልተዘረጋም::ይህ አሰራር ከተዘረጋ ግን ወደ ሀገር የገባውን የኬሚካል አይነትና መጠንን፣የመጠቀሚያ ጊዜ ለመከታተል ያመቻል:: በቁጥጥርና ክትትሉም አንዱ ያልተጠቀመበትን ሌላው እንዲጠቀምበት በማድረግና ሀገር ውስጥ የገባው ሳያልቅ ሌላ ግዥ እንዳይፈጸም ለማድረግ ያግዛል::

የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ያላገኘ አምራች ኢንደስትሪ ወደ ሀገር ማስገባት አይችልም:: በዚህ መልኩ ውጤታማ ለመሆን፣ የአሰራር ሥርአቱን በመዘርጋት ረገድ የመንግሥት እገዛ ወሳኝ ነው::በህገወጥ የሚገባውን ለመቆጣጠር የሌላ አካል እገዛም ያስፈልጋል:: የኬሚካሉን ትክክለኛነት የሚያረጋግጥበት ቤተሙከራ(ላቦራቶሪ) በኢኒስቲትዩቱ አለመደራጀቱም ለሥራው ቅልጥፍና ችግር ሆኖበታል:: ይሄም ቢሟላለት የተሻለ አፈፃጸም ይኖረዋል:: አምራች ኢንደስትሪዎች የሚያስወግዱትን ቆሻሻ መጠን የመመዝገብ ባህል ስሌላቸው የሚወገደውን መጠን ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በአምራች ኢንደስትሪዎቹ ታክሞ የተወገደውን ደረቅ ቆሻሻ ከሲሚንቶ ጋር ተቀላለቅሎ ለእግረኛ የመንገድ ንጣፍ እንዲውል በኢኒስቲትዩቱ በኩል ጥረት እየተደረገ ነው::

ኢኒስቲትዩቱ በየአመቱ አቅዶ በሚያደርገው እንቅስቃሴም በጥናትና ምርምር በአምራች ኢንደስትሪው ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመለየት እንዲታረሙ ማድረግ መቻሉን የጠቆሙት አቶ ዳዊት እንዳስረዱት ኢኒስቲዩቱ በቀለም ፋብሪካዎች ላይ ባካሄደው ጥናት ከፋበሪካዎቹ የሚለቀቀው ኬሚካል ከወጣው ደረጃ በላይ መሆኑ ተረጋግጧል:: የሚያስወግዱትን ፍሳሽ የሚያጣሩበት ወይንም የሚያክሙበት ቴክኖሎጂ እንደሌላቸው ተረጋግጧል::ሊድ የተባለው የኬሚካል አይነት በስፋት የመጠቀም ልምድ ነበር::ካንሰር የሚያስከትል አደገኛ ኬሚካል ነው::ወደ ግጦሽና ወደ ወንዝ የሚለቀቅ ነበር:: ከጥናት ግኝቱ በኋላ ከሊድ ነፃ የሆነ ኬሚካል እንዲጠቀሙ በተሰጠው ምክር መሠረት በሌላ የኬሚካል አይነት በመተካት ምክሩን ተግባራዊ ያደረጉ ፋብሪካዎችም ይገኙበታል:: ቀለም ፋበሪካዎች በአንድ የኢንደስትሪ መንደር ውስጥ ተሰባስበው የሚያስወግዱትን ፍሳሽ አክመው ለመጠቀም የሚያስችላቸው ቴክኖሎጂ (ዌስት ወተር ትሪትመንት ፕላንት)እንዲኖራቸው በኢኒስቲትዩቱ በኩል ጥረት ተደርጎ አልተሳካም::

ከፍተኛ የገንዘብ ወጭ የሚጠይቅ በመሆኑ አልተሳካም::እያንዳንዱ ፋብሪካም ደረጃውን የጠበቀ የማከሚያ ፋብሪካ ማቋቋም ስለማይችል ነበር በአንድ ቦታ እንዲሰበሰቡ ለማድረግ የታቀደው:: ማንኛውም አምራች ኢንደስትሪ ግንባታ ከማካሄዱ በፊት በአካባቢ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ መገምገም፣ ለሚደርሰው ተጽዕኖ ደግሞ መፍትሄዎቹ መቀመጥ አለባቸው የሚል 2002ዓም ላይ የወጣውን የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ አብዛኞቹ ከአዋጁ በፊት በመቋቋማቸው ተግባራዊ ለማድረግ ያስቸግራል:: ኢኒስቲትዩቱ በተመሳሳይ በሀዋሳ የኢንደስትሪ ፓርክ ላም ውጤት ያስገኘ ተግባር አከናውኗል::ፓርኩ አክሞ የሚያውጣውን ውሃ መልሶ ይጠቀማል::ጠጣሩን ወይንም ደረቅ ቆሻሻውን ግን የሚያስወግድበት አልነበረውም::

ኢኒስቲትዩቱ ደረቅ ቆሻሻው ለአግንባታ ግብአት እንዲውል በማድረግ አግዟል:: ተረፈምረቱ ከሲሚንቶ ጋር ተደባልቆ ለሸክላ ጡብ እንዲውል በማድረግ ብክለትን መቀነስ ተችሏል::ከቆዳ ኢንደስትሪ የሚወገደውንም በተመሳሳይ ጥቅም ላይ ለማዋል፣ለዕቃ መያዣ የሚውለው ፕላስቲክም ደረጃውን ጠብቆ እንዲመረት፣ የውሃ መያዣ የፕላስቲክ ጠርሙስም መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ኢንስቲትዩቱ ግንዛቤ በመፍጠርና በጥናትና ምርምር በማገዝ እየሰራ ይገኛል::

የኢንሲስትዩቱ ተልዕኮና ተግባር በኬሚካልና በኮንስትራክሽን ግብአቶች በማምረት ዘርፍ የተሰማሩ አምራች ኢንደስትሪዎችን በጥናትና ምርምር መደገፍ፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ አቅም በመገንባት ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፣ ይሄንኑ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል::በንግድና ኢንደስትሪ ሥር የሚገኝ፣ ከተቋቋመም ገና አስር አመት ያልሞላው ተቋም ነው::አምራች ኢንደስትሪዎች ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ ምርት እንዲያመርቱ፣ ታዳሽ ኃይል እንዲጠቀሙ በማድረግ በአዋጅ ስልጣን ተሰጥቶታል:: በኢኒስቲትዩት የአካባቢ ጥበቃ ሙያ ደህንነትና ኢነርጂ ዳይሬክቶሬት ዘርፍ በሀገር ወደ አነስተኛና መካከለኛን ጨምሮ ወደ 6500 አምራች ኢንደስትሪዎችን ይከታተላል::ግንዛቤ በመፍጠርና በጥናትና ምርምር እያገዛቸው ይገኛል::

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሰኔ  3/2013

Recommended For You