ማን ያድምጥ?

“ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል” ከሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ይልቅ አሁን ላይ “ዝም ባለ አፍ ዝምብ አይገባም” የሚለው የተመረጠ ይመስለኛል:: በእርግጥ ምንም አለመናገር መልካም አይደለም፤ነገር ግን ብዙ ከመናገር ብዙ ማድመጥ የተሻለ በመሆኑ ላይ ግን ሁሉም ያምናል:: ቦታና ጊዜን ለይቶ ሁኔታና አጠቃላይ ጉዳይን መርምሮ የሚናገሩትን ጠንቅቆ አውቆ ለሌላ ለማሳወቅ መሞከር የበለጠ ይጠቅማል::

ዛሬ ላይ ሁሉም እኔ የምለውን ስሙኝ ፤የእናንተን ማድመጥ አልፈልግም የሚል መብዛቱ ነው የቸገረን :: ጎበዝ ሰዎች መግባባት እንዲችሉ የእነሱን ሀሳብ ለሌላው ከማስተላለፍ ባለፈ የሌሎችንም መስማት እንዳለባቸው ስለምን ይዘነጋሉ?

ለብዙ ስህተቶች የምንጋለጠው ትንሽ ሰምተን ብዙ በመናገራችን ምክንያት ነው:: የማድመጥን ጠቀሜታ የምንረዳው ከመናገር ይልቅ ብዙ የሚያደምጡ ሰዎች ስኬትን ስንመለከት ነው፤ እነዚህ ሰዎች የሚናገሩት ሁሉ ከአፍ ጠብ የማይል ፍሬ ነገር ያለው ሲሆን ነው የማዳመጥን ጠቀሜታ የምንረዳው::

በአለም ላይ ታላቅ አበርክቶ ካላቸው ሰዎች መካከል ይጠቀሳል፤ ታላቁ ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን:: በምድር ላይ የቆየበት ዕድሜ ከ72 አመት አይበልጥም፤ እስከ ዛሬ ድረስ በተለይም በፊዚክስ ዘርፍ አቻ አልተገኘለትም :: አንስታይን ብዙ ከማውራት ይልቅ ማድመጥን ይወድ እንደነበር ይነገራል:: በነገራችን ላይ አንስታይን ብዙ አለመናገሩ ከልጅነቱ ጀምሮ የተላመደው ተግባሩ ነው :: አፉን ሳይፈታ ፣ ሳይናገር መቆየቱ ወላጆቹን ግራ አጋብቷቸውም ነበር::

አንስታይን መጀመሪያ የተናገረበት አጋጣሚ የሚገርም ነበር :: አንድ ቀን እናቱ ሩዝ አቅርባለት እየበላ ነው :: ሩዙን ለማጣፈጥ የተጠቀመችበትን ቅመም አብዝታው ኖሮ አንስታይን እየበላ እያለ መሀል ላይ “ሩዙ በጣም ያቃጥላል” ብሎ ይናገራል:: በዚህም ቤተሰቡ በጣም ይደናገጣል:: የልጁ አለመናገር ሲያሳስባቸው የቆዩት ቤተሰቦቹ የእሱ በዚህ አጋጣሚ መናገር መጀመር አስገርሟቸው ይደነቃሉ:: ንግግሩም መኮላተፍ የሌለበትና ቃላቱን በትክክል የገለጸበት ነበር::

ታዲያ ቤተሰቦቹ በዚህ ንግግሩ በመደመም “እንዴት መናገር እየቻልክ እስከ ዛሬ አንዲት ነገር ሳትተነፍስ ትቆያለህ፤ ለምንስ አሳሰብከን?” ብለው ይጠይቁታል፤ እሱም “እስካሁን ከሰማሁት ሁሉ ለማውራትና ለመጠየቅ የሚሆን የረባ ነገር አላገኘሁበትም ፤ለዚያ ነው ያልተናገርኩት” ሲል የሚደንቅ መልስ ይሰጣቸዋል::

ይህ ታላቅ ሊቅ በህይወት ዘመኑ ሁሉ ለዓለም ያበረከታቸው ታላላቅና የማይተኩ አስተዋጽኦዎቹ ብዙ ሳይናገር የከወናቸው ፣በብዙ ጥረት የተገኙ ስራዎቹ ናቸው ::

ይህ ሲባል ግን አንስታይን በወሳኝ እና አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አስተያየት አይሰጥም ነበር ማለት ግን አይደለም:: እንደውም ያወቀውን ለሌሎች ለማሳወቅ የተለያዩ መድረኮች እያዘጋጀ መልካም ነገር ለብዙዎች አድርሷል :: የእሱ ልምድ የነበረው ፍሬያማ የሆኑ ነገሮች ላይ ትኩረት አድርጎ ብዙ አድምጦና የሚረባውን መርጦ መንገር ላይ ነበር::

ውዶቼ ንግግርም ዝምታም ቦታቸውን አውቆ በትክክል ለተጠቀመባቸው አንጋሾች ናቸው:: ተገቢ ንግግር አለመናገር ወይም ጩኸት ሲያስፈልግም መታፈን ጉዳት ነው:: ንግግር ያስፈልጋል፤ አላስፈላጊ ንግግርና አለመደማመጥ ነው ከባድ:: እኛ የበዛውን ተናግረን ያነሰ ማድመጣችን ላይ ነው ችግራችን:: የራሳችን ብሎም የማህበረሰባችንን የቆየ ልምድ እና አሁናዊ ልማድ ብንመለከት ከማድመጥ ይልቅ መናገር ከማዳመጥ ይልቅ ማስደመጥን እየወደድን ይመስላል::

አለማዳመጥ የችግሮቻችን ቁልፍ ጉዳይ ያለመግባባታችን ዋንኛ መሰረት ነው፤ ስሙኝ ፤ነገር ግን የእናንተን አልሰማም ማለት:: መጀመሪያ ነገር በሌሎች እንድንደመጥ የሌሎችን ንግግርና ሀሳብ አድማጭ መሆን ይኖርብናል :: የእኛ ሀሳብና ንግግር በሌሎች ተቀባይነት እንዲያገኝ የሌላውን ሀሳብና ንግግር መቀበል ያስፈልገናል:: ሳይቀበሉ መስጠት፣ ሳይሰጡ መቀበል እዚህች ምድር ላይ አይሰራም:: ሁሉም በሰጠው ልክ ነው የሚያገኘው:: እንካ ሲባል እሺ አንተም እንካ ነው ቀመሩ::

የሰጥቶ መቀበል ስሌት ነው የሚያገኝ:: እንካ የአንተን አልወስድም ግን ውጤቱ ጥሩ አይደለም:: የራስንም ያስነጥቃል:: በነገራችን ላይ ወዳጆቼ ሀሳብ ገበያ ነው:: ሀሳባችንን ለሌሎች ለመሸጥ የሌሎችን ሀሳብ መቀበል ይገባናል:: ከዚህ ስሌት የተላቀቀ ከራሱ ጋር ቀድሞ መታረቅ ይኖርበታል::ከዚህ እውነት ጋር ለመግባባት ትክክለኛውን መረዳት ያስፈልጋል::

የምንናገረው ሌላውን ዝም ለማስባል አልያም የእኛ እንዲደመጥ አስበን ከሆነ ንግግራችን መሬት አይነካም፤ ጠብ የሚል ፍሬ አይኖረውም:: ነገር ግን ሌሎችን ብዙ አድምጠን የእኛን በትንሹ ለሌላው ለማቅረብ ከሞከርን ያ ንግግራችን ፍሬ ያለው፣ በሌሎችም ተቀባይነትን የተላበሰ የመሆን እድሉ ከፍ ያለ ይሆናል :: ብዙ ከመናገር ይልቅ ብዙ መስማትም የሚወደደው በዚሁ ምክንያት ነው::

የምንናገረውን በውል ተረድተን ሌላው የሀሳባችንን ውል እንዲረዳ ለማድረግ ቀድመን እሱ ያለበትን እውነት መረዳት ይኖርብናል :: ያን የምናገኘው ደግሞ ከመናገራችን በፊት ማድመጣችን ሲቀድም ነው :: ብዙ ከመናገር ይልቅ ብዙ ማዳመጥን የመሰለ ጣዕም ምድር ላይ የለም ::

በነገራችን ላይ በእኛ ንግግር የሚጠቀሙት ብዙውን ጊዜ ሌሎች ናቸው :: ለእኛ የሚጠቅመን ከምንናገረው ይልቅ ብዙውን ጊዜ የምንሰማው ነው :: ለምሳሌ ከፍ አድርገው ድምጽን ለሌላው አጉልተው ከሚያሰሙት ይልቅ፣ ያንን የሚጮኸውን ድምፅ የሰሙት ሰዎች ከተጮኸበት ክፉ ነገር ይድናሉ::

አሁን ላይ የእኔን እንጂ የሌላውን ልስማ የሚል ስንሰማ ይደንቀናል:: ምክንያቱም ሁሉም ስሙኝ ነዋ ልማዱ:: ስሙኝ ስንል እሺ ለመባል ስማኝ ሲባል መስማት የሚቀድም መሆኑን እንዴት ሳይገባን ቀረ :: እንደ ማህበረሰብ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንድንችል አንዱ የሚያወራውን ሌላው መስማት ሌላውንም መረዳት ይኖርበታል:: በማድመጥ ውስጥ የሚገኝ ፍሬ ነገር፣ ተናግረው ከሚስቱት የላቀ መሆኑን መረዳት ይገባል::

መድረኮች ላይ ንግግር የሚያበዛን ያህል ተሳሳች የመድረክ መሪ የለም:: ዝም ማለትን የሚወድ ሰው ያህል ከንግግሩ መሐል የሾለከ አነስተኛ ስህተት የሚገኝበት አይኖርም:: አድማጭ ከተናጋሪ የተሻለ ተጠቃሚ ነውና ሁሌም አብዝተው ከሚናገሩት ይልቅ አብዝተው ከሚያደምጡት ለመሆን እንጣር:: አበቃሁ ፤ቸር ይግጠመን::

 ተገኝ ብሩ

አዲስ ዘመን ሰኔ  3/2013

Recommended For You