አርባ ስምንት ሰዓት ሳይሞላው በኢትዮጵያ እጅ የገባው ክብረወሰን

ለ23 ዓመታት በቻይናዊት አትሌት ተይዞ የቆየው የ10 ሺ ሜትር የሴቶች የዓለም ክብረወሰን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በርቀቱ ፈርጦች ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን ሳይሰበር መቆየቱ ለብዙዎች ሚስጥር ነበር። ሆኖም ባለፈው የ2016 ሪዮ ኦሊምፒክ እንቁዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት አልማዝ አያና ሳትጠበቅ 29:17:45 በሆነ ሰዓት የዚህን ክብረወሰን የዘመናት ሚስጥር በአስደናቂ ብቃት መመለስ ችላለች።

ይህ ክብረወሰን ባለፉት አምስት ዓመታት ሳይደፈር ከመቆየቱ ባሻገር በቅርብ ዓመታት ይሻሻላል ብሎ የገመተም አልነበረም። ባለፈው እሁድ ግን ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድ አትሌት ሲፈን ሀሰን ማንም ባልገመተው ውድድር የአልማዝን ክብረወሰን 29:06:82 በሆነ ሰዓት የግሏ በማድረግ ዓለምን አነጋግራለች።

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ከኮቪድ-19 ማግስት በኢትዮጵያውያን ለዓመታት ተይዘው የቆዩ በርካታ የዓለም ክብረወሰኖች በሌሎች አገራት አትሌቶች መሰበራቸው ለኢትዮጵያውያን ጥሩ ዜና አልነበረም። በተለይም በጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ ሳይሰበሩ የቆዩት የ5 ና 10ሺ ሜትር ክብረወሰኖች በዩጋንዳዊው አትሌት ጆሽዋ ቺፕቴጌ በአንድ ወር ልዩነት መሰበራቸው ያልተጠበቀ ነበር።

በዚህ ላይ ባለፈው እሁድ በኢትዮጵያውያን እጅ ያለው ትልቁ የሴቶች የ10 ሺ ሜትር ክብረወሰን መሰበሩ የሚያስቆጭ ነበር። የዚህ ክብረወሰን ከኢትዮጵያውያን እጅ መውጣት የፈጠረው ቁጭት ግን ለአርባ ስምንት ሰዓት እንኳን አልዘለቀም። ምስጋና ለመዘናችን እንቁ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ይግባና ከኢትዮጵያውያን እጅ ያፈተለከው ክብረወሰን ሳይውል ሳያድር ከትናንት በስቲያ ምሽት በኔዘርላንድስ ሄንግሎ ላይ በተካሄደው የኢትዮጵያውያን የኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር ላይ ወደ አገሩ ተመልሷል። ለተሰንበት በሲፈን የተያዘውን ክብረወሰን 29:01:03 በሆነ ሰዓት በመስበር በኔዘርላንድስ እጅ የገባው ትልቅ ታሪክ ከሁለት ቀን የዘለለ እድሜ እንዳይኖረው አድርጋለች።

የዓለም አገር አቋራጭ የሁለት ጊዜ ቻምፒዮኗ አትሌት ለተሰንበት ዘንድሮ የኢትዮጵያውያን ክብረወሰኖች በሌሎች አገራት አትሌቶች ባልተጠበቀ ሁኔታ ሲሰባበሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዘንድሮም ክብረወሰኖችን መስበር እንደማይገዳቸው ከወራት በፊት አስመስክራለች። ለአስራ ሁለት ዓመታት በረጅም ርቀት ንግስቷ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ተይዞ የቆየውን የ5 ሺ ሜትር ክብረወሰን ለተሰንበት ባለፈው ጥቅምት 14:06:62 በሆነ ሰዓት በመስበር የርቀቱ ታሪክ በኢትዮጵያውያን ስር እንዲቆይ ትልቅ ተጋድሎ አድርጋለች። በውድድር ዓመቱ የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የዓለም ክብረወሰንንም በእጇ በማስገባት የብቃቷን ጣሪያ እያሳየች ትገኛለች። የ5 ና 10ሺ ሜትር ርቀቶችን የዓለም ክብረወሰን በአንድ ላይ የግሏ በማድረግም እኤአ ከ1986 እስከ 1993 ኢንግሪድ ክርስቲንሰን ወዲህ ለተሰንበት የመጀመሪያዋ አትሌት ሆናለች።

ለተሰንበት በሄንግሎው ምሽት አልተሳካላትም እንጂ ዓለም ይግረመው ብላ 10ሺ ሜትሩን ከ29 ደቂቃ በታች ለመሮጥ አስባ እንደነበር ከውድድሩ በኋላ ተናግራለች። ‹‹የዓለም ክብረወሰን ለመስበር አስቤ ነው ወደ ውድድር የገባሁት›› ያለችው የሃያ ሶስት ዓመቷ ድንቅ አትሌት ዳግም ርቀቱን ከ29 ደቂቃ በታች ለማጠናቀቅና የራሷን ክብረወሰን ለማሻሻል ፍላጎት እንዳላት ገልፃለች፡፡

የርቀቱ ክብረወሰን ሁለት ቀን ባልሞላ ጊዜ እንዲሰበር ያደረጉት ሲፈንና ለተሰንበት አሁን ከሰሩት ታሪክ በላይ ከሁለት ወራት በኋላ በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በርቀቱ ሊያደርጉት የሚችሉት ፉክክር መነጋገሪያ ሆኗል። ሁለቱ አትሌቶች በ2019 የኳታር የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በርቀቱ ተገናኝተው ለተሰንበት አጨራረስ ላይ በሰራችው ጥቃቅን ስህተቶች በሲፈን ተቀድማ የብር ሜዳሊያ ማጥለቋ ይታወሳል።

ለተሰንበት በክብረወሰን ታጅባ በደመቀችበት የሄንግሎው የኢትዮጵያውያን የኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር ኢትዮጵያ በቶኪዮ ኦሊምፒክ በተለያዩ ርቀቶች አዲስና ጠንካራ የአትሌቲክስ ትውልድ ይዛ እንደምትቀርብ ለዓለም ያሳየችበት ሆኗል።

በሴቶች 10ሺ ሜትር ለተሰንበትን ተከትላ አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ በአንድ ደቂቃ ልዩነት በመግባት ኢትዮጵያን በኦሊምፒክ ለመወከል የሚያበቃትን ውጤት አስመዝግባለች። ፅጌ ባለፈው ሃምሳኛ ዓመት የኢትዮጵያ ቻምፒዮና አዲስ አበባ ስቴድየም ላይ ሲካሄድ በርቀቱ ቀዳሚ ሆና ማጠናቀቋ ይታወሳል።

የማጣሪያ ውድድሩን 30:29:19 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው አትሌት ፀሐይ ገመቹ ከባለክብረወሰኗ ለተሰንበትና ፅጌ ገብረሰላማ ጋር ኢትዮጵያን በኦሊምፒክ 10ሺ ሜትር የምትወክል ሶስተኛዋ አትሌት መሆኗን አረጋግጣለች። 30:20:77 በሆነ ሰዓት አራተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው በርቀቱ በተጠባባቂነት ተይዛ ከሶስቱ አትሌቶች ጋር ለኦሊምፒክ የምትዘጋጅ ይሆናል።

 ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሰኔ  3/2013

Recommended For You