የአሸናፊነት የትርክት ለውጥ ለጀመርነው የብልጽግና ጉዞ ስኬት መሰረት ነው !

የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አጠቃላይ ውጤት ይፋ ተደርጓል ፡፡ ምርጫው ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያ ያሸነፉበት ታሪካዊ ምርጫ ከመሆኑ አንጻር ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ለሁሉም የአሸናፊነት ድል ያጎናጸፈ ፤አገርን እንደ አገር ማሻገር ያስቻለ ነው ።

በተለይም ሕዝባችን ከሚፈልገው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ብልጽግና አንጻር ምርጫው ለእውነተኛ ዴሞክራሲ በየዘመኑ ሕይወታቸውን የገበሩ ዜጎቻችን መስዋዕትነት ፍሬ ማፍራት እንደጀመረ ተጨባጭ ማሳያ ነው ።

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ነው ። ድንገት ተጀምሮ የሚጠናቀቅ ማህበራዊ እውነታ አይደለም ። የየዘመኑን ትውልድ ተሳትፎ የሚጠይቀው፤ በተሳትፎው መጠን እየጎለበተ የሚሄድ ማህበረሰቡን ወደተሻለ ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያሻግር ነው።

በዚሕ ሂደት ውስጥ የቀደመው ትውልድ አስተሳሰቡን በማህበረሰቡ ውስጥ ከማስረጽ ጀምሮ አስተሳሰቡ ሥጋና ደም ለማልበስ ከፍ ያለ መስዋዕትነት ከፍሏል ። የከፈላቸው መስዋዕትነቶች በራስ ወዳድ ግለሰቦችና ቡድኖች የሴራ ትብታብ ተጠልፈው ትርጉም አልባ ደረጃ ወርደው የታዩበት እውነታ የትናንት ትዝታ ነው ።

በአንድ በኩል ይዘነው የመጣነውና በየዘመኑ ከፍ ያለ ዋጋ ያስከፈለን አገርን ጭምር አደጋ ውስጥ የሚከት የአሸናፊና የተሸናፊነት ትርክት ፤ትርክቱ የፈጠረው ያልተገባ የአስተሳሰብ መሰረት እንደ ማህበረሰብ ለቀጣይ እድገታችን ያስፈልገን የነበረውን በሰከነ ህሊና የመነጋገርና የመስማማት ሰብዓዊ እድል አሳጥቶናል።

ከዚህ ይልቅ አጠቃላይ እውነታዎችን በአሸናፊነትና በተሸናፊነት መንፈስ ውስጥ ሆነን እየመዘንን በየዘመኑ መንፈሱ በሚያላብሰን ያልተገባ ስሜትና ስሜቱ በሚወልደው የተዛባ ማንነት እየተገራን አንድ እርምጃ ፈቀቅ የማንልበት የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ረጅም ዘመን ለመቆየት ተገደናል ።

በነዚሕ ረጅም ዘመናት ውስጥም አስተሳሰቡ ለወለደው ድርጊታችን ለመክፈል የተገደድነው ዋጋ አገርን የድህነት ፣ የጉስቁልና፣ የረሀብና የግጭት ማዕከል ከማድረግ ባለፈ ያስገኘልን አንዳች ነገር የለም ። እንዲያውም አስተሳሰቡ በፈጠረው ትርክት አገርን እንደ አገር አደጋ ውስጥ የከተተ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ።

በዚሕ አስቸጋሪና ፈታኝ ታሪካዊ ወቅት ያካሄድነው ምርጫ በብዙዎች ዘንድ የተጨማሪ ግጭትና ትርምስ ምንጭ እንደሚሆን ተገምቷል ። አገርንም ወደ መበተን ሊወስድ የሚችል አደጋም እንደሆነ ብዙ ተብሏል ። ለዚህም የመጣንበት የፖለቲካ ባህል የተገዛበት የተዛባ አስተሳሰብ እንደሆነም ለመገመት አይከብድም ።

የፖለቲካ ባህላችን በተለይም ለፖለቲካ ድል የነበረን አስተሳሰብ እና የድል ማግስት ልምምዶቻችን ካልተገባ የአሸናፊነት መንፈስ የሚመነጩ ትናንቶችን ፈጥነው የሚረሱና አዲስ ዛሬን በተዛባ የአሸናፊነት እና የተሸናፊነት ትርክት ለመፍጠር የሚጥሩ ፤ በተረኝነት መንፈስ የተቃኙ ናቸው ።

የአዲሱ ባላተራ የድል ጉዞ በብዙ ስጋቶች የተሞሉ ስለሚሆኑ ሥጋቶቹን ለማስወገድ የሚከናወኑ የሴራ መንገዶች ፤በራሳቸው አዲስ የስጋት ምንጭ እየሆኑ ሕዝባችን አሸናፊዎች የአሸናፊነት መንፈስን ለማስቀጠል በሚሰሩት ሴራ እረፍትና እፎይታ እንዲያጣ ሆኗል ።

በምርጫው አገር አሸንፋለች የሚለው የዛሬው አዲስ ትርክት የቀደመውን አገራዊ የፖለቲካ ባህል የሚዋጅ ፤ ትርጉም ከፍ ያለ አገርና ሕዝብን የማሻገር አቅም ያለው ነው ። የቀደሙትን ትውልዶች ከመስዋዕትነት ባሻገር የነበረና ያለውን የመሆን መሻት እውን ማድረግ የሚያስችል የህያው ቃል ዘር ፍሬ ነው ።

ዛሬ ላይ አገርና ሕዝብ ከነበሩበት ከፍ ያለ ፈተናና ተግዳሮት ማውጣት ያስቻለ ፤ ላሰብናቸውና ለመከርንባቸው የተሻሉ ነገዎች ከፍ ያለ አቅም መሆን የሚያስችል ነው ። የቀደመውን የፖለቲካ ባህላችንን በመዋጀት አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር እድል የሰጠን ነው ።

ብዙዎች ስለኛ እጅግ ብዙ ክፉ ነገሮችን ባሉበት ፤በቃ ! አበቃላቸው የሚል ትርክት አየሩን በያዘበት ፤ስጋትና ፍርሀት ገዥ ሆነው ስሜቶችን በተቆጣጠሩበት አገራዊና ዓለም አቀፋዊ አውድ ውስጥ በድል አድራጊነት እንድንሻገር አድርጎናል።

በእርግጥም የአገር ማሸነፍ ከግለሰብ እና ከቡድኖች አሸናፊነት በላይ አገርን የሚያሻግር አልፋና ኦሜጋ አቅም ያለው እንደሆነው ከዛሬው ታሪካችን መማር ችለናል ። ብዙ ዋጋ ትውልዶችን ካስከፈለ ያሸናፊና ተሸናፊ ትርክት ወጥተን ሁላችንንም አሸናፊ ወደሚያደርግ የአገር አሸናፊነት ተሻግረናል ። ይህ የትርክት ለውጥ ለጀመርነው አገራዊ ብልጽግና ስኬት መሰረት ነው ።

አዲስ ዘመን ሐምሌ  5/2013

Recommended For You