አሸባሪው ህወሓት ግብዓተ መሬቱን አፋጥኗል!

አሸባሪው ህወሓት መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ በመወሰን ለትግራይ ህዝብ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ለህዝቡ የሚቀርበው ሰብዓዊ ድጋፍ ይበልጥ እንዲሳለጥ፣ አርሶ አደሩም ሙሉ አቅሙን በመኸር እርሻው ላይ እንዲያውል ማድረግ ሲገባው ህጻናትን ለጦርነት መማገዱንና ክልሉንም የጦርነት ቀጠና ማድረጉን ቀጥሎበታል። ለህግ ማስከበር የገባው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል መቆየቱ ሰብዓዊ ድጋፍን የሚያስተጓጉልና አርሶ አደሩን ከእርሻው የሚያፋታ አርጎ ሲከስ የከረመው ይሄ ቡድን ዛሬም ድረስ በየአቅጣጫው ትንኮሳውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

አሸባሪ ቡድኑ ዛሬም እንደትናንቱ ባልተጎናጸፈው ድል ከበሮ እየደለቀ ፣ እስክስታ እየወረደ ህዝቡን በሀሰት ሲያታልል ቆይቷል፤ በዚህ ሀሰተኛ ወሬው የትግራይን ህዝብ አሁንም ለጦርነት እየማገደው ነው። ‹‹ከአማራ ክልል ጋር የማወራርደው ሂሳብ አለኝ›› ሲል የቆየው አሸባሪው ቡድን በአማራ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች ጥቃቶችን ሰንዝሯል። በዚህም አልበቃ ብሎት ተመሳሳይ ጥቃት በአፋር ክልል ላይም መሰንዘሩን ቀጥሏል።

ይሄ የአሸባሪው ቡድን ትንኮሳ የአማራ ክልልን ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል ፤ ለአጠፋዊ እርምጃም አነሳስቷል። የኢትዮጵያ ልጆች በአራቱም አቅጣጫ የጁንታውን ዕቅድ ለመቀልበስ ሆ ብለው ተነሳስተዋል። የየክልሎቹ ኃይሎች ውለው ሳያድሩ ጥቃቱ ወደ ተሰነረዘባቸው አካባቢዎች በመንቀሳቀስ አጋርነታቸውን በተጨባጭ አስመስክረዋል።እናቶች ስንቅ በመሰነቅ፣ የመንግሥት ሠራተኛውና ነጋዴው የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ሌላው በሞራል እና በቁሳቁስ ጭምር እገዛ እያደረጉ ናቸው ።ይሄ በአንድ ክልል ላይ ሳይሆን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያለመ ሴራ በመሆኑ ሁሉም ህዝብ ከህይወት መሰዋዕትነት እስከ ትንሹ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቆራጥነቱን ዳግም አሳይቷል።

ጁንታው ቡድን አሁንም ሲያደርገው የኖረውን ህዝብን የመከፋፈል ስትራቴጂውን ተጠቅሞ ህዝብን ከህዝብ ለመለያየት በርካታ ጥረቶችን አድርጓል ።ሆኖም ሁሉም ህዝብ አስቀድሞ ሴረኛነቱን ተረድቷልና እንደቦይ ውሀ የሚፈስ ህዝብ አላገኘም ። የህዝቡም አጸፋዊ ምላሽ በተቃራኒው ሆኗል። ህወሓት ካለፈው ስህተቱ ዛሬም አልተማረም። ከጥፋቱ ከመማር ይልቅ በጥፋት ላይ ጥፋት እየደራረበ በገዛ ዱላው እየተወገረ ይገኛል ። ይሁን እንጂ ከአፍርኩ አይመልሰኝ ብሎ በእኩይ ተግባሩ ቀጥሏል። እንደ አበደ ውሻ እየተክለፈለፈ ይገኛል። በአማራና አፋር ክልሎች ላይ እየፈጸመ ያለው ጥቃት የእብደቱን ደረጃ የሚያመለክት ነው ።

ጁንታው ቡድን ቆምኩላችሁ የሚላቸውን የትግራይ ክልል ህጻናት፣ ሴቶች፣ ቄሶች ፣ አዛውንቶች ጭምር በጦርነት እየማገደ ይገኛል። እነዚህ ወገኖች ዛሬ የሚያስፈልጋቸው ሰብዓዊ ድጋፍ ፣ትምህርት፣ ልማት እንጂ ጦርነት አልነበረም።ጦርነትን ላለፉት 50 ዓመታት በሚታይም በማይታይም መልኩ ኖረውታል። ልጆቻቸውን ለጦርነት ገብረዋል።ጧሪ ቀባሪ አጥተዋል። የጁንታው አኗኗሪ ሆነዋል ይሄ ኃላፊነት የማይሰማው ቡድን ግን ለይስሙላ ስለሰብዓዊ ድጋፍ በአንድ በኩል እያወራ በሌላ በኩል ህዝቡን እያሰቃየ ነው።

እንደሚታወቀው አሸባሪው ቡድኑ ከሞተ ቆይቷል። እሱ የሞተው በህግ ማስከበሩ ወቅት ነው። አብዛኞቹ መሪዎቹ ተደምስሰዋል፤ ቀሪዎቹ በህግ ጥላ ስር ሲሆኑ ትርፍራፊዎቹ የተካኑበትን ሴራ ቀጥለዋል፤ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እያናፈሱ የውጪውን ዓለምና የትግራይን ተወላጆች በማደናገር ተጠምደዋል። አዎን! ቡድኑ ከሞተ ቆይቷል። የቀረው ግብዓተ መሬቱ ነው። አሁን የሚንቀሳቀሰው በደጋፊዎቻቸው ምዕራባውያንና አውሮፓውያኑ እስትንፋስ ነው። ሰው ሰራሽ እስትንፋስ ደግሞ ወቅታዊ እንጂ ዘላቂ ህልውና አይኖረውም። ምንግዜም አሸናፊው ህዝብ ነው። ሀቅ ነው። እውነትን የያዘ፣ ለሀገሩ ልማትና ብልጽግና የቆመ፣ በአንድነቱ የጠነከረ ህዝብ ነው። ይሄን ደግሞ ደጋግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ አስመስክሯል።

የተናጠል የተኩስ አቁሙ የተደረገው ለትግራይ ህዝብ ሲባል ነው።ጭር ሲል አልወድም የሚለው ቡድን ህዝቡ የሰላም አየር እንዳይተነፍስ ፣ከተረጂነት እንዳይወጣ ዳግም በጦርነት እንዲታመስ ፈርዶበታል። ይሁን እንጂ አሁንም መንግሥት የአንድ ወገን የተኩስ አቁሙን አክብሮ ለጸብ አጫሪው ቡድን ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል። ለዚህም ሁሉም ህዝብ ዝግጁ መሆኑን ደግሞ ደጋግሞ በተግባር አረጋግጧል።

አሸባሪው ህወሓት ለሰላም የተዘረጋ እጆችን እንደ ሽንፈት ቆጥሮ በተደጋጋሚ ጊዜ ዕድሉን አኮላሽቷል። አሁንም ለሀገራችን ነቀርሳ ሆኖ ቀጥሏል። በአማራ እና በአፋር ክልል ላይ እያካሄደ ያለው ጥቃትም የዚህ አንዱ ማሳያ ነው። ይሄ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ስር የሰደደ ቶሎ የማይድን በሽታ በመሆኑ ይሄንን በሽታ ከነሰንኮፉ መንቀል እና እንዳይመለስ አድርጎ አርቆ መቅበር ይገባል። ይሄ የሚሆነው ዛሬም እንደ ትናንቱ አለንልሽ በምንላት የኢትዮጵያ ልጆች ብቻ ነው።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም

Recommended For You