ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት የጽናትና የይቻላል መንፈሳችን ውጤታማነት ማሳያ ነው!

የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የጀመርነው “በይቻላል መንፈስ” እንደምንጨርሰው ተስፋ በማድረግ ብቻ ሳይሆን ከፍ ባለ ሀገራዊ ቁርጠኝነትም ጭምር ነው። ግንባታው በዘመናት ትውልዶች ሲመኙት የነበረውን የአባይን ወንዝ መግራትና ሀገራዊ ፋይዳ እንዲኖረው የማስቻል መሻትን እውን በማድረግ ኃላፊነትን መወጣትን ያካተተ የትውልዶች ተልዕኮ ጭምር ነው።

በርግጥ የግድቡ ግንባታ ይዞት ሊመጣ የሚችለው ሀገራዊ ተግዳሮት ቀላል እንደማይሆን ከማንም ይልቅ ለመላው ህዝባችን ግልጽ የነበረ የአደባባይ እውነታ ነው። በግንባታው ሂደት የታየውም የህዝባችን ሁለንተናዊ ንቃትና ተሳትፎ ከዚሁ እውነታ የመነጨ፣ ከዚህም በላይ ለጽናትና የይቻላል የተሀድሶ መንፈስ ግንባታ መሰረት የሚጥል የአዲስ ታሪክ ጅማሬ ነው።

ለዘመናት የአባይ ወንዝ የእኔና የእኔ ብቻ ነው ከምትለው ግብጽ ጀምሮ በሷ የተዛቡ ትርክቶች ሰለባ በሚሆኑ ሀገራት እና ኃይሎች በኩል ከፍ ያሉ ተግዳሮቶች እንደሚጠብቁን፤ እንደጠበቅነውም እንዳጋጠሙንና አሁንም እየተፈታተኑን ስለመሆኑ መናገር አዲስ እውነት አይደለም። በቀደሙት ዘመናት ጭምር ጥላ ሆኖ ሲከተለን የነበረ ፤ እንደሀገር ብዙ ዋጋ ሲያስከፍለን የኖረ ነውና።

በአንድ በኩል ኢትዮጵያውያን ሰላም ካገኙ የውሃ ሀብታቸውን ይጠቀማሉ፤ በዚህም የወንዙን ውሃ ያለ ከልካይ የመጠቀም መብታችን አደጋ ውስጥ ይገባል በሚል፤ ከዚያም በላይ ኢትዮጵያውያን የውሃ ሀብታቸውን መጠቀም ከጀመሩ መነሳት ይሆንላቸዋል ይህም አካባቢያዊና አለም አቀፋዊ የፖለቲካ አሰላለፍ መጣረዝ ያመጣል በሚል ስጋት ሃገርን እንደ ሀገር እስከ ማፍረስ የዘለቁ ሴራዎች ታቅድዋል፤ተተግብረዋል፤ እየተተገበሩም ነው።

ዛሬም ቢሆን ሀገርና ህዝብ ዋጋ እያስከፈሉ ካሉ የባንዳ የግጭት ተልዕኮዎችም ሆነ ሀገር ከማፍረስ እኩይ ተግባራት በስተጀርባ ያለው እውነታ የአባይን ወንዝ ያለ ከልካይ የመጠቀም ጊዜ ያለፈበት መሻት የፈጠራቸው ሴራዎች ናቸው። እነዚህን ሴራዎች ለማክሸፍ እየከፈልነው ያለውም ዋጋ በአንድም ይሁን በሌላ እንደ ጀመርነው እንጨርሰዋለን ብለን ከተነሳንበት ቁርጠኝነት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደሀገርም ሆነ እንደ ህዝብ በየትኛውም ዘመን ድንበር ተሻግረን የሌላውን ሀገርም ሆነ ህዝብ ጥቅም አደጋ ውስጥ የሚከት ስጋት ፈጥረን አናውቅም። ትልቁ ታሪካችን የሚያጠነጥነውም አትንኩን፤ አትድረሱብን በሚለው የነጻነት ተጋድሎ ላይ ነው። በፍትሃዊነትና እውነት ላይ የተመሰረተ ነበርና በአትንኩኝ ባይነታችን ያደረግናቸው የተጋድሎ ታሪኮችም ለብዙዎች የተጻነት ጮራን ፈንጥቀዋል። የሚታይና የሚጨበጥ ሕያው ተሞክሮ ሆነውም አገልግለዋል።

ዛሬ ላይም ቢሆን የታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመገንባት ስንነሳ በወንዙ ውሃ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብታችንን የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ባደረገ የአስተሳሰብ መሰረት ላይ ቆመን እንደሆነ ገና ከጅምሩ ለመላው ዓለም በአደባባይ አሳውቀናል። ከዚሁ የጋራ ተጠቃሚነት መሰረት ላይ ቆመን መሰረቱ በሚፈቅደው፤ ከሚፈቅደውም በላይ ተጉዘን ዓላማችንን ዓለም እንዲረዳው ሞክረናል፤ ዛሬ ላይ ደግሞ በተጨባጭ ማሳየት ችለናል።

የቀደሙት የለውጥ ሀዋሪያ የሆኑ አፍሪካውያን አባቶቻችን በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ለአፍሪካና ለህዝቦቿ ትንሳኤ በጋራ መደጋገፍና መደማመጥ ወሳኝ መሆኑን ሰብከዋል፤ እጣ ፈንታችንን የሚወስኑት በቀደመው የቅኝ ገዥዎች መንፈስ ላይ ቆመው የተገነቡ አስተሳሰቦች ሳይሆኑ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተው አዲሱ አፍሪካዊ አስተሳሰብ እንደሆነም አመላክተው አልፈዋል።

እኛ አፍሪካውያን ይህንን እውነታ በአግባቡ ማጤን ባለመቻላችን በብዙ ሴራዎች ተጠላልፈን በተቀደደልን የግጭት ቦይ በመፍሰስ ላለፉት 60 ዓመታት ከፍያለ ዋጋ ለመክፈል ተገደናል። ከድህነት ወደ ከፋ ድህነት፤ ከጉስቁልና ወደ ከፋ ጉስቁልና፤ ከግጭትም ማቆሚያ ወዳጡ ግጭቶች ገብተናል። ለዚህም ብዙ ዋጋ ከፍለናል፤ እየከፈልንም ነው።

የታላቁ ህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከሁሉም በላይ የአለመተማመንና የግጭት ምንጭ የሆኑ ቅኝ ገዥዎች ለእነሱና ለእነሱ ብቻ ያስቀመጧቸው ስምምነቶች ትርጉም አልባ መሆናቸውን በማሳየት በአስተሳሰቡ የታሰሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን አእምሮዎችን ነጻ በማውጣት የይቻላልን መንፈስ የሚያጎናጽፍና ከግጭት ወደ ትብብር ማሻገር የሚያስችል፤ አፍሪካውያን የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ አዲስ የተስፋ ሕልም እንዲያልሙ የሚረዳ ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገርና ህዝብ የፓን አፍሪካኒዝምን አስተሳሰብ መሰረትን ከጣሉ ህዝቦች በዋነኛነት የምንጠቀስ እንደመሆናችን መጠን ፤ ከወንድም የአፍሪካ ህዝቦች ጋር የሚኖረን የትኛውም አይነት ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብራችን የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ነው። ይህም እጣ ፈንታችን ከአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ጋር የተሳሰረ ነው ከሚል የአስተሳሰብ መሰረት የሚነሳ ነው።

ዛሬም የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ ማከናወናችንን ለመላው ዓለም ስንገልጽ እውነታው ግድብ ላይ ውሃ ከመሙላት ባለፈ ባልተገቡ አስተሳሰቦች በአለመተማመንና በስጋት ውስጥ ያሉ አፍሪካውያን ነጻ የሚወጡበትና በጋራ ተጠቃሚነት ችግሮችን የሚፈቱበት ጊዜ በተጨባጭ እየቀረበ መሆኑን የሚያመላክት ነው!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2013

Recommended For You