መነሳሳትን የፈጠረው የክልሉ የማእድን ዘርፍ

አስናቀ ፀጋዬ

የከበሩና ከፊል የከበሩ እንዲሁም ለኮንስትራክሽንና ለኢንዱስትሪ ግብአትነት የሚውሉ ማእድናት በስፋት ከሚገኙባቸው ክልሎች አንዱ የአማራ ክልል ነው። በዚህ ክልል በተለይ ወርቅና ኦፓል ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ዋነኛ ማእድናት ሲሆኑ ሌሎች ለኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ግብአትነት የሚውሉ ማእድናት በአብዛኛው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ይውላሉ።

በበጀት ዓመቱ የማእድን ዘርፉ በተለይ በወርቅ የወጪ ንግድ የታየው አፈፃፀም ከፍተኛ ሲሆን ክልሉም ለብሄራዊ ባንክ ወርቅ በማቅረብ ለአፈፃፀሙ ከፍተኛነት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል ። ጥሬና እሴት የተጨመረባቸው ኦፓል ማእድናትን ለገበያ በማቅረብም ለውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል። ክልሉ ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ በማቅረብ ከእቅዱ በላይ የፈፀመ ቢሆንም ከሌሎች የክልሉ ማእድን ዘርፍ ጋር በተያያዘ በጋጠሙ የተለያዩ ችግሮች ምክንያት ዝቅተኛ አፈፃፀም አሳይቷል።

የአማራ ክልል የማእድን ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይታየው ተስፋሁን እንደሚገልፁት፤ በ2013 በጀት ዓመት ክልሉ ከአጠቃላይ የማእድን ዘርፍ ማለትም ከፍቃድ እና አስተዳደር፣ ከሮያሊት፣ከመሬት ኪራይና ከልዩ ልዩ 100 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 63 ሚሊዮን 104 ሺህ 39 ብር ሰብስቧል። ይህም ከእቅድ አኳያ አፈፃፀሙ ዝቅተኛ ነው። የመስሪያ ቤቱ አደረጃጀት በክልል ላይ የተንጠለጠለ መሆን፣ የኮቪድ ወረርሽኝና የእቅዱ መለጠጥ ደግሞ ለአፈፃፀሙ ዝቅተኛነት አስተዋፅኦ አድርጓል። ይሁንና እቅዱ ከአምናው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በግማሽ እድገት አሳይቷል።

ከሥራ እድል ፈጠራ አኳያ በበጀት ዓመቱ በክልሉ በማእድን ዘርፍ 43 ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ የነበረ ሲሆን ለ32 ሺህ 707 ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። የእቅዱን ሰባ አምስት ከመቶ ያህሉን ማሳካትም ተችሏል። ይሁንና ከተያዘው እቅድ አኳያ የዚህም አፈፃፀም ዝቅተኛ ነው። አፈፃፀሙ ዝቅተኛ ሊሆን የቻለውም አብዛኛዎቹ ፍቃድ የተሰጣቸው የማእድን አውጪዎች በቶሎ ወደ ሥራ ባለመግባታቸው ነው።

በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ 4 ሺህ 694 ነጥብ 06 ኪሎ ግራም ጥሬ ኦፓል እና 130 ነጥብ 775 ኪሎ ግራም እሴት የተጨመረበት ኦፓል ለውጭ ገበያ በማቅረብ 3ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል። የተገኘው ገቢ ከተያዘው የ4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ እቅድ አኳያ ሲታይ ግን ዝቀተኛ ነው። በተለይ ምርቱ በሚመረትበት አካባቢ የገበያ ማእከል አለመኖር ለአፈፃፀሙ ዝቅተኛነት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል። ከዚህ ባሻገር የኮቪድ ወረርሽኝና የኮንትሮባንድ ንግድ ለአፈፃፀሙ ዝቅተኛነት የጎላ ድርሻ ይዘዋል ። ምርቱ በተገቢው መንገድ ቢመረትና በተለይ የኮንትሮባንድ ንግዱ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ቢደረግ ከዚህም ማእድን ዘርፍ የተሻለ ገቢ ማግኘት ይቻል ነበር።

አቶ ይታየው እንደሚገልፁት፤ ከወርቅ ጋር በተያያዘ የአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ 5 ኪሎግራም ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ለማቅረብ አቅዶ የነበረ ቢሆንም ከያዘው እቅድ በላይ 7 ኪሎግራም ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ማቅረብ ችሏል። ይህም በወርቅ ማእድን የወጪ ንግድ ለተገኘው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። ወደ አንድ ማእከላዊ ገበያ ከመቅረብ ይልቅ በተበታተነ መልኩ ማእድኑ ለገበያ መቅረቡ ነው እንጂ ከዚህም በላይ መጠን ያለው ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ማቅረብ ይቻል ነበር።

ኤጀንሲው ባለፈው በጀት ዓመት ለ 2 ሺህ 512 የማእድን ማምረት እና ምርመራ ፈቃዶች የሰጠ ሲሆን እነዚህም 32 በከፍተኛ ኮንስትራክሽን ማዕድን ማምረት፣ 7 በአነስተኛ የኢንዱስትሪ ማዕድን ማምረት ፣ 77 በአነስተኛ ኮንስትራክሽን ማዕድን ማምረት ፣ 150 የተለያዩ ማዕድናትን መመርመር ፣ 2191 በባህላዊ ማዕድን ማምረት ፣ 19 የከበሩ ማዕድናት ዕደ ጥበብ (ላፒደሪ) እንዲሁም 33 ነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች ችርቻሮ ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው። ከዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ፍቃድ ወስደው በሥራ ላይ የሚገኙ ሲሆን አርባ አንዱ ከሁለት ዓመት በላይ ሆኗቸው ወደ ሥራው ባለመግባታቸው ከክልሉ ማኔጅመንቱ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል።

የበጀት ዓመቱ የክልሉ የማእድን ዘርፍ አፈፃፀም ከአምናው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ችግሮች እንዳሉ ሆነው በተለይ ከማእድን ፍቃድ አሰጣጥና ከገቢ ጋር በተያያዘ መልካም እንቅስቃሴ የታየበት ነው። በርካታ ባለሃብቶችም በማእድን ማምረት ሥራ ፍቃድ ወስደው ወደ ሥራ ገብተዋል። በተለይ ከግራናይት ማእድን ጋር በተያያዘ በርካታ አምራቾች ወደ ሥራ በመግባታቸው ከውጪ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት አስችሏል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም

Recommended For You