የዋጋ ግሽበቱን ማረጋጋት – የአዲሱ መንግሥት የቤት ሥራ

ሰላማዊት ውቤ

የኑሮ ውድነቱ በየዕለቱ ተባብሶ ቀጥሏል። ጠዋት የተገዛ ዕቃ ከሰዓት ዋጋ ይጨምራል። አሁን አሁን ደግሞ በሰዓታት ዋጋ ወደ መጨመር ተገብቷል።ከደቂቃዎች በፊት 20 ብር የተገዛ የፍጆታ ዕቃ በ30 ደቂቃ ውስጥ 40 ብር ገብቶ ይገኛል።በየጊዜው የዋጋው ማሸቀቡ ምክንያት በውል ግልጽም አይደለም።

የሕዝብ ብዛትና የፍጆታ አቅርቦት መጣጣም አለመቻል ፣አምና በተወሰኑ አካባቢዎች በነበረ ግጭት ምርት አለመመረት፣ የነጋዴና ደላሎች አሻጥር ፣ ሸማቹ አብዝቶ በመሸመት ማከማቸት የሚለውን በተደጋጋሚ የሚሰሙ ምክንያቶች ናቸው። ይሁን እንጂ ሸማቹ ይህን ምክንያት መስማቱ ብዙም ትርጉም የለውም።ቸርቻሪው የጨመረው ጅምላ አከፋፋዩ ጨምሮ በመግዛቱ መሆኑን ሲናገር ማድመጡም ተለምዷል።ለምን ጨመረብህ ቢባል ያመጣበት ጨምሮ ሸጦለት የመሆኑን ምክንያት ማድመጡ ያሰለቻል። ሆኖም አሁን ላይ ችግሩ በመባባሱ ሸማቹ መንግሥት መፍትሄ ይስጠን ወደማለቱ ገብቷል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም ለኑሮ ውድነቱ መፍትሄ የሚያመጣው አዲሱ የሚመሰረተው መንግሥት መሆን እንዳለበት ይናገራሉ።

በዓለም አቀፍ የዕድገት ማዕከል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስት ዶክተር ቴዎድሮስ መኮንን እንደሚሉት አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበትን በዘላቂነት የማረጋጋቱን የቤት ሥራ መውሰድ አለበት።ወስዶም ችግሩን እኔነት በተላበሰ የባለቤትነት መንፈስ መፍታት ይጠበቅበታል ።ትኩረቱን የዋጋ ንረቱን ለማስተካከል በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ የሚደረጉ ሥራዎች ላይ ማድረጉም እንዲሁ የመንግሥት ድርሻ ነው ብለው ያምናሉ።

ዋነኛው የገንዘብ ልቀቱን መጠነኛ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ነው። ወጪዎቻችን ምንድናቸው፣ ምን ላይ ነው የሚወጡት የሚለውን በትክክል ማየት ይኖርበታል።ከዚሁ ጋር የባንክ ስርዓታችን ምን ይመስላል የሚለውንም መፈተሽ ያስፈልገዋል።በተጨማሪም የገበያ ስርዓትን ጠለቅ ብሎ ተመልክቶ ማስተካከል ያለባቸውን ማስተካከል ይጠይቃል። ይሄ ለሚመሰረተው መንግሥት ትልቅ የቤት ሥራ ይሆናል።

የዋጋ ግሽበትን በዘላቂነት ለማረጋጋት ወደ ገበያ በሚለቀቀው የገንዘብ መጠን ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን ይገባል። በገበያ ስርዓት ላይ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልገዋል። የፋይናንስ ዘርፉም እያስመዘገበ ያለው ዕድገት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ማድረግም ይኖርበታል ።እንዲሁም ይላሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ፤ለኢንቨስትመንት የሚያቀርበውንም ብድር ማሳደግ ይጠበቅበታል።

የዋጋ ማስተካከያ በመደረጉ ምክንያት ብዙ ወርቅ መሸጥ መቻሉ መዘንጋት የለበትም ። በመሆኑም በሌሎቹም በወርቅም የውጪ ንግድን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በሚፈለገው መጠን ለማሳካት ምርታማነትን ማሳደግ ግድ ነው ባይ ናቸው። ነገር ግን በመሰረታዊነት የውጪ ንግዳችን (ኮታችንን) ሊያሳድግ የሚችለው ምርትና ምርታማነትን አብዝቶ በማሳደግ እንደሆነም ዶክተር ቴዎድሮስ ያሰምሩበታል።

ምርታማነት ደግሞ ተወዳዳሪ እንድንሆን ያስችለናል።መገንዘብ ያለብን ተወዳዳሪ ካልሆንን መሸጥ አለመቻላችንን ነው። ለክስረትም የምንዳረግበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።በመሆኑም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ጉዳይ ላይ ሳያሰልሱ ቀን ከሌት መትጋት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ።

በቅርቡ ወርቅ ላይ እንደተደረገው ማሻሻያ ሌላውንም በማስተካከል የተሻለ ነገር ማምጣት ይቻላል።በ2014 ዓ.ም ደግሞ ቡና፣ ሰሊጥ፣ኑግ፣ተልባና ሌሎች የቅባት እህሎች በአግባቡ ክፍተቱን በመሸፈን የተሻለ አፈፃፀም ይኖራል ብለው ያምናሉ።

የኢትዮጵያ ዕዳ ጫና ከጥቅል ሀገራዊ ምርት አንፃር ያለው ድርሻ አሁን ጤናማ የሚባል ደረጃ ላይ ነው ይላሉ ።ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከውጭ የሚገኘውንም ጥቅም በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል አስፈላጊ መሆኑን ይመክራሉ። በተቻለ መጠን የገበያ የወለድ መጠን የሌለው ዓይነት ብድር መውሰድ የሚበረታታ እንደሆነ ነው የሚጠቁሙት።እንዲህ ዓይነት ብድር መውሰድና የምናገኘውን ብድር በትክክል ቦታው ላይ መዋሉን ማረጋገጥ ተገቢም መሆኑን አበክረው ያስረዳሉ ።

የተወሰደው ብድር ኢንቨስትመንት ላይ የሚውል ከሆነ ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኝ እንደሚችልም ይጠቅሳሉ። ይሄ የሚያስገኘው ጥቅም በቀላሉ የሚታይና የሚናቅ እንዳልሆነ ይናገራሉ።እጅግ ትልቅ ፋይዳ አለውም ባይ ናቸው።

የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ቴዎድሮስ እንዳብራሩት፤ የተወሰደው ብድር ኢንቨስትመንት ላይ የሚውል ከሆነ ሀገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ትሆናለች።በተጠቀመች ቁጥር ደግሞ ብድሯን የመክፈል አቅሟ በእጅጉ ይጨምራል። የብድር ተጠቃሚነቷ በተሻለ ደረጃ ያድጋል። ሆኖም በከፍተኛ ደረጃ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ መኖሩ መዘንጋት እንደሌለበትም ያሳስባሉ ።ይሄውም የምንበደረውን ገንዘብ በትክክል መጠቀማችንን ማረጋገጥ መቻል ነው።ዓላማችን የዋጋ ግሽበትን በዘላቂነት ማረጋጋት ከሆነ የምንበደረውን ገንዘብ በትክክል መጠቀም ወሳኝ ነው። ይሄን ሁሉ የማድረግ ኃላፊነት ደግሞ አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ኃላፊነት ይሆናል።

መንግሥት ሁሉንም ነገር ብቻውን ሊያሳካው አይችልም ። ሸማቹ፣ ነጋዴው ፣ ባለሀብቱ ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት በሙሉ እገዛን የሚፈልግ መሆኑ ከግንዛቤ መግባት አለበት። የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት በመሆኑ ሌሎቹን አካላት ከማስተባበር በዘለለ በጉዳዩ ዙሪያ ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን መውሰድና ውሳኔዎችን ማሳለፍም ይጠይቀዋል ። መልካም ንባብ!

በዓለም አቀፍ የዕድገት ማዕከል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስት ዶክተር ቴዎድሮስ መኮንን

አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም

Recommended For You