ከእውቅና ውጪ የሚደረግ የመማር ማስተማር ሂደት ትልቁ ሣንካ!!

ዳንኤል ዘነበ

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአንድ ሀገር ውስጥ የተማረን ዜጋ ከማፍራት ባሻገር የሚፈጠሩ ልዩ ልዩ ችግሮችንና ማነቆዎችን መፍቻ የዕውቀት በሮች ቁልፍ እንደሆኑ ይታመናል። የአንድ ሀገር ጥንካሬም ሆነ ድክመት የሚመሠረተው በእነዚሁ ተቋማት ድክመትና ጥንካሬ ላይ ይወሰናል። ይህን ሀገራችንም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለማስፋፋት ትኩረት ሰጥታ ስትሰራ ቆይታለች።

በተለይ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ልዩ ትኩረት በመስጠት ከመንግሥት ባሻገር በግሉ ዘርፍ ትውልድ ተሻጋሪ ሥራ ተሰርቷል። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሃገር ሁለንተናዊ ዕድገት ጉልበት እንደመሆናቸው ተቋማቱን ቁጥራቸውን ለማሳደግ የተሰራውን ተግባር አወድሰን፣ ከትምህርት ጥራት አኳያ የተፈፀመውን ሀገርና ትውልድ ገዳዩን ትልቁን ስህተት መመልከት የግድ ይላል። ስለዚህ በተለይ ደግሞ የግሉ ዘርፍ በመነጠል እንመልከት።

በ1987 ዓ.ም በሀገራችን የወጣው አዲሱ የትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲ ተከትሎ፣ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቁጥራቸው እንደበዛ መረጃዎች አሉ። በአሁኑ ወቅትም በሀገራችን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር 278 መድረሱን የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ መረጃ ይነግረናል። እነዚህ ተቋማትም በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በየዓመቱ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያስመርቃሉ።

በግሉ ዘርፍ በዚህ ደረጃ የተማረ ዜጋ የመፍጠር አቅም መኖሩ እንደ ስኬት የምንቆጥረው ቢሆንም፤ ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ የሚታዩና የሚሰሙ ችግሮች ትልቅ ሥጋት የሚፈጥሩ ናቸው። በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚሰሙት ተቋማቱ ለሀገር ዕድገት ከሚጫወቱት ሚና ይልቅ የሀገርን ውድቀት የሚያፋጥኑ ሲሆኑ ታዝበናል። የተቋማቱ እንዝህላልነት ከቀን ቀን እየጨመረ በመሄድ ለተማሪ እውቀትን ለመሸጥ መቋቋማቸውን እስከመዘንጋት ደርሰዋል።

በተደጋጋሚ ሲነገር እንደተመለከትነው በተለይ እውቅና እና ፈቃድ ሣይኖራቸው፣ የእውቅና ፈቃድ መመሪያን በመጣስ ከሕግ ውጪ በሆነ መንገድ የሚያስተምሩ በርካቶች መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል።

የትምህርት ማስረጃን ሱቅ ውስጥ እንደሚገኝ ሸቀጥ ማንም ገዝቶ በእጁ እንዲያስገባ የሚያደርጉ ሀገር ገዳይ ተቋማት እንዲበዙ ሆኗል። በመንግሥት በኩል ሣይቀር የችግሩን ሥር መስደድ በማመን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ነበር። የችግሩ አሳሳቢነት ዛሬም ጉዳይ ሆኖ መነሳቱም የበለጠ ቁጥጥር ማድረግ የሚገባ መሆኑን ይነግረናል።

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 ተግባርና ኃላፊነት የተሰጠው እንደመሆኑ ኤጀንሲው ራሱን ሊፈትሽ የሚገባው ስለመሆኑ ያመላክተናል። ኤጀንሲው ተቋማቱ የእውቅና ፈቃድ ያላቸው መሆኑን፣ የእውቅና ፈቃድ ዕድሣት በተሰጠበት የትምህርት መስክ እና ካምፓስ ብቻ ተማሪዎችን ተቀብለው እያስተማሩ መሆኑን በየጊዜው የማረጋገጥ ሥራን ይጠይቃል። የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከእውቅና ውጪ የሚደረግ የመማር ማስተማር ሂደት ትልቅ ሣንካ መሆኑን በማመን፤ ከባለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በልዩ ትኩረት እየሰራ ስለመሆኑ ለመረዳት ችለናል። ኤጀንሲው የተለያዩ ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተቋማቱን መቆጣጠር እና መከታተል የሚያስችል ሥርዐት ዘርግቷል። በእርሱ በኩል እነዚህና መሰል ማሻሻያዎችን በመደረጉ ብቻ ውጤት ማምጣት እንደማይቻል አስታውቋል። በመሆኑም የእውቅና ፈቃድ መመሪያን የሚጥሱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መከላከል የሚቻለው ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት ሲችል እንደሆነ አሳስቧል።

ኤጀንሲው ከሰሞኑ በማህበራዊ ገጹ ባወጣው መረጃ እንዳብራራው፤ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የሕግ ጥሰት የሚፈፅሙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሥርዓት የማስያዝ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። ይኼንኑ ተግባሩንም አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። ነገር ግን ይህ ጥረቱ ደግሞ ፍሬያማ እንዲሆን ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ ቀጣሪና የሙያ ፍቃድ የሚሰጡ ድርጅቶች እና መላው ህብረተሰብ እገዛ የግድ ይላል።

ማንኛውም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በከፍተኛ ትምህርት በመረጠው የትምህርት መስክ ደረጃና መርሃ-ግብር ለማስተማር ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የእውቅና ፈቃድ ሊሰጠው ወይም ተሰጥቶት የነበረው እውቅና ፈቃድ ሊታደስለት የሚገባ መሆኑን ይገልጻል። ነገር ግን በርካታ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሕግ ውጪ በሆነ መንገድ የሚሰሩ እና የእውቅና ፈቃድ መመሪያን በመጣስ ሕገ ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ መሆኑን አስታውቋል።

ኤጀንሲው ለአብነት ያህል ሲገልጽ፤ የእውቅና ፈቃድ ባልተሰጣቸው ካምፓስ ተማሪ መዝግበው በማስተማር ፈቃድ ባገኙበት ለሌላ ካምፓስ አስተምረው ለማስመረቅ የሚጥሩ፣ በርቀት ትምህርትም ተማሪ መዝግቦ የሚቻለው የእውቅና ፈቃድ በተሰጠባቸው ቢሆንም፣ እውቅና ባልተሰጣቸው ማዕከላት የሚያስተምሩ፣ በበይነ-መረብ የከፍተኛ የትምህርት የእውቅና ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ መሠረት ተገምግሞ በኤጀንሲው የእውቅና ፈቃድ ከተሰጣቸው በስተቀር ሣይፈቀድላቸው የተፈቀደላቸው በማስመሰል በበይነ -መረብ ትምህርት (online learning) ለመስጠት ራሣቸውን የሚያስተዋውቁ በርካታ ተቋማት መኖራቸውን ኤጀንሲው አመልክቷል።

የእውቅና ፈቃድ መመሪያን የሚጥሱ ተቋማትን የመከላከሉን ሥራ በጋራ መከላከል ከተቻለ ውጤት ማምጣት የሚቻል መሆኑን የሚገልፀው ኤጀንሲው በመሆኑም ሁሉም ህብረተሰብ እንዲህና መሰል ሕገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ ተቋማትን ሥርዐት ለማስያዝ በሚደረግ ጥረት የመሣተፍ እና የጥፋቱ ሰለባ ከመሆን ቅድመ ጥንቃቄ ሊያደርግ የሚገባ መሆኑን አስታውቋል። በተለይ በቅድመ-ምረቃ እና በድህረ-ምረቃ መርሃ-ግብር ለመማር ከመመዝገብዎ በፊት ተቋሙ በየትኛው ካምፓስ በምን ዓይነት የትምህርት መስኮች የእውቅና ፈቃድ እንደተሰጠው እና የእያንዳንዱ ትምህርት መስክ የእውቅና ፈቃድ ስለመታደሱ ሊያረጋግጡ የሚገባ መሆኑን አስታውቋል።

አክሎም፤ “የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከማንኛውም ሀገር በቀልና ከውጭ ሀገር የግል ድርጅቶች ጋር ሣይፈቀድላቸው የትብብር ሥልጠና መስጠት አይችሉም። በመሆኑም ተማሪዎች ከመመዝገባቸው በፊት ከኤጀንሲው ያገኘውን የእውቅና ፈቃድ ደብዳቤ ተቋሙን ጠይቀው በማየት የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው። ተቋሙም ትክክለኛውን የእውቅና ፈቃድ ደብዳቤ ለተጠቃሚው ማሳየት የሚኖርባቸው ሲሆን፤ ተቋማት በማሳየት ግዴታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል። ስለዚህ ከሕግ ውጪ ተመዝግበው ለሚማሩ ኃላፊነቱ የተማሪው እና የተቋሙ ብቻ ነው” ሲል አስታውቋል።

እንደ ኤጀንሲው ማብራሪያ፤ አንድ ተቋም ተማሪ ለመቀበል በተለያዩ መንገዶች ራሱን ሊያስተዋውቅ ይችላል፤ ኤጀንሲው በፈቀደለት የእውቅና ፈቃድ መሠረት የሚያስተዋውቅ ይኖራል፤ በተቃራኒው ደግሞ ፈቃድ ሣይሰጠው የተሰጠው በማስመሰል በመገናኛ ብዙሃን ወይም በሌላ ራሱን በማስተዋወቅ የዜጎችን ገንዘብ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚቀበሉ አሉ። በመሆኑም ተቋሙ በቴሌቪዥን፣ በራዲዮ ወይም በበራሪ ወረቀት ራሱን ስላስተዋወቀ ብቻ የእውቅና ፈቃድ ወይም የእውቅና ፈቃድ ዕድሣት ማግኘቱን አያረጋግጥም።

የተቋሙን ማስታወቂያ እንደ መረጃ መውሰድ እንችላለን፤ ነገር ግን እንደማስረጃ የሚያገለግለን ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የተሰጠውን የእውቅና ፈቃድ ደብዳቤ በተጨባጭ ማየት ሲቻል ብቻ ነው። “በመሆኑም ይህን ማድረግ ሲቻል ተቋሙ በየትኛው ካምፓስ በምን ዓይነት የትምህርት መስክ እስከ መቼ ድረስ ፈቃድ ተፈቀደለት? ለሚለው ጥያቄ አስተማማኝ ማስረጃ ማግኘት የሚቻለው።

ለዚህም ነው በተደጋጋሚ የሚነገረው፤ ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ለተቋማት የተሰጣቸውን የእውቅና ፈቃድ ደብዳቤ ተቋማቱ እንዲያሳዩን እናድርግ፤ ለዚያ ካምፓስ የተፈቀዱለትን የትምህርት መስኮች መኖራቸውን ስናረጋግጥ ብቻ ገንዘባችንን አውጥተን እንመዝገብ፤ ከዚህ ውጪ ይህን ቀላል ኃላፊነታችንን ሣንወጣ ቀርተን ከገንዘባችንም ሆነ ከጊዜያችን ሣንሆን የምንቀረው ለምን? በግለሰብ ደረጃ ያለውን ኃላፊነት መወጣት የዜግነት መገለጫ ነው” ሲል ኤጀንሲው ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም

Recommended For You