የልዩነትን ግንብ ያፈረሰ ግድብ

በአገሪቱ ባለፉት 50 ዓመታት በተፈጠረው የመደብና የፖለቲካ ጭቆና ምክንያት በርካቶች አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል ።በተለይም ባለፉት 29 ዓመትት ዜጎች በብሔርና በቋንቋ ተለይተው በባላንጣነት መንፈስ ሲተገበር በቆየው የፖለቲካ ሴራ ሳቢያ እትብታቸው የተቀበረባትን ምድርና ያፈራቸውን ወገን ርቀው ለመኖር ተገደዋል።ይህ የፖለቲካ ጭቆና በተለይም በውጭ የሚኖረውን ዜጋ የአገሩ ጉዳይ ባይተዋር አድርጎት ቆይቷል ።በሌላ በኩልም አገሪቱ ፈጣሪ በለገሳት ፀጋ ሳይቀር መጠቀም ያለመቻሏና ዜጎቿ ድህነትን ሽሽት ከዓለም ጫፍ ድረስ ይሰደዱበት የነበረውን ሁኔታ በብዙዎች ዘንድ ቁጭት ፈጥሮ ኖሯል።

ይሁንና ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ በተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ ከያሉበት አገር አኩርፈው ተቀምጠው የነበሩ፤ አለፍ ሲልም ከነበረው መንግሥት ጋር በጠላትነት ተፈራርጀው የነበሩ ዜጎች ዳግም የአገራቸውን አፈር መርገጥ የሚችሉበትን እድል ፈጥሯል።በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስክ እኩል ተሳትፎ የሚያደርጉበትም እድል ተመቻቸ።ይህንን ተከትሎ ለወትሮ ‹‹በምን ያገባኛል›› ስሜት ተሸብቦ የኖረው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊም የእኔ የሚላትን አገር ክብር እና ገናናነት ዳግም ለማስመለስ ሲል የራሱን ጠጠር ለመወረር ፈቃደኝነቱን በጉልህ አሳይቷል።

በተለይም የመላው ኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት የሆነውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን ሁሉም ከያለበት የድርሻውን ለማበርከት ደፋ ቀና ብሏል።ከህፃን እስከ አዛውንት በቦንድ ግዢና በስጦታ መልክ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ አለኝታነቱን አስመስክሯል ።በዚህም አላበቃ፤ በግድቡ ላይ የሚነሱ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን በመከላከልም የኢትዮጵያ የቁርጥ ልጅ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ደግሞ ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው መደላደል አማካኝነት ግድቡ ራሱ በመንግሥትና በዲያስፖራው መካከል ያለውን የዘመናት አለመግባባት በማፍረስ ይበልጥ እንዲቀራረቡ ድልድይ መፍጠሩን ይናገራሉ ።በተለይም የግድቡ ግንባታ ላይ የነበሩ ችግሮች እንዲፈቱና የግንባታው ሂደት በፍጥነት እየተጓዘ መምጣቱ ዲያስፖራውን በከፍተኛ መጠን እንዲነቃና በአገሩ ልማት ዋነኛ ተዋናይ እንዲሆን ያደረገው መሆኑን ይገልፃሉ።

 እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ከዚህ ቀደም በዲያስፖራውና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት የባላንጣነት መንፈስ የተላበሰ ነበር ።ሁለቱም ወገኖች በተገናኙበት አጋጣሚ ሁሉ እርስበርስ ከመወቃቀስ ባለፈ ተቀራርበው በመስራት ለአገሪቱ እድገት የየበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከትም ሆነ ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት መደጋገፍ የሚችሉበት እድል እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም ።በተለይም ከነበረው መንግሥት ጋር ተናቦ የመስራት ችግር ነበር ።ተቃውሟቸውን ከመግለፅ በተጨማሪ ድጋፋቸውን በተግባር የሚገልፁበት ሁኔታ አልነበረም።

ይሁንና ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ መንግሥት ራሱንም ሆነ የሚሰራውን ስራ ግልፅ በማድረግ፣ ያሉትን ችግሮችንም ሆነ ምቹ ሁኔታዎች ለዲያስፖራው ማሳወቅ በመቻሉ በመካከላቸው ያለው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ነው የሚያነሱት።‹‹በተለይም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የነበሩ ችግሮችን በግልፅ በመናገርና ሂደቱን እየተከታተለ መረጃ እንዲያገኙ በማድረጉ በመካከላቸው መተማመን እንዲፈጠር አድርጓል›› ሲሉ ይጠቅሳሉ።

‹‹ህዳሴ ግድብ በውጭም ሆነ በውስጥ ያለው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዋጋ የከፈለበት፤ ገንዘቡን ያወጣበት፤ ሞራሉንም ጭምር የገነበባት ነው።ልክ እንደዳግማዊ አድዋ ተደርጎ የሚወሰድ ፕሮጀክት ነው›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ከጫፍ እስከጫፍ ያለ ልዩነት ዜጎችን ያሰባሰበ ግድብ መሆኑ የተለየ እንደሚያደርገው አንስተዋል።ይህም ማንኛውም አስተሳብ ይሁን ልዩነት አለን ብለው ዳርና ዳር የቆሙ ሰዎችን ሳይቀር በአንድ ላይ ተሰብስበው የሚመክሩበት ድጋፋቸውን የሚለግሱበት ሁኔታ መፍጠሩን ያስረዳሉ።ይሄ በራሱ መተዋወቅ ፣ መተባበርን፣ መተሳሰር እንዲኖር ያደረገበት አግባብም በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ነው ያመለከቱት።

 በዋነኝነት ደግሞ ግድቡ በራሱ በመንግስትና በዲያስፖራው መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ እንዲፈርስ ከማድረጉም ባሻገር በተለይም በአገሪቱ ውስጣዊ ጉዳዮች እየደረሱ ያሉትን ዓለምአቀፍ ጫናዎችን በጋራ ለመከላከል እያገዘ መሆኑንም ነው የሚያነሱት ።በአሁኑ ወቅት ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የህዳሴ ግድብም ሆነ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ አለምአቀፍ ጫና ከመቃወም አኳያ ዲያስፖራዎች በጋራ የመቆም፤ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ፤ በጽሑፍ የመግለፅ፤ ሚዲያ ላይ ወጥቶ የመናገር የመሳሰሉትን ሁኔታዎችን በማካሄድ የኢትዮጵያን መብት የማስከበር ፤ የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም የማስጠበቅ ስራዎች ላይ በደንብ እየተሳተፉ መሆናቸውንም ያስረዳሉ።

‹‹ዲያስፖራውን የሚከታተል፤ መረጃ የሚያቀብልና እንደዚሁም በጋራ ከእነሱ ጋር የሚሰራ ፣ ለሚመጡበት ጉዳይም ሁኔታዎችን የሚያመቻችና የሚያስተባበር ኤጀንሲ መቋቋሙ በራሱ ዲያስፖራው በአገሩ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን አድርጎታል›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ መረጃዎችን በወቅቱ እያገኘ እንዲሄድና ከመንግሥት ጋር ተመሳሳይ አቋም እንዲያራምድ በማድረግ ረገድ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ያነሳሉ።ይህም በባለቤትነት መንፈስ በግድቡ ላይ ለሚነሱ አለማቀፍ ጫናዎች ዘብ እንዲቆሙ ማድረጉን ያመለክታሉ።

የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ዲያስፖራው በመንግስት ላይ ያለው ጥርጣሬ እንዲቀረፍ ካድረጉም ባሻገር ዳር ቆሞ ከመመልከት ይልቅ የየራሱን አወንታዊ አስተዋፅዖ እንዲያበርክት ያደረገው መሆኑን ያነሳሉ።ለህፃናት ልጆቻቸውም ቦንድ በመግዛት የአገር ፍቅር ስሜት እንዲያጎለብቱ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ነው የጠቆሙት።

እንደዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ የመጀመሪያው ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌትን ተከትሎ በተፈጠረው መነቃቃት እና በተሰራው ሰፊ የማስተባበር ስራ 200 ሚሊዮን ብር ከዲያስፖራው ለመስበስ ታቅዶ 192 ሚሊዮን 171ሺ ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል። ይህም የእቅዱን 96 በመቶ ማሳካት ያስቻለ ሲሆን ከተሰበሰበው ውስጥ 98 ሚሊዮን 577 ሺ ብር በላይ በስጦታ መልክ አስተዋፅዖ ማበርከት ተደርጓል። ይህም ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።አሁን ደግሞ ሁለተኛውን ሙሌት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከፍተኛ እንቅቃሴ እያደረገ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት በተሻለ ድጋፍ ለማሰባሰበ ከዲያስፖራ ጋር የተቀናጀ ሥራ እየተሰራ ይገኛል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2013

Recommended For You