የዲፕሎማሲ የበላይነት መገለጫ

ኢትዮጵያውያን ስለታላቁ ወንዛቸው አባይ በግጥሙ ፣በአባባሉ፣ በተረቱ ፣ ወዘተ ብዙ ብለዋል። ሁሉም ግን ቁጭቶች የተገለጸባቸው ናቸው። ውሃቸውን፣ አፈራቸውን፣ ከብቶቻቸውን፣ ወዘተ እየጠራረገ እብስ ሲል ከማንጎራጎር የዘለለ ሊያደረጉ የሚችሉት ነገር ለዘመናት አልነበራቸውም።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመር ግን ይህን ምእራፍ ዘግቶታል። ግድቡ የአባይ ወንዝ ጉዳይ ለዘመናት ሲያብከነክናቸው ለኖሩት ኢትዮጵያውያን ትልቅ የምስራች ይዞ ነው የመጣው። ግድቡ ከቁጭት ወጥተው ወንዛቸውን ወደሚያለሙበት ከዚያም ተጠቃሚ ወደሚሆኑበት ሁኔታ ወሳኝ ታሪካዊ ምእራፍ አሸጋግሯቸዋል።

የግንባታው መጀመር ወንዛቸው እራት እና መብራት ይዞላቸው ሊመጣ መሆኑን አበሰራቸው። ልማታቸውን ሊያሳልጥላቸው ከድህነት አረንቋ ስቦ ሊያወጣቸው ሆነ። እናም ግንባታው እንዲሳለጥ ከአፋቸው ከፍለው ገንዘብ ማዋጣትን፣ የግድቡን ግንባታ ከማናቸውም ጥቃት መጠበቅን፣ በቀጣይ ግድቡ በደለል አሉታዊ ተጽእኖ እንዳይደርስበት ለማድረግ በተፋስስ ልማትና ችግኝ ተከላ ማካሄድን ስራቸው እንዲያደርጉ አረጋቸው። ከአስር አመታት በላይ በዘለቀ ጽናት በእዚህ ዘለቁበት።

ግድቡ ታላቅ ግድብ ነው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ግድቡ 5ሺ250 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ሀይል እንዲያመነጭ ታስቦ ነው ግንባታው የተጀመረው፤ ግንባታውም በ80 ቢሊየን ብር ነው የሚካሄደው። ከፍታው 145 ሜትር ርዝመቱ ደግሞ 1ሺ 800 ሜትር ሲሆን፣ 74 ቢሊየን ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም አለው። ውሃው በአንድ ሺ 680 ስኬዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ ነው። የጣና ሀይቅን እጥፍ ውሃ የመያዝ አቅም አለው። ስለግድቡ ግዝፈት እነዚህ ማሳያ ይሆናሉ።

ኢትዮጵያ ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ (እስካሁን ማለት ነው) እሱን የሚያህል ግድብ አይታም አስባም አታውቅም። በአፍሪካም ይህን ያህል ግድብ የለም፤ በአለም ከሚጠቀሱት መካከልም ነው። ሀገሪቱን ከቁጥቁጥ የኤሌክትሪክ ሀይል ልማት ስራ በወሳኝ መልኩ የሚያወጣ መሆኑ ታምኖበት ነው ወደ ተግባር የተገባው።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በአባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን ቁጭት የሚወጡበት ግድብ ሆኖ ተገኝቷል። ለእዚህም ነው የግድቡ ግንባታ ከተበሰረበት ከመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም አንስቶ እስከ አሁንም ድረስ ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ ድጋፉን እያደረገ ያለው።

የግድቡ ግንባታ እነዚህን በመስራት ብቻ የሚፈጸም አልነበረም። በዲፕሎማሲው መስክም ሰፊ ስራ መስራትን ጠይቋል። ባለፉት ዘመናት ሀገራችን አባይን በመገደብ የኤሌክትሪክ ሀይል ለማልማት ሙከራዎች ብታደርግም በግብጽና ወዳጆቿ ረጃጅም እጆች የተነሳ የብድር አገልግሎት ማግኘት ፈታኝ ሆኖባት ኖራለች። በዚህ የተነሳም ይህን ግንባታም ለማካሄድ የወሰነችው በመንግስት አቅምና በህዝብ ተሳትፎ ነው።

ይህ እቅድም ስኬታማ ሆኗል። መንግስት ግድቡን ለመግንባት ከሚያስፈልገው ሀብት 13 ቢሊዮኑን በዜጎች ድጋፍ ቦንድና በመሳሰሉት ለማድረግ አቅዶ እስከ አሁን 15 ቢሊየን ብር ተገኝቷል። ህዝቡ ድጋፉን በስጦታ፣ በቦንድ ግዥ፣ በህዳሴ ዋንጫ ፣ወዘተ ማረጋገጡን አጠናክሮ ቀጥሏል። ህዝቡ ግድቡን በገንዘብ ብቻ በመደገፍ አላቆመም። እንደ አይኑ ብሌን በመጠበቅ ፣ ከደለል ሊጠበቅ የሚችልበትን የተፋሰስ ልማትና የችግኝ ተከላ በማካሄድ በብዙ ቢሊየን ብር የሚገመት ስራ አከናውኗል።

በቀደሙት ዘመናት አባይን በሚያህል ግድብ ላይ ግድብ ለመስራት አይደለም ጥናት ለማካሄድ የውጭ ብድር መፈለግ የግድ ነው። ለግንባታ የውጭ ምንዛሬ በብዛት የሚያስፈልግ እንደመሆኑ አለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማትን ደጅ መጥናት ፣ ከሀገሮች ጋር በትብብር መስራት እና የመሳሰሉት ያስፈልጉ ነበር። ሀገራችን በአባይ ግድብ ለመስራት አይደለም በገባሮቹ ላይ የመስኖና የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫዎችን ለመገንባት ብዙ ፈተናዎች ገጥመዋታል።

ከእነዚህ ፈተናዎች ጀርባ ደግሞ የግብጽና ወዳጆቿ እጆች ሁሌም አሉ። በተለይ የግብጽ እጆች በግልጽም በስውርም ሲሰነዘሩ ፣ በማያገባቸው ስፍራ ሁሉ ዘው ሲሉ ኖረዋል። የግብጽ ድርጊት ተጠናክሮ የቀጠለው ግን ታላቁ የኢትዮጵየ ህዳሴ ግድብ እውን ከሆነ በኋላ ነው። ሱዳን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በግንባታው ተቃውሞ ያልነበራትቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በግብጽ እየተጎተተች ትገኛለች።

ግብጾች የሚናገሩትና የሚያደርጉት ሁሌም የተለያየ ነው። አባይ ኢትዮጵያና ግብጽን እንደ እትብት ሆኖ የሚያገናኝ ነው፤ እትብት እናትና ጽንስን እንደሚያገናኝ ሁሉ አባይ ለኢትዮጵያና ግብጽ አብሮነት ወሳኝ ነው እያሉ የእናቲቱ ኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ውስጥ እንዲገባ ይሰራሉ።

የናይል ውሃ በሙሉ የኛ ነው ብለው በድፍረት ሲናገሩ ምንም ቅር አይላቸውም። ጠብታ ውሃ ከአባይ ላይ ሊነካብን አይገባም ይላሉ፤ አሁንም ይህንኑ ያስተጋባሉ። ግድቡን አብሬ ካላስተዳደርኩ የምትል ደፋር ሀገር ናት። ኢትዮጵያ በውሃው የመልማት መብት አላት፤ የእኛ የውሃ ድርሻ ግን ጠብታ እንኳ መነካት የለበትም እያሉ አሁንም ድረስ ይናገራሉ።

የውሃ ድርሻችን ብለው የሚያስቡት ደግሞ የአባይን ውሃ በሙሉ ነው። የድፍረታቸው ድፍረት አንዳንዴ ኢትዮጵያ በቂ የዝናብ ውሃ አላት አባይን ትልቀቅልን ይላሉ። ከናይል ወንዝ ውሃ 86 ከመቶው ከኢትዮጵያ የሚገኝ ነው። ይህ ውሃ በሙሉ የእኔ ነው የሚል አቋም አላት። ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት የማያነጋግር በሆነበት ሁኔታ ግብጽ ኢትዮጵያን ባላካተተው የቅኝ ግዛት ውል መሰረት የማገኘው ውሃ እንዳይነካ ትላለች።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በአባይ ወንዝ ዙሪያ ሁለት የሁለትዮሽና የቅኝ ግዛት ስምምነቶች አሉ። ከነዚህ መካከል የ1929ኙ በግብፅና በእንግሊዝ (የምሥራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛቶችን በመወከል) መካከል የተደረገው የውሃ ክፍፍል ስምምነት ነው።

በዚህ ስምምነት መሰረት በአባይ ወንዝ ላይ ማንኛውም ዓይነት ግንባታ ሲካሄድ በግብፅ እውቅናና ፈቃድ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። በወቅቱ ኢትዮጵያ ነፃ ሀገር ነበረች። የድርድሩ አካል አልነበረችም። ስምምነቱም እንደማይመለከታት በተለያዩ ጊዜያቶች ስትገልጽ ቆይታለች።

እአአ በ1959 ሌላ ስምምነት በሱዳንና ግብጽ መካከል ተደርጓል። ሱዳን እና ግብጽ ነጻነታቸውን ካገኙ በኋላ የተፈራረሙት ስምምነት ነው። ስምምነቱም የአባይን ወንዝ ሁለቱ ሀገራት አሟጠው ለመጠቀም የተፈራረሙት ነው። ግብፅና ሱዳን ለወንዙ 86 በመቶ የምታበረክተውን ኢትዮጵያ ወደ ጎን በመተው ያደረጉት ስምምነት ነው። ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የትኛውም አጀንዳ ሲነሳ ይዛቸው የምትነሳው እነዚህን ስምምነቶች ነው።

የናይል ወንዝ የውሃ መጠን የሚለካው በግብጹ አስዋን ግደብ ውሃ የመያዝ መጠን ነው። በዚህ ግድብ ልኬት መሰረት የናይል ውሃ 84 ቢሊየን ሜትር ኩብ ነው። ኢትዮጵያን ባላከተተው የ1959 ስምምነታቸው መሰረት ግብጽ ከዚህ ውሃ 55ነጥብ 5 በመቶውን ትወስዳለች፤ ሱዳን ደግሞ 18 ነጥብ 5 በመቶው ይሰጣታል። ቀሪው 10 በመቶ ለትነት በሚል ተይዟል። ኢትዮጵያ ባዶ። ግብጽ የውሃ ድርሻዬ መነካት የለበትም የምትለው ይህ ስምምነት እንዲጠበቅ በመፈለግ ነው።

በእነዚህ ያረጁ ያፈጁ ስምምነቶች ላይ ቆማ ነው እንግዲህ የኢትዮጵያን በአባይ ወንዝ የመልማት ጥረት ጥያቄ ውስጥ በመክተት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግንባታ እንቅልፍ የነሳት። የተንኮላቸው ብዛት የግድቡ ግንባታ ገና በተጀመረበት ወቅት የግብጽ አርሶ አደሮች መስኖ ቦዮች ደረቁ እያሉ ያላዝኑም ነበር። አሁንም ከዚያ ባልተለየ መልኩ የኢትዮጵያን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንደግፋለን ጠብታ ውሃ ግን እንዲቀርብን አንፈቅድም ይላሉ።

ኢትዮጵያ የታችኛው የተፋሰሱን ሀገሮች በተለይ ግብጽን ለማሳመን ብዙ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ሰርታለች። ግድቡን የምትገነባው የኤሌክትሪክ ሀይል ለማመንጨት ብቻ መሆኑን ደጋግማ አስረድታለች። ውሃው ሀይል አመንጭቶ ጉዞውን ወደ ታችኞቹ ተፋሰስ ሀገሮች ያደርጋል። ግብጾቹም ይህን አያውቁም አይባልም።

ኢትዮጵያ ግድቧን እየገነባች ግንባታ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር እንደሚያደርግ ምንም ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት እንደሌለ ስታስገነዝብ ቆይታለች። በመንግስት ደረጃም በግንባታው ዙሪያ በርካታ ውይይቶች ተካሂደዋል። መሪዎቹ በግብጽ በኢትዮጵያም እየተገናኙ በጉዳዩ ላይ መክረዋል። ይህ ብቻም አይደለም በተለያዩ አጋጣሚዎች በውጪ ሀገሮች ሲገናኙም በመሪም በሚኒስትሮች ደረጃም ተወያይተዋል። ውይይቶቹ በተለይ በግብጽ ሳቢያ ሲቋረጡ የነበሩ በሶስትዮሽ ደረጃ ሲካሄዱ የነበሩ ድርድሮችና ውይይቶች እንዲቀጥሉ አድርገዋል።

የግብጽ የሕዝብ ዲፕሎማሲ ቡድን ግንባታው በተጀመረበት አመት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በዚህ ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶታል። ኢትዮጵያ ውሃ እንዳታስጠማን ሲሉ ስጋታቸውን በወቅቱ መግለጻቸውን አስታወሳለሁ። በዚህ በኩል ምንም አይነት ስጋት እንደሌለ በወቅቱ ተገልጾላቸዋል። የኢትዮጵየ የህዝብ ዲፕሎማሲ ቡድንም በተመሳሳይ ወደ ግብጽ በሄደ ጊዜም ለማስረዳት ተሰርቷል።

ግድቡ ጠቀሜታው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለግርጌው ሀገሮች ግብጽና ሱዳን የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተለይም ሀገሮቻቸውንና ዜጎቻቸውን ከጎርፍ እንደሚጠብቅ ለማስረዳት ተሞክሯል። ግብጾች ግን ይህ ሁሉ እየተደረገም ስለ ቅኝ ግዛት ስምምነት ነው የሚያወሩት።

ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል። ይህ እንዲሆን ግን አሁንም ድረስ የማትረግጠው ስፍራ የለም። አለም ባንክ፣ አሜሪካ፣ አውሮፓ ህብረት ፣ አረብ ሊግ ፣ወዘተ እግሯ እስከሚነቃ ተመላልሳለች። የኢትዮጵያ አቋም ግን አንድና አንድ ሆኖ ዘልቋል። መፍትሄው ያለው አፍሪካ ውስጥ መሆኑን አስታውቃ በአፍሪካ በሚካሄደው ድርድር ላይ ቆማ እየተጠበቀች ትገኛለች።

እነሱ ግን የአቋም ለውጥ ማድረግ ሲገባቸው በየጊዜው አዳዲስ ሀሳብ እያነሱ ግንባታውን እንዲጓተት እንዲስተጓጎል ለማድረግ ሞክረዋል። ኢትዮጵያ ግን በሚያነሷቸው ስጋቶች ላይ በቂ ማብራሪያ በመስጠት ግንባታውን ቀጥላለች። የሶስቱ ሀገሮች የቴክኒክ ኮሚቴ ፣ ተደራዳሪዎች ላለፉት አስር አመታት በግድቡ ውሃ አያያዝና አለቃቅ ላይ በርካታ ድርድሮችንና ስብሰባዎችን አድርገዋል። በቴክኒክ ኮሚቴው በኩል ብዙ የተከናወኑ ነገሮችም አሉ። ድርድሩ ግን አንዴ እየተቋረጠ ሌላ ጊዜ እየቀጠለ አሁንም ድረስ አለ።

ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል ስምምነት ተደርሶም ድርድሮች ሲካሄዱ ቆይተዋል። ከዚህ ድርድርም አንዴ ግብጽ ሌላ ጊዜ ሱዳን ራሳቸውን እያገለሉ ጉዳዩ እንዳለ አለ።

በዚህ መሀል ግን ግብጾች የማይረግጡበት ቦታ አልነበረም። ከአመት በፊት ድርድሩ በአሜሪካ ታዛቢነት ካልተካሄደ ብላ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ በተገኙበት መካሄድ ጀምሮ ነበር። አሜሪካ ከታዛቢነት ሚናዋ እየወጣች ላደራድር እያለች በማስቸገሯ ኢትዮጵያ አካሄዱ ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽ ከድርድሩ ራሷን ያገለለችበት ሁኔታም ይታወሳል።

በቅርቡ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን እንዲመለከተው በሚል እነ ግብጽ ለጸጥታው ምክር ቤት አቅርበውት ነበር። ኢትዮጵያ በዚህ መድረክ ላይ በመገኘትም ጉዳዩ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት የሚያመጣው ምንም ነገር እንደሌለ በመጥቀስ የልማት ጉዳይ ጸጥታው ምክር ቤት ሲቀርብ ይህ የመጀመሪያው መሆኑን በመግለጽ አስረድታለች። በዚህ ላይ በመመስረትም ምክር ቤቱ ጉዳይ እዚያው በተጀመረበት የአፍሪካ ህብረት መድረክ እንዲካሄድ የምክር ቤቱ አባላት መግባባት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በግድቡ ድርድር ጉዳይ ያላት አቋም የጸና ነው፤ እንደ ግብጽ እና ሱዳን ተለዋዋጭ አይደለም። አሁንም ድረስ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው አቋሟ ጸንታለች። ይህ አቋሟ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ውይይት ላይ የተንጸባረቀና አሸናፊ ሆኖ የወጣ ነው። ግድቧን እየገነባች ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን አጠናክራ በመቀጠል አሸናፊ ሆናለች። የግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ሌላው የዲፕሎማሲ ስኬቱ መገለጫ መንገድ ነው። ግንባታ ቆሞ እንደራደር ይባል የነበረበትን ሁኔታ ማስታወስ ይገባል። ወደ ተመድ የጸጥታው ምክር ቤት የተሄደውም ግድቡን የጸጥታ ስጋት አድርገው በመውሰዳቸው መሆኑ ይታወቃል። ኢትዮጵያ የልማት ጉዳይ የፀጥታ ጉዳይ ሆኖ አያውቅም ብላ ማስረዳቷን ተከትሎ ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ህብረት መድረክ እንዲመለስ የምክር ቤቱ አባላት መግባባት ላይ ደርሰዋል።

አሳሪ ስምምነት ላይ እስከምንደርስ ድረስ ግንባታ ይቁምልን ብለው ተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቢሄዱም አልተሳካላቸውም። የግድቡ ግንባታም ቀጥሏል። መቀጠል ብቻም አይደለም የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትም ትናንት ተጠናቅቋል። ከዚህ በላይ የዲፕሎማሲ ድል ከየት ይገኛል። ግድባችን የዲፕሎማሲ የበላይነት መገለጫችን ልንለውም እንችላለን።

ኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2013

Recommended For You