‹‹የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ይቻላልን ያሳየ የኢትዮጵያውያንን የመልማት ተስፋ ያለመለመ ነው›› ፕሮፌሰር አደም ካሚል የአረብ አገራትንና የመካከለኛውን ምስራቅ ጂኦ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ተንታኝ

አዲስ አበባ፡- የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ይቻላልን ያሳየ የኢትዮጵያውያንን የመልማት ተስፋ ያለመለመ መሆኑን ፕሮፌሰር አደም ካሚል ገለጹ። ለሕዝበ ሙስሊሙ እንኳን አደረሳችሁ፤ መላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

 የአረብ አገራትንና የመካከለኛውን ምስራቅ ጂኦ ፖለቲካ እንቅስቃሴ በመተንተንና ስለህዳሴ ግድቡ በመሞገት የሚታወቁት ፕሮፌሰር አደም በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ይቻላልን ያሳየ የኢትዮጵያውያንን የመልማት ተስፋ ያለመለመ ነው።

 ግብጾችና ሱዳኖች ግድቡ ህይወት እንዳይኖረው ያልሸረቡት ሴራ የለም። ግብጻውያን በውጭ ዲፕሎማሲው እርዳታና ድጎማ ኢትዮጵያ እንዳታገኝ ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያላንኳኩት በር የለም። ነገር ግን ኢትዮጵያ ይቻላልን በማንገብ እውነትን በመያዝ ሰርታ ማሳየቱዋን አስታውቀዋል።

ግብጾች በግድቡ ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ ምርጫ እንዳይደረግ ከሰኔ 11 እስከ 14 ድረስ ደባ በመሸረብ መንቀሳቀሳቸውን የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ፤ ሳዑዲን በማግባባት ጀኔራል አምሪኮ በሚባል የልዩ ኃይል አዛዥ ኢትዮጵያውያን ካሉበት ታድነው እንዲወጡ ጫና ለማሳደርና ኢትዮጵያን ለማጨናነቅ ሲተጉ እንደነበርም ገልፀዋል።

45 ሺህ በላይ ስደተኞች እንዲወጡ በማድረግ ጫና ለመፍጠር መሞከራቸው አንዱ ማሳያ ነው ያሉት ፕሮፌሰር አደም፤ የሶስት ቀን አራስ ሳይቀር ደሟ ሳይደርቅ እንድትመለስ ማድረጋቸውን አመልክተዋል ።

እውነትን በመያዝ በፀጥታው ምክር ቤት ድርድር በአፍሪካ ህብረት እንዲታይ መደረጉ የድሉ ብስራት ማሳያ መሆን ችሏል ብለዋል።

ግብጾች በተለያዩ መንገዶች ጫና ለማሳደር ጥረት አድርገዋል፣ ለመከፋፈል ያላቀዱትና ያልሰሩት የለም። ነገር ግን ይህን ሁሉ በመቋቋም ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት በማጠናቀቅ ዳግም የአፍሪካ ኩራት ለመሆን እንደበቃን አስታውቀዋል።

‹‹አሁን ሁሉም ሴራ ከሽፎ ግድባችን ሞልቶ ሳየው ደስ ተሰኝቻለሁ›› ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ አሁን ከእኛ የሚጠበቀው አንድነት፣ ሰላምና ህብረት በመፍጠር ከሕገ ወጥ ስደት ለመውጣት በአገር ሰርቶ ለመለወጥ መነሳሳት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ትሰራለች እንጂ ብዙ ጊዜ አታወራም። በዲፕሎማሲው መስክ ከአረብ ሊግ ጀምሮ እስከ አሜሪካ፣ አውሮፓ ድረስ እነሱ ያላንኳኩት በር የለም። ኢትዮጵያ ግን ፀጥ ብላ በራሷና በፈጣሪዋ በመተማመን ስራዋን ሰርታ ማሳካቱዋን ገልጸዋል።

ከአሁን በኋላ እነ ግብጽ ወደ እኛ እጅ ይነሳሉ። ስለሆነም በብሔርና በጎሳ ሳንከፋፈል አንድነታችንንና ህብረታችን ማጠንከር ይገባናል ብለዋል።

ግብጾች አፍሪካዊነታቸውን ክደው አረብነታቸውን በማንፀባረቅ አጀንዳው የአረብና የአፍሪካ ጉዳይ አድርገውት ነበር ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ አሁን ድርድሩም በአፍሪካ ህብረት እንዲካሄድ ስለተደረገ ኢትዮጵያ ኮርታ የምትደራደርበት ቀን እንደሆነ አመልክተዋል።

የእስልምና እምነት ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ ለመስራት፣ በዘመናዊ ግብርና ለማምረት መትጋት ይገባል። በተለይም በመከባበርና በአንድነት ከድህነት መውጣት ይገባል። የሃይማኖት መሪዎችም አርአያ በመሆን ትውልዱን በመልካም መምራት፣ መምከርና ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2013

Recommended For You