ግድቡ ወደ ኃይል ማመንጨት መሸጋገሩን በጉጉት እንደሚጠብቁ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፡- የእያንዳንዱን ኑሮ የሚያሻሽል እንደመሆኑ ግድቡ ወደ ኃይል ማመንጨት መሸጋገርንም በጉጉት እንደሚጠብቁት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ ። ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ እንዳስደሰታቸው ገለጹ።

ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ አስመልክቶ ለዝግጅት ክፍሉ አስተያየት የሰጡት አባ ተክለማርያም ባዩ፣ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የሚያስደስት ነው ።

ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝ ማህበረሰብን ኑሮ የሚያሻሽል፣ ድህነትን የሚያስወግድ፣ በጨለማ የሚኖረውን የህብረተሰብ ክፍል ወደብርሃን የሚያሸጋግር እንደመሆኑ ኃይል ወደ ማመንጨት መሸጋገሩን በታላቅ ጉጉት እንጠብቀዋለን ብለዋል።

በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝ የማህበረሰብ ክፍልን ኑሮ በማሻሻል ብልጽግናን የሚያመጣና ድህነትን የሚያስወግድ፣ በጨለማ የሚኖረውን የህብረተሰብ ክፍል ወደብርሃን የሚያመጣ ግንባታ ነው ያሉት አባ ተክለማሪያም፣በእያንዳንዱ የዕለት ተዕለት እንቅሰቃሴዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በጨመረበት ወቅት የሙሌቱ መጠናቀቅ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

ግድቡ የአክቲቪስቱ፣ የፖለቲከኛው፣ የሃይማኖት መሪዎች ወይም የግለሰብ ሳይሆን አጠቃላይ የኢትዮጵያውያን ነው ሲሉም አመልክተዋል።

ግድቡ ኢኮኖሚ በማሻሻልና እድገትን ከማፋጠን አኳያ የጎላ ሚና አለው ። ከድህነት ለማላቀቅ ከግንባታው ጀምሮ እስካሁን ድረስ ብዙ የሥራ እድል እየፈጠረ የሚገኝና ለወደፊቱም ብዙ የሥራ እድል የመፍጠር አቅም እንዳለውም አመልክተዋል።

የህዳሴ ግድቡን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል ሳይሆን የጋራ ጠላት የሆነውን ድህነትን ለማጥፋት የምንጠቀምበት መሳሪያ ነው ። ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ድጋፌን አላቋርጥም ብለዋል ።

መምህር መሐመድ ብርሃን በበኩላቸው ፣ሁለተኛ ዙር የግድቡ ሙሌት ለወጣቱ ዘርፈ ብዙ የስራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር አመልክተዋል ። ቀጣዩ ትውልድ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲሄድ በማድረግ ጉልህ ሚና ስለአለው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የግድቡ መጠናቀቅ ከማደግ ጋር የተያያዘ ነው ። የፖለቲካ ጨዋታውም ከመጠቀምና ካለመጠቀም ጋር ሳይሆን የአገራችንን የቀጠናውን ተጽዕኖ ፈጣሪነት በመቃወም ነው ብለዋል።

በርካታ ዜጎቻችን በስደት ዓለም ውስጥ በመሆናቸው እየተሰቃዩ ነው ያሉት አቶ መሐመድ፤ የህዳሴ ግድቡ ሲጠናቀቅ በማህበራዊ ረገድም የሰላም ኑሮ ለመኖር እንደሚያስችል ጠቁመዋል። የአባይ ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም አንድ ሆኖ ቀሪውን ሙሌት ለማጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

ተማሪ ትዝታ ግርማ በበኩሏ፣ የኃይል አቅርቦት ተደራሽነት በማሳደግ አንድነትን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው። እንደ አገር ያለውን የኃይል ፍላጎትና አቅርቦት ተደራሽ በማድረግ በገጠር የሚገኙ እናቶችና እህቶች ከኩራዝ ወደ መብራት ተጠቃሚነት እንዲሻገሩ ያደርጋል ብላለች።

በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ከ ICT ቴክኖሎጂ ጋር የተዛመዱ ክህሎት በትምህርት ቤት ለማሳለጥ የኃይል መቆራረጥ እንዲቀንስ በማድረግ፣ የሳይንስ ተማሪዎችም በቤተ ሙከራ ውስጥ የሚሰሩትን ስራዎች እንዲቀላጠፍ በማድረግ ጥቅሙ የላቀ ነው ብላለች ። ኃይል ማመንጫ እስከሚጀምርም የአቅሟን ድጋፍ እንደምታደርግም ገልጻለች ።

በአራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ አካባቢ የወንዶች ፀጉር አስተካካይ አቶ ሰይፈ ሰይድ፣ የውሃ ሙሌቱ መጠናቀቅ ከዚህ በፊት ለስራቸው የሚያስፈልጋቸው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቆራረጥና ችግር በደንበኞቻቸው ላይ የሚደርሰውን እንግልት ይፈታል ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል። ‹‹ለወደፊት ጥሩ ተስፋ አለን እስከሚጠናቀቅ ድረስ በምንችለው አቅም ድረስ ድጋፋችንን እንቀጥላለን›› ብለዋል ።

በንግድ ስራ የሚተዳደሩት የአቶ ሰይፈ ደንበኛ አቶ አበራ ናስር በበኩላቸው የግድቡ ሙሌት ሁለተኛ ዙር መጠናቀቅ ለልጆቻችን የምናስተላልፈው ታሪክ ነው ። በኢኮኖሚው ዘርፍ ለኢንዱስትሪና ለኢንቨስትመንት ዘርፎች የኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን በማሳደግ ለሥራ አጥ ወጣት የሥራ እድል የሚፈጥር እንደሆነ አስታውቀዋል።

ገመቹ ከድርና በሐይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2013

Recommended For You