‹‹ዲጂታል መገናኛዎችን በመጠቀም ህዝብን ከህዝብ ጋር የምናገናኝበት መንገድ መፍጠር ይገባናል››ዶክተር አህመዲን መሐመድ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ

አዲስ አበባ፡- ዲጂታል መገናኛ መንገዶችን በመጠቀም ህዝብ ከህዝብ ጋር የሚገናኝበትን መንገድ መፍጠር እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ አስታወቁ።

ሚኒስትር ዴኤታው የኢትዮጵያ መንግስትና የስድስት ከተሞች የፖርታል ምርቃት መርሃ ግብር ላይ ትናንት እንደገለጹት፤ ዲጂታላይዜሽን መራራቅ ፈጥሮት የነበረውን ተግዳሮት በማስቀረት ብዙ ነገሮችን እያቀለለ ነው።

ለአገልግሎት የበቁት የኢትዮጵያ መንግስት ፖርታሎች፣ የአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ ሃዋሳ፣ አዳማና አርባምንጭ ከተሞች ናቸው።

ዘመኑ የፈጠረልንን ዲጂታል መገናኛ መንገዶች በመጠቀም ህዝብን ከህዝብ ጋር የምናገናኝበትን መንገድ መፍጠር ይገባናል። ከሀገራችን ባለፈ የአገራችን ከተሞች ከሌሎች አገሮች ከተሞች ጋር የሚገናኙበትን መንገድ መፍጠርም አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ቴክኖሎጂ ለኢኮኖሚያዊ እድገት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ የበርካታ አገራትና ታላላቅ ድርጅቶች ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አመልክተው፤ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ወደፊት የሚመጡና የሚያድጉ ከተሞች በባህል፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካራሳቸውን ለሌላው ዓለም ክፍት ያደረጉ ከተሞች እንደሆኑ ጠቁመዋል።

ዲጂታላይዜሽንን አጠናክረን ስንቀጥልና ለቴክኖሎጂ ቅርብ ስንሆን ትልልቅ አቅም ያላቸውን ድርጅቶች በመሳብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን ማሳደግ እንደሚያስችል ተናግረዋል። ከተሞች የራሳቸው ፖርታል እንዲኖራቸው መደረጉ አገራችንን ለተቀረው ዓለም ክፍት የምናደርግበት አንዱ መንገድ ነው ብለዋል።

እንደ ዶክተር አህመዲን ገለጻ፤ ከለውጡ ዘመን ጀምሮ እየተወሰዱ ከሚገኙ እርምጃዎች አንዱ ዲጂታል ኢኮኖሚን አንዱ የስትራቴጂክ እቅድ አድርጎ መንቀሳቀስ ነው። ከተሞቻችን የራሳቸው ፖርታል እንዲኖራቸው መደረጉም አንዱ የዲጂታላይዜሽን አካል ነው።

ፖርታሎቹ ዜጎች አገልግሎት የሚያገኙበትና የሚጠይቁበት፣ የተሟላ መረጃ የሚያገኙበት፣ የውጭ ጎብኚዎች ስለ ከተሞቹና ስለ ኢትዮጵያ በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ፖርታሎቹ ዜጎች ባሉበት ሆነው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የከተማ ፖርታሎቹ ሳይቆራረጡ ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡና በወቅታዊ መረጃዎች የተሞሉ እንዲሆኑ የየከተማዎቹ ኃላፊዎች በትኩረት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

ለየከተሞቹ ባለሙያዎች ፖርታሉን እንዲያስተዳድሩ፣ መረጃ እንዲያከማቹ፣ አዳዲስ ማሻሻያዎችን እንዲጨምሩ፣ አጠቃቀሙን እንዲያውቁ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ስልጠና ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

 ፖርታሎቹ ዜጎች አገልግሎት የሚያገኙበትና የሚጠይቁበት፣ የተሟላ መረጃ የሚያገኙበት፣ የውጭ ጎብኚዎች ስለ ከተሞቹና ስለ ኢትዮጵያ በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውም ገልጸዋል።

 በ10 ዓመቱ እቅድ ማብቂያ ላይ 85 በመቶ የሚሆነውን የመንግስት አገልግሎት በኦንላይን ለማድረግ የታቀደ ሲሆን፤ የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ተጠቃሚዎችንም 60 ሚሊዮን የማድረስ እቅድ እንዳለ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2013

Recommended For You