የቀድሞ የአዲስ አበባ ከንቲባ ዘውዴ ተክሉ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

አዲስ አበባ፣ የአዲስ አበባ ከተማ 22ኛ ከንቲባ የነበሩት ኢንጂነር ዘውዴ ተክሉ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈፀመ።

የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ኢንጂነር ዘውዴ ተክሉ በተወለዱ በ85 ዓመታቸው ነው ባለፈው እሁድ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን ሥርዓተ ቀብራቸውም በትላንትናው እለት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል ።

የከንቲባ ዘውዴ ተክሉ የህይወት ታሪክ እንደሚያስረዳው፤ ከአባታቸው ከባሻ ተክሉ አመኑና ከእናታቸው ከወይዘሮ አስካለ ደገፉ በቀድሞ ሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በሐረር ዙሪያ አውራጃ ኤጀርሳ ጎሮ ወረዳ ገንደጋራ በሚባል አካባቢ መጋቢት 7 ቀን 1926 ዓ.ም ነው የተወለዱት።

በሕፃንነታቸው ወራት የጣሊያን ወራሪ ጦር በምሥራቅ ግንባር በኩል ድንበር ገፍቶ በመምጣቱ ‘የሀገራችንን ድንበር አናስደፍርም!’ ካሉ ኢትዮጵያውያን አንዱ የነበሩት አባታቸው ከሁለት ወንድ ልጆቻቸው ጋር ዘመቱ።

የወገን ጦር በመጨረሻም በተፈታ ጊዜ ብዙዎች ወደየቤታቸው ሲመለሱ ባሻ ተክሉ ግን እስከ መጨረሻው በመዋጋት በድንበር ላይ የተሰዉ ጀግና ናቸው።

ከአባታቸው ህልፈት በኋላ በእናታቸው እንክብካቤ ከሌሎች ወንድሞችና እህቶቻቸው ጋር ከቆዩ በኋላ ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ በእናታቸው በተወሰነው መሠረት ወደ ሐረር ከተማ በመምጣት በቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ፊደል ቆጥረዋል።

በመቀጠልም በከተማዋ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመማር አባታቸው በጦር ሜዳ የወደቁ የባለውለታ አርበኛ ልጅ መሆናቸውን አስመስክረው በአዳሪነት መደበኛ ትምህርት በመከታተል በከፍተኛ ውጤት አጠናቀቁ።

ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ተመድበው ለአራት ዓመት ይሰጥ የነበረውን የሕንጻ ንድፍና የቅየሳ ትምህርት በመከታተል ላይ ሳሉ በግቢው ውስጥ ከነበሩ ምርጥ ተማሪዎች አንዱ በመሆንና በላቀ የትምህርት ውጤት ተመርጠው በኮሌጁ በአዳሪነት እንዲማሩ ተደረገ።

ወጣቱ ዘውዴ በሕንፃ ኮሌጁ የሚሰጠውን ትምህርት በመከታተል ወደማጠናቀቂያ ላይ እንደደረሱ ከዩጎዝላቪያ የነጻ ትምህርት ዕድል በመገኘቱ ለዚህም ከተመረጡት ጥቂት ተማሪዎች አንዱ ሆኑ።

በዩጎዝላቪያም የተመደቡበት የቤልግሬድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ወጣቱ ዘውዴ የሚያዘነብሉበትን በመመለከት በአርክቴክትና በከተማ ፕላን በጣምራ የሚሰጠውን ትምህርት እንዲከታተሉ አደረገ።

በዩጎዝላቪያ ለትምህርት በቆዩባቸው ዘጠኝ ዓመታት በኢትዮጵያና የውጭ ሀገር ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት በመሆን ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ብሮዝቲቶ ጋር የመገናኘት ዕድል አጋጥሟቸዋል።

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩጎዝላቪያን በኦፊሴል በጎበኙበት ወቅትም ለማስተናገድ ችለዋል።“የዘመኑን ዕውቀት ቀስማችሁ እንድታገለግሏት አገራችሁ ትጠብቃችኋለች” ያሉትን ንጉሣዊ ቃል በማክበር በ1961 ዓ.ም ወደ እናት ሀገራቸው በመመለስ በጊዜው የውኃ ሀብት ልማት ሚኒስቴር ይባል በነበረው መሥሪያ ቤት ተመድበው በአርክቴክትነት በኋላም ዋና አርክቴክት ሆነው አገልግለዋል።

በ1965 ዓ.ም አጋማሽ ላይ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ከነበሩት የምህንድስና ባለሙያዎች ውስጥ በሙያ ብቃትና በአገልግሎት ዘመን በሚኒስትሩ በመመረጥ በወቅቱ የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት በዋና መሐንዲስነት እስከ ጥቅምት 1967 ዓ.ም ድረስ ሠርተዋል።

ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው በብሔራዊ ሐብት ልማት ሚኒስቴር አስተዳደር ሥር የመንግሥት ቤቶች ሥራ አስኪያጅነት፤ በመቀጠል በ1968 ዓ.ም በከተማ ልማት እና ቤት ሚኒስቴር የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ድርጅቱን በማቋቋም ለ2 ዓመታት መርተዋል።

በአገር አስተዳደር ሚኒስቴር ሥር የነበሩ 115 የከተማ አስተዳደሮች /አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤትን ጨምሮ/ የከተማ ፕላንና ቦታ አስተዳደር በማደራጀትና መምሪያ ኃላፊ በመሆንም ሠርተዋል።

ከንቲባ ዘውዴ የከተማ ነዋሪዎች ማኅበራት በአዲስ መልክ ለማደራጀት በተደረገው ጥናት በከተማ ፕላኑ አደረጃጀትና አሰራር ረገድ ጉልህ ተሳትፎ አድርገዋል።

ከዚያም በ1973 ዓ.ም በተደረገው 3ኛ ዙር የከተማ ነዋሪዎች ማህበራት ምርጫ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በመሆን እስከ 1981 ዓ.ም አገልግለዋል።

 በግንቦት 1983 ዓ.ም የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ለሁለት ዓመታት በእስር ቆይተው ፍርድ ቤት በመቅረብ በነፃ ተለቀዋል።

ከንቲባ ዘውዴ ተክሉ በጡረታ ላይ በነበሩበት ወቅትም ቢሆን አገርና ወገንን ከማገልገል አልተቆጠቡም። በዚህም መሠረት በ1997 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ፎረም ሲመሰረት የፎረሙ ሰብሳቢ በመሆን እስከ እለተ ሞታቸው አገልግለዋል።

በተጨማሪም የሙስና ወንጀል ለመከታተል የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የግልጽነት (Transparency International) መስራችና አባል በመሆን ሰርተዋል።

ማኅበረሰቡን ለረጅም ጊዜ በማገልገል የሚታወቁት ከንቲባ ዘውዴ ተክሉ ለረጅም ጊዜ በሰሯቸው ማኅበረሰብ ተኮር ተግባራት የ2007 ዓ.ም ዓመታዊ የበጎ ሰው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ከንቲባ ዘውዴ ተክሉ ከወይዘሮ ራሄል ዘውዴ ጋር በመስከረም 1965 ዓ.ም ጋብቻ በመመስረት በትዳር በቆዩባቸው 48 ዓመታት ሦስት ሴት ልጆችንና ስድስት የልጅ ልጆችን ለማየት በቅተዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2013

Recommended For You