ፍትህና እውነት ያሸነፉበት የውሃ ሙሌት

 የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ከትላንት በስቲያ ይፋ ተደርጓል። ይህ ቀን በኢትዮጵውያን ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረ በመሆኑም የብዙዎችን ቀልብ የሳበና አፈጻፀሙም ልብን በሃሴት የሞላ ነው። ምክንያቱም ይህ ቀን እውን እንዳይሆን ለብዙ ጊዜ ከፍተኛ ትግል ነበርና።

ይህ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠለት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ አተካራና ዛቻ ሳይለየው ለአስር አመታት የዘለቀ ነው። ገና ከመነሻ ጀምሮ ኢትዮጵያ ግድቡን እውን ለማድረግ ስትጥር ግብጽና ሱዳን እኛ ሳናውቀውና ሳንፈቅድ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ መስራት መፈለጓ አግባብነት የለውም ከሚለው ሃሳባቸው በተጨማሪ የግድቡን መጀመር አናምንም ያሉበት ሂደት የሚታወስ ነው። በተለይ ከግብጽ ወገን አውሮፓ፣ አረብ አገራትንና ሌሎች ያግዙኛል ብለው ወደሚያስቧቸው አገሮችና ተቋማት ዘንድ እየተዘዋወሩ ኢትዮጵያን የማጠልሸት ሥራ የሰሩት ለኢትዮጵያ እጅግ ከባድ ፈተና ነበር።

ግብጾች በአባይ ላይ ግድብ ጀምሬያለሁ የምትለውን ቀልድ ታቁም የሚለው ዛቻቸው የሀሳባቸው መጀመሪያ ነበር። ለዚህ ደግሞ ለአንድ ጠብታ የናይል ውሃ አንድ ጠብታ ደም እንከፍላለን እስከማለት የደረሱበት ጊዜ የሚታወስ ነው። ከዚህም አልፎ በቅርቡ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጭምር ለግብጽ በመወገን ግብጽ ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች በሚል ፈጽሞ ከዲፕሎማሲና ከዘመናዊ አስተሳሰብ ያፈነገጠ ሃሳብ ማራመዳቸው ግድቡ ምን ያህል በፈተናዎች ታጅቦ ሲካሄድ እንደነበር ማሳያ ነው።

ግብጽና ሱዳን የማደናቀፊያ እቅድ ሲያጥራቸው ግድቡ የተፋሰሱ ሃገራትን ያጠፋል፤ ጥራት የለውም ወደማለትም ገብተውም ነበር። ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ከሶስቱም አገራት እና ከሌሎች ሃገራት የተውጣጡ ባለሙያዎች በስፍራው በመገኘት ጥናት ካደረጉ በኋላ ግድቡ የጥራት ችግር የሌለበት ስለመሆኑ በማረጋገጣቸው ዳግም የመከራከሪያ ሃሳባቸው ከሸፈባቸው። ይህም ያልተሳካላቸው እነዚህ አገራት ወደሌላ ጩኸት ውስጥ እንዲገቡ ሆኑ።

 በመቀጠል ግድቡ አይስፋ ትንሽ ግድብ ይሁን የሚል የመጠን ጥያቄ አነሱ። ነገር ግን ይህም ሀሳባቸው ተቀባይነት አላገኘም። ይበልጥ ኢትዮጵያዊያን ስለ ህዳሴ ግድባቸው በግልጽ መነጋገር ፣ መተረክና መጠየቅ፣ ማወቅና መምከር ሲጀምሩ ቁርጡን በመረዳታቸው ከእነርሱ በላይ ሀይል እንደሚያስፈልግ ተረዱ። ሌሎች እንዲያግዟቸው ጭምር መስራት ጀመሩ።

በዚህ ሂደትም በተለይ ግብፅ መላውን የዓለም ሃገራት በመዞር የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለመኮነንና ኢትዮጵያ ይህንን ፕሮጀክት እንድታቋርጥ ለማድረግ ጥረት አድርጋለች። ከብዙዎችም አዎንታዊ ምላሽ ስታገኝ ከሌሎቹ ደግሞ ብዙም ጆሮ ሳታገኝ ተመልሳለች።

ለግብጾች ጆሮ ሰጥተው በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ከሞከሩ ሃገራት መካከል አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሀብረትና የአረብ ሊግ ይጠቀሳሉ። እነዚህ ሃገራት እና የሃገራት ስብስቦች ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን የምትገነባበትን እውነታ ከስሩ አጥንቶ ፍትሃዊ ፍርድ ከመስጠት ይልቅ ከግብጽ ጋር ባላቸው ፖለቲካዊ ግንኙነት ብቻ ግድቡን ሲኮንኑ መስማት ዓለም ምን ያህል ከፍትህ የተጣላች መሆኗን የሚያሳይ ነው። ሆኖም የወሰኑት ውሳኔ ሄዶ ሄዶ ምን ያህል ፍርደገምድል መሆናቸውን ከማሳየት ውጭ አንዳችም ውጤት አላስገኘም።

በመጨረሻ ጊዜም በዚሁ ጉዳይ ላይ የተሰበሰበው የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩ በዚህ ተቋም መታየት እንደሌለበትና የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩን እንዲታዘበው በመወሰን የግብጽን የብዙ ወቅቶች ሙከራ አክሽፏል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የአስር ዓመታት ፈተና ከውጪው ብቻ ሳይሆን ከውስጥም ጭምር የነበሩበት ነው። ሥራው የህዝብ ገንዘብን የያዘ እስከማይመስል ድረስ ብዙ ችግሮች ተፈጥረውበታል። ትክክለኛ መሳሪያ በተገቢው ጊዜ አቅርቦና ትክክለኛ ሰዎችን መርጦ ማሰራቱ ላይም ሆነ መከታተሉ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እንዝላልነት የታየበት እንደነበር አይካድም። በዚያ ሁኔታ አገርን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል። መጀመሪያ 80 ቢሊዬን ብር ይፈጃል የተባለው ፕሮጀክትም በእጥፍ እንዲጨምር አድርጓል።

እነሆ የለውጡ መንግስት መምጣት ለዚህ ፕሮጀክትም ትልቅ የተስፋ ብርሃን እንዲፈነጥቅ ምክንያት ሆኗል። የለውጡ መንግስት የታላቁ ህዳሴ ግድብን ከወደቀበት አንስቶ ዳግም ነፍስ እንዲዘራ በማድረግ ወደፍጻሜው እንዲጓዝ ማድረግ ችሏል። በዚህ መሰረት ከብዙ የውስጣዊና ውጫዊ ትግሎች በኋላ ግድቡ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በድል ማጠናቀቁ ትልቅ ስኬት ነው። ይህ የውሃ ሙሌት ደግሞ በአንድ በኩል በኣለም ማህበረሰብ ዘንድ ኢትዮጵያ የምትናገረውን ከመፈፀም ወደኋላ የማትል ሃር መሆኗን በተግባር ያሳየችበት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለህዝቦቿ ቃል የገባችበትን ስራ ፈጽሞ ወደኋላ ሳትል መፈጻም እንደምትችል በተግባር ያረጋገጠችበት ነው። ለወደፊትም በኢትዮጵያውያን አንድነትን ካስቀደምን የማይበገር ክንዳችንን እንደምናሳይ እምነት ጥርጥር የለውም። ፍትህና እውነትን ይዘን አሸናፊነታችንን እያረጋገጥን እንጓዛለን።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2013

Recommended For You