በኢንቨስትመንቱ ተሳትፎ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ መደጋገፍን ለመፍጠር

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት ሁለንተናዊ ለውጥን ከማምጣት አንፃር እምብዛም ስኬታማ እንዳልነበር የተለያዩ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልፃሉ።ኢኮኖሚው በበርካታ መዋቅራዊና የዘርፍ ማነቆዎች የተተበተበ በመሆኑ የተገኘውን ዕድገት ዘላቂ አድርጎ ማስቀጠል የማይቻልበት ሁኔታ ፈጠሯል። የገቢ ዕድገት በዋናነት የመነጨው በሀብት ክምችት በመሆኑ አነስተኛ ምርታማነት ታይቷል።

የተለያዩ የምጣኔ ሃብት ምሁራን እንደሚያስረዱት፣ ከሆነም አገሪቱ የኢኮኖሚ ምርታማነት እድገት ማነቆዎች ከመዋቅራዊና ተቋማዊ ድክመቶች የመነጩ ናቸው። የውጭ ምንዛሬ፣ የፋይናንስ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረቶች፣ ፣ውስን የብድር አቅርቦት ከማነቆዎቹ መካከል ተጠቃሽ ሆነው ይቀርባሉ።

ከፍተኛ የመንግስት ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ለማድረግ የተሄደበት መንገድ የዕዳ ጫና ማሳደጉ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ፋይናንስን ለመንግስት የልማት ድርጅቶችና በመንግስት ቅድሚያ ለተሰጣቸው ዘርፎች ብቻ እንዲውል መደረጉ እንዲሁም ፕሮጀክቶችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ማስተዳደር አለመቻሉ የማክሮ-ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትን ማስከተሉ ይነገራል።

የገቢ ዕቃዎች ፍላጎት ሲጨመር፣ የወጪ ንግዱ አፈጻጸሙ ደካማ መሆን የንግድ ሚዛን ጉድለት እንዲሰፋና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲከሰት አድርጓል።ምንም እንኳ የውጭ ብድር ከሀገሪቱ ጠቅላላ ምርት ያለው ድርሻ በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ከፍተኛ ነው ባይባልም የፕሮጅክቶች አፈጻጸም ደካማ መሆን እያሽቆለቆለ ከመጣው ከገቢ ንግድ አፈጻጸም ጋር ተዳምሮ የሀገሪቱን የዕዳ ጫና ሁኔታ ከፍተኛ ስጋት ደረጃ እንዲመደብ አድርጎታል። ከአገር ውስጥ መንግስት በስፋት የወሰደው ብድር የግሉን ዘርፍ የመበደር እድል አጥብቦታል።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ባላት ሃብት ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማግኘት እና የኢንቨስተሮችን ቀልብ ለመቆጣጠር የምትቸገር አይደለችም።ይሁንና የሃብቷን ያህል ተጠቃሚ መሆን ግን አልሆነላትም። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ይዘረዘራሉ።

ከሁሉ በላይ የመንግስት እጅ በኢኮኖሚ ምህዋር በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ውስጥ ከሚገባው በላይ ጠልቆ መግባት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ እና ህልውና በመገዳደር መስጠት የሚገባውን እንዳይሰጥ ምክንያት ሆኖ ታይቷል። የግል ሴክተሩን ኪራይ ሰብሳቢ የሚል ታርጋ ተለጥፎለት፣ቀማኛ እና ሙሰኛ ተብሎ ከተሳትፎው ገሸሽ እንዲል መደረጉም በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ኪሳራ ሲከስት ቆይቷል።

የምጣኔ ሃብት ምሁራን እንደሚያስረዱት ከሆነም የማንኛውም አገር መንግስት ሃላፊነት እና ዋነኛ ግብ ንግድ አይደለም። ህግ እና ስርአት የሰፈነባት የተረጋጋች፣ ለህዝቦቿ የምትመች እና ዲሞክራሲያዊት አገርን መገንባት ብሎም ማስቀጠል ነው።

ይሁንና ባለፉት አመታት በአገሪቱ ኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ውስጥ ከግሉ ዘርፍ ይልቅ የመንግስት እጅና ኢንቨስትመንት በእጅጉ ከፍ ብሎ ታይታል። ይህ የመንግስት ሚና እና ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አቅም መፍጠሩ የማይካድ ቢሆንም የጥቅሙን ያህል ከባድ ጉዳት እና ኪሳራዎችን ማስከተሉም ከማንም የሚሰወር አይደለም። መንግስት በአገሪቱ ኢኮኖሚው ምህዋር ላይ ዋነኛ ተሳታፊ በመሆኑ በተለይም የሚያምናቸው አሊያም የሚፈልጋቸው በልዩ ጥቅም የተሳሰሩ ግለሰቦች እንዲያሳትፍ እድል ፈጥሮለታል።

ይህም አጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በጣት የሚቆጠሩ ባለሃብቶች እንደፈለጉ የሚዘውሩት እንዲሆን አድርጎታል። ከሁሉም በላይ የአገር እድገት ዋነኛ ማነቆ የሆነው ሙስና በከፍተኛ መጠን እንዲያገነግን ምክንያት ሆኖ ታይቷል።

ይህን ምስል ለመቀየር የወሰነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ የሚመራው መንግስትም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ (ሪፎርም) ይፋ አድርጓል። ማሻሻያውም እስካሁን የተገኙ ስኬቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ፣ ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች ለመፍታትና አዳዲስ ዕድሎችን ለመፍጠር ብሎም የፖሊሲና ተቋማዊ ማዕቀፎችን ደረጃ ማሻሻል ታሳቢ በማድረግ የተቀመረ ስለመሆኑ ይነገርለታል።

የማሻሻያው አንዱ አቅጣጫም በአገሪቱ ኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት ውስጥ የመንግስትን እጅ መቀነስና የግሉን ዘርፍ በዋናነት ማሳተፍ የግድ መሆኑ ተመላክቷል። የግሉን ዘርፍ በመዘንጋት የሚገኝ እድገት አይታሰብም ያለው መንግስት የግሉ ዘርፍን በማሳተፍ ፈጣን ድሎችን ለማስመዝገብም የፖሊሲ የሕግና ሌሎችም ማእቀፎች ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።

በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ መካከልም መበላለጥ ሳይሆን መደጋገፍን መፍጠር፣ያለፈውን ማረምና ሳንካዎችን ማስወገድን አላማው አድርጓል። የማሻሻያ የመጨረሻ ግብም ከፍተኛ የስራ እድል መፍጠር ሁሉን አካታች ልማትና ድህነት ቅነሳ መሆኑ ተሰምሮበታል።

የምጣኔ ሃብት ምሁራንም፣ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻው የመንግስትን የተሳትፎ መጠን ከመቀነስ ባሻገር የኢኮኖሚውን ፈተናዎችን ለመሻገርና የግሉ ዘርፍ የተሳትፎ እድገት ለማጎልበት ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ስለመሆኑ ሲያስረዱ ይደመጣል።

ከዚህም ባሻገር የመንግስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አቅጣጫ በተለይ ለግሉ ዘርፍ የተሻለ ትኩረት የሚሰጥና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር በመሆኑም እንደ አገር የተሻለ እድል የሚሰጥና ተወዳዳሪ መሆን እንደሚያስችል ይገልፃሉ።

ከባለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በዋነኝነት የኢንቨስትመንት ከባቢውን የማሻሻል ብሎም አናቂ የሆኑ ህግና አሰራሮችና ማነቆዎችን ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው። በአሁኑ ወቅትም መንግስት ቀደም ሲል ለግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት አይነኬ የሚባሉ ዘርፎች እንዲሁም ዝግ ተደርገው የነበሩ ተሳትፎ በሮችን ክፍት ማደረግ ጀምረዋል። የተለያዩ ዘርፎች ለውጭ እና ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች በሩን ክፍት አድርጓል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የምጣኔ ሃብት ምሁራንም ቀደም ሲል የነበረውን የመንግስት የኢኮኖሚ ምህዋር ተሳትፎ በማስታወስ፣ አሁን ላይ ይህን ለመቀየር እየተከናወኑ ስለሚገኙ ተግባራት አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

የሃረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክ መምህሩ ፍሬዘር ጥላሁን፣ በአንድ አገር ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት የኢንቨስትመንት ተሳትፎ አያስፈልግም ለማለት የማይታሰብ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ በሚባልና ለግሉ ዘርፍ የተሳትፎ እድል በማይሰጥ ብሎም በማያፈናፍን መልኩ በቁጥጥሩ ስር ማዋሉ ግን ኪሳራው የጎላ እንደሆነ ያስረዳሉ።

አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምን ጨምሮ ሌሎችም ግዙፍ አለም አቀፍ ተቋማት መሰል የመንግስት የጎላ ተሳትፎን የማይቀበሉ እና የፕራይቬታይዜሽን አማራጭን የሚያበረታቱ መሆናቸውን የሚያስረዱት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው፣ይህም ሙሉ በሙሉ አልያም በከፊል ተፈፃሚ የሚሆንበት አማራጭ መቀመጡን ያወሳሉ።

‹‹በተለይ አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መንግስት ከንግድ ተሳትፎ እንቅስቃሴ መውጣት አለበት የሚል አቋም ማራመድን ምርጫው ለማድረግ የወሰነበት ምክንያት በዋነኝነት ከአፈፃፀም ብቃትና ከኢኮኖሚ ልማት አንጻር ነው››የሚሉት አቶ ፍሬዘር፣በአገር ኢኮኖሚ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ውስጥ መንግስት ከፍተኛውን ድርሻ በሚወስድበት ወቅት ተፎካካሪነት ውጤታማነት ስለማይኖር ኢኮኖሚው በሚፈለገው መጠን እንደማያድግ ታሳቢ በማድረግ መሆኑንም ያስረዳሉ።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ስትቃኝ በተለይም የቀድሞ መንግስት በከፍተኛ መጠን እጁን ኢኮኖሚ ውስጥ በመንከር አቅራቢ ሆኖ ይሰራ እንደነበርም የሚያስታውሱት አቶ ፍሬዘር፣ በአነስተኛ ወጪ በግል ሴክተሩ መያዝ የሚችሉ ንግዶችን ሳይቀር በመጠቅለል እና ለአገር ኢኮኖሚ ወሳኝ ሚና የላቸውም በሚባሉ ዘርፎች ላይ በመሳተፍ ነጋዴ ወደ መሆኑ በመሸጋገር ሱቅ ከፍቶ መቸርቸር ቀርቶት ነበር። አረቄ እና ሲጋራ ፋብሪካ እንዲሁም ሆቴሎችም ነበሩት።

ይሁንና በግል ዘርፍ መያዝ ሲገባቸው በመንግስት የተያዙ ኢንተርፕራይዝ ኢንቨስትመንቶችም ምንም እንኳን ፋይዳ የላቸውም ለማለት ባያስደፍርም፣ ጉዳትም ግን መጠኑ ከፍ የሚል መሆኑ መዘንጋት እንደሌለበት ያስገነዝባሉ።

ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ በመሆኑም በቀዳሚነት የሃብት አጠቃቀም ጉዳት ማስከተሉን የሚያስታውሱት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ መንግስት ተወዳዳሪ የሌለው በመሆኑ ውጤታማነቱ ዝቅተኛ፣ እንዲሆን አድርጎታል፣የተለያዩ ኢንተርፕ ራይዞች ኪሳራዎችን ሲያስተናግዱም አዋጭ ካልሆኑ አካሄዶችን ከማስተካከል ይልቅ ከመንግስት በጀት ድጎማ በማድረግ ያስቀጥላቸው ነበር››ይላሉ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ኢትዮ ቴሌኮምን የመሳሰሉ በመንግስት እጅ የነበሩ አትራፊ እና ምርታማ ድርጅት እና ኢንቨስትመንቶች መኖራቸው የማይካድ ቢሆኑም የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችም በአንጻሩ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ተጨማሪ የህዝብ ገንዘብ ያስወጡ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ይህ ችግር መሆኑን በመረዳት አሁን ላይ ኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንቱ በመጠንም በአይነትም ሆነ በተሳትፎ መለወጥ አለበት በሚል በመከናወን ላይ የሚገኙ እንቅስቃሴዎች የሚደነቁ እና ተስፋ ሰጪ ሆነው እንደሚታዩ የሚጠቁሙት አቶ ፍሬዘር፣ የፕራቬታይዜሽን ውሳኔም ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ሳይጠቁሙ አያልፉም።

ይሁንና የመንግስት የኢኮኖሚ በተለይም የኢንቨስትመንት ተሳትፎ በመቀነስ ሂደት ግን ፕራይቬታይዝድ ማድረግ ብቻውን በቂ ነው ተብሎ መወሰድ እንደሌለበት አፅንኦት የሚሰጡት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው፣ ‹‹ውጤታማነታቸው በቀጣይ የሚገመገም ቢሆንም አንድን ግዙፍ ድርጅት በግሉ ዘርፍ ማስተላለፍ በተለይ በግለሰብ እንዲያዝ ማድረግ መልሱ ጠቅላይነትን የሚፈጥር በመሆኑ፣ ቁጥራቸውን ከፍ በማድረግ ተወዳዳሪነት የሚመጣባቸውን መንገዶችን ጎን ለጎን ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋልም ነው››ያሉት።

የፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ዋና አስተዳዳሪ እና የምጣኔ ሃብት ምሁሩ አቶ ክቡር ገናም፣በአንድ አገር የመንግስት የኢኮኖሚ ምህዋር ተሳትፎ ይቅር ማለት የማይደፈር ቢሆንም፣ መጠኑ ግን ውስን ሊሆን የሚገባው ስለመሆኑ ይስማሙበታል።

በሌላው አለም የግሉ ዘርፍ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዋነኛ ሞተር ነው ተብሎ ይታመናል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ጠንካራ የሚባል አይደለም የሚሉት አቶ ክቡር፣ የመንግስት ተሳትፎ አስፈላጊ የሚሆንባቸውን በርካታ ዘርፎች ስለመኖራቸውን ያስገነዝባሉ።

ቀደም ባሉት አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስት ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ሆኖ የተስተዋለው የግሉ ዘርፍ የሚፈለገውን ያህል አቅም መፍጠር ባለመቻሉ እንደሆነ የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ጠቅሰው፣ለግሉ ዘርፍ ክፍት ተደርገውም ባለሃብቶች ያልገቡባቸው እንደነበሩ እና ይህም አዋጭ አይደለም በሚል እሳቤ መሆኑንም ይጠቁማሉ።

በአሁኑ ወቅትም የአገሪቱ የኢኮኖሚ አደረጃጀት በዋነኝነት የግሉን ዘርፍ ታሳቢ ያደረገ እና ፕራቬታይዜሽንን የሚደግፍ መሆኑ በኢንቨስትመንቱ ተሳትፎ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ መካከልም መበላለጥ ሳይሆን መደጋገፍን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ደረጃ በደረጃ ሞኖፖሊን የማስቀረት ውሳኔ ወሳኝ የሚባል እርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ይጠቁማሉ።

ይሁንና አሁንም ቢሆን መንግስት ሁሉን ለግሉ ዘርፍ ትቶ መውጣት አለበት የሚለው የሚያዋጣ እንዳልሆነ ነው የሚያሰምሩበት አቶ ክቡር። የግሉን ዘርፍ በማበረታታት ሂደት ፕራይቬታይዜሽንን ከመከተል ባለፈ አዳዲስ ድርጅቶች የመፍጠር ሂደት ላይ የሚስተዋለውን ድክመት ማስተካከል እና ከተገነቡት ባለፈ አዳዲስ ድርጅት ብሎም ኢንቨስትመንቶች ላይ የግሉ ዘርፍ ባለሀብት እንዲያተኩር ማድረግ እንደሚገባም ሳያስገነዝቡ አላለፉም።

 ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ  14/2013

Recommended For You