የሳምባ ምችና ሊወሰዱ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች

ልጆች በክረምት ወራት በወንዞች አካባቢ የሚጫዋዎቱ ሲሆን፤ ይህ ለበሽታ ከማጋለጡ ባለፈ በጎርፍ ሊወሰዱ ስለሚችሉ ልጆች ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ዶክተር ሄኖክ ዘውዱ፣ የሕፃናት ህክምና ስፔሻሊስትና የ“ልጅ በዕድሉ አይደግ መፅሐፍ” ደራሲ መክረዋል።

ዶክተር ሄኖክ እንደሚሉት ከክረምትና ከቀዝቃዜ ጋር ተያይዞ የመተንፈሻ አካላት ህመሞች ይከሰታሉ። ከእነዚህም ዋነኛው የሳንባ ምች ነው። ይህ በሽታ በቫይረስ በባክቴሪያ እንዲሁም በፈንገስ አማካኝነት የሚሰራጭ መሆኑን መክረዋል፡፡

እንደ ዶክተር ሄኖክ ገለጻ ሪስፓይራቶሪ ሲንሲቺአል ቫይረስ ግንባር ቀደም የሳምባ ምች መንስኤ ነው። ሌሎች እንደ ኢንፍሉዬንዛና ፓራ ኢንፍሉዬንዛ ቫይረሶችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ስትሪፕቶኮካል ኒሞኒያ ደግሞ ከባክቴሪዎች ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ ባክቴሪያ የሚከሰተው የሳንባ ምች እጅግ አደገኛና ለአብዛኛዎቹ ከሳንባ ምች ጋር ለተገናኙ ጉዳቶችና ሞት ምክንያት ነው፡፡

ይህን ካልን ዘንዳ ሕፃናትን ለሳንባ ምች አጋላጭ የሆኑ ነገሮች ምን ምን ናቸው? የሚለውን እንመልከት። ሕፃናትን ለሳንባ ምች የሚያጋልጡት አለመከተብ፤ የምግብ እጥረት፤ የቫይታሚን ዲ እጥረት (ሪኬትስ)፤ በቤት ውስጥ ለጭስ መጋለጥ (ቤት ውስጥ ማብሰል በተለይ በከሰል)፤ ተፈጥሯዊ የሳንባ ችግሮች፤ የልብ በሽታ የሰውነት የበሽታ አቅም መከላከል መቀነስ ለምሳሌ በኤች.አይ.ቪ. ኤድስ ምክንያት ናቸው።

ለመሆኑ የሳምባ ምች ምልክቶች ምንድን ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ስመልስ ይላሉ ዶክተሩ፤ የአፍንጫ ፈሳሽ መብዛት፤ ትኩሳት፤የትንፋሽ መፍጠን፤ የትንፋሽ ማጠር፤ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፤ ማቃሰት፤ የደረት ህመም፤ የከንፈር መጥቆር ዋነኞቹ የሳንባ ምች ምልክቶች በመሆናቸው እነዚህን ምልክቶች ያሳየ ሕፃን ቶሎ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ አለበት፡፡

በቤተሰብና በማህበረሰብ ደረጃ የሳምባ ምችን ለመከላከል የሚረዱ ስትራቴጂዎች መከተል እንደሚገባቸው የሚናገሩት ዶክተር ሄኖክ እነዚህም ክትባት ማስከተብ፤ የተመጣጠነ ምግብ ለሕፃናት መስጠት፤ማዕድ ቤት ላይ ብቻ ማብሰል እንዲሁም ጭሳጭስ በቤት ውስጥ አለማጨስ፤ የእንሰሳት መኖሪያን ከሰው መለየት፤ የእጅ ንፅሕናን መጠበቅ፤ ከታመመ ሰው ጋር ንክኪ አለማድረግ ናቸው።

ሳምባ ምች (ኒሞኒያ) ማለት የሳምባችን የታችኛው እና የመጨረሻው ክፍል መቆጣት እና መታመም ነው:: እንደሚታወቀው ሳምባችን ለሰውነታችን ኦክስጅን የሚባለውን ጠቃሚ አየር የምናስገባበት እና ካርቦንዳይኦክሳይድ የሚባለውን የተቃጠለ አየር የምናስወግድበት አካላችን ሲሆን፤ ይህ አካል ደሞ ኒሞኒያ በሚባለው በሽታ ሲጠቃ ሳምባችን ውስጥ ያሉ ህዋሳት በከፍተኛ መጠን ስለሚቆጡ አየር የሚቀያየርበት የሳምባ ቅንጣት አካላት(Alveolus) በፈሳሽ ነገር ይሞላል፤ በዚህም ምክንያት ሰውነታችን በቂ የሆነ ኦክስጅን አያገኝም::

የልጆች ሳምባ እና አየር ቧንቧዎች በደምብ ያልዳበሩ እና ጠባብ ስለሆኑ በቀላሉ ሊዘጉ እና ሊታመሙ ይችላሉ። በወቅቱ ካልታከሙም እስከ ሞት ሊያደርሳቸው ይችላል::

እንደ ዓለም የጤና ድርጅት(WHO) መረጃ መሰረት በ2017 ብቻ በዓለም ላይ 808,694 ዕድሜያቸው ከ 5 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት በሳምባ ምች ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል የሚሉት ዶክተር ሄኖክ፤ ይህም ከአጠቃላይ የልጆች ሞት 15 በመቶውን የሚይዝ መሆኑን እስረድተዋል::

በተለይ ከ 5 ዓመት በታች ያሉ ልጆች ላይ የሳምባ ምች ብዙ ጊዜ መንስኤው ቫይረሶች ሲሆኑ የሚጀምረውም ከጉንፋን መሰል ምልክቶች ነው:: ልጆችን ለሳምባ ምች(ኒሞኒያ) የሚያጋልጡ ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. የላይኛው የትንፋሽ አካላት ኢንፌክሽን ለምሳሌ ጉፋን፤ የቶንሲል ኢንፌክሽን እና የመሳሰሉት

2. ቤት ውስጥ የሚጨሱ ማንኛውም የጭስ ዓይነቶች ለምሳሌ የሲጋራ የከሰል እና የእንጨት ጭሶች በሀገራችን በከፍተኛ መጠን ብዙ ሕፃናትን ለሳምባ ምች እያጋለጣቸው ይገኛል::

3. ዝቅተኛ የበሽታ መከላከል አቅም (በምግብ እጥረት ወይም በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት)

4. በጣም ተጠጋግቶ መኖር እና በቂ የሆነ የአየር ዝውውር በሌለበት ቤት እና አካባቢ መኖር፡፡

5. የሳምባ እና የልብ የአፈጣጠር ችግሮች፡፡

6. የቫይታሚን ዲ እጥረት(ሪኬትስ)፦ በተለይ ፀሐይ በደምብ ያልሞቁ ሕፃናት ለሳምባ ምች ተጋላጭ ናቸው::

እንደ አጠቃላይ የመተንፈሻ ህመሞች ብርድ የሚባል በሽታ ጋር ሲያያዙ እንመለከታለን። ይህ ብርድ የሚባል በሽታ አለ ወይስ የለም ለሚለው ጥያቄ ስናልፍ በዘመናዊ ህክምና ብርድ የሚባል በሽታ ባይኖርም በቀዝቃዛ አየር የሚባባሱ በሽታዎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል አስተሳሰብ እንዳለ ዶክተሩ ያስረዳሉ። ለምሳሌ አንዳንዴ አለርጂ ዓይነቶች በቀዝቃዛ አየር ስመጣ ሳል ሊያመጡ ወይም ሊያባብሱ ይችላሉ::

በተለይም በክረምት ወራት ልጆች ትምህርት ቤት ዝግ በመሆኑ በመኖሪያ አካባቢያቸው በውሃ፣ በጎርፍ የመጫወት ነገር ያሳያሉ። ይህ ደግሞ ሕፃናቱን ለበሽታ ከማጋለጡም በላይ በጎርፍ ሊወሰዱ ስለሚችሉ ወላጆች በኃላፊነት ልጆቻቸውን መጠበቅ የሚገባቸው መሆኑን ዶክተር ሔኖክ አሳስበዋል።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ሐምሌ  29/2013

Recommended For You