“ስለ ኢትዮጵያ ሀገራችን ዛሬ ያሉባትን ችግሮችና ፈተናዎች ሁሉ ተሻግራ ነገ ሌላ ቀን እንደምታይ ያሳየ አልበም ነው”ካሙዙ ካሳ የሙዚቃ አቀናባሪ

ጥበብ ኢትዮጵያን ሰርታለች፤ ጥበብ የኢትዮጵያን የጋራ ህልም አበጅታለች፤ ጥበብ የኢትዮጵያን የጋራ ፈተናዎች ተዋግታለች፤ ጥበብ ከጥንት እስከ ዛሬ ኢትዮጵያ ስለ ኢትዮጵያ እንዳለች አለች።

በተለያዩ ጊዜያትም በርካታ አርቲስቶች ኢትዮጵያን የሚያወድሱ ታሪኳን ባህሏን አልደፈር ባይነቷን የሚያንጸባርቁ ስራዎችን በመስራትም ኖረዋል አሁንም እየሰሩ ነው።በተለይም ኢትዮጵያ በርካታ ወዳጆች ያሏት አገር እንደመሆኗ ብዙ የሚጠሏት፣ እድገት ልምላሜዋ እንቅልፍ የሚነሳቸው፣ መፈራረሷን መበታተኗን ብቻ የሚፈልጉ በሁለት አግሯ ቆማ እንዳያዩዋት የሚመኙ ሃይላት በተነሱባት ጊዜ ጥበብ አገርና ህዝብን አንድ አድርጋ በማሰለፍ ረገድ የተጫወተችው እንዲሁም የምትጫወተው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

በተለይም የእናት ጡት ነካሽ የሆነው የጁንታው ቡድን ከተለያዩ የኢትዮጵያን እድገት ከማይመኙ የውጭ ሃይላት ጋር በማበር የከፈተባትን ጦርነት ለመመከት ህዝቡ በአንድ አፍ ተናጋሪ በአንድ ልብ መካሪ እንዲሆን የሚያስችል በርካታ አንጋፋና ወጣት የጥበብ ሰዎች ድንቅ ኢትዮጵያዊነታቸውን ያሳዩበት አልበም ተዘጋጅቶ ለአድማጭ ከተበረከተ ቀናቶች ተቆጥረዋል፡፡

“ስለ ኢትዮጵያ” በተሰኘው የሙዚቃ አልበም ላይ ከጥንቶቹ የጥበብ ሰዎች ከነ አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ፣ ነዋይ ደበበ፣ ስለሺ ደምሴ፣ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜዎቹ አርቲስት ጸደንያ ገብረማርቆስ፣ ሀሊማ አብዱራሀማን ፣ አብነት አጎናፍርና ቤተልሄም ጌታቸው (ቤቲ ጂ) እንዲሁም ሌሎች ስለ እናት አገራቸው ብለው እውቀታቸውን ጊዜያቸውን እንዲሁም ገንዘባቸውን ሳይቆጥቡ ያለምንም ክፍያ ተሳትፎን በማድረግ አልበሙ ወጥቶ አድማጮች ዘንድ ደርሷል።

በዚህ አልበም የኢትዮጵያ ድንቅ የጥበብ ልጆች ስለ አገራቸው ዘምረዋል፣ ዘክረዋል፣ ፎክረዋል፣ ተንብየዋል፣ ለምነዋል ፣ ኢትዮጵያ ማንም የማይደፍራት መሆኑን አበክረው በመናገርም አስጠንቅቀዋል።በዚህ ስራ ላይ ደግሞ የድምጻውያኑ ልፋት ፍሬ ያፈራ ዘንድ ሙዚቃውን በማቀናበር በኩል በርካታ ስመጥር አቀናባሪዎች ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎን አድርገዋል፡፡

ከነዚህ አቀናባሪዎች መካካል ደግሞ በበርካታ ስራዎቹ የምናውቀው የሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሳ አንዱ ነው።አቀናባሪ ካሙዙ በዚህ “ስለ ኢትዮጵያ” በተሰኘ አልበም ላይ ያለምንም ክፍያ ሁሉንም ሙዚቃዎች በማቀናበር ባለሙያዎችን በማስተባበር ሙያዊ ግዴታውንም ለመወጣት ችሏል፡፡

እኛም የሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሳ “ስለ ኢትዮጵያ” ስለተሰኘው የሙዚቃ አልበም እንዲሁም ጥበብ በአገር ግንባታ ላይ ሊኖራት ስለሚገባው ሚና ቃለ መጠይቅን አድርገንለታል፡፡

አዲስ ዘመን ፦ ስለ ኢትዮጵያ የተሰኘው አዲስ አልበም የስራው መነሻ ሃሳብ ምን ይመስላል?

አቀናባሪ ካሙዙ፦ አገራችን አሁን ሁላችንም እያየን እንዳለነው ያለችበት ሁኔታ እጅግ ፈታኝ ብሎም እርስ በእርሳችን መዋደድና መረዳዳት እንዲሁም በኢትዮጵያዊ ፍጹም ወንድማማችነት አብረን መቆምና ችግሮቻችንን ተጋፍጠን ማለፍ የሚጠይቀን ጊዜ ነው።በተለይም ደግሞ ጥበብ ከጥንትም ጀምሮ በአገር ግንባታ እንዲሁም አገር ችግር ውስጥ ስትሆን ህዝብን አስተባብራና መርታ ችግርን ድል የማድረግ አቅም ያላት በመሆኑ አሁን ላለንበት ችግርም ዘላቂ መፍትሔ እንድናመጣ ጥበብና ጥበበኛው የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ በማሰብ በበጎ ፈቃደኝነት ፍጹም ኢትዮጵያዊ በሆነ ሁኔታ አርቲስቶች ተሰባስበን የሙዚቃ ስራውን ለመስራት ችለናል፡፡

በኢትዮጵያ ያሉ ችግሮች ዘርፈ ብዙና በርካታ ሃሳቦችንን የያዙ በመሆኑ ይህንን ሁኔታ ደግሞ ህዝቡ ሊረዳው የሚችለው በተለይም በሚያከብራቸውና በሚዝናናባቸው የጥበብ ሰዎችና የጥበብ ስራ ነው። ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው ለሚሉ አካላት ስለኢትዮጵያ አልበም ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል።በመሆኑም ስለ ኢትዮጵያ ሀገራችን ዛሬ ያሉባትን ችግሮችና ፈተናዎች ሁሉ ተሻግራ ነገ ሌላ ቀን እንደምታይ ያሳየ አልበም ነው።ለዚህ ደግሞ የህዝቦቿ ትብብርና አንድነት ከምን ጊዜውም በላይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፦ በዚህ ስለ ኢትዮጵያ በተሰኘው አልበም ላይ ምን ያህል አርቲስቶች ተሳተፉ የተሳትፏቸው መጠንስ እንዴት ይገለጻል?

አቀናባሪ ካሙዙ፦ እንግዲህ ይህንን አልበም ለመስራት ብዙ ነገሮች ናቸው መነሻዎቹ።በተለይም ከላይ እንደገለጽኩልሽ ኢትዮጵያ በከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ የምትገኝበት ወቅት ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የውስጥ ጠላቶች ከውጭ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት አገርን ካላፈረስን ብለው ተነስተዋል ከመነሳትም አልፈው አፍራሽ ተግባራትን ያለማቋረጥ እያደረጉ፤ ሰው እየገደሉ ፣ እያፈናቀሉ ፣ ንብረት እያወደሙ በጠቅላላው አገር ወደ አዘቅት እንድትገባ የሚችሉትን ሁሉ እየሞከሩ ይገኛሉ።ነገር ግን እኔ እንደዜጋ ይህንን ተግባር እንዴት ነው አገሬ እንድታልፍ ላደርግ የምችለው ብዬ ሳስብ ወደ አእምሮዬ የመጣው ነገር በሙያዬ አንድ ነገር ማበርከት እንዳለበኝ ነው።በመሆኑም ይህንን ስለ ኢትዮጵያ የተሰኘውን አልበም በመቅረጽ አርቲስቶችን አሰባስቦ ወደ ስራ በማስገባት በኩል የበኩሌን አድርጌያለሁ።እዚህ ላይ ግን ለስራው አውን መሆን ብዙ ዋጋን የከፈሉ አርቲስቶችም አሉ፡፡

በተለይም አንጋፋውና ሁላችንም በስራዎቹ የምናከብረው አቀናባሪ አበጋዝ ክብረወርቅ ፣አቤል ጳውሎስ፣ ሚካኤል ሀይሉ፣ ጊልዶ ካሳ፣ አሌክስ ይለፍ፣ እንዲሁም ፋሲል የሺጥላ እና ሌሎችም ከፍተኛ እገዛና ተሳትፎን ያደረጉ ሲሆን አብዛኛውን የሙዚቃ ስራዎቹን ማቀናበር ግን የእኔ ሃላፊነት ነበር፡፡

አዲስ ዘመን ፦ የሙዚቀኞቹ ፍቃደኝነትና ተሳትፎስ በተለይም የአንጋፋዎቹ እንዴት ይገለጻል?

አቀናባሪ ካሙዙ፦ ዋው! ተሳትፏቸው ፍላጎታቸው በጣም ደስ የሚል ነበር።እዚህ ላይ እነዚህ አንጋፋ ብለን የምንላቸው አርቲስቶቻችን አይተሽ እንደሆን ከዚህ ቀደምም አገር ከእነሱ በምትፈልገው ነገር ሁሉ ደከመን ሰለቸን ወይም ጥቅም እናገኛለን ሳይሉ በሙሉ ልብ ተሳትፎ የሚያደርጉ ናቸው።

ከዚህ ቀደም በነበሩ ጦርነቶች ላይ ግንባር ድረስ በመሄድ ራሱ ሰራዊቱን በብዙ መልኩ አበረታተዋል።በተቻላቸው መጠን በዘፈኖቻቸው ላይ የአገራቸውን ፍቅር የወደፊት ተስፋ የህዝቧን ባህልና እምነት እንዲሁም አብሮነት ሳያንጸባርቁም የቀሩበት ጊዜ የለም፤ ከዚህ የተነሳ አሁንም አገር በዚህ መልኩ በባንዳዎች ተከድታ ችግር ውስጥ ስትወድቅ ግንባር ፈጥረው ጥቅም ሳያሳሳቸው ጊዜያቸውን ጉልበታቸውን እንዲሁም የጥበብ እውቀታቸውን ሳይሳሱ ነው እየሰጡ ያሉት፡፡

ተሳትፏቸውን ብነግርሽም አለማየሁ እሸቴ፣ ጸጋዬ እሸቱ፣ ነዋይ ደበበ፣ ጸደንያ ገብረማርቆስ፣ ሀሊማ አብዱራማን ፣ አለማየሁ ደመቀ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ወጣት አርቲስቶችም የነቃ ተሳትፎን አድርገዋል።በዚህም ሊመሰገኑ ይገባል።ሌሎችም በተመሳሳይ አገራዊ ችግርን በጋራ ለማለፍ የሚያግዙ ስራዎች ላይ የነቃ ተሳትፏቸውን እንዲያደርጉ መንገድ የጠረገም ይመስለኛል፡፡

አዲስ ዘመን ፦ እንደዚህ አይነት በተነሳሽነት የሚሰሩ ስራዎች ትርፍ የማይገኝባቸው ከመሆኑ አንጻር ድምጻውያኑን ማሰባሰብ እንዲሁም ስራውን ስትሰሩ የመደማመጥና የመስማማት ሁኔታውን እንዴት ትገልጸዋለህ?

አቀናባሪ ካሙዙ፦ አዎ ጥሩ ጥያቄ ነው፤ ልክም ነሽ በተነሳሽነት የሚሰሩ ስራዎች ብዙ መሰናክል ያጋጥማቸዋል፤ በዚህ ስራ ላይ ግን ለየት ያለ ነገር የምንግርሽ ስለ ኢትዮጵያ ሲባል ገና ተሳትፎ ለማድረግ ሁሉም ፍቃደኛ ነኝ ብሎ ነው ዝግጁነቱን ያረጋገጠው፡፡

በሚገርም ሁኔታ ስለኢትዮጵያ ማንም ይሁን ማን በአገሩ ጉዳይ ላይ አንድ መሆኑን ያሳየ አልበም ነው።በመሆኑም ስራው በህብረት በፍቅር በአንድነት ስሜት የተሰራ ነው፡፡

አንድ አልበም ለመስራት ብዙ ጊዜ ወጪ የሰው ሃይልና ሌሎችም በርካታ የሚያስፈልጉ ነገሮች አሉ።ነገር ግን በዚህ ስራ ላይ ከፍተኛ የሆነ ህብረትና መተባበር ስላለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁለት አልበምን ለመስራት ችለናል።በጣም እስከ አሁንም ድረስ እየገረመን ያለው ነገር ደግሞ በስራው ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች በሙሉ የነበራቸው ኢትዮጵያዊ ስሜትና ወኔ ነው።እውነት ለመናገር ይህንን ኢትዮጵያዊ አንድነት በሌሎቹም ስራዎቻችን ላይ መድገም ከቻልን አገራችንን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንለውጣታለን የሚልም ከፍተኛ እምነት አለኝ፡፡

አዲስ ዘመን ፦ አልበሙን ለመስራት ምን ያህል ጊዜ ፈጀ ወጪውንስ ማነው የሸፈነው?

አቀናባሪ ካሙዙ፦ አዎ የሚገርመው ነገር በዚህ ነገር ላይ በርካታ ሰዎች የተለያየ አመለካከት ያላቸው ከመሆኑም በላይ ብዙ ነገሮች ይባላሉ፤ ግን ሰዎች እንደሚሉት ወይም እንደሚያስቡት ሳይሆን ለስራው መንግስተም ሆነ ሌሎች አካላት አንድም ወጪ አላወጡም።በአልበሙ ስራ ላይ የተሳተፍን በሙሉ ከኪሳችን እያወጣን ከመስራት በቀር የወጣ ወጪ የለም።ለምሳሌ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች በነጻ ነው የሰሩት፤ ግጥምና ዜማ የሰሩትም በተመሳሳይ ክፍያ አልጠየቁም፤ እኔም ያቀናበርኩት ማንም ምንም ሳይከፍለኝ ለአገሬ በሙያዬ አስተዋጽዖ ማበርከት አለብኝ ብዬ ነው።እዚህ ላይ ምን ልልሽ ፈልጌ ነው፤ ከየትኛውም የመንግስትም ይሁን የፓርቲ አካል ይህንን ስራ እንድንሰራ አምስት ሳንቲም አልተከፈለንም።ሁላችንም ስለ አገራችን ብለን አገራችንን እናድን ነገም ሌላ ቀን እናያለን በማለት የሰራነው ነው፡፡

አርቲስቶች በሙሉ ስለ አገራቸው ፍቅር ብለው ዋጋ ከፍለው ከራሳቸው ኪስ ወጪ እያወጡ ምግባቸውን ትራንስፖርታቸውን እየቻሉ የሰሩት ነው።ሌላው የሚገርመው ነገር ደግሞ ይህ አልበም ለገበያ ከበቃም በኋላ ቢሆን ገቢው ሙሉ በሙሉ ለአገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እንዲሆን ስለተወሰነ በቀጣይም አገርን ከመርዳት የዘለለ ጥቅም እንደማይገኝበት እናውቃለን፡፡

ያለን ነገር ጥበብ ነው፤ በጥበብ ደግሞ የደከመን ማበርታት ችግር ውስጥ የገባን ማዳን ብሎም የአገርና አንድነትና የህዝቦች ወንድማማችነት ማጠናከር ስለሚቻል እኛም ያለንን እንሰንዝር በማለት በደስተኝነትና በሙሉ ፍቃደኝነት የሰራነው ስራ ነው።ይህ ደግሞ ከጥቅምም በላይ ነው።ምክንያቱም ሰው ሰርቶ መጠቀም ባገኘው ገንዘብ ራሱንና ቤተሰቡን መምራት በጠቅላላው መኖር የሚቻለው አገር ሰላም ውላ ስታድር በመሆኑ አገራችን አሁን ላይ ደግሞ ይህ ሰላም ውሎ የማደር ሁኔታዋ በመጠኑም ቢሆን እየተናጋ ስለሆነ ይህ የቀደመ ሰላሟን አብሮነቷና ገናናነቷ ይመለስ ዘንድ እኛም የጥበብ ሰዎች በዚህ ላይ የራሳችንን አሻራ እንዳኖርን ይሰማኛል፡፡

አዲስ ዘመን ፦ ከዚህ ቀደምም ሀገር በተመሳሰይ ችግር ውስጥ ስትወድቅ የጥበብ ሰዎች ሰብሰብ ብለውም እንዲሁም በተናጠል አገርን ከችግር ለማውጣት ህዝብን አስተባብሮ ለተቃጣው ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ጥበብን እንደ መሳሪያ ይጠቀሙ ነበርና አሁን በዚህ ዘመንም ተመሳሳይ ተግባር እየተፈጸመ ነው ፤ እንደው ያንና ይኼንን ስታነጻጽረው ምን ይሰማሃል?

አቀናባሪ ካሙዙ፦ አዎ፤ ከዚህ ቀደም በርካታ ጊዜያት ላይ አገርን የሚገልጹ ስራዎች ሲሰሩ ነበር፤ በዚህም በርካታ የጥበብ ሰዎች ተሳትፎን አድርገዋል።ለምሳሌ በደርግ ጊዜ ማንኛውም አርቲስት (ሙዚቀኛ) ስለ እናት አገሩ እንዲዘፍን የሚደረገው እራሱ ፈልጎ አስቦበት ተዘጋጅቶበት ወይንም ደግሞ ያስፈልጋል ብሎ አምኖበት ሳይሆን ሌሎች ስራዎቹ እንዲያልፉ የግድ አንድ ዘፈን ስለ አገር መዘፈን አለበት ተብሎ ስለሚገደድ ነበር።በእርግጥ ይህም ቢሆን ኢትዮጵያዊ ሁሉ አገሩን ወዳድ በመሆኑ በተለይም ደግሞ የጥበብ ሰዎች ስለ አገራችው በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስቡና የሚጨነቁ በመሆናቸው ግዳጅም ቢሆን ጥሩ ጥሩ ዘመን ተሻጋሪ የአገር ፍቅርን የሚጨምሩ ልብን ሞቅ አድርገው ወኔ ውስጥ የሚከቱ ስራዎችን አበርክተውልናል፡፡

የአሁኑ ትውልድ በተለይም ከ30 ዓመት ወዲህ ያለውን ስናይ ያን ያህል አገርን የሚያወድሱም ሆነ ህዝብን በአንድነት የሚያነሳሳ ስራዎች በብዛት ተሰርተዋል ብዬ አላስብም።አሁን እኛ በሰራነው ልክ ደግሞ በአንድነትና ለየት ባለ የአገር ፍቅር ስሜት 28 ዘፈኖች በተለያየ መንገድ አገርን የሚያንብጸባርቅ ስራ አልተሰራም።ስራውም በተለይም ከዚህ በኋላ ላሉ በርካታ ዓመታት ማንም ስለ ኢትዮጵያ ሲናገር ማጀቢያ አድርጎ እንዲያቀርበው ሆኖ የተሰራ ነው።በመሆኑም ይህ ትውልድ ወይንም ደግሞ በዚህ ስለ ኢትዮጵያ በተሰኘው አልበም ላይ ተሳትፎ ያደረጉ ሁሉ ከፍተኛ የሆነ ምስጋናና አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን፦ እንደዚህ ዓይነት ስራዎች በምን ያህል ትውልድን ያንፃሉ፤ የታለመውን ግብ ከመምታት አንጻርስ ያላቸው አቅም እንዴት ይገለጻል?

አቀናባሪ ካሙዙ፦ እንግዲህ ሙዚቃ ለሰው ልጆች ኀዘናቸውን ደስታቸውን ፍቅራቸውን የሚገልጹት መግባቢያቸው ነው ብንል ማጋነን አይሆንም።ስሜታቸውን ከመግለጽም በላይ ከተለያዩ መጥፎ ስሜቶች ለመውጣትም በራሱ ሙዚቃን ይጠቀማሉ።የአገር ፍቅር ስሜትን ለመግለጽም ሙዚቃ ያለው አቅም ትልቅ ነው።በጠቅላላው ሙዚቃን የማይፈልግ ሰው አለ ለማለት ከባድ ነው።እኛም ይህንን ሙዚቃ ስንሰራ ከማዝናናቱ ወይም ከሙዚቃነቱ ባሻገር ዓላማ ይዞ የተሰራ ስራ ነው።በመሆኑም ትውልዱ አገሩ ያለችበትን ሁኔታ ጠንቅቆ ይረዳ ዘንድ የወደፊት ተስፋዋ ምንድነው የሚለውን እንዲያውቅ ያም ብቻ አይደል፤ አገሬ በሰላም እንድትኖር በልጽጋና አድጋ ሌሎች አገሮች የደረሱበት ደረጃ ላይ እንድትደርስ ከእኔ ምን ይጠበቃል የሚለውንም እንዲገነዘብ ሆኖ የተሰራ ስራ ነው። ከዚህ አንጻር ትውልዱን በአገር ፍቅር ስሜት ውስጥ ከማስገባትና በዛ መንገድ እንዲሄድ ከማድረግ አንጻር የሚኖረው ሚና ቀላል አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን ፦ አንተ እንግዲህ በበርካታ የሙዚቃ ስራዎች ላይ በሙያህ ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎን ስታደርግ ኖረሃል፤ አሁን ደግም እኔም ለአገሬ ብለህ በዚህ መሰሉ ታሪካዊ ስራ ላይ የራስህን አሻራ አስቀምጠሃልና ይህኛው ስራ ከዚህ ቀደም ከሰራሃቸው ስራዎች አንጻር ስትመዝነው ምኑ ይበልጥብሃል?

አቀናባሪ ካሙዙ፦ በበኩሌ በርካታ አገራዊ ዘፈኖችን ሰርቻለሁ።በብሔር ብሔረሰቦች ዙሪያም ያሉ ስራዎች አሉኝ።ይህ አልበም ግን የተሰራበት መንገድ ይለያል፤ እኔም ለስራው ከፍተኛ የሆነ ዋጋን ከፍያለሁ።ለምሳሌ ሙሉውን ስራ በማቀናበር ሌሎችን በማስተባበር እንዲሁም ተመሳሳይ ነገሮችን በማድረግ ተካፍዬበታለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም አድርጌው በማላውቀው መልኩ 20 እና 25 ቀናት ብዙ ጊዜ ሰጥቼ ሌትም ቀንም ሰርቼዋለሁ።ወደፊት እንኳን እኔ ለአገሬ በሙያዬ ምን ሰራሁ ብዬ ሳስብ ወደ ጭንቅላቴ የሚመጣ ስራ እንደሚሆን አልጠራጠርም።በጠቅላላው ከሌሎች ስራዎቼ ጋር ሳነጻጽረው ይህ በጣም ትልቅ እርካታ ያለው ነው፡፡

አዲስ ዘመን ፦ አሁን ሙዚቃው ከወጣ በኋላ ያለውን የህዝብ አቀባበል እንዲሁም ወደፊት የሚኖረውን ሁኔታ እንዴት ትገልጸዋለህ?

አቀናባሪ ካሙዙ፦ ይህ ሙዚቃ የኢትዮጵያ ነው ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደግሞ በአገሩ ቀልድ ያውቃል ብዬ አላስብም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስራው አገርን ከችግር ለማውጣት ቢሆንም ለሰዎች ጆሮ በሚመጥን መልኩ አሉ የተባሉ የግጥምና ዜና ደራሲያን የተሳተፉበት ትላልቅ አርቲስቶች ያቀነቀኑበት በጥሩ ሁኔታ የቅንብር ስራው የተሰራለት ምን አለፋሽ ከለመድነው የሙዚቃ ስራ አንድ እርምጃ ከፍ ያለ በመሆኑ አሁን ላይ ያለው አቀባበል ጥሩ ነው።የእውነት ኢትዮጵያ በልቡ ያለች ዜጋ ሁሉ ደግሞ ይህንን የሙዚቃ ሲዲ ገዝቶ በማድመጥ ገቢውም ለታሰበለት ዓላማ እንዲውል የበኩሉን ይወጣል ብዬ አምናለሁ፤ መወጣትም አለበት፡፡

አዲስ ዘመን ፦ አሁን አገራችን ካለችበት ፈታኝ ሁኔታ አንጻር እንዲህ አይነት የጥበብ ስራዎች የሚኖራቸው አገራዊ ፋይዳ እንዴት ይገለጻል?

አቀናባሪ ካሙዙ፦ ጥበብ ከዚህ ቀደምም አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ቀድማ እየተገኘች ብዙ አስተዋጽዖን እንዳበረክተች እናውቃለን፤ አሁን ላለችበት ሁኔታም በዚህ መልኩ ይመጥናል ያልነውን የጥበብ ስራ ሰርተናል፤ ይህ ደግሞ አሁን ላለችበት ብቻ ሳይሆን የወደፊቱንም ብሩህ ጊዜ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ ፋይዳው እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም።

ጥበብ ዘመን ተሻጋሪ ነው፤ በመሆኑም አልበሙን የሚሰማ ሁሉ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ከመረዳቱም በላይ ወደፊት ምን ልትሆን እንደምትችልም የሚረዳበት ነው፤ ማንም ሰው ይህንን ሙዚቃ በሰማ ቁጥር ፍጹም ኢትዮጵያዊ የሆነ ስሜት ውስጥ መግባቱ እንደማይቀር ደግሞ በሙሉ ልቤ መናገር እችላለሁ።

የአገርን ዳር ድንበር ለማስከበር እኛ በሰላም ወጥተን እንድንገባ ሰርተን እንድንበላ ወልደን ልጆቻችንን እንድናሳደግ በማለት በዱር በገደሉ እየተዋደቁ ያሉ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላትንም ለመደገፍ ያለመ በመሆኑ አስተዋጽዖው ዘርፈ ብዙ ነው ማለት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ በርካታ የሙዚቃ ባለሙያዎች ዘርፉን እየተቀላቀሉ ከመሆኑ አንጻር እንደው የአገር ፍቅር ስሜትን የሚገነቡ ብሩህ ተስፋን የሚያጭሩ ስራዎችን ሰርተው በማቅረብ በኩል ምን ዓይነት ሚና ሊኖራቸው ይገባል ትላላህ?

አቀናባሪ ካሙዙ ፦ አገር የአንድ ወይንም የሁለት ሰዎች ብቻ አይደለችም ፤ በተለይም እንደዚህ አይነት ችግሮችን መመከት ለመንግስት ወይንም ደግሞ በመንግስት ለሚታዘዝ የመከላከያ ሰራዊት ብቻ የሚተው አይደለም።አገር የሁላችንም ናት፤ ከዚህ አንጻር ደግሞ ሁሉም ሰው ለዚህች አገር በሁለት እግር መቆም ብሎም ዳር ድንበሯ መከበር የበኩሉን መወጣት አለበት።በመሆኑም የአገራችን ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነው ብለን በሚቻለው አቅም ሙዚቀኛውም ገጣሚውም አቀናባሪውም እንዲሁም በሌሎች ሙያዎች ላይ የተሰማሩ ሁሉ ከልባቸው ምን ማድረግ አለብኝ ብለው ሊሰሩ ይገባል።

አዲስ ዘመን ፦ በመጨረሻም ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ካለ?

አቀናባሪ ካሙዙ፦ ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት፤ ጉዳቷ ችግሯ የሌሎች አካላት ብጥበጣና መልካም አለመመኘት ሁሉ ይመለከተናል።ከዛም በላይ ደግሞ እንደ አገርና ህዝብ የሚያለያዩን የተለያዩ ችግሮችና ምክንያቶች ቢኖሩ እንኳን በእንዲህ ያለው ወቅት አንድ ላይ በመቆም ጠላትን መመከት ማሳፈር ይገባናል።ይህንን ስናደርግ ብቻ ነው እኛ ኢትዮጵያዊ ነን ብለን ቀና ብለን መሄድ የምንችለው።በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ስለ ኢትዮጵያ የተሰኘ አልበም ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።የሙዚቃ አልበሙ ሲሰራ ለመንግስት ወይንም ደግሞ ለሌሎች ፓርቲዎች ሳይሆን በቀጥታ ለኢትዮጵያውያን የተሰራ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ገዝቶ በማድመጥና መልዕከቱንም በትክክል ተርጉሞ አጸፋዊ ምላሽ በመስጠት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል።

በመጨረሻ ግን ይህ አልበም በአጭር ጊዜ ተሰርቶና ተጠናቆ ኢትዮጵያውያን ጋር እንዲደርስ ላደረጉ የሙዚቃ ባለሙያዎችና ድምጻውያን ሁሉ ላቅ ያለ ምስጋናን ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

አቀናባሪ ካሙዙ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2014

Recommended For You