ከአሮጌ ዕቃ ሻጭነት ወደ አስመጪነት

 በኢትዮጵያ የፈርኒቸር ኢንዱስትሪ ረጅም ታሪክ ያስቆጠረ ነው። በዚህ ረጅም ታሪክ ውስጥ ኢንዱስትሪው የተለያዩ የአሠራር ጥበቦችን፣ ዓይነቶችንና ጊዜውን የዋጁ አቀራረቦችን እየተከተለና ዋጋውም እያደገ ዛሬ ላይ ደርሷል። ዛሬ ላይ የተለያዩ የፈርኒቸር ውጤቶች በሀገር ውስጥ በዘመናዊ ሁኔታ ከመመረት አልፈው የዘመናዊነት ጥግ የደረሱትም ከባህር ማዶ ወደ ሀገር ውስጥ በስፋት እየገቡ ነው።

በአሁኑ ጊዜ በሀገር ውስጥ የሚመረቱትም ሆነ ከውጭ ሀገር የሚገቡት የፈርኒቸር ውጤቶች በዋጋ ላቅ ያሉ፣ ዘመናዊ የሆኑ፣ ለአጠቃቀምም ምቹና ቀላል፤ ቦታም የማይፈጁ ሆነዋል። ሚስማርና ኮላ አያይዟቸው ባሉበት ለዓመታት የሚዘልቁ ሳይሆኑ ተበታትነው በአንድ አነስተኛ ካርቶን ውስጥ ታሽገው የሚጓጓዙና በትናንሽ ብሎኖች በቀላሉ ተገጣጥመው ጥቅም ላይ የሚውሉም ሆነዋል።

ምንም እንኳን ከንፁህ እንጨት ተሰርተው ለገበያ የሚቀርቡ የፈርኒቸር ውጤቶች ገበያ ላይ ያሉ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በተለያየ መንገድ ብዙ እንጨት ሳይወጣባቸው ከሌሎች ማቴሪያሎች ጋር በመዋሃድ በቀላሉ ተመርተው ጥቅም ላይ የሚውሉ ፈርኒቸሮች ገበያውን በአጭር ጊዜ እያጥለቀለቁት መጥተዋል። እንደዘመኑ ፋሽን እየተቆጠሩ በመምጣቸውም አብዛኛው ሰው ወደነዚህ ምርቶች ላይ አዘንብሏል።

የነዚህ ምርቶች ዘመናዊነት፣ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ለማንቀሳቀስ ቀላልነት፣ ውበት የተላበሱ መሆናቸውና ለአጠቃቀምም ምቹ ሆነው መሰራታቸው ደግሞ አብዛኛው ሰው ወደነዚህ የፈርኒችር ውጤቶች ላይ እንዲያዘነብል በእጅጉ ገፋፍተውታል። በብዛት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትም እነዚሁ ምርቶች ናቸው።

ይህንኑ ተከትሎ ታዲያ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ግለሰቦች እነዚህን የፈርኒቸር ውጤቶች ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። እነዚሁ የፈርኒቸር ውጤቶች በብዛት የሚገኙባቸው የምርት ማሳያዎችና መደብሮችን እዚም እዚያም ማየትም ተለምዷል።

ላለፉት አስራ ሦስት ዓመታት ዘመናዊ የፈርኒቸር ውጤቶችን ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለግለሰቦችና ለልዩ ልዩ ተቋማት በማቅረብ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በራሱም በማምረት ስኬታማ ከሆኑ አስመጪዎች መካከልም አንዱ ቲ ዲ ኤፍ ፈርኒቸር ነው።

አቶ ደጀኔ ለማ የቲ ዲ ኤፍ ፈርኒቸር ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ውልደታቸውና እድገታቸው እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ሰባተኛ አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዘነበወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአየር ጤና ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ውጤት ስላልመጣላቸው የግድ ኑሮን ለማሸነፍ ሥራ መስራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆነባቸው። ዝቅተኛ ገቢ ካለው ቤተሰብ የወጡ እንደመሆናቸውም ቤተሰባቸውን ሰርተው መደገፍ እንዳለባቸው ተረዱ። በጊዜው የነበረው ሁኔታም የግድ ሥራ ሰርቶ የሚታደርበት በመሆኑ ወደ ሥራ ለመግባት አላቅማሙም። ብዙ ጊዜ ሳያባክኑም ወዲያው ወደ ሥራ ገቡ። ያገኙትን ሥራ ሁሉ መስራት ጀመሩ። አየር ባየር ንግዱንም አጧጧፉ።

በአንድ አጋጣሚ መንግሥት ያገለገሉ ዕቃዎችን ለመሸጥ የሚያወጣቸውን ጨረታዎች ተመለከቱና እየተወዳደሩ መግዛት ጀመሩ። ከመንግሥት በጨረታ አሸንፈው የሚገዟቸውን ያገለገሉ ልዩ ልዩ ዕቃዎችን እያደሱ መልሰው መሸጥ ቀጠሉ። ይህም ሥራቸው በመንግሥት በኩል በሚገዙት ዕቃ ብቻ አልቆመም። ይልቁንም ወደታች ወርደው የተለያዩ ግለሰቦች የሚሸጧቸውን ያገለገሉ ዕቃዎች በመግዛትና ዕቃዎቹን በመጠገን መልሰው ለገበያ ማቅረባቸውን ተያያዙት። በሂደትም ከስር ከስር ሥራውን የሚያግዟቸው ሰዎችን በሥራቸው ቀጠሩ። በዚሁ ሥራም ለሦስት ዓመታት ያህል ቆዩ።

ቀስ በቀስ በዚሁ ሥራ ለውጥ እያመጡ ሲሄዱ ጊዜው ጥሩ የነበረ በመሆኑ በ100 ሺ ብር መነሻ ካፒታል ከአስራ ሦስት ዓመት በፊት ሶፋዎችን፣ ወንበሮችን፣ ጠረጴዛዎችን፣ አልጋዎችንና ሌሎችንም ልዩ ልዩ የቤትና የቢሮ ዕቃዎችን በቀጥታ ከውጭ ሀገር ወደማስመጣቱ ሥራ ገቡ። ይኸው የአስመጪነት ሥራቸው በሂደት እያደገ ሲመጣ በጨረታ የቤት ዕቃዎችን ለሚሸጡ ሰዎች አስመጥተው ማከፋፈል ጀመሩ።

የራሳቸውን ሱቅም ጭምር በመክፈት ከውጭ ሀገር የሚያስመጧቸውን ዕቃዎች መሸጥ ቻሉ። ወቅቱ የቤት ዕቃዎች ይበልጥ የሚፈለግበትና ገበያም ያላቸው በመሆኑ ዕቃዎቹን ቶሎ ቶሎ በመሸጥ ገቢያቸውን አሳደጉ። ቀስበቀስም ከውጭ ሀገር የሚያስገቧቸውን የቤትና የቢሮ ዕቃዎችን በመጠን ከፍ እያደረጉ መጡ። በሂደት ደግሞ ልዩ ልዩ የቢሮ ፈርኒቸር ውጤቶችን በብዛት ወደሀገር ውስጥ ማስገባት ጀመሩ።

በአሁኑ ጊዜ ድርጅታቸው ቲ ዲ ኤፍ ፈርኒቸር ጨረታዎችን እየተጫረተ በማሸነፍ ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ለመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ ለገቢዎች፣ ለግዢ ኤጀንሲ፣ ባንኮችና ለሌሎች በርካታ የግል ድርጅቶች ልዩ ልዩ የፈርኒቸር ዕቃዎችን ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ያቀርባል። ለአዲስ አበባና በዙሪዋ ለሚገኙ ነዋሪዎችም በተመሳሳይ እነዚህኑ ዕቃዎች በስፋት ያቀርባል።

ከዚህ ባሻገር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ወንበሮችና ጠረጴዛዎችን፣ የሲኒማ ቤቶችና የቢሮ ወንበሮችን፣ የቢሮ ወንበሮችን፣ ሼልፎችንና ጠረጴዛዎችንም ከውጭ ሀገር አስመጥቶ ያቀርባል፤ ይገጥማል። በመንግሥት ደረጃ የተሰሩ ትላልቅ አዳራሾችን ወንበሮችንም በአስፈላጊው ዲዛይን ከውጭ ሀገር በማስመጣት የገጠማ ሥራም አከናውኗል።

ድርጅቱ አብዛኛውን የቤትና የቢሮ ዕቃዎችንና ከውጭ ሀገር የሚያስመጣ ቢሆንም ልዩ ልዩ የእንጨት ውጤቶችን በተለይ ወንበሮችን፣ ሶፋዎችንና ጠረጴዛዎችን እዚሁ በራሱ ያመርታል።

 ከውጭ ሀገር የሚያስመጣቸውንም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚያመርታቸውን የቤትና የቢሮ ዕቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋና ጥራት ለገበያ የሚያቀርብም ሲሆን ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርቶቹ በመንግሥት ተቋማት፣ በግል ድርጅቶችና በግለሰብ ደረጃ ተፈላጊ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

በተለይ ደግሞ በፈርኒቸር ውጤቶች አቅርቦት በመንግሥት ተቋማት በኩል ትልቅ እውቅናን አትርፎለታል። በርካታ ደንበኞችንም ማፍራት ችሏል። ምርቶቹንም በአብዛኛው የሚያስገባው ከቻይና ሲሆን የመንግሥትም ሆኑ የግል ድርጅቶች በሚፈልጉት የጥራት ደረጃ ልክ ምርቶቹን ያቀርባል። ከሌሎች አቻ የፈርኒቸር ውጤቶች አስመጪ ድርጅቶች ልቆ ለመገኘትም ሁሌም ጥራትን አስቀድሞ ይሰራል።

በአሁኑ ጊዜ የድርጅቱ ካፒታል ሃምሳ ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ሰላሳ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። የሰው እጥረት ሲያጋጥመው ደግሞ ሰዎችን በኮንትራት ቀጥሮ ያሰራል። ይህም ድርጅቱ በቋሚነት ቀጥሮ ከሚያሰራቸው ሠራተኞች በተጨማሪ በኮንትራትም ለተጨማሪ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።

ድርጅቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ካፒታሉ እያሳደገ በመምጣቱም ሰሚት አካባቢ በተከራየው ቦታ ላይ ልዩ ልዩ የፈርኒቸር ምርቶችን ያመርታል። በሱሉልታም በራሱ ቦታ ላይ በገነባው ፋብሪካ ተመሳሳይ የፈርኒቸር ምርቶችን እያመረተ ይገኛል። በአዲስ አበባ ከተማ ውሃ ልማት ፊትለፊት የራሱን ምርቶች የሚያሳይበትና ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል ባለስምንት ወለል ሕንፃም ገንብቷል። በቀጣይ ሕንፃውን ወደ አስራ አንድ ወለል ለማሳደግም እየሰራ ይገኛል።

በቀጣይም በሀገሪቱ የሚታየውን ሰፊ የፈርኒቸር አቅርቦት ችግር ለመፍታት ምርቶቹን በሀገር ውስጥ በማምረት ለደንበኞቹ በስፋት የማቅረብ ትልቅ አቅድ ይዟል። በተለይ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ከፍተኛ የፈርኒቸር ውጤቶች የሚፈልግበትና የሚገዛበት ጊዜ ከመሆኑ አኳያ ይህን ፍላጎት ለማሟላትና እጥረቱን ለመቅረፍ እንደ አንድ የፈርኒቸር ውጤቶች አስመጪና አምራች ድርጅት ሰፊ ጥረት ያደርጋል።

የፈርኒቸር ኢንዱስትሪ ዘርፉ በርካታ ችግሮች ያሉበት ነው የሚሉት አቶ ደጀኔ በተለይ ከታክስ አኳያ ሲታይ ምርቱ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ የሚጣልበት ታክስ ወጥነት የጎደለውና የተለያየ መሆኑን ይጠቁማሉ። የውጭ ምንዛሬ በጨመረ ቁጥር ችግሩ ጎልቶ እንደሚታይም ይጠቅሳሉ። ከዚህ አኳያ መንግሥት እነዚህን ችግሮች ማስተካከል እንደሚኖርበት ያመለክታሉ።

ላለፉት አስራ ሦስት ዓመታት ልዩ ልዩ የፈርኒቸር ውጤቶችን ከውጭ ሀገራት በማስመጣትና ለሀገር ውስጥ ገበያ በማከፋፈል ረገድ ስኬታማ ነኝ የሚሉት አቶ ደጀኔ፤ ድርጅቱ ሥራውን ሲጀምር በ100 ሺ ብር እንደነበርና ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ የድርጅቱ ካፒታል 50 ሚሊዮን ብር መድረሱን፣ የራሱን ሕንፃ እየገነባ መሆኑን፣ የራሱን የፈርኒቸር ውጤቶች ለማምረት የሚያስችለውን ቦታ መረከቡንና በስሩ ሠራተኞችን ቀጥሮ እያሰራ መሆኑንና እነዚህም የስኬቱ ማሳያዎች መሆኑን ያብራራሉ።

‹‹በብዙ ሚሊዮን ብር የሚቆጠሩ የፈርኒቸር ዕቃዎችን ጨረታ በመወዳደርና በማሸነፍ ለመንግሥት ማቅረብ በራሱ አንድ ስኬት ነው›› የሚሉት አቶ ደጀኔ ይህም በነዚህ ሁሉ አስራ ሦስት ዓመታት ድርጅታቸው ትልቅ አቅም እየገነባ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን ይጠቁማሉ። ከዚህ አንፃር ሥራው ሰዎች ጠንክረው ከሰሩበት ውጤታማ የሚያደርግ ስለመሆኑም ይገልፃሉ። በሥራቸው ከሰላሳ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውና በኮንትራትም ጭምር ማሰራታቸው የድርጅታቸው ሌላኛው የስኬት ማሳያ መሆኑንም ይመሰክራሉ።

በተመሳሳይ ሌሎችም በዚሁ የፈርኒቸር አስመጪነትና ማምረት ሥራ ገብተው መስራትና ውጤት ማምጣት ለሚፈልጉ ሰዎች በቅድሚያ ከራስ የሚመነጭ ጥንካሬ እንደሚያስፈልጋቸው ይጠቁማሉ። የራስ ጥንካሬና አቋም ካላቸው ሥራ ሰርተው በቀላሉ መለወጥ የማይችሉበት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለም ይገልፃሉ።

 አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2014

Recommended For You