ፓን አፍሪካዊው

የጸረ ቅኝ አገዛዝ አንቂና ፖለቲከኛ ነበሩ፤ እአአ ከ1961 እስከ 1962 ቀድሞ ታንጋኒካ ትባል የነበረችው የዛሬዋ ታንዛኒያ ጠቅላይ ሚኒስትርና ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል።ሀገሪቱ ታንዛኒያ መባል ከጀመረችበት ከ1964 እስከ 1985 የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ሰርተዋል።

ከታንጋኒካ አፍሪካን ብሄራዊ አንድነት / ታኑ/ ፓርቲ መስራቾች አንዱና የፓርቲው መሪም ነበሩ።በ1954 በተመሰረተው በዚህ ፓርቲ ሀገራቸው ታንጋኒካን ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነጸ ለማውጣት ታግለው አሳክተዋል።ፓርቲው እአአ ከ1954 እስከ 1990 ቻማ ቻማ ፒንዱዚ ወደ ሚባለው ፓርቲ ሲቀየርም ፕሬዚዳንቱ እሳቸው ነበሩ።ጁሊየስ ካምባራጌ ኔሬሬ ፡፡

የዛሬው የሳምንቱ በታሪኩ ርእሰ ጉዳያችንም በእኚህ የአፍሪካ ታላቅ ሰው ላይ ያጠነጠነ ነው።ቅኝ ግዛትን በመቃወም፣ የአፍሪካ ሀገሮች ውህደት እንዲፈጠር ለእዚህም አካባቢያዊ ውህደቶች ወሳኝ ስለመሆናቸውና የምስራቅ አፍሪካ ፌዴሬሽን እንዲመሰረት እንዲሁም ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለው ጽኑ እምነታቸው ደግሞ ከወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር ያላቸው ተዛምዶ ጉዳያችን እንድናደርጋቸው ምክንያት ቢሆነንም፤ እኚህ ታላቅ መሪ ከዚህ አለም በሞት የተለዩትም በዚህ ሳምንት ጥቅምት 4 ቀን 1992 ዓ.ም መሆኑም ትኩረታችን እንዲሆኑ አድርጓል።

ኔሬሬ እአአ ሚያዚያ 13 ቀን 1922 በያኔዋ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ታንጋኒካ ማራ በተሰኘው ግዛት ቡቲያማ መንደር ነው የተወለዱት።የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ በኡጋንዳ ማኬሬሬ ኮሌጅ፣ ከዚያም በስኮትላንድ ኤደንበርግ ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።በ1952 ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በመምህርነት ሰርተዋል።ወገኖቻቸው “ምዋሊሙ” አስተማሪው በሚል ይጠራዋል፡፡

በአመለካከታቸው የአፍሪካ ብሄረተኛ /አፍሪካን ናሽናል/ በመባል የሚታወቁት እኚህ ታላቅ መሪ፣ የአፍሪካ ሶሻሊስት በመባልም ይታወቃሉ።በትብብር ኢኮኖሚ ላይ የተመሰረተ ርእዮት የሚያራምድ ኡጁማ የተሰኘ የፖለቲካ ፍልስፍናን ያስተዋወቁም ናቸው።

ከ1958 እስከ 1959 በተካሄደ ምርጫ ነው ወደ ህግ አውጪው አካል የመጡት።በ1960 ምርጫ ደግሞ ፓርቲያቸውን ታኑ በመመራት ለድል አብቅተውታል።ይህን ተከትሎም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተደርገዋል።.

እኚህ የህንዱ የነጻነት መሪ ማህተመ ጋንዲ ተጽእኖ ያረፈባቸው በመባል የሚታወቁ መሪ፣ አላማቸውን ለማሳካት ነውጥ አልባ ተቃውሞ ምርጫቸው ነበር።ከአንግሊዝ ባለስልጣናት ጋር በተደረገ ድርድርም ሀገራቸው በ1961 ነጸነቷን ተቀዳጅታለች።

እአአ 1962 ታንጋኒካ ሪፐብሊክ ስትሆን፣ የአዲሲቱ ሀገር የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሆነው የመጡትም እሳቸው ናቸው። ሲቪል ሰርቪሱን ከቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብ ነጻ ለማውጣትና አፍሪካዊ አመላካከትን የሚያቀነቅን ለማድረግ በመንግስታቸው በኩል ብዙ ሰርተዋል።በአፍሪካዊያን እና የእሲያና አውሮፓ ዝቅተኛ/ አናሳ/ ማህበረሰቦች መካከል አንድነት እንዲመጣ መሰራታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ፓን አፍሪካኒዝም

ኔሬሬ አፍሪካውያንን በአንድ የሚያስተዳድር መንግስት እውን እንዲሆን ፍላጎቱ ነበራቸው።ይህ ባይሳካላቸውም ፓን አፍሪካኒዝም በማቀንቀን ሀገራቸው ኬንያና ኡጋንዳ በጋራ የምስራቅ አፍሪካ ፌዴሬሽንን እንዲመሰረቱ ጥረት አድርገዋል።

በአፍሪካ ውህደት ላይ የያዙትን አቋም በመቀጠልም እአአ ሰኔ 1963 ከኬንያ ፕሬዚዳንት ጆሞ ኬኒያታ ፣ ከኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ሚልተን ኦቦቴ ጋር በናይሮቢ ተሰብስበው በዚሁ አመት መጨረሻ ሀገሮቻቸውን ወደ አንድ የምስራቅ አፍሪካ ፌዴሬሽን ለማዋሀድ ተስማሙ።ይህ ግን እውን ሳይሆን ቀረ።ይህም ሁኔታ የአመቱ ትልቁ ውድቀት ሆነ።በምትኩ በሶስቱ ሀገሮች መካከል ትብብሮች እንዲኖሩ የሚያስችለው የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ በ1967 እውን ሆነ።ኔሬሬ ግን የምስራቅ አፍሪካ ፌዴሬሽንን እውን ማድረግ ባለመቻላቸው በስልጣን ዘመናቸው ያጋጠማቸው ትልቁ ውድቀት አድርገው ቆጠሩት፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ፌዴሬሽን አውን ሊሆን ባይችልም፣ እሳቸው ግን ተስፋ ቆርጠው አልተቀመጡም።ዋና መቀመጫውን ታንዛኒያ አሩሻ ያረገው በታንዛኒያ ኡጋንዳና ኬንያ የጋራ ገበያ እና አስተዳደር አንድነት ተመሰረተ።

በዛንዚባር 1964 የተካሄደውን አብዮት ተከትሎም ደሴቲቷ ዛንዚባር ከታንጋኒካ ጋር ተዋህዳ ታንዛኒያ ከተመሰረተች በኋላም ኔሬሬ በራስ መተማመናቸው ጨመረ፤ የህብረተሰባዊነት/ ሶሻሊዝም/ ርእዮተ አለም መከተል ላይ አተኮሩ።የእሳቸው ሶሻሊዝም ከማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርእዮተ አለም የተለየ ነበር።ታንዛኒያ በወቅቱ በማርክሲዝም ርእዮት ከምትከተለው ቻይና ከማኦ ሴቱንግ ጋር የቅርብ ግንኙነት ማድረግ ውስጥ ገባች።

ኔሬሬ በዘመናቸው ወሳኝ መሪ እየሆኑ መጡ።የጸረ ቅኝ አገዛዝ አቋማቸውና በስልጣን ዘመናቸውም ይህንንም በተግባር ለማሳየት ያደረጉት ጥረት በመላ አፍሪካ ታላቅ ክብርን አጎናጸፋቸው።ሀገራቸው ታንዛኒያም ነጻነቷን ከተቀዳጀችበት ጊዜ አንስቶ ለበርካታ አስርት አመታት ከሌሎች ጎረቤት ሀገሮች ይልቅ የተረጋጋችና አንድነቷን የጠበቀች መሆን ችላለች።

እየቆየ ግን የመሰረቱት ባለ አንድ ፓርቲ መንግስት እና ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ዜጎች ለእስር ይዳረጉ የነበረበት ሁኔታ፣ መንግስታቸውንና እሳቸውን አምባገነን ያሰኛቸው ጀመር።በሀገሪቱ በምጣኔ ሀብት አስተዳደር በኩል ይታይ የነበረው ክፍተት ጥያቄ እንዲቀርብባቸው እያረገ መጣ።እንዲያም ሆኖ ግን በታንዛኒያውያን ዘንድ ምዋሊሙ /መምህሩ / መባላቸው የቀጠለው ኒሬሬ፣ የሀገር አባት/ ፋዘር ኦፍ ዘኔሽን/ እየተባሉም ይጠሩ ነበር።

እአአ ታህሳስ 9ቀን 1962 ታንጋኒካ ነጻነቷን ከተቀዳጀች አንድ አመት በኋላ ሪፐብሊክ ተባለች።ኔሬሬም በዳሬሰላም ወደሚገኘውና ቀድሞ በቅኝ ግዛት ዘመን የብሪታኒያ መሪዎች መኖሪያ ወደ ነበረው ቤተመንግስት ገቡ።

ኔሬሬ ግን ይህን የቤተመንግስት ህይወት አልወደዱትም።እንዲያም ሆኖ እስከ 1966 ድረስ በዚያው ቆዩ።በአፍሪካና በሌሎች የተለያዩ ሀገሮች በርካታ ጉብኝቶችን አድርገዋል።በአሜሪካ ጉብኝታቸው ከጆን ኤፍ ኬኔዲ ጋር መወያየት ቢችሉም፣ በግል አንዳቸው ለአንዳቸው ጥሩ ግምት ያላቸው ቢሆኑም ኔሬሬ ኬኔዲ በደቡብ አፍሪካ የነጮች የበላይነት መንግስት ላይ አቋም እንዲያሳዩ ለማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

የኔሬሬ የቀደሙት ፕሬዚዳንታዊ ጊዜያት በአብዛኛው በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ነበሩ።በመጋቢት 1963 የአፍሮ ኢሲያን ሶሊዳሪቲ ጉባኤ በሞሺ ተሳትፈዋል።በዚህም ጉባኤ ላይ የወቅቱ የኮንጎሊዝ ሁኔታ ኒኦ ኮሎኒያዝም በአፍሪካ ስለመኖሩ ምሳሌ እንደሆነ አስታውቀዋል።ሁኔታውንም የአፍሪካን ሁለተኛው መቀራመት ዘመን አድርገው ተመልክተውታል።

በዚሁ አመት ግንቦት ወር ላይ ደግሞ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ተገኝተዋል።በወቅቱም ፊቱንም ይሉት የነበረውን በመድገም አፍሪካ አሁንም ነጸ አይደለችም በማለት እየሆነ ያለውን ድርጊት አሳፋሪ ሲሉ ገልጸውታል።አፍሪካን ነጻ ለማውጣት አሁንም የአፍሪካውያን የጋራ ጥረት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ነጻ አውጪ ኮሚቴ በዳሬሰላም እንዲካሄድ አድርገዋል።በደቡብ አፍሪካ ይካሄድ ለነበረው ጸረ ኮሎኒያሊዝም ንቅናቄ የጦር መሳሪያና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ይታወቃሉ።

የአፍሪካ ብሄረተኛ

የፓን አፍሪካኒስት አመለካከትን በማራመድ አፍሪካ አንድ እንድትሆን አንድ መንግስት እንዲኖራት ኒሬሬ አጥብቀው ይሹ ነበር።ይህ አቋማቸው ግን አንድነት በፍጥነት መፈጸም አለበት ከሚሉት የጋነው ፕሬዚዳንት ክዋሚ ኒኩሩማ ጋር የተለየ ነው።በቅድሚያ ለአጭር ጊዜ ክፍለ አህጉራዊ ፌዴሬሽኖች እንዲቋቋሙ ይፈልጉ ነበር።ይህም ለአህጉሪቱ ውህደት አንድ ደረጃ እንደሚያገለግል ያስቡ ነበር።

ኔሬሬ የአፍሪካ ብሄረተኛ በመባል ይታወቃሉ።ለቅኝ ግዛት ከፍተኛ ጥላቻ ነበራቸው።በዚህ የተነሳም በታንጋኒካ የነበረውን ቅኝ አገዛዝ በጽኑ ተቃውመዋል፤ ያካሂዱ በነበሩት የጸረ ቅኝ አገዛዝ ዘመቻዎች ሁሉ በአሜሪካና በፈረንሳይ አብዮት መርሆዎች በጽኑ እንደሚያምኑ የሚናገሩት ኔሬሬ፣ አአአ 1947 ህንድን ነጻ ያወጣት የህንድ የነጻነት ንቅነቄ ተጽእኖ ያረፈባቸውም ነበሩ።

በቅኝ ግዛቱ ዘመን በታንጋኒካ ያለው አጠቃላይ ሁኔታ አመጽ የሌለበት እንቅስቃሴ ብቻ ማድረግን የሚፈልግ ነው ብለው ያመኑ ነበር።ይህን አስመልክተው ሲናገሩም ‹‹ እኔ የአመጽ መንገድን በመከተል በኩል የጋንዲን አይነት አይደለሁም፤ አመጽ የግድ አስፈላጊ ካልሆነ በቀር ማንም ሊመርጠው የማይችል ክፉ ነገር ነው፤ ወንጀልም ነው፤ ›› ብለዋል።የሀገራቸው መሪ ከሆኑም በኋላ በደቡብ አፍሪካ ይካሄዱ የነበሩ የጸረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄዎች የተለያዩ የቁሳቁስ፣ የዲፕሎማሲና የሞራል ድጋፎችን ያደርጉም ነበር፡፡

ምስራቅ አፍሪካዊነት

ቅኝ ገዥ አውሮፓውያንን የሚቃወሙ ቢሆኑም፣ በሁሉም ነጮች ላይ ተቃውሞ የላቸውም፤ ከተሞክሯቸው በመነሳትም ሁሉም ነጮች ቅኝ ገዥዎችና ዘረኞች አይደሉም የሚል አቋም ነበራቸው።ከነጻነት በፊት በቅኝ ገዥዎች ላይ የሚደረገው ትግል ከዘረኝነት የጸዳ መሆን እንዳለበት ያምናሉ።አውሮፓውያኑና እስያውያኑ ከአፍሪካውያኑ ጋር እኩል መብት አላቸው ባይም ናቸው።በምስራቅ አፍሪካ የነበሩ አውሮፓውያንንና የእሲያ ዜጎች ከአፍሪካውያን ጋር እኩል መብት ሊኖራቸው አይገባም የሚሉ አፍሪካውያንንም በጽኑ ታቀውመዋል።

አአአ በ1951 በኤደንበርግ ዩኒቨርሲቲ ባቀረቡት መጣጥፍም ‹‹ የምንገነባው ማህበረሰብ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ እንጂ በዘር ላይ የተመሰረተ ማህበረሰብ መሆን የለበትም›› ብለዋል።ማስተዋል የሚችሉ አውሮፓውያንና ህንዶች በሙሉ ራሳቸውን የታንጋኒካ ዜጋ አድርገው እንዲቆጥሩም አስገንዝበዋል።ሁላችንም ታንጋኒካዊ ነን፤ ሁላችንም ምስራቅ አፍሪካዊ ነን ብለዋል፡፡

የውጭ ግንኙነት

በውጭ ግንኙነት በኩልም ምእራባውያን ሀገሮች ኔሬሬ ከቻይና ምንም አይነት ድጋፍ እንዳይከጅሉ አጥብቀው ያሳስቧቸው ነበር፤ እሳቸው ግን ለዚህ ቦታ አልሰጡትም።በቻይናው መሪ ማኦ ሴቱንግ በኩል እአአ በ1964 ሰባት ቻይናውያን የዩኒቨርሲቲ መምህራንና አራት ተርጓሚዎችን በማስመጣት ከሰራዊቱ ጋር ለስድስት ወራት እንዲሰሩ አድርገዋል።ከዚያ በኋላ ባሉት አመታትም ቻይና የታንዛኒያ የውጭ ግንኙነት ተጠቃሚ ሆናለች።

ከቻይና ጋር ያላቸውን ግንኙት ይበልጥ በማጠናከርም ፣እንደ አእአ 1965 ኔሬሬ በቻይና የ8 ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አርገዋል።በዚሁ አመት ሰኔ ወር የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዡ ኢንላይ ዳሬሰላምን ጎብኝተዋል።ቻይና ለታንዛኒያ በሚሊኖች የሚቆጠር ፓውድ በብድርና በእርዳታ ሰጠች።የጨርቃ ጨርቅ፣ የግብርና ሌሎችንም በርካታ የኢንቨስትመነት ፕሮጀክቶችንም ጀመረች። ታንዛኒያ ለምታካሂደው የባቡር መስመር ዝርጋታ ከምእራባውያን ሀገሮች አጥታው የነበረው የገንዘብ ድጋፍም በቻይና በኩል ተገኘ።

ለአፍሪካ ችግር የምእራባውያን ሳይሆን አካባቢያዊ መፍትሄ

ኔሬሬ በመጨረሻዎቹ አመታታቸው / 1994–1999/ በአለም አቀፍ ጉዳዮች ውስጥ በስፋት ይሳተፉ ነበር።በ1997 በጋና 40ኛ የነጸነት በአል ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ለፓን አፍሪካ ንቅናቄ የሚደረገው ድጋፍ መጠናከር እንዳለበት አስገንዘበዋል።በመላ አፍሪካ እየታየ ስላለው ወደ ጎሳ የመወሸቅ አባዜ አስጊነትም አሳስበዋል።የአውሮፓ አንድነትን በአውሮፓ ህብረት ለማምጣት ይደረግ የነበረውን እንቅስቃሴም በምሳሌነት በመጥቀስም ለአፍሪካ ሀገሮች ያለውን ፋይዳ አስገንዘበው ሊኮረጅ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በ1995 በተካሄደው ምርጫ አልተወዳደሩም፤ ራሳቸውን ከእጩነት በማግለል ሌላ እጩ ድጋፍ ወደ ማድረግ ገብተዋል።በዚህም ስልጣን በገዛ ፈቃድ በመልቀቅ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ እስከ መባል ደርሰዋል።የፕሬዚዳንትነት ቦታቸውን ከለቀቁ በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለቡሩንዲ የእርስ በርስ ጦርነት መፍትሄ ለማምጣት ኔሬሬ አደራዳሪ እንዲሆኑ ጥሪ ያቀርባል።እሳቸውም ሃላፊነቱን ተቀብለው መስራት ውስጥ ገቡ፡፡

ለእዚህም በ1996 መዋሊሙ ፋውንዴሽንን በመመስረት ድርድሮችን በፋውንዴሽኑ በኩል ለማድረግ ይወስናሉ።ፋውዴሽኑ የአሜሪካውን የካርተር ማእከል በሚመስል መልኩ ነው የተዋቀረው።በዚሁ አመት ሁለት ድርድሮችን በፋውንዴሽኑ ማካሄድ ተችሏል።ኔሬሬ ከዚህም አንድ ነገር ተረዱ።ለሰላም የሚደረግ ድርድር መፍትሄ መምጣት ያለበት ከአውሮፓ ሃያላን ሀገሮች ሳይሆን ከአካባቢያዊ ተቋማት የሚል አቋም ያዙ፡፡

በቡሩንዲ ሰላም ለመምጣት ባከናወኑት ተግባር ሰላም ለማምጣት የሚደረግ የድርድር ሂደት አሳታፊ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፤ ቅንጣት የምትባለዋ የፖለቲካ ቡድን ሳትቀር በድርድሩ መሳተፍ እንዳለባት አመልክተዋል።የሲቪል የፖለቲካ ተቋማት ለዘላቂ ሰላም ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው የሚናገሩት።ይህ ድርድርም ኔሬሬ ህይወታቸው እስከሚያልፍ ድረስ የቀጠለ ሲሆን፣ ድርድሩ በኒልሰን ማንዴላ አማካይነት እንዲፈጸም ተደርጎም ነበር።

የመጨረሻ የህይወት ዘመን

ኔሬሬ በ1998 በሉኪሚያ በሽታ ይሰቃዩ ነበር፤ ችግሩ ግን ለህዝብ ይፋ አልተደረገም ።የታንዛኒያ መንግስትና ሰራዊቱ ገንዘብ በማሰባሰብ ለኔሬሬ በትውልድ አካባቢያቸው ያስጀመሩት የመኖሪያ ቤት ግንባታ በ1999 ተጠናቅቆ ኔሬሬ ቢገቡበትም ከሁለት ሳምንት በላይ አልኖሩበትም።መስከረም 1999 ወደ እንግሊዝ ተወስደው ህክምና ሲከታተሉ ቢቆዩም ሊተርፉ አልቻሉም።እአአ ጥቅምት 14 ቀን 1999 ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።የሀገሪቱ መንግስት የ30 ቀናት የሀዘን ቀን አውጆ በዳሬሰላምና በትውልድ አካባቢያቸው ታላቅ መንግስታዊ ስርአት ተደርጎ ቀብራቸው በትውልድ ስፍራቸው ቡቲያማ ተፈጸመ፡፡

ኃይሉ ሣህለድንግል

Recommended For You