“ኢትዮጵያን በመሰለች ውብና የነፃነት ምድር መፈጠር ኩራት ነው” – አርቲስት ደበበ እሸቱ

ድንቅ ከያኒ፣ አይነተ ብዙ ሙያተኛ፣ የዘርፈ ብዙ ክህሎት ባለቤት ነው።የኢትዮጵያን ኪነ ጥበብ በጥልቅ ገብቶ ዋኝቶበታል፤ ሁሉንም አዳርሶ አስደማሚ ችሎታውን በጥበብ አፍቃሪያን ዘንድ አስመስክሯል።ዘመናትን በማይዋዥቅ አቋም መድረክ ላይ ፈክቶ የቆየ፣ በአድናቂዎቹ ልብ ውስጥ ታላቅ ቦታ ያለው የጥበብ አባት ነው፡፡

ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ዕድገት የላቀ አስተዋፅኦ ያበረከተ ብርቱ ሰው።ለብዙዎች የሙያ አባት ነውና ጋሼ እያሉ ይጠሩታል።ሲሰሙት በቀላሉ የሚለዩት አስገምጋሚ ድምፁ ከብዙዎች ዕዝነ ህሊና ሊሰወር ከቶም አይችልም።አርቲስት ደበበ እሸቱ፡፡

መድረክ ላይ በልዩነት በተሳተፈበት የትያትር መስክ ነግሷል።በአዘጋጅነት የተዋጣለት ስራዎቹም በብዙዎች የተወደሰ ከያኒ ነው።ዘርፈ ብዙ ሙያተኛው ደበበ ከመድረክ ባሻገር በቴሌቪዥን ድራማዎችና ፊልም ሥራዎች ላይ ብቁ መሆኑን አስመስክሯል።

የዚህ ድንቅ የጥበብ ሰው ስራዎች በአገር ውስጥ ብቻ የተገደቡም አይደሉም ፤ በተጋባዥነት በተለያዩ አገራት ፊልሞች ላይም ተውኗል።ከትወና ድርሰት እና ዝግጅት በተጨማሪም በርከት ያሉ የታሪክና የሥነ ፅሁፍ የውጪ አገር ደራሲያን ስራዎች ወደ አማርኛ ቋንቋ ተርጉሞ ለአንባቢያን አበርክቷል።

የጥበብ ጅማሮ

ውብ የሆነው የልጅነት ጊዜው ያሳለፈበት ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ለከያኒነቱ ምክንያት የፈጠረለት አጋጣሚ መከሰቻ ቦታ ነው።በተማሪነት ዘመኑ ስመ ጥሩ ተስፋዬ ገሠሠና መኮንን ዶሪ “ስስታሙ መንጠቆ” የተሰኘውን ቲያትር መድረክ ላይ ሲተውኑ ተመልክቶ እነሱን መሆን አሰኘው፤ልክ እንደነሱ መድረክ ላይ ወጥቶ ቲያትር መስራት ህዝብ ፊት ቆሞ ተውኔት መጫወት ተመኘ፡፡

ከዚያ ቀን ጀምሮ እሱ ትያትረኛ መሆን ዋንኛ ህልሙ፤ መድረክ ላይ ስራዎቹን ማቅረብ መድረሻ ግቡ አደረገ።የዚህ ብርቱ ሰው ህልምና ውጥን የማሳካት እንቅስቃሴ በእዚያው የብዙ ተፅዕኖ ፈጣሪ ኢትዮጵያዊያን መፍለቂያ በሆነው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተጀመረ።

መድረክ ላይ ባየው ትዕይንት ልቡ የተሰቀለው ብላቴና ትያትር የሚታይበትን መዋያው፣ ትርኢት የሚታይበት መድረክን ማምሻው ማድረግ ጀመረ።በወቅቱ ጓደኛው ከነበረው ወጋየሁ ንጋቱ ጋር የትያትር ቤት መድረክ መጋረጃ በመክፈትና መዝጋት ሥራ ላይ ተጠመዱ።በዚህም ሳቢያ ትያትር ሲታይ በነፃ የመመልከት ዕድል አገኙ፡፡

የመጀመሪያው መድረክ

በልጅነቱ በትያትር ፍቅር ውስጡ የተሞላው ደበበ ከጓደኛው ጋር ስምንተኛ ክፍልን ሲጨርሱ ለትምህርት ቤት መዝጊያ መርሀ ግብር ለቤተሰብ የመሰነባበቻ ዝግጅት ትያትር እንዲሠሩ በቀለም አባት በሆኑት መምህሮቻቸው ግብዣ ቀረበላቸው።የሚደንቀው ነገር ደግም በደበበ የመጀመሪያ ገጠመኝ ውስጥ አብሮ ተከሰተ።

በወቅቱ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ወንድ ተማሪዎችን ብቻ ተቀብሎ ያስተናግድ ስለነበር ደበበና ጓደኞቹ መድረክ ላይ ወጥታ የምትተውን ሴት በማጣታቸው ደበበ መድረክ ላይ የሴት ገፀ ባህሪ ወክሎ መጫወት ግድ ሆነበት።መድረክ ላይም በብቃት ሙሽራ ሆኖ ተወነ፤ በተመልካቹም ትወናው ተወደደ፡፡

ሌላኛው መንገድ

በትምህርቱ ጎበዝና ከፊት ተሰላፊ ተማሪዎች ውስጥ የነበረው ደበበ፣ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ አየር ሀይልን ተቀላቅሎም ለተወሰነ ጊዜ ስልጠና ወስዷል።በአየር ሀይል መኮንኖች የአለባበስ ስርዓት ተማርኮ ተቀላቅሎ የነበረው ደበበ በስልጠና ሂደት እየገጠመው የነበረው ሁኔታ አሰላቸውና ትቶ በመውጣት የመምህርነት ስልጠና በደብረብርሃን የመምህራን ማሰልጠኛ መውሰድ ጀመረ።

ከሁለት ዓመት የመምህርነት ሥልጠና በኋላ ተመርቆ ጎሬ ተልኮ ለአንድ ዓመት አገልግሏል።እዚያ ሆኖ ማትሪክ ተፈተነና ወደቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አመራ::

እንደገና ወደ ኪነ ጥበብ

ዩኒቨርሲቲ ሲገባ መምህር ጴጥሮስ ወልደማርያም ከተባሉ የቀድሞ መምህሩ ጋር ይገናኛል።ለመምህሩም ህግ መማር እንደሚፈልግ ሲነግራቸው እሳቸው የደበበን የኪነ ጥበብ ሰው መሆን ቀድሞ አይተው ነበርና መማር ያለበት ቴአትር መሆኑን ነገሩት።

ደበብም የመምህሩን ቃል አክብሮ ባሉትና በመከሩት አምኖ የትያትር ትምህርት ለመማር ወስኖ እሱን ጀመረ።ኪነጥበብ በገባቸው ስነ ፅሁፍ በጥልቀት በተረዱት መምህራኖቹ ተስፋዬ ገሠሠ፣መንግስቱ ለማ፣ ሃሊም ኤልዳብና ዶ/ር ፊሊፕ ካፕላን የትያትር እና ስነ ፅሁፍን እውቀት በመቅሰም ለሁለት አመት ተኩል ቆዩ።

የተጋረጠው ፈተና

ትያትርን ወደው ይማሩ የነበሩት እነ ደበበ ትምህርታቸው ሊቋረጥ ተቃረበ።በወቅቱ ለትምህርት ስራው ድጋፍ ያደርግ የነበረው “ሮክፌለር ፋውንዴሽን” ድርጅት የድጋፍ መርሀ ግብሩን አቋረጠ። ደበበና እድል ደጋግሞ ያገናኛቸው የነበረው የልጅነት ጓደኛው ወጋየሁ በዩኒቨርሲቲም አብረው ይማሩ ነበርና እጅጉን ተቸግረው ሀሳብ ገባቸው።

የተስፋ መንገድ

በወቅቱ ከነበሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ካሳ ወ/ማርያም ጋር ተማክረው ትምህርት ሚኒስቴር ሄደው የውጪ አገር የትምህርት ዕድል እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።ነገር ግን ባሉት የትያትር ትምህርት ዘርፍ የውጪ አገር ትምህርት ማግኘት እንደማይችሉ ይነገራቸዋል።እነ ደቤ ግን ተስፋ ሳይቆርጡ በተለያዩ ኤምባሲዎች እየዞሩ የትምህርት እድል እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ ወሰኑ፡፡

የሀንጋሪ ኤምባሲ በትያትር ትምህርት ቦታ እንደሌለውና ግን በእርሻ ትምህርት እድሉ ሊሰጣቸው እንደሚችል ሲገልፅላቸው እድሉን ለመጠቀም ወስነው ተሳካላቸው፡፡እዚያ ሄደው ግን ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል የትያትር ትምህርት የመማር ዕድል አገኙ።እዚያ በነበረው ቆይታቸውም ወቅት መድረክ ላይ በመተወን የትወና ብቃታቸውን አስመሰከሩ።በእዚያ አገር ባልተለመደ ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ ደበበና ወጋየሁ መድረክ ላይ የተወኑ የመጀመሪያ ጥቁሮች ለመሆን በቁ።

ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ አገር ቤት ሲመለሱ ግን፤ ትያትር ቤት ተቀጥሮ የመስራት አልያም ደግሞ ቲያትር ለተማረ ሰው የሚሰጠውን ስራ ማግኘት አልቻሉም ፤ደበበና ጓደኛው ወጋየሁ።ምክንያቱ ደግሞ ሀንጋሪ ሶሻሊስት ሃገር መሆኗና እነሱ እዚያ ተምረው በመመለሳቸው ነበር። ለትያትር ቤቱ ሙያተኞች ስለሶሻሊዝም ስርዓት ምንነት እየነገርን እንዳናበላሽ ታስቦ ይመስለኛል በማለት በወቅቱ ስለገጠማቸው ሁኔታ ያስረዳል፡፡

ለወራት ያለ ስራ ተቀምጠው በመጨረሻም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የራሳቸውን ቲያትር ለመስራት አስበውና ፍቃድ አግኝተው የትያትር ስራ ጀመሩ።ስራዎቻቸውን ለተማሪዎች እያሳዩ ገቢ ማግኘትም ጀመሩ።በወቅቱ ግጥምና ሌሎች የስነ ፅሁፍ ዘርፎችን ለተማሪው ያቀርቡም ነበር።በዚህም በተማሪው ዘንድ ተቀባይነትና አድናቆት አተረፉ፡፡

እውናዊው የትያትር ጥበብ ትምህርት

ውጪ አገር ላይ ትያትርን ተምሮ የመጣው ደበበ እውነተኛውን የመድረክ ጥበብ የተማርኩት ከደራሲ ፀጋዬ ገ/መድኅን ነው በማለት የፀጋዬን የጥበብ ጥልቀት ይመሰክራል።በተለይ ከፀጋዬ ገ/መድህን የትያትር ጥበብን የተማረው “የበጋ ሌሊት ራዕይ” የተሰኘ ትያትር ሲያዘጋጅ ከጌታቸው ደባልቄ፣ ተስፋዬ ሳህሉ፣ አስናቀች ወርቁ፣ አስካለ አመነሸዋና ጠለላ ከበደ ጋር በተጋባዥ ተዋናይነት አብሮ በሠራበት ጊዜ እንደነበር ደበበ ይናገራል።

ከስራዎቹ መካከል

በመሪ ተዋናይነት የተጫወታቸው ቴአትሮች ፡- እናት ዓለም ጠኑ፣ ፍልሚያ፣ ናትናኤል ጠቢቡ፣ ያላቻ ጋብቻ፣ ሀሁ በስድስት ወር፣ የቬኒሱ ነጋዴ።የተሰኙቱ ዋና ዋናዎቹ አድርጎ መጥቀስ ይቻላል፡፡

በፊልም ተዋናይነት፡- በአገር ውስጥ ፊልሞችና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች የተሳተፈባቸው ለመጥቀስ ያህል “ሰባ ሰላሳ”፣ “የልብ ጌጥ”፣ “ትውልድ”፣ “ስውር ችሎት”፣ “ደርሶ መልስ” እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል:: ከውጪ ፊልሞች ደግሞ “ሻፍት በአፍሪካ” (Shaft in Africa)፣ የሚሸል ፓፓታኪስ ዝግጅት በሆነው ጉማ ፊልም በመሪነት ተዋናይነት ተጫውቷል።“አፍሪቃ” (Afrika) እና “ዜልዳ” (Zelda)፣ “ቀያይ ቀምበጦች”፣ ፣ “A Season in Hell” (አንድ ወቅት በገሃነም) በተሰኙ ዓለማቀፍ ፊልሞች ላይ በመስራት ድንቅ ብቃቱን አስመስክሯል፡፡

በተለይ መሪ ተዋናይ ሆኖ በሰራበት “ቀያይ ቀምበጦች” (Red Leaves) በተሰኘው ፊልሙም ደበበም ሽልማቶችን አግኝቷል።በዓመቱ የምርጥ መሪ ተዋናይነት ዘርፍ ደበበ አሸንፏል::

አገሩን ኢትዮጵያ ከልቡ የሚወደው፤ ለህዝቡ ታላቅ አክብሮት ያለው አርቲስት ደበበ፤ የት ተወልድክ ብለህ ብትጠይቀው ኢትዮጵያ ይልሀል።“ኢትዮጵያን በመሰለች ውብና የነፃነት ምድር መፈጠር ኩራት ነው” በማለት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ታላቅነት ያስረዳል።

ያዘጋጃቸው ትያትሮች፡- “ጎርፉ”(ራሱ የተረጎመው)፣ “የአዛውንቶች ክበብ”፣ “ኪንግ ሊር” (ሊር ነጋሲ)፣ “ጠልፎ በኪሴ”፣“ዳንዴው ጨቡዴ”፣ “ተሃድሶ”፣ “ጠያቂ”፣ “አይጦቹ” (እራሱ የተረጎመው)፣ ወዘተ. የተሰኙትን ተውኔቶች ይገኙበታል፡፡

ሽልማቶችና እውቅና

ይህ ባለ ዘርፈ ብዙው ከያኒ አለም አቀፍ ተቋማትና አገራት ለታላለቅ ስራዎቹ ሽልማትና እውቅናን ሰጥተውለታል።ከእነዚህም ውስጥ፡- አፍሪካውያን የራሳቸው ቴያትር ቤት እንዲኖራቸው ላደረገው ጥረት የ“ማላካይድ ስቶን” የሚባል የክብር ድንጋይ በማስታወሻነት ከመጀመሪያው የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ተበርክቶለታል።በቴያትር መስክ ላደረገው አገልግሎት ከጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል “የሕይወት ዘመን ሽልማት” ተቀብሏል።ኢትዮ የፊልም ማዕከል የ“ጉማ አዋርድ”ን ሸልሞታል:: በሰራቸው ስራዎች በአገር ውስጥ በርካታ ሽልማቶች ተበርክቶለታል።

ይህ የኪነ ጥበብ እንቁ ለወጣት የኪነ ጥበብ ሙያተኞች መልዕክት አለው።ሙያውን በደንብ አውቀው እንዲሰሩት ከሌሎች ዓለማት የጥበብ ስራ ሰዎች የሚያንሱበት ምንም ነገር የሌለ መሆኑን በመረዳት ለውድድር ተሳትፎ ራስን ማዘጋጀትና ሁሌም ለሙያው የሚያበቃ በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።ኢትዮጵያዊያን የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ብቃት እንዳላቸውና ይህንን ችሎታቸውን ለማውጣት ሁሌም መጣር እንዳለባቸው ይመክራል።

የዕረፍት ጊዜ

ለብዙዎች ኪነጥበብ በሰጠችው ክህሎቱ የዕረፍት ጊዜ ሀሴት መዝሪያ የሚሆኑ ገፀ በረከቶች በእድሜው ሙሉ እያበረከተ የቆየው አርቲስት ደበበ የእሱም መዝናኛ ኪነ ጥበባዊ ጉዳዮች ናቸው።ለሰዎች ደስታ መፍጠር የሚያስደስተው አርቲስት ደበበ ህይወትን ቀለል አድርጎ በደስታ መኖር በሳቅ ማድመቅ እንደሚያስደስተው ይናገራል፡፡

ማንበብ የደበበ ዋንኛ ልምድና ወዶ ደጋግሞ የሚያደርገው ተግባሩ ነው።ሲያነብ ያገኘው መልካም ነገር ለአገርና ህዝብ ይጠቅማል።እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ብዙ መስዋዕትነት የከፈለው ደበበ ለዚህች ሀገር ያለው ፍቅር ጥልቅ ነው።የሚሳሳላት አገሩን እጅጉን የሚወደው፣ የኢትዮጵያ ህዝብን የሚያፈቅረው ደበበ የኢትዮጵያን ታሪክ መመርመር ታሪኳን በጥልቀት ማጥናትና ስለ አገሩ መፃፍ ያዘወትራል።

ተገኝ ብሩ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 2014 ዓ.ም

Recommended For You