የምዕራባውያን ጫና መንግሥትን አስወግዶ በተላላኪ መንግስት ለመተካት መሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፡- የምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና መንግሥት የእነሱን ፍላጎት እንዲፈፅም አሊያም እሱን አስወግደው በታዛዥና ተላላኪ ኃይል ለመተካት ነው ሲሉ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር መኮንን አለኸኝ(ዶክተር) ገለፁ።

ፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ መኮንን አለኸኝ(ዶክተር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ተደጋጋሚ ጫና አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት የእነሱን ፍላጎት ስላልፈጸመላቸው ነው። አላማቸውም የእነሱን ፍላጎት ለማሳካት ጫና በማሳደር መንግሥትን ወደ ሚፈልጉት መስመር ማምጣት አልያም ይህ ካልተሳካም እሱን አስወግዶ በሌላ ታዛዥና ተላላኪ ኃይል ለመተካት ነው ብለዋል።

ምዕራባውያን ያልተገደበ ጫና የሚያሳድሩት የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር መሆኑን አመልክተው፤ ኢትዮጵያም ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ከግንብና ከድንጋይ ጋር በቀጥታ መጋጨት ሳይሆን ብልሃት በታከለበት የዲፕሎማሲ ሥራዎችና ውስጣዊ አንድነቷን በማጠናከር መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀር ለተወሰኑት ኃያላን አገራት ጉዳይ አስፈጻሚ መሆናቸውን ጠቁመው፤ እያንዳንዱ አገር የራሱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ተኝቶ ስለማያድር ምዕራባውያን ፍላጎታቸውን ለማሳካት የተለያዩ ጫናዎችን ያሳድራሉ ሲሉ ተናግረዋል።

ማንም ጠንካራ አገር ስለሆነ እንደፈለገ ጠምዝዞ የራሱን ብሔራዊ ፍላጎት ፈፃሚ አገር ማድረግ አይችልም። እንደ አገር ብሔራዊ ጥቅማችንን አስጠብቀን ለማስቀጠልና ተንበርካኪ መንግሥት ላለመሆን ኢትዮጵያ ዓለም ላይ ያላትን የመደራደርና የተደማጭነት አቅሟን ማሳደግ ይገባል። ለዚህም የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የሰራዊት ግንባታ ሥራዎችን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ወደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚሄዱ ጉዳዮችን በአፍሪካ ህብረት እንዲቋጩ ተፅዕኖ ለማሳደር አሁንም በርካታ ሥራዎች እንደሚጠብቃት የጠቆሙት መምህሩ፣ የአፍሪካ አገራትም እንደ ኢትዮጵያ የምዕራባውያን አገራት ጫና ሲመጣባቸው ለመቀልበስ የራሳቸውን ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራና አፍሪካዊ አንድነትን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ህብረትና ሌሎች ክፍለ አህጉራዊ ተቋማትን በመጠቀም ኢትዮጵያ መብቷንና ጥቅሟን ለማስጠበቅ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል።

በእነዚህ ተቋማት ላይ ተጨባጭ የዲፕሎማሲ ሥራ በማከናወን የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ድርድርን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች ጭምር ቢቻል በኢጋድ ባይቻል በአፍሪካ ህብረት መፍትሄ እንዲያገኙ በማስረዳት፤ በመከራከርና በማስገንዘብ ጥቅማችንን ማስጠበቅ እንችላለን ብለዋል።

አገራት ሽኩቻ ከሚያደርጉባቸው የጂዮ-ፖለቲካል ቁልፍ ቦታዎች መካከል አንዱ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የቀይ ባህር መስመር መሆኑን ገልጸው፤ ይህን ቦታ ለመቆጣጠር የሚችሉት በምስራቅ አፍሪካ አገሮች በተለይም በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ሲችሉ እንደሆነ ገልጸዋል።

ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ላይ ተደጋጋሚ ጫና የሚያሳድሩት አገሪቱ በአፍሪካ ውስጥ ባላት ተፅዕኖ ፈጣሪነት፤ የህዝብ ቁጥሯ ከፍተኛ በመሆኑ እና በአሁኑ ወቅት ያለው መንግሥት የአገሩን ጥቅም ለማስከበር ያለውን ቁርጠኝነት በመመልከት ነው ብለዋል።

ፀጋዬ ጥላሁን

አዲስ ዘመን ጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓ.ም

Recommended For You