የሃይማኖቱ አስተምህሮ የሆኑትን መተጋገዝና መደጋገፍ ሙስሊም ህብረተሰብ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

አዲስ አበባ፡- የእስልምና ሃይማኖት መገለጫ የሆኑት መተዛዘን፣ መተጋገዝና መደጋገፍ ሁሉም ዜጎች ዘንድ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሃይማኖቱ አስተማሪዎች ተናገሩ።

በአንዋር መስጊድ የልጆች ቁርዓን አቅሪና ኡስታዝ ኑርሁሴይን ሰኢድ የመውሊድ በዓል ትላንት መከበሩን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት አስተያየት፤ መውሊድ በአማኞቹ ዘንድ የሚከበርበት ዋና ምክንያት እዝነትን፣ መልካምነትን፣ መረዳዳትን ለማሳደግ ነው። ይህም በብሄር፣ በቀለም፣ በዘር፣ ሳንለያይ አብሮነትን በማጠናከር እንደ አገር በጋራ ለማደግ ነው።

የሃይማኖት አስተምህሮ መሰረት የሆኑት የነብዩ መሐመድ (ሠ.ዐ.ወ) መወሊድ ለዓለም ህዝቦች ትልቅ ትሩፋትን አስገኝቷል ያሉት ኡስታዝ ኑርሁሴን፤ የሃይማኖቱ ተከታዮች ዋነኛ የደስታ ምንጭ መሆናቸውንም አመላክተዋል።

ነብዩ መሐመድ (ሠ.ዐ.ወ) የተራቡትን ማብላት፣ የተጠሙትን ማጠጣት፣ የታረዙትን ማልበስና መልካም ነገሮችን ሁሉ ማድረግን አስተምረዋል፤ አማኞቹና የዓለም ህዝቦች ይህን መልካም ተግባር ወደፊትም አጠናክርን በመቀጠል በመተጋገዝ፣ በመደጋገፍ፣ በመተዛዘን፣ አንድነታችን ማስቀጠልና አብሮ መኖር መቻል አለብን ብለዋል።

ዘንድሮ ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ በመሆኗ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ሳይገድበን ዜጎች የአገርን ክብር ለማስጠበቅ እንዲነሱም ጥሪ አቅርበዋል።

ለተፈናቃዮችና ለአገር ክብር ሲሉ ግንባር ለተሰለፉ የሠራዊት አባላት ድጋፍ ማድረግ የግድ የሚልበት ወቅት ላይ ነን ብለዋል። እኛም በፆሎታችን፣ በሀብታችን በምንችለው ሁሉ ድጋፍ በማድረግ የወገናችንን ሰቆቃ እንጋራለን ሲሉም ገልፀዋል።

ኡዝታዝ አማር ሙሀመድ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ሀገራችን ካጋጠማት ወቅታዊ ችግር ነጻ እስከምትሆን ድረስ የሃይማኖቱ ተከታዮች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረጋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

“ሁሉም ነገር ከአገር በላይ አይደለም”፣ ልክ ነብዩ ሙሀመድ (ሠ.ዐ.ወ) ከጎናቸው የነበሩትን አጋዦቻቸውን እንዳሰባሰቡት ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄረሰብ፣ የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮችና ሁሉም ዜጋ የአገሩን ክብር ለማስጠበቅ በአንድነት መቆም ይኖርበታልም ብለዋል።

ነብዩ መሐመድ (ሠ.ዐ.ወ) ለሰው ልጆች መልካም ነገሮችን ሁሉ ማድረግን ለዓለም ህዝቦች አስተምረዋል ያሉት ደግሞ ሼህ አዎል ኽድር ናቸው። ስለሆነም የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እነዚህን መልካም ተግባሮች በማሰብና በሚችሉት ሁሉ እንዲያስቀጥሉ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለህልውና ዘመቻው የሚደረገውን ድጋፍ በማጠናከር ሀገራችን ወደ ሰላምና መረጋጋት እንድትመለስና በቀጣይም የልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ የሚያስችሉ ሥራዎችን መስራት እንደሚጠበቅበት ሼህ አዎል አመላክተዋል።

የነብዩ ሙሀመድ (ሠ.ዐ.ወ) መልካም ተግባሮች ህዝበ ሙስሊሙ በቀጣይም በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው ችግር ላይ ለወደቁ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደየ አካባቢያቸውና ወደ መደበኛ ህይወታቸው እስኪመለሱ ድረስ መደገፍ እምነቱ የሚያዘው አገራዊ ግዴታ እንደሆነም አስታውሰዋል።

ሙሳ ሙሀመድ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓ.ም

Recommended For You