ቤላሩስ የፈረንሳይ አምባሳደርን አባረረች

በአውሮፓዊቷ ቤላሩስ የነበሩት የፈረንሳይ አምባሳደር አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ በታዘዙት መሠረት ወደ መጡበት መመለሳቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የኤምባሲው ቃል አቀባይ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል እንደተናገሩት አምባሳደር ኒኮላስ ደ ላስት ቤላሩስን ለቀው የወጡት እሑድ ዕለት ነው።

የቤላሩስ መንግሥት አምባሳደሩ ዋና ከተማዋ ሚኒስክን ለቀው እንዲወጡ እስከ ሰኞ ድረስ ቀነ ገደብ ሰጥቶ ነበር።

የ57 ዓመቱ አምባሳደር ኒኮላስ ባለፈው ዓመት ነበር በቤላሩስ የፈረንሳይ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት።

የቤላሩስ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት አምባሳደሩ የሥራ ፈቃዳቸውን ለፕሬዝደንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አላቀረቡም።

ፈረንሳይ ልክ እንደሌሎቹ የአውሮፓ አገራት የቤላሩሱ መሪ ሉካሼንኮ ባለፈው ዓመት ነሐሴ የተደረገውን ምርጫ አሸንፍኩ ብለው ለስድስተኛ ጊዜ ፕሬዝደንት ሆነው መመረጣቸው አልተዋጠላትም።

አምባሳደሩ ባለፈው ታኅሣሥ ፕሬዝደንቱን በማግኘት ፈንታ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቭላድሚር ማኬይን ነው ያገኙት።

ለኤኤፍፒ በተላከ መግለጫ የፈረንሳይ ኤምባሲ ቃል አቀባይ “የቤላሩስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደሩ ከሰኞ በፊት ለቀው እንዲወጡ ነው ያዘዘው” ብለዋል።

“ሁሉንም የኤምባሲውን ሠራተኞች ተሰናብተው ነው የሄዱት። ለቤላሩስ ሕዝብ በተንቀሳቃሽ ምስል ቀድተው ያስቀመጡት መልዕክት በኤምባሲው ድረ-ገፅ ይለቀቃል።”

የአውሮፓ ሕብረት በተደጋጋሚ ባለፈው ነሐሴ የተካሄደው ምርጫ “ነፃና ፍትሐዊ” ነው ብሎ እንደማያምን አሳውቋል።

ሕብረቱ አልፎም በፕሬዝደንት ሉካሼንኮ አገዛዝ ላይ ማዕቀብ መጣሉ የሚዘነጋ አይደለም።

ፕሬዝደንቱ ከምርጫው በኋላ ለዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ተቃውሞ እያሰሙ ያሉ ዜጎች ላይ ከፍተኛ የኃይል እርምጃ ወስደዋል።

ምንም እንኳ የምዕራቡ ዓለም ማዕቀብ ቢጥልባቸውም ሉካሼንኮ ሥልጣናቸውን ተቆናጠው እንደያዙ ናቸው።

የ67 ዓመቱ የቤላሩስ መሪ አገራቸውን በፈረንጆቹ ከ1994 ጀምሮ ገዝተዋል። ዘንድሮ ከአውሮፓ አገራት በደረሰባቸው ጫና ምክንያት ከአብዛኛዎቹ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠዋል።

የፕሬዝደንቱ ዋነኛ ደጋፊ የሚባሉት የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

ባለፈው መጋቢት የቤላሩስ መንግሥት የላትቪያ አምባሳደርን ጨምሮ ሁሉንም የኤምባሲ ሠራተኞች ማባረሩ ይታወሳል።

ይህ የሆነው በላትቪያ በተካሄደ የበረዶ መንሸራተት ጨዋታ ላይ የቤላሩስ ተቃውሞን የሚያንፀባርቅ ባንዲራ በመታየቱ ነው።

የቀድሞ የሶቪዬት ግዛት የነበረችው አገር ባለፈው ነሐሴ ደግሞ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ወደ ቤላሩስ ሊጓዙ ለነበሩት ጁሊ ፊሸር የሥራ ፈቃድ እንደማትሰጥ አሳውቃ እንደነበር የዘገበው ቢቢሲ ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2014

Recommended For You