‹‹በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የማይታወቁ የማዕድን አይነቶች አሁን እየወጡ ነው››ዶክተር ወራሽ ጌታነህ

የኢኮኖሚክ ጂኦሎጂ ምሁር ናቸው። በተማሩት የትምህርት ዘርፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነምድር ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ከመማር ማስተማር ጎን ለጎንም በዘርፉ የምርምር ሥራዎችን ይሰራሉ።

በኢትዮጵያ ስለሚገኘው የማእድን ሀብትና መጠን እንዲሁም ሀብቱን ጥቅም ላይ በማዋል ለምጣኔ ሀብት እድገት አስተዋጽኦ እንዲኖረው በማድረግ ረገድ እየተሰራ ስላለው ሥራና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ አድርገዋል። የዛሬው ‹‹የምድር በረከት›› አምድ እንግዳችን ዶክተር ወራሽ ጌታነህ።

አዲስዘመን፦ በቅድሚያ ማዕድን ምን ማለት እንደሆነ ቢገልጹልኝ?

ዶክተር ወራሽ፦ በሥነ ምግብ ማእድን የሚባል ነገር አለ። በሥነ ምድርም እንዲሁ አለ። ነገር ግን ሁለቱም የተለያዩ ናቸው። በሥነ ምግብ የተሟላ የሰውነት ጤንነትን የሚያመጣ፣ሰውነት የሚገነቡ ማእድናት አሉ። በሥነ ምድር ማእድን የምንለው ግን የተለየ ነው።ማእድን ማለት በተፈጥሮ በምድር ውስጥ የሚገኝ ህይወት የሌላቸውን ነገሮች የሚያካትት ነው። ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ወይንም የኢኮኖሚ ጥቅም ያለው ሲሆን፣ በፈሳሽና በጋዝ መልክ እንዲሁም በጠጣር የሚገኝ ነው። ዋናው የማእድን መመዘኛ ግን የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ነው።

አዲስዘመን፦ ኢትዮጵያ ያላት የማእድን ሀብቷ ይታወቃል? የሚታወቅ ከሆነ ምን ያህል ነው? የማእድኖቹ አይነትስ?

ዶክተር ወራሽ፦ ማእድን አለ ወይንም የለም ብሎ ቀጥተኛ መልስ ለመስጠት ያስቸግራል።ምክንያቱም ማእድን በተፈጥሮ መሬት ውስጥ የሚገኝ ወይንም የተቀበረ በመሆኑ ነው። እርግጠኛ መሆን የማይቻለው። ሀብቱ ስለመኖሩ ፈትሾ መረጃ ለማግኘትም ከፍተኛ ገንዘብ ይፈልጋል። የሚጠይቀው ገንዘብ ደግሞ ራሱን ችሎ እንደ ኢንቨስትመንት የሚቆጠር ነው።በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ ይፈልጋል። ማእድን የተለየ ባህሪ አለው።በማእድን ኢኮኖሚ ቋንቋ፣ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ ያልተረጋገጠ ማእድን እንደ ተራ ድንጋይ ይቆጠራል። ማእድን መኖሩን መረጃ ለመሰብሰብ፣ ማእድኑን ከመሬት ውስጥ ለማውጣትና ጥቅም ላይ ለማዋልም የሚሰራው ሥራ ትርፍ ካላስገኘ አዋጭ አይደለም። ከዚህ አንጻር ነው ተገምግሞ ማእድን አለ የለም ማለት የሚቻለው።

ኢትዮጵያ የተሟላ የማእድን ሀብት ቆጠራ አላካሄደችም። በኢንግሊዝኛ “Mineral Resource Inventory” ይሉታል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ያላትን የማእድን ሀብት በግልጽ ለመናገር ይከብዳል። ለቆጠራውም ትኩረት ተሰጥቶታል ለማለት አያስደፍርም። የማእድን ሀብት ቆጠራ የማካሄድ ኃላፊነት የተሰጠው በማእድን ሚኒስቴር ሥር ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የሚባል ክፍል ተቋቁሟል። ይሁን እንጂ ክፍሉ ከተቋቋመ ገና አጭር ጊዜ በመሆኑ ኢትዮጵያ ካላት የመሬት ስፋት አንጻር ሁሉንም አካባቢ በማዳረስ ሙሉ በሙሉ ተሰርቷል ለማለት አይቻልም። ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረትም አናሳ ነው። በአፄ ኃይለሥላሴ የአገዛዝ ዘመን በመጠኑም ቢሆን እንቅስቃሴ ነበር። በደርግ የመንግሥት ሥርአት ደግሞ ሀገሪቱ በጦርነት ውስጥ ስለነበረች ተዘንግቷል። ከዚያም በኃላ በመጣው ለውጥ ከ1980ዎቹ ወዲህ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ አልነበረም። በአጠቃላይ ዘርፉ ተዳክሟል ማለት ይቻላል።ክፍተቶቹ እንዳሉ ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ አዋጭነታቸው የተረጋገጠ፣ እየለሙ ያሉ የማእድን ሀብቶች አሉ።

የማእድን ሀብቶች የተለያዩ ሲሆኑ፣ብረት ነክ፣ ብረት ነክ ያልሆኑ እንዲሁም የነዳጅና የድንጋይ ከሰል በሚል ከፍሎ ማየት ይቻላል። ብረት ነክ የሆኑት ሲባል ብረትና ተያያዥ የሆኑት ናቸው። ከነዚህ መካከል ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ወርቅ ነው። በታሪክም ትልቅ ድርሻ ያለውና አሁንም ድረስ በጥሩ ሁኔታ በመልማት ላይ የሚገኝ ሀብት ነው። በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ አዶላና በተለያዩ የአካባቢው ሥፍራ ይገኛል። ይህንን አካባቢም በኢትዮጵያ ካሉት አንዱ የወርቅ መቀነት ነው ልንለው እንችላለን። ሁለተኛው የወርቅ መቀነት በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው ሲሆን፣ ከጋምቤላ ተነስቶ ትግራይ ሽሬ አካባቢ አልፎም ወደ ኤርትራ የሚገባው ነው።

ሌላው ታንታለም የሚባለው የብረት ሀብት ነው። ይህም አዶላ ነው የሚገኘው። እስከቅርብ ጊዜ ድረስም በመንግሥት ባለቤትነት እንደነበር ነው መረጃው ያለኝ። ሀብቱ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን በተለያየ ችግር ሀብቱ ከመሬት እየወጣ አይደለም። ወለጋ ውስጥ ደግሞ ፕላቲኒየም የሚባል ሀብትም እንዲሁ ጥቅም ላይ ይውል ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን እንቅስቃሴ የለም። በአካባቢው ያለው ይህ ሀብት አልቋል እየተባለም ነው። ግንዛቤ መያዝ ያለበት ማእድን እንደ አትክልትና ፍራፍሬ የሚበቅል አይደለም። ያልቃል። በአንድ አካባቢ ቢያልቅም በሌላ አካባቢ መኖርና አለመኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

ማንጋኒዝ የሚባል ማእድን ደግሞ አፋር ዳሎል ውስጥ ይገኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ ጣሊያኖች በነበሩ ጊዜ በስፋት በማውጣት ጥቅም ላይ ያውሉት ነበር። ክምችቱም አነስተኛ ነበር። በሥራው ላይ የነበሩት የጣሊያን ዜጎች ሥራውን ሲያቆሙ ማእድኑን የማውጣቱ ሥራም ቆመ። እነርሱ ሲያወጡት የነበረው ሀብት ስለመኖሩና በሌላም አካባቢ ይገኝ እንደሆነ ተከታትሎ መሥራት ይገባ ነበር ግን አልሆነም። በስፋት ለግንባታ የሚውለው ብረትም እንዲሁ ሀብት ሲሆን፣ ሀብቱም አለ ግን ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ለማለት አያስደፍርም። ሀብቱ ወለጋ ውስጥ ግምቢ ቢቂላ፣ በባሌ አካባቢዎች ይገኛል። ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት አዋጭነቱ መረጋገጥ አለበት። በመሆኑም የሀብቱ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባለመፈተሹ ጥቅም ላይ አልዋለም።

እንደ ነሐስ፣መዳብ ያሉ ማዕድናት መኖራቸው ይነገራል።ምልክቶችም አሉ። ነገር ግን ጥቅም ላይ ቢውሉ አዋጭ መሆናቸውና አለመሆናቸው ምላሽ አላገኘም። የተለያዩ ለጌጣጌጦች የሚውሉ የከበሩ ድንጋዮች ሀብትም በስፋት በተለያዩ ሀገሪቱ ክፍሎች ይገኛሉ። በተለይም ኦፓል እና ኢመራልድ የሚባሉት ማእድናት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት እየተመረቱ ይገኛሉ።

በሀገር ደረጃ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት ግን ጥቅም ላይ ሳይውል የቀረው ለማዳበሪያ የሚውለው በአፋር ዳሎል ውስጥ የሚገኘው ፖታሽ የተባለው ጥሬ እቃ ነው። ብዙ ኩባንያዎች ቢንቀሳቀሱም ብዙም ሳይቆዩ ጥለው እየወጡ ሳይለማ ቀርቷል። ድንጋይ ከሰልና ነዳጅም እንዲሁ ሀብቱ ቢኖርም ትኩረት ተሰጥቷቸው ለምተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ አልተደረገም። ጣሊያኖች ደሴ ውጫሌ አካባቢ በተወሰነ ደረጃ የድንጋይ ከሰል ጥቅም ላይ ሲያውሉት ነበር። ጎንደር ጭልጋና በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢ ይገኛል። በተለይ ግን በጅማ አካባቢ በስፋት የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ለማልማት ብዙ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ነዳጅን በተመለከተ ለነዳጅ ኃይል የሚውለው ክሩድ ፈሳሽ ነዳጅ ስለመኖሩ የተረጋገጠ ነገር የለም።ምልክቶች ግን አሉ። ምልክቱ ግን አዋጭ ክምችት ስለመኖሩ ዋስትና ሊሆን አይችልም፤ ጥልቅ ጥናት ተደርጎ መረጋገጥ አለበት። ቡታጋዝ ወይንም ስሊንደር እየተባለ ለማብሰያ ጥቅም ላይ ለሚውለው ጋዝ የተባለው ሀብት ግን አለ።ነገር ግን ለምቶ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም። የሥነ ምድሩ (ጂኦሎጂው) ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ማእድናት መኖራቸውን ያሳያል። ተስፋም ይሰጣል። ይህ ማለት ግን ማእድናቱ በእርግጠኝነት አሉ ማለት እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል።

አዲስ ዘመን፦ በአንድ በኩል ሀብቱ አለ? በሌላ በኩል ደግሞ ቆጠራ ስላልተካሄደ ሀብቱን ማወቅ አይቻልም የሚል ነው የተረዳሁት። ግልጽ ቢያርጉልኝ?

ዶክተር ወራሽ፦ ቃሉ ሊያስሳት ይችላል። ስለቆጠራ ሲነሳ የሚቆጠረው ያለው ሀብት ነው።ምን አለ? ምን የለም? ለማለት ግን ሀብቱ መታወቅና መጠናት አለበት። ቀደም ብለን የተነጋገርንባቸውና የገለጽኳቸው የታወቁት ናቸው። ማእድናት ሲባል በሺ የሚቆጠር ነው።ለምሳሌ በብረታብረት ነክ ብቻ ብዙ የማእድን አይነቶች ናቸው የሚገኙት። ብረት ነክና ብረት ነክ ባልሆኑት ተብለው በተለዩት ውስጥ በርካታ የማእድናት አይነቶች ይገኛሉ።ለምሳሌ የወርቅ አቅም እንዳለን ይታወቃል። ነገር ግን ያልታየ ፣ያልተዳሰሰና ያልተጠና አካባቢ በመኖሩ የኢትዮጵያ የወርቅ አቅሟ ይታወቃል ማለት አይቻልም። ከአፈር ውስጥ ወርቅ እያወጡ አጥበው የሚሸጡ ሁሌም በፍለጋ ላይ ናቸው። አንድ ቦታ ሲያልቅ ሌላ ቦታ ሄደው ማውጣቱን ይቀጥላሉ። ይህ ማለት ሀብቱ አለ ግን ምን ያህል እንዳለ አይታወቅም።አንዳንድ በተለይም ያደጉት ሀገሮች በእያንዳንዱ ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሬት ውስጥ ያለውን ሀብታቸውን ያውቃሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በዚህ ረገድ ገና ብዙ መሥራት ይኖርብናል።

አዲስዘመን፦ ኢትዮጵያ የተለያየ ሀብት አላት? ድንግል ናት? እየተባለ እስከመቼ ይቀጥላል? ነገሮችን ደረጃ በደረጃ እየፈቱ ሀብቱን ጥቅም ላይ ማዋል አይቻልም?

ዶክተር ወራሽ፦ የማእድን ሀብታችንን ለምን አላለማነውም በሚል መልኩ ብናየው ይሻላል።ቀላል ነገር አይደለም።ባህላችንም መፈተሽ አለበት። ድንጋዩ ላይ ቴክኖሎጂና ኢንቨስትመንት ካልተጨመረበት ሀብት አይሆንም። ለማእድን ሀብት ያለን እውቀት፣ ፍላጎትና ትኩረት አናሳ ነው። አብዛኛው ማህበረሰብ ከማእድን ይልቅ ስለ ግብርና የተሻለ እውቀት አለው። በጎረቤት ሀገሮች ደቡብ አፍሪካ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ እና በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ሰፊ ልዩነት ነው ያለው። የሁለቱ ሀገራት ሰዎች ለማእድን ቅርብ ናቸው። ለመጠቀሚያ መሳሪያዎቹና ለቴክኖሎጂው በአንጻራዊነት ቅርብ ናቸው። እነርሱ ባህል አድርገውታል።ከፖሊሲው ጀምሮ ፖለቲካውም በዚህ መቃኘት አለበት። የማእድን ሥራ ትልቅ ኢንቨስትመንት ወይንም የካፒታል አቅም ይጠይቃል። አሁን ባለው የሀገር ውስጥ የገንዘብ አቅም የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት መሳብ አይቻልም። ከውጭ እንዲመጣ ለማድረግ ደግሞ ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠይቃል። በተለይ የተረጋጋ ሰላም ሀገር ውስጥ መኖሩ ለዘርፉ እጅግ አስፈላጊ ነው። ሀብቱን ፈልጎ ጥቅም ላይ ለማዋል ረጅም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ የውጭ ኩባንያዎች ያወጡትን ገንዘብ ለመመለስም ሆነ ለማትረፍ ያለሥጋት መሥራት ይፈልጋሉ።

አስተማማኝ የሥነምድር የተደራጀ መረጃም መኖር ይኖርበታል። ሥነምድር ካርታ መዘጋጀት ነበረበት። በተለይ ከቅርብ ጊዜያቶች ወዲህ የመረጃ ካርታ የመሥራት ሥራ ተዳክሟል። የሥነምድር ካርታ የማእድን አይነት፣ መጠንና ጥራት የሚገኝበትንም አካባቢ ለማሳወቅ ይረዳል። በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልም በሚፈለገው ልክ አይደለም። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመማር ፍላጎት ያለው እንኳን ጥቂት ነው። ከማእድን ሀብት አስተዳደር ጋር በተገናኘ ጋባዥና አስቻይ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል። ሀገርበቀል የማእድን ኩባንያን ለመመስረት የሚቻልበትን ዕድልም ማመቻቸት ይገባል። በአጠቃላይ ዘርፉን ለኢንቨስትመንት ምቹና ሳቢ ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው።

አዲስዘመን፦ እርስዎ ከገለጹልኝ አኳያ ብዙ ሥራዎች ይጠይቃል።ነገር ግን በዘርፉ ያለው ተስፋ እንዴት ይታያል?

ዶክተር ወራሽ፦ በዘርፉ የሚደረገው እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ ነው።ከጥቂት አመታት በፊት የማይታወቁ የማእድን አይነቶች አሁን እየወጡና ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው። ከከበሩ ድንጋዮች ኢመራልድን መጥቀስ ይቻላል። ውድ አረንጓዴ ሀብት ነው።ኦፓልም እንዲሁ። የበለጠ መጠቀም እየተቻለ ግን ሂደቱ አዝጋሚ መሆኑ ነው ክፍተቱ።ቆጥሮ ለሚያለማ አካል መስጠት ያስፈልጋል። የሀገር የኢኮኖሚ ምሶሶ ማድረግ ይገባል።

አዲስዘመን፦ በዘርፉ ያካሄዷቸው የምርምር ሥራዎች ካሉ በምን ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው? ውጤታቸውስ?

ዶክተር ወራሽ፦ በከበሩ ድንጋዮች፤ በግንባታ ግብአቶች፤ በታንታለምና ወርቅ ላይ ሰርቻለሁ። የማእድን ማውጣት ስራ በተፈጥሮ አካባቢና በማህበረሰብ ተጠቃሚነት ላይም የተወሰኑ ጥናቶችን አካሂጃለሁ። በአብዛኛው ምርምሩ የሀብቱን አፈጣጠር፣ መጠን፣ ጥራቱ፣ጥቅሙ የፍለጋ መመዘኛዎች ላይ ያተኩራል።

አዲስዘመን፦ ተመራማሪውና አስፈፃሚው ተቋም ተናብቦ በመስራት ረገድ ያላቸውን ግንኙነት እንዴት ይገልጹታል?

ዶክተር ወራሽ፦ ግንኙነቱ የለም ማለት ይቻላል። ከሁለቱም ወገን በመሆኑ ክፍተቱን መጋራት ያስፈልጋል። በማእድን ዘርፍ የሚካሄደው የምርምር ሥራ በስምጥ ሸለቆው ላይ እንደሚደረገው አይነት ሰፊ አለመሆኑም ምርምሩ ዘርፉን አግዞታል ማለት አይቻልም።

አዲስዘመን፦ ዶክተር ወራሽ ያሎትን ጊዜ ሰጥተው ሙያዊ ሃሳብዎን ስላካፈሉን ከልብ እናመሰግናለን።

ዶክተር ወራሽ፦ እኔም አመሰግናለሁ።

ለምለም መንግሥቱ           

አዲስ ዘመን ኅዳር   17/2014

Recommended For You