ለጦርነት የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት

ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት አገር ለማፍረስ ከሚታትሩ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ጋር እየታገለች ነው። ከሶስት አስርተ ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ ተሳፍሮ ካልጋለብኳችሁ ቢልም በሕዝባዊ አመፅ ወደ ዳር ተገፍቶ ቆይቷል። ይህን እኩይ ሕልሙን የማሳካት ፍላጎቱ ያልከሸፈው አሸባሪው ትህነግና መሰል አጋሮቹ ግን አሁንም ድረስ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ርብርባቸውን አላቆሙም። ይሄ ሕልማቸው ደግሞ ሉዓላዊነታችንን ተዳፍረው የልማት እንቅስቃሴያችንን ለማጨናገፍ በሚጥሩ የጎረቤት አገራትና አንዳንድ ምዕራባውያን እየተደገፈ ይገኛል።

በሕዝብ ይሁንታ ተመርጦ መንግሥት የመሰረተው ቡድን ከፊት ለፊቱ ሁለት ፈተናዎች ተጋርጠውበታል። አንደኛው አገር አውዳሚ የሆኑትን ቡድኖችና አጋጣሚውን ተጠቅመው ኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ጫና ውስጥ ለማስገባት የሚጥሩ ቡድኖችን ታግሎ ማሸነፍ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የአገር እድገትና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ነው።

በእርግጥ እነዚህን በሁለት ወገን የሚጎትቱ ጉዳዮች አስታርቆ መቀጠል አስቸጋሪ ቢሆንም አንዱን ጥሎ ሌላኛውን አንጠልጥሎ መሄድ በራሱ ኢትዮጵያ ከተደገሰላት ክፋት የሚታደጋት አይሆንም። ይሄን ጉዳይ ግልፅ ለማድረግ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉትን የሠላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ የተናገሩትን ልብ ማለት ግድ ይላል። ይዘቱ የሚከተለውን ነጥብ ይይዛል።

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ላይ እየወጡ የሚገኙት ማስጠንቀቂያዎች ዓላማቸው ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ማዳከሚያ ሌላው የጦርነት አካል ነው። የሌሎች አገራት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ላይ መተማመን እንዳይኖራቸው፣ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ፣ የመጡትም ቶሎ ሸሽተው እንዲወጡ በማድረግ ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ የማዳከሚያ የጦርነቱ አካል ነው።

“ጦርነቱ እየተካሄደ ያለው በመሣሪያ ብቻ አይደለም” ያሉት አቶ ታዬ፤ በዋናነት በፕሮፖጋንዳና በማኅበራዊ ሚዲያ የሚካሄድ የሥነ ልቦና ጦርነት መሆኑን ተናግረዋል። የአሜሪካ ኤምባሲ ለረጅም ጊዜ የውሸት መረጃዎችን በማሰራጨት በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአሸባሪውና አገር አፍራሹ ሕወሓት ጋር ጦርነት ውስጥ መሆኑን አስታውሰው፤ አሸባሪ ቡድኑ ጦርነቱን ብቻውን አያካሂድም ከጀርባ ሆነው በተለያየ መልኩ ድጋፍ የሚሰጡት ኃይሎች አሉ። ምዕራባውያንም ግንባር ቀደም ሆነው ድጋፍ እያደረጉለት ይገኛሉ ብለዋል። ኢትዮጵያ ከአጎዋ እንድትወጣ ማዕቀብ ተደርጓል። ከሌሎች አገራት የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮች በስጋት ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ፣ የመጡትም እንዲሸሹ የማድረግ አካሄድ የጦርነቱ አካል መሆኑ ግልጽ ነው ።

መሰረተ ልማት

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ኢትዮጵያ የያዘችው የህልውና ጦርነት በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚደረግ አይደለም። ይህ ማለት ግንባር ላይ በሠራዊቱ የሚካሄድ ዘመቻ ብቻ ሳይሆን ጠላቶቻችን የዘረጉትን የኢኮኖሚ አሻጥርና የመሠረተ ልማት ግንባታችንን ለማደናቀፍ የሚያደርጉትን እርብርብ ማክሸፍ ነው።

ከአንድ ዓመት በላይ በተደረገው የህልውና ትግል መረዳት እንደቻልነው አሸባሪዎቹ ቡድኖች ለቁጥር የሚታክቱ የመሠረተ ልማት ዘርፎችን አውድመዋል። መንግሥት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው የአየር ማረፊያዎች፣ የኤሌክትሪክ ማሰራጫዎች፣ ድልድይና የአስፋልት መንገዶች፣ በግንባታ ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪ መንደሮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የቴሌኮም የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች፣ የግድብና ሌሎች ለቁጥር የሚታክቱ የልማት ዘርፎች ላይ አሸባሪው ቡድን ውድመት አድርሷል። አሁንም ተመሳሳይ ጥፋት እያደረሰ ይገኛል ።

ኢትዮጵያውያን ትህነግን የሚፋለሙት ለእኩልና ፍትሐዊነት ብቻ ሳይሆን እያደረሰ የሚገኘውን አገር የማጥፋት ተልዕኮ መከላከል መሆኑን ከዚህ መረጃ መገንዘብ ይቻላል ። በቅርብ ቀን በጦር ግንባር በአካል በመገኘት አውዳሚ ቡድኑን ፊት ለፊት ለመፋለም የሄዱት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አቢይ ጦርነቱ ሁለት መልክ ያለው መሆኑን ተናግረዋል። አንደኛው ግንባር ድረስ በመሄድ የሽብርተኛውን ቀብር ማፋጠን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያ የያዘቻቸውን ታላላቅ የመሠረተ ልማትና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በስኬት መምራት፣ መልካም አስተዳደርን ማስፈንና ለጦርነት የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት ነው።

በዚህ ረገድ ሠራዊቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቆራጥ አመራር ተከትሎ ሽብርተኛውን ሲያመክን በመደበኛው የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኘው አመራርና ፈፃሚ ኢኮኖሚው በጦርነቱ ምክንያት እንዳይደቅ፣ የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከምንግዜውም በላይ ኃይሉን፣ እውቀቱን፣ ጉልበቱንና ሞራሉን አዋህዶ የመሥራት ኃላፊነት እንዲሸከም ተደርጓል ። ይህን መነሻ ይዘን ጥቂት መነሻዎችን እናንሳ ካልን የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ሂደት ያለምንም ፀጥታ ስጋትና የሥራ መጓተት እየተካሄደ መሆኑን መታዘብ እንችላለን። ምንም እንኳን ዓለም አይኑን ቢጥልበትም፣ እጅግ የገዘፉ ሴራዎችና የማደናቀፍ ሙከራዎች ቢጋረጡበትም ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ለአፍታም የኃይል መሠረተ ልማት ግንባታው ታላቅ መሰረት የሆነው ግድቡን እውን ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት አላቋረጡም። ይሄ አንዱና ዋነኛው ምሳሌ መሆን ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት ባለፉት ሶስት ዓመታት አዳዲስና ታላላቅ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ይፋ አድርጎ እየሠራ ይገኛል። ምንም እንኳን ሽብርተኞች የኢትዮጵያውያንን የመልማት ውጥን የሚያከሽፍ ተደጋጋሚ ሴራ ቢጎነጉኑም እነርሱን የመታገልም ሆነ ፕሮጀክቶቹን ዳር የማድረስ ክንውኑ ለአፍታም አልቆመም።

ሁለተኛው በምሳሌነት የምናነሳው ታላቅ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ የቴሌኮም ዘርፉን የሚዳስስ ነው። የህልውና ዘመቻውን እያካሄድን ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትና የቴሌኮም ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ግንባታው ለአፍታም አልቆመም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ታሪካዊ ውሳኔ” ያሉት የኢትዮጵያን የቴሌኮም መሠረተ ልማት በእጅጉ የሚያልቀው ፕሮጀክት “በሳፋሪ ኮምና” በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር ወደ ተግባር ለመግባት ጫፍ ላይ ደርሷል። ኢትዮጵያውያንም በሽብር ቡድኖቹ እኩይ ድርጊት ልማቱ እንዳይደናቀፍ የቡድኖቹን እስትንፋስ እስከመጨረሻው ለማቋረጥ እየሰሩ ይገኛሉ። በተመሳሳይ የመሠረተ ልማት ግንባታውን አንድ ብሎ ለማስጀመር ካምፓኒውና የመንግሥት አካላት ወደ ትግበራ ደረጃ እየደረሱ ነው። የሳፋሪ ኮም የኢትዮጵያ አመራሮች ዋና ሥራ አስፈፃሚውን አንዋር ሶሳን ጨምሮ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ቡድኑ ለኮምሽነሯ በኢትዮጵያ ውስጥ እያከናወነ ያለውን የቴሌኮም ኢንቨስትመንት እና የደረሰበትን ደረጃ ያስረዳ ሲሆን በቅርቡ በይፋ የምርቃት መርሐ ግብር አዘጋጅቶ የሥራ ጅማሪውን ለማብሰር እየሠራ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ ይህ ማለት ልማቱም ሆነ የህልውና ዘመቻው ጐን ለጐን እንደሚሄዱና ውጥንቅጡን ተከትሎ የሚመጣውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቋቋም የሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጅት መደረጉን የሚያሳይ ነው።

የመሠረተ ልማት ውድመት

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው የህልውና ዘመቻው ኢትዮጵያን ከዘራፊዎችና አውዳሚዎች መታደግን ኢላማው ያደረገ ነው። ይሄ ደግሞ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች እንዳይደናቀፉ ከማድረግ ባሻገር በሥራ ላይ የሚገኙትን ጥፋት እንዳይደርስባቸው መከላከልንም ያካትታል። ለአብነት በቅርቡ አሸባሪው ትህነግ የአማራ ክልል የተለያዩ ወረዳዎችን በመውረር ያደረሰውን ጥፋት ብንመለከት አሁን እየተካሄደ የሚገኘው ቡድኑን የማጥፋት እርምጃ ለምን እንደሚወሰድ በእጅጉ ግልፅ ይሆንልናል።

የአማራ ክልል የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንሙት በለጠ በቅርቡ የተደረገውን የዳሰሳ ጥናት መነሻ በማድረግ በጥፋት ቡድኑ የደረሰውን አጠቃላይ የመሠረተ ልማትና የኢኮኖሚ ውድመት ይፋ አድርገዋል። እንደ እርሳቸው ገለፃ ፤ ሽብርተኛ ቡድኑ በገባባቸው በአምስቱ ዞኖች ማለትም በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜን ጎንደር፣ በዋግ ኽምራ እና በደቡብ ወሎ በከፊል በሚገኙ 45 ወረዳዎች ውስጥ በአማጽያኑ 280 ቢሊዮን ብር የሚገመት ዘረፋና ውድመት ደርሷል።

ይህም አኃዝ በቅርቡ ጦርነቱ የተስፋፋባቸውን የደቡብ ወሎ ዞን እና አንዳንድ የሰሜን ሸዋ አካባቢዎችን አያካትትም። በጦርነቱ ምክንያት የደረሱ ጉዳቶችን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ከተለያዩ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ጋር በጥምረት በሠራው የዳሰሳ ጥናቱ ለማወቅ መቻሉን ያሳወቁት ኃላፊው በተለይ በግብርናው ዘርፍ የደረሰው ውድመት ከፍተኛ መሆኑን በቅርቡ ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የዳሰሳ ጥናቱ በርካታ ቦታዎችን ለመሸፈን ውስንነት እንዳለው የገለጹት አቶ አንሙት የደረሰው ውድመት 280 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚገመት ነው ብለዋል። ኃላፊው ጦርነቱ ጠንካራ ኢኮኖሚ ወዳላቸው ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች እንዲሁም የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች በመስፋፋቱ በክልሉ የደረሰው ውድመት ከተገለጸው በላይ ከፍተኛ እንደሚሆን አስረድተዋል። አቶ አንሙት እንዳሉት የዳሰሳ ጥናቱ በተካሄደባቸው ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮች፣ የጤና ጣቢያዎች እና የመንግሥት መሠረተ ልማቶች ወድመዋል ። በተለይ የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ መፈፀሙን ነው የተናገሩት ።

ችግሩን ለመከላከል

ኢትዮጵያውያን አንድ አባባል አለን። አንድ ችግር ሲከሰት እርሱ ለመፍታት “እሾክን በእሾክ” የሚል። ይህ ብሂል ሲፍታታ አንድ የተከሰተን መጥፎ አጋጣሚ ለመፍታት በተፈጠረበት አግባብ ልክ ውሳኔ ማሳለፍ እንደሚገባ ነው። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ መንግሥት በጦርነት ወቅት “የኢኮኖሚ ጫና” እንዳይከሰት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው።

በዋናነት የመሠረተ ልማትና የእድገት ፀር የሆነውን ትህነግ አደብ ማስገዛት የቅድሚያ ቅድሚያ ሲሰጠው፤ በተያያዘ አዳዲስ የኢኮኖሚ አውታሮችን መገንባት፣ የኢንቨስትመንት ትግበራዎች በሁከቱ ምክንያት እንዳይደናቀፉ መከላከል፤ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተጀመሩት የትምህርት፣ የኃይል፣ የግብርና፣ የመንገድና ሌሎች የልማት ክፍሎች ከወትሮው በተለየ ወኔ ማስተግበር የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ከቻልን ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን ፈተና (ምንም ያህል ከባድ ቢሆን) እንድትሻገር ማድረግ ያስችለናል። ከሁሉም በላይ ግን አገራችን ከድል በኋላ ኢኮኖሚያዊ ጫና እድገቷን ወደ ኋላ እንዳይጎትተውና ተጨማሪ ዋጋ እንዳንከፍል ዋስትና ይኖረናል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ኅዳር   18/2014

Recommended For You